“ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም” የሚለውን ስም ኢትዮጵያውያን ቀድም ሲልም ስንሰማው የቆየን ቢሆንም፣ ከአውሮፓውያኑ የዘመን አቆጣጠር 2016 ጀምሮ የጤና ጉዳይን በተመለከተ በዓለማችን ላይ በተደጋጋሚ የምንሰማው ስም ሆኖ ቆይቷል።
ሰውየው የበላበትን ወጪት ሰባሪ ሆኖ አንጂ በኢትዮጵያውያን ሀብት ተምሮ፣ በኢትዮጵያውያን መንፈስ ተቀርፆ ፣ክፉ አይንካህ እንቅፋት አይምታህ ተብሎ ለጥሩ ደረጃ እንዲደርስ እንትፍትፍ ተብሎለት በአገሩ ጉያ ውስጥ ያደገና አሁን ለሚገኝበት ዓለም አቀፍ ስፍራም የደረሰ ነው።
ከጤና ኦፊሰርነት እስከ ጤና ጥበቃ ሚኒስትርነት የደረሰ የተለያዩ የግል ስኬቶች ማስመዝገቡ የሚነገርለት ከመሆኑ አኳያም ለጥቂት ዓመታትም ቢሆን ሁሉም ኢትዮጵያዊ ይህን ሰው በሥራውና በእውቀቱ አሞግሶታል ፤ አክብሮታል። ሰውዬው ለሀገር ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካም ይጠቅማል በሚል መንግሥት ከፍተኛ መዋእለ ነዋይ አውጥቶ በዓለም የጤና ድርጅት የዳይሬክተር ጀነራልነት ስልጣንን እንዲጨብጥ ብዙ የዲፕሎማሲ ሥራ ሠርቷል። ይህም ለአገርም፣ ለአህጉሩም ለራሱም ክብርና የኩራት ደረጃ እንዲቀዳጅ አግዞታል።
ለዚህ ነበር በ2016 ግንቦት ወር ላይ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር የነበሩት ደቡብ አፍሪካዊቷ ዲላሚኒ ዙማ ዶክተር ቴዎድሮስ ለዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጀነራልነት እንደሚወዳደር ይፋ ሲያደርጉ ብዙዎቻችን ደስታችንን የገለጽነው።
ኢትዮጵያውያን ከሚከፍሉት ታክስ ተሰብስቦ በሎቢስቶች ጉትጎታ ምርጫውን እንዲያሸንፍ የተደረገ ሲሆን፣ በዓለም ጤና ድርጅት መሪነት ለአፍሪካውያን ብቸኛውና የመጀመሪያው የሆነው ሰው ስልጣኑን እንዲቆናጠጥ ያለምንም ተቃውሞ ኢትዮጵያውያንም አፍሪካውያንም ድምፅ በመስጠት ደግፈውታል።
ሀገሪቱ ግለሰቡ የአለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ሆኖ እየሠራም ጭምር ድጋፍ ከማድረግ አልተቆጠበችም። በተለይ በዓለም የጤና ድርጅት ውስጥ ዳይሬክተር ጀነራል ከሆነ በኋላ በተከሰተው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት ሃያሏን አሜሪካ ጨምሮ በርካታ የዓለም አገራት “ወረርሽኙ ዓለም አቀፍ ስጋት ነው በሚል በተገቢው ጊዜ አልታወጀም። በዚህ ምክንያት የዓለም የጤና ድርጅትና ዳይሬክተር ጀነራሉ ተጠያቂ ናቸው። ከቻይና የሙከራ ላብራቶሪ ውስጥ የተነሳ ሰው ሠራሽ ባይሎጂካል መሳሪያ ነው። መረጃ ይፋ እንዳይደረግ ሽፋን ሆኗል” የሚል ክስ እየቀረበበት ከስልጣኑ እንዲገለል ከፍተኛ ጫና ሲደረግበት ኢትዮጵያውያን ይህን ለመቃወም የቀደማቸው አልነበረም። መንግሥትም አፍሪካውያንን በማስተባበር ጭምር ከ“ጎንህ ነን” በሚል ከፍተኛ ንቅናቄ በማድረግ ታግሎለታል።
ይህ ሀገር ብዙ የወጣችበትና የደከመችበት ሰው ግን ሀገሩ በምትፈልገው ወሳኝ ሰዓት ላይ ክዷታል። የአሸባሪው ህወሓት ቀኝ እጅ ሆኖ በዓለም አቀፍ ደረጃ የያዘውን ስልጣን በመጠቀም ኢትዮጵያን መካዱን የሚያመለክቱ በርካታ ወንጀሎችን ፈጽሟል። ይህ ግለሰብ አሁን እያደረገ ያለው የጥፋት ተግባር ሲታሰብ ፊትም የአሸባሪው ትህነግ ሥራ አስፈፃሚ ሆኖ የብዙዎችን ህልም ሲያከሽፍና አገር በማፍረስ የሴራ ጉንጎና ውስጥ ሲሳተፍ አልቆየም ተብሎ አይታሰብም ብሎ መናገር ስህተት አይሆንም።
“ባጎረስኩ እጄን ተነከስኩ” እንደሚለው የአገሬ ሰው በአገር ውስጥ ሃይ ባይ ያጣው አሸባሪው ትህነግ በሰሜን እዝ ላይ የፈጸመውን ክህደት ተከትሎ የህግ ማስከበር ዘመቻ ሲካሄድ አንስቶ ግን የለበሰው “የበግ ለምድ ሲገለጥ” ማንነቱ ቁልጭ ብሎ ወጥቷል። በህግ ማስከበር ዕርምጃው የተደናገጠውና ጀሌዎቹ የተነኩበት ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም አራስ ነበር ሆኖ እንዳበደ ውሻ ተክለፍልፎ ብዙ የሚያስተዛዝቡ ድርጊቶችን በአስተማረውና ደግፎ ባቆመው የኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ወስዷል።
የመጀመሪያው ድርጊቱ ያለውን ዓለም አቀፍ ግንኙነትና ስልጣን ተጠቅሞ መንግሥታት የተሳሳተ መረጃ እንዲያገኙ፣ መንግሥትና ኢትዮጵያውያን በትግራይ ህዝብ ላይ ግፍና መከራ እያደረሱ ነው የሚለውን የማስመሰል ዕርምጃውን የጀመረው ወዲያውኑ ነበር። በዚህ ሳያበቃ ኃያላን አገራት በኢትዮጵያውያን ጣልቃ አንዲገቡ ጫና እንዲያሳድሩ ፣ በአንጻሩ ደግሞ ተደቁሶ የቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ የገባውን ትህነግ ከገባበት ጎሬ አውጥተው እንዲደግፉ ለማድረግ ያላንኳኳው በር፣ ያልጠናው የባለስልጣን ደጅ የለም።
አፍሪካውያን ሳይቀሩ ከኢትዮጵያውያን በተቃራኒ እንዲቆሙ እዚያው በራፋቸው ድረስ እየሄደ ይለምንና ያለውን ኔትወርክና ስልጣን በቀጥታም በተዘዋዋሪም በመጠቀም ጫና እንዲደረግ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም። አሁንም ይህንኑ እያደረገ ይገኛል። በዚህ ድርጊቱ ለጊዜውም ቢሆን የሚዲያውንና የዲፕሎማቶችን ዓይን በተሳሳተ መረጃ በማንሸዋረር ኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲፈጠር አድርጓል።
የዚህ ሰው ጭካኔና የኃያላኑ አገራት ዝምታ አስገራሚ እየሆነና ልባችንን እየሰበረ የመጣው አሸባሪው ትህነግ አከርካሪው ሲሰበርና ዳግም በክራንች እንኳን እንዳይቆም ሲመታ ህዝቡን በተለይ ደግሞ “ሕፃናትን” በግዳጅ ወደ ጦር ግንባር እየማገደ ባለበት ሁኔታ ከጀርባ ቀጥተኛ ድጋፍ እያሳየ መሆኑን ስንመለከት ነው።
ይህ ሰው እና የአሸባሪው ትህነግ ባለስልጣናት ልጆቻቸውንና የልጅ ልጆቻቸውን በአውሮፓና አሜሪካ አስቀምጠው የሰፊውን የትግራይ ህዝብ ልጆች ለስልጣናቸው ማራዘሚያ እያፈሱ ወደ ግንባር እያላኩ ይገኛሉ። እነዚህን ጨቅላዎች መሳሪያ እያሸከሙ፣ ሀሺሽ እንዲጠቀሙ እያደረጉ ለጦርነት እየማገዷቸው ነው።
“እባብ ቆዳውን ይቀይራል እንጂ ባህሪውን አይለውጥም” የምንለው ደግሞ ዶክተር ቴዎድሮስም ቃለመሃለ የፈፀመለት ኢትዮጵያን የማፍረስ ዘመቻን የዓለም ትልቁና ዋንኛው “የጤና ድርጅትን” እየመራም እንኳን ከእኩይ ተግባሩ አለመታቀቡን ስናይ ነው። ለዚህ ህልሙ ማስፈፀሚያ ደግሞ “ሕፃናትን” የእሳት እራት ማድረጉ በእጅጉ የሚነድ ነው።
በዓለም የጤና ድርጅት ውስጥ ያለውን ስልጣን፣ ከአሜሪካ ተራዶ ድርጅት መሪ “ሳማንታ ፓወር”፣ የአሜሪካ የአገር ውስጥ ፖሊሲ አማካሪና የቀድሞው የህወሓት ወዳጅ “ሱዛን ራይዝ”፣ አልጀዚራ፣ ቢቢሲና መሰል ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችና ከሌሎች ዲፕሎማቶች ጋር ቀጥተኛ ያልሆነ ግንኙነት በመመስረት ህግ የማስከበር ዘመቻው “የትግራይ ህዝብን ለማጥፋት፣ ሴት ለመድፈርና ለስልጣን ሽኩቻ” የሚደረግ ተደርጎ እንዲታይ በማድረግ ለጊዜውም ቢሆን የውሸት መጋረጃ እንዲሠራ አድርጎታል። በዚህ መነሻ ታዳጊ ሕፃናት መሳሪያ አንስተው የመትረየስ ጭዳ እንዲሆኑ ሲያደርግ በጦር ወንጀል የሚጠይቀውና “ሃይ” የሚለው አንድ ኃይል እስከአሁን አልተገኘም።
ዶክተር ቴዎድሮስ የሀገራችን የጤና ሚኒስትር በነበረ ጊዜ በኤችአይቪ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ሕፃናት ተረክቦ ያሳድግ አንደነበር አስታውሳለሁ። ታዲያ አሁን ሕፃናት እየታፈሱ ለጦርነት ሲማገዱ ፣ ሀሺሽ እንዲጠቀሙ ሲደረጉ ለምን ዝም አለ?
እነ አሜሪካ “በኮቪድ ወረርሽኝ” ምክንያት ጥቅማቸው ሲነካ የዓለም የጤና ድርጅትን በማብጠልጠል፣ የገንዘብ ድጋፍ በማቆም እንዲሁም አፍሪካውያን ትላልቅ ተቋማትን መምራት አይችሉም የሚሉ ምክንያቶችን በማንሳት ከፍተኛ ጫና ሲፈጥሩ የቆዩ ቢሆኑም ፣ አሁን ግን በቀጥታ በዳይሬክተር ጀነራሉ ድጋፍና ምክር ጭምር “ሕፃናት” በጦር ሜዳ እንዲሰለፉ ሲደረግ፣ በምስጢር በዘረጋው ኔትወርክ አማካኝነት ጦር መሳሪያ ሲያስታጥቅ “አርምሞ” ውስጥ መግባታቸው ከምን የተነሳ ይሆን?
ድርጊቱ ግን እንኳን የድርጅቱን ስልጣን ይዞ እንዲቆይ አይደለም በቀጥታ ወደ ወህኒ እንዲወረወር የሚያደርግ “በጦር ወንጀለኝነት” የሚያስጠይቅ ነበር። ይሁን እንጂ ሁሉንም ጉዳይ ከራሳቸው ጥቅም አንፃር “የሚሰፍሩት” የበለፀጉት አገራት ፍትህን፣ ሰብዓዊነትን፣ ዴሞክራሲንና በስልጣን መባለግን ችላ በማለት “እውነትን አደባባይ” ሰቅለዋታል። ለመሆኑ ይህ እብደትና ዝምታቸው እስከመቼ ይሆን የሚዘልቀው?
ሰውየው ልጆቹን የልጅ ልጆቹን ጨምሮ በቅንጡ ህይወትና ትምህርት በአውሮፓና በሰለጠኑ አገራት እያኖረ የትግራይ ሕፃናት ወደ ጦር ግምባር እንዲዘምቱና በአጭሩ ህይወታቸው እንዲቀጭ እየገፋፋ ይገኛል። ለመሆኑ እርሱስ ቢሆን ከዚህ እብደትና ቅዠቱ መቼ ይሆን የሚነቃውና ራሱን ለፍርድ የሚያበቃው? ጊዜ ፍርዱን ይሰጣል!!
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18/2013