ፋሽን በተለያየ መንገድ ይገለጻል። በተለይ “ፋሽን” የሚለውን ትክክለኛ መገለጫ የሚይዘው በአንድ የተወሰነ ወቅት ላይ በከተሞች፣ አገራትና፣በአህጉር ደረጃ ተደጋግሞ የሚከወን ድርጊት ሲሆንና በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ሲያገኝ መሆኑን የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ይህ ዘርፍ በተለየ መንገድ በአልባሳትና የውበት መጠበቂያዎች ላይ እንደሚያተኩር ይገለጽ እንጂ ግኡዝ የሆኑ አካላት ላይም የሚስተዋልና በሰው አረዳድና ፍላጎት ልክ እንደሚደራጅ ነው እነዚሁ የዘርፉ ባለሙያዎች የሚያስረዱት።
ወቅትና ፋሽን ጥብቅ ትስስር አላቸው ይባላል። ለምሳሌ ያህል መስከረም ምድርን በአበባ ፍንጣቂ አጊጣ በውብ ቢጫ ቀለም ታደምቀዋለች። ይሄ መስከረም የምትከተለው ፋሽን ነው። ክረምቱ በበጋ ወቅት ያልነበሩ እፅዋትን በተዓምራዊ የተፈጥሮ ስበት ከምድር ጉያ ውስጥ ፈልቅቆ አውጥቶ ድንቅ መስህብ ያላብሳል። ይሄ ተፈጥሮ ስታጌጥ ፋሽን ስትከተል እንደማለት ነው።
የሰው ልጆችም እንደየ አካባቢው ሁኔታና፣ ባህልና ወግ መሰረትም ውበታቸውንና አለባበሳቸውን ያስተካክላሉ። ያ ምቾትን ከማጎናፀፉ ባሻገር የአንድ ወቅት የሰው ልጅ ልማድ ይሆናል። ከዛ አለፍ ሲልም የማህበረሰቡ መገለጫና ባህላዊ እሴት ይሆናል።
ለዛሬ እኛም በፋሽን ገፃችን የአብዛኛው የመንዝ፣ጎጃም እና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች ተፈጥሮን ተረድተውና ከከባቢ አየሩ ጋር ተስማምተው የሚጠቀሙባቸውን የክብር አልባሳት አዘገጃጀትና ምንነት ልናስቃኛችሁ ወድደናል። ድሮ ድሮ ይሄ በመንዝ ማህበረሰብ በተለይ የሚታወቀው “በርኖስና መለወሻ” በዚያው በነዋሪው ዘንድ ይዘወተር የነበረ ቢሆንም አሁን አሁን በተለይ ክረምቱን ተከትሎ “የቡሄ በዓል” ሲከበር እንደ ፋሽን ተወስዶ በተለያዩ ከተማዎች ውስጥ “ፋሽን” ተደርጎ ይለበሳል።
በርኖስ በበግ ፀጉር የሚሠራና በካባ መሰል ቅርጽ ተዘጋጅቶ የሚለበስ ሀገረሰባዊ ልብስ ሲሆን፣ በአብዛኛው የሚለበሰው በጣም ቀዝቃዛና ደጋማ በሆኑ አካባቢዎች ነው፡፡ በርኖስ የእጅ ማስገቢያ እጅጌ እንዲሁም በቀኝ ትከሻ በኩል ወደላይ ቀጥ ብሎ የወጣና እንደጌጥ የሚያገለግልና የመሣሪያቸውን አፈሙዝ ደግፎ በመያዝ አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡
በርኖስ በጥንት ጊዜያት በቀዝቃዛና በደጋማ አካባቢዎች የሚለበስ የዘወትር ልብስ የነበረ ሲሆን፣ በሌሎች የማኅበረሰቡ አካባቢዎች ግን ተጨማሪ አገልግሎት አለው፡፡ በዚህም መሠረት በሠርግ ጊዜ ሴቷ ሙሽራ ለወላጆቿ ቤት ወደ ወንዱ ቤተሰብ ስትሄድ የምትለብሰው ልብስ ሲሆን፣ በሙሽራውም የክብር ልብስ በመሆን ያገለግላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በርኖስ ወንዶች/አባቶች በኀዘን ጊዜ የሚለብሱና ኀዘን እንደገጠማቸው የሚያመለክት ሲሆን፣ በጎጃም ማኅበረሰብ አንድ ሰው በርኖስ ገልብጦ በውስጠኛው መልክ ከለበሰ ኀዘን እንደደረሰበትና የቅርብ ዘመዱን በሞት እንደተነጠቀ ያመለክታል፡፡
በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ በርኖስ የሚለበሰው በሽምግልና ወቅት፣ ለጋብቻ ጥየቃ ጊዜ፣ በክብረ በዓላት ወቅት/ጥምቀት፣ ገና፣ ፋሲካ፣ በለቅሶ ወቅት፣ በተለይም ትልልቅ ሰዎች በሚሞቱበት ጊዜ በአጠቃላይ በክብር ቦታዎች ላይ የክብር መገለጫ ሆኖ የሚለበስ ነው፡፡
በአካባቢው ማኅበረሰብ በርኖስ የሚለብሱት አዛውንቶች፣ ታዋቂ ወንዶችና የትልልቅ ሰዎች ባለቤት፣ ለልጆቻቸው አርአያ መሆን የቻሉ ጨዋ ሴቶች ሲሆኑ፣ ወጣቶች አይለብሱም፤ እንዲለብሱም አይፈቀድም፡፡ ወንዶቹና ሴቶቹ የሚለብሱት በርኖስ ልዩነቱ አሰፋፉ ላይ ብቻ ነው፡፡ አሠራሩ ግን ተመሳሳይ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡
የለቅሶ ጊዜ አለባበስን በተመለከተ የውስጡ ወደላይ ተገልብጦ እጀታው ታጥፎ ሲሆን፣ በደስታ ጊዜ ግን በትክክለኛ መልኩ በኩል እጀታው ብቅ ብሎ ይለበሳል፡፡ ከዚህ ሌላ በአካባቢው ማኅበረሰብ ዘንድ አንድ ኀዘን የደረሰበት ሰው ኀዘንተኛ መሆኑን ለመግለጽ በርኖሱን ገልብጦ በመልበስ ይታወቃል፡፡
አዘገጃጀቱ
የበርኖስ ሥራን ለመሥራት በጥሬ ዕቃ አቅርቦት የሚመረጠው የጥቁር ጠቦት በጎች ብቻ መሆኑ፣ የበጎቹ የጸጉር ቁርጥ ወይም ሽለታ የመጀመሪያ ብቻ መሆኑና ሁለተኛ ቁርጥ አለመሆኑ ነው፡፡
ከዚህ ሌላ በርኖሱ ከተሸመነ በኋላ አረጋገጡ ከባና ዝግጅት መለየቱ ነው፡፡ ይኼውም የበርኖሱን የመጀመሪያ የሽመና ሥራ ወይም ሽክሽክ ጸጉሩ እንዲደፍንና እንዲለሰልስ በሚል ለመጀመሪያ ጊዜ ለሁለት ቀናት ያህል ሳይቋረጥ ይረገጣል፡፡ ከዚህ በኋላ በቀጥታ ለአገልግሎት ከመዋሉ በፊት አልጋ ወይም ቁርበት ስር እስከ አንድ ወር ድረስ ተነጥፎ ይቆያል፡፡ ከአንድ ወር ቆይታ በኋላ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ለሦስት ቀናት ያህል በድጋሚ ተከልሶ ይረገጣል፡፡
በዚህ ሁኔታ ተረግጦ ጸጉሩ ከለሰለሰ በኋላ ፀሐይ ላይ እንዲደርቅ ይደረጋል ከደረቀ በኋላ እየተቀደደ ቅርጹን በማውጣት በዶሮ ላባ ይሰፋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ስፌቱ ካለቀ በኋላ በ‹መሀራረብ› ጃኖ መልክ ክር ዙሪያውን በመቀምቀም ለአገልግሎት ይውላል፡፡ የበርኖስ ሥራ ላይ ወንዶቹም ሆነ የየራሳቸው ተሳትፎ አላቸው፡፡
ሴቶቹ የበጉን ጸጉር በማባዛት ወይም መፈታታት፣ በመፍተል፣ በማዳወርና የመሳሰሉት ወንዶች ደግሞ በጎቹን ከማጠብ ጀምሮ በመሸመን፣ በውኃ ዘፍዝፎ በመርገጥ፣ በርኖሱን ቅርጹን ጠብቆ ሰፍቶ ለአገልግሎት እስኪውል ድረስ ባለው ሒደት ተሳትፎ አላቸው፡፡ የበርኖስ ሥራ ካባና ሥራ የሚለየው የሚለበስበት ጊዜ የተለየ መሆኑ ነው፡፡
መላወሻ
በማንኛውም የኀብረተሰብ ክፍል ሴቶቹም ሆኑ ወንዶቹም የየራሳቸው የአለባበስ ሥርዓት አላቸው፡፡ ከዚሁ ጋር የሥራ፣ የቤት፣ የክትና የአደባባይ ልብሶች ተብለው እንደየሁኔታው ተለይተው የሚለበሱ ልብሶችም ይኖራሉ፡፡ ከዚህ አኳያ በመንዝ ማኅበረሰብም ‹‹መላወሻ›› የሴቶች የክትና የክብር ልብስ ተብሎ የሚታወቅ እንደሆነ መረጃ ሰጪዎች ይገልጻሉ፡፡
መላወሻ እንደ ዝተትና ባና ተመሳሳይ የሽመና ቁሳቁስና የአሸማመን ወይም የአሠራር ሥርዓት አለው፡፡ የመላወሻ ዕደ ጥበብ ውጤት ከሌሎች የዕደ ጥበብ ውጤት የሚለየው የበጎቹ የፀጉር ሁኔታ ነው፡፡ ሥራውን ለማከናወን ከሕፃናት በቀር በየደረጃው ያሉ ሴቶችም ሆነ ወንዶቹ ይሳተፋሉ፡፡
በዚህ ሥራ የሴቶቹ ተሳትፎ ፀጉርን ማብዛት፣ መፍተል፣ ማዳወርና መንደፍ ይሆናል፡፡ ወንዶቹ በበኩላቸው በጉን በማጠብ፣ የበጉን ፀጉር በመሸለት ወይም በመቁረጥ፣ በመሸመን፣ በመርገጥና በመገተር ወይም በመወጠር ይሳተፋሉ፡፡ የመላወሻ ሥራ ዕውቀት የተገኘው እንደባናና ዝተት ሥራ ሲወርድ ሲዋረድ ከመጣ ከቤተሰብና ከሙያው ባለቤቶች ሙያውን በመልመድና በመቅሰም እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
የመላወሻ ዕደ ጥበብ ውጤት የሴቶች ብቻ የክት ልብስ ሲሆን፣ አለባበሱ እንደጉርድ ቀሚስ ዙሪያውን በመቀነት ሰብስቦ በማሰርና ከላይ እንደ አላባሽ ጥለት ያለው ነጠላ በትከሻና ትከሻቸው ነጥሎ፣ እንደሁኔታውም በኀዘን ወቅት ጥለቱን አዘቅዝቆ በመልበስ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 17/2013