ጅግጅጋ፡- ከተሞች ዘመናዊና ደህንነታቸው የተጠበቀ እንዲሆኑ ለማድረግ ከሚሰሩ ሥራዎች በተጓዳኝ ከፕላን ውጪ የሚከናወኑ
የቤት ግንባታዎች ጉዳይ ለድርድር መቅረብ እንደማይገባው የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ካሳሁን ጎፌ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ በከተሞች ያለውን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ለመፍታት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ቢኖሩም፤ ከፕላን ውጪ የሚከናወን የቤቶች ግንባታ በበርካታ የአገሪቱ ከተሞች የሚታይ ችግር ነው፡፡ ይህ ደግሞ ዘመናዊና ደህንነቱ የተጠበቀ ከተማን ከመፍጠር አኳያ ትልቅ ፈተና እንደመሆኑ ከፕላን ውጪ የሚከናወኑ ግንባታዎችን ጉዳይ ለድርድር መቅረብ የለበትም፡፡
እንደ አቶ ካሳሁን ገለጻ፤ በከተሞች የሚስተዋሉ ሕጋዊ ያልሆኑና ደረጃቸውን ያልጠበቁ ቤቶችን ከመቆጣጠር አንጻር ዋናው መፍትሄ ሕጋዊና ደረጃቸውን የጠበቁ ቤቶችን ማቅረብ ነው፡፡ ሆኖም ይህ በአጭር ጊዜ የሚሳካ አይደለም፡፡ ችግሩን ለመከላከል ግን ምንም ይሁን ምን የከተማ ፕላን ጉዳይ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም፡፡ ለዚህም የከተሞች ፕላን የከተማው ማህበረሰብ አውቆት ፕላኑን የማስጠበቅ ኃላፊነቱ ያለባቸው እንደመሆኑም፤ ከፕላን ውጪ የሚከናወኑ ግንባታዎች ለድርድር መቅረብ የለባቸውም፡፡
ከዚህ አኳያ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ሰፋፊ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆናቸውን የጠቀሱት ሚኒስትር ዴኤታው፤ ህዝቡም ማወቅ ያለበት ከፕላን ውጪ የሚደረጉ የቤት ግንባታዎች አንደኛ፣ ነዋሪውን የማይጠቅሙ መሆናቸውን፤ ሁለተኛም ቤቶቹ ፈራሽ ስለሆኑ የገነባውንም አካል እንደማይጠቅሙ፤ የመንግስት አገልግሎቶችንም ለማድረስ ከባድ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ካሳሁን አባባል፤ ለምሳሌ ያክል፣ አዲስ አበባ ውስጥ በዚህ መልኩ የተገነቡ ቤቶች አንድ ችግር ቢፈጠር እንኳን የእሳት አደጋ መኪና መግባት አይችልም፡፡ ውሃና መንገድን የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶችም ሊቀርቡበት አይችሉም፡፡ በእንዲህ አይነት ሁኔታ ውስጥም ደግሞ ደረጃውን የጠበቀና ለነዋሪዎች ምቹ የሆነ ከተማ መፍጠር እንደማይቻል እና ከፕላን ውጭ የሚከናወኑ ግንባታዎች ጉዳይ ተጨማሪ ችግር የሚፈጥር መሆኑ ታውቆ መታረም ይኖርበታል፡፡ ፕላንን የማስከበር ጉዳይንም ለድርድር ከማቅረብ መቆጠብ ያስፈልጋል፡፡
ሕገወጥ ግንባታን የሚያከናውኑ የቤት እጥረት ያለባቸው ብቻ አይደሉም፤ የፕላን ጥሰትን መቆጣጠር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ከከተሞች ከንቲባ የሚጠበቀው አንዱ ዋና ስራም ፕላን ማስከበር እንደመሆኑ፤ ችግሩን ለህዝቡ ማሳወቅና ህዝቡ እንዲቆጣጠረው ማድረግ ይገባል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትም፣ ቤት ማቅረብ እና የከተማውን ፕላን አዘጋጅቶ የመከተል ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 17/2011
ወንድወሰን ሽመልስ