በዛሬው የአዲስ ዘመን ዱሮ አምዳችን በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ በተለያዩ ዓመታት የወጡ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ፣ ስፍር በማጭበርበር የተፈጸሙ ወንጀሎችንና ሌሎች ጉዳዮችን የሚመለከቱ ዘገባዎችን ይዘን ቀርበናል፡፡
ከዋጋ በላይ የሸጡ 30 ነጋዴዎች $ 2,620 ተቀጡ
(ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት)
ከተመኑ በላይ ዋጋ ጨምረው ሲሸጡ የተገኙ ፴ የልዩ ልዩ ሸቀጣ ሸቀጥ ነጋዴዎች ፍርድ ቤት ቀርበው ፪ ሺህ ፮፻፳ ብር የተቀጡ መሆናቸውን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድና ሥራ ዋጋ መቆጣጠሪያ መምሪያ ትናንት ገለጠ፡፡
ሠላሳዎቹ የሸቀጣ ሸቀጥ ነጋዴዎች የተጠቀሰውን የገንዘብ ቅጣት ፍርድ ቤት ቀርበው የተበየነባቸው ለተጠቃሚው ሕዝብ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ካወጣው ሕጋዊ የገበያ ዋጋ ተመን በማስበለጥ ዕቃዎችን በመሸጣቸው ፤እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ ዕቃዎች መደብራቸው ውስጥ ደብቀው የለንም በማለት ሸማቹን ሕዝብ በመመለሳቸው ነው፡፡
እነዚሁ ነጋዴዎች የቆርቆሮ ሰርዲን ፣ ዕንቁላል፣ የኤሌክትሪክ አምፖል፣ ሲጋራና እንዲሁም ሳሙና ከተተመነው ሒሳብ አስበልጠው መሸጣቸውን ከዋጋ መቆጣጠሪያ ክፍሉ የተሰጠ መግለጫ ያረጋግጣል፡፡
ከዚህም ሌላ ሁለት ሴቶች በመስቀል ተራራና በካዛንቺስ አካባቢ ያፈቃድ የአልኮል ንግድ ቤት ከፍተው በመነገዳቸው የ5ኛ ወረዳ ፍርድ ቤት ቀርበው እያንዳንዳቸው ፻ ብር መቀጣታቸው በተጨማሪ ተገልጧል፡፡
(ሰኔ 6 ቀን 1967 ከወጣው አዲስ ዘመን)
ሥፍሩን በማጉደል ገበያተኛ ያጭበረበረ 50 ብር ተቀጣ
ደሴ(ኢ-ዜ-አ-)፡- እህል የሚሰፈርበትን ቆርቆሮ ውስጡን በልዩ ልዩ ዘዴ በጨርቅ ጠቅጥቆ ሥፍሩን በማጉደል ሲሸጥ የተገኘው አሰፋ በዛብህ ፶ ብር መቀጫ እንዲከፍል የራያና ቆቦ አውራጃ ፍርድ ቤት ባለፈው ሳምንት ፈረደ፡፡
አሰፋ በዛብህ የተባለው ይኸው የእህል ነጋዴ ይህ ቅጣት ሊደርስበት የቻለው ባለፈው ወር በአላማጣ ከተማ ቅዳሜ ገበያ ላይ አለፎም ፀጋዬ ለተባለው ሰው በዚሁ በጨርቅ በተጠቀጠቀ ጣሳ ማሽላ ሲሸጥ በሥራ ላይ በነበሩት በክፍሉ ፖሊሶች መከታተል ተይዞ ነው፡፡
አሰፋ በዚሁ አድራጐቱ ተከሶ ጥፋተኛነቱን ራሱ ከማመኑም በላይ በማስረጃም ስለተረጋገጠበት ከላይ የተጠቀሰውን መቀጫ እንዲከፍል ተወስኖበታል ሲሉ የወሎ ጠቅላይ ግዛት ፖሊስ ማስታወቂያ ክፍል ገልጧል፡፡
(ሐምሌ 2 ቀን 1962 ከወጣው አዲስ ዘመን)
የሆድ ቁርጠት አድናለሁ ብሎ በጥይት ገደላት
ኤፌሶን፡-(ኢ-ዜ-አ-)፡- የሆድ ቁርጠት ትታመም የነበረችውን አንዲት ወጣት በጠመንጃ አስፈራርቶ ለማዳን የተደረገው ሙከራ የወጣቷን ሕይወት አጠፋ፡፡
በዚሁ በአላዋቂነትና ቸልተኝነት በተፈጸመው ሙከራ ከሆዷ ላይ በጥይት ተመትታ የሞተችው ወ/ሮ ተዋበች ማሞ የተባለች የ20 ዓመት ወጣት ናት፡፡
ይኸው ድርጊት የተፈጸመው በይፋትና ጥሙጋ አውራጃ ግዛት በካራ ቆሬ ከተማ ነሐሴ ፭ ቀን ፷፪ ዓ/ም ሲሆን ፤ወጣቷ በዚሁ ጠንቅ ሕይወትዋ ያለፈው በማግስቱ መሆኑ ታውቋል፡፡
ይኸው አደጋ ሊደርስ የቻለው ፤እመት ማሚቴ የተባሉት የሟችዋ ወላጅ እናት የሆድ ቁርጠት ያደረባትን ወጣቷን ልጃቸውን ለማዳን አቶ ወርቁ ወልደየስ የተባለውን የጎረቤት ሰው ጠሩት፡፡
ከዚያም አቶ ወርቁ የባለቤትየውን ፍሎበር ጠብመንጃ ከራስጌ አስወርዶ ቃታውን በመክፈትና በመግጠም ‹‹ ውጋት እኔ ቀደምኩህ ›› እያለ ከታመመችው ወጣት ሆድ ላይ አፈሙዙን አዙሮ ማላጩን በመሳብ የገደላት መሆኑ ታውቋል፡፡
የአካባቢው ሕዝብ የዚህ ዓነቱን በሽታና የመከላከያ ዘዴ ‹‹ጉስምት›› ብለው እንደሚጠሩት ለማወቅ ተችሏል፡፡
(ነሀሴ 12 ቀን 1962 ከወጣው አዲስ ዘመን)
ቶዮታ መኪና በደራሽ ጐርፍ ተወሰደች
ጎንደር፡-(ኢ-ዜ-አ-)፡- አብርሃም ዓምደ ማርያም በተባለው ሹፌር ይነዳ የነበረው ቁጥር 3237 አዲስ አበባ የሆነ ቶዮታ መኪና ባፈው ረቡዕ ድርማ በተባለው ወንዝ ደራሽ ጎርፍ ተወሰደ፡፡
የስዊድን መንግሥት ተራድኦ ድርጅት ንብረት የሆነው ቶዮታ መኪና የተወሰደው ድርጅቱ ከሰቀልት ም/ወረዳ ሕዝብ ጋር በመተባበር በዚሁ ቀበሌ ለሚሠራው ት/ቤት መሣሪያዎች አድርሶ ሲመለስ ወንዙን በማቋረጥ ላይ እንዳለ ድንገት በደረሰው ጐርፍ ነው፡፡
ይሁን አንጂ በመኪናው ላይ ተሣፍረው የነበሩት ሾፌሩና የክፍሉ አላፊ አቶ ዮሐንስ ሥዕሌ ምንም ጉዳት ሳያገኛቸው ከአደጋው ተርፈዋል፡፡
ጐርፉም መኪናውን አንድ ኪሎ ሜትር ያህል ከወሰደ በኋላ ፤ከአንድ ከቆመ ድንጋይ ተደግፎ ይታያል፡፡ ሆኖም ከጠቅላይ ግዛቱ ፖሊስ መምሪያ ለርዳታ የተላኩት የትራፊክ ፖሊሶችና ቴክኒሺያኖች የውሃው ሙላት ወደ መኪናው ሊያቀርባቸው ስላልቻለ በርቀት ፎቶግራፍ ብቻ አንስተው መመለሳቸውን የመቶ አለቃ ብርሃኑ አመራ የጠቅላይ ግዛቱ ፖሊስ የወንጀል መከላከያ ዋና ሹም አስታውቀዋል፡፡
በቤጌምድርና ሰሜን ጠቅላይ ግዛት በጐንደር አውራጃ በደንቢያ ወረዳ የሚገኘው ይኸው የድርማ ወንዝ በዚሁ ቀን በተመሳሳይ ሁኔታ ለእንጨት ለቀማ የተሰማሩ ሁለት ሴቶች የወሰደ መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡
(ነሀሴ 12 ቀን 1962 ከወጣው አዲስ ዘመን)
በኢትዮጵያ 22 የወሬ ወኪሎች ይገኛሉ
በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኘው የውጭ አገር የወሬ ወኪሎች ማህበር ሚያዝያ 20 ቀን 1956 ዓ.ም ባደረገው ልዩ ስብሰባ ሚስተር አንድሬ ዳቪ የተባሉትን ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ ሆኖ የቀይ ባህር አካባቢ አገሮች የአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ዳይሬክተርን ለአንድ ዓመት የማህበሩ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ በአንድ ድምጽ መርጧል፡፡
በተደረገው ስብሰባ የማህበሩ አባሎች ኮሚቴው አንዲስፋፋ ሀሳብ ለሀሳብ ተለዋውጠው ቀጥሎ በተመለከተው አይነት የማህበሩን ስራ መምሪያ አባሎች መድቧል፡፡
ፕሬዚዳንት ሚስተር አንድሬ ዳቪ ምክትል ፕሬዚዳንት ሚስተር ግራም ታያር አስቲዋርት የብስራተ ወንጌል ራዲዮ ጣቢያ ወሬ ዋና አዘጋጅ ፣ ጸሀፊ ሚስተር ክሬመር የዴይሊ ኤክስፕሬስ ጋዜጣ ወኪል ፣ የፐብሊክ ሪሌሽን መኮንን ሚስተር አህመድ ሻዲ የሚድል ኢስት ኤጀንሲ ወሬ ወኪል ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙት የውጭ አገር የወሬ ወኪሎች ቁጥር 22 መሆኑ የሚታወስ ነው፡፡
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 17/2013