ኢትዮጵያ ረጅም የነፃነት ታሪክ ያላት፣ በሉዓላዊነቷ የማትደራደርና ልዩ ቦታ የምትሰጥ፣ በመከባበር ላይ ለተመሰረተ ግንኙነት ቦታ የሚሰጡ ወዳጆቿን ከልብ የምታከበር ታላቅ አገር ናት። ከዚሁ በተቃራኒ ባርነትን የማትቀበልና የምትጸየፍ፣ ለቅኝ ገዢዎች የአግር እሳት የሆነች፣ ዳቦን ከነፃነት ጋር ፈጽሞ የማታነጻጽርና ክብሯን ለሚዳፈር ቦታ የሌላት የዓለም የነፃነትና የወዳጅነት ተምሳሌት የሆነች ታላቅ አገር ናት።
አገራችን ባሳለፈችው ረጅም ዘመን ሉዓላዊነቷንና ክብሯን ለመድፈር ከቅርብ ከሩቅም ብዙ ተሞክሯል። ችግር ውስጥ በነበረችባቸው ጊዜያትም ዳቦና ዶለር እያሳዩ ክብሯን በዳቦ የምትቀይር መስሏቸው የማይሞከረውን የሞከሩና የዳከሩ አገራት ብዙዎች ናቸው። ደስ የሚለው ነገር ግን ሉዓላዊነቷን ለመዳፈር የሞከሩትም ሆኑ ነፃነቷን በዳቦ ለመለወጥ የዳከሩ ሁሉ ትርፉ ትዝብት ሆኖ አፍረው ቀርተዋል።
ሉዓላዊነቷን ለመዳፈር ሞክረው የሐፍረት ሸማ ከተከናነቡት ውስጥ ጣልያንን፣ ግብፅንና ሶማሊያን በምሳሌነት ማንሳት ሲቻል ነፃነቷን በዳቦ ለመለውጥ ሞክረው ካፈሩት ውስጥም አሜሪካንና አንዳንድ ምዕራባውያን አገራትን መጥቀስ ይቻላል። በ1960ዎቹ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በተስፋፊዋ ሶማሊያ በተደፈረበት ወቅት አገራችን ነፃነቷን ለማስከበርና ራሷን ከጥቃት ለመከላከል በራሷ ገንዘብ የገዛችውን መሳሪያ እንዳትወስድና መሳሪያም እንዳትገዛ ያደረጉ አገራት በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ በጥቁር ቀለም ተመዝግበዋል።
አሳፋሪው ነገር ደግሞ ኢትዮጵያ በራሷ ሀብት መሳሪያ እንዳትገዛ ተከልክላ እነዚሁ አገራት ለወራሪዋ ሶማሊያ መሳሪያ በዕርዳታ በገፍ የሰጡበት ሁኔታ መኖሩ ነው። ይህ ሁኔታም ይህንን የፈጸሙ ሀገራት ምን ህል መርህ አልባ እንደሆኑና ለወዳጅነትና ለታሪክ ደንታ ቢስ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው። ይሁንና ኢፍትሐዊዎቹ አገራት ለወራሪዎች ሊሰጡ የሚችሉት መሳሪያ እንጂ ልብና ወኔን አልነበረምና አውነትን ይዘው የዘመቱት ኢትዮጵያውያን በአኩሪ ጀብድ ወራሪን ጠራርገው በማስወጣት ከጀርባ ሆነው የደገፉ አገራትን ጭምር አሳፍረዋል።
ከእኛው ከኢትዮጵያውያን ምድር ከ85 በመቶ በላይ እየመነጨ ለዘመናት ሳንጠቀምበት በኖርነው በታላቁ የዓባይ ወንዛችን ላይ የታችኞቹን የተፋሰስ አገራት ጥቅም ሳንጎዳ ተጠንቅቀንና በሌለን አቅም በራሳችን አንጡራ ሀብት ታላቁን የህዳሴ ግድባችንን መገንባት በጀመርንበት ጊዜም እነዚሁ ኢፍትሐዊና ምንይሉኝን የማያውቁ አገራት ከኢፍትሐዊዋ ግብፅ ጋር አብረው ሊያሸማቅቁንና ቢችሉም ሊያስቆሙን ያልቆፈሩት ገደል አልነበረም።
ሆኖም አሁንም እውነትና የእውነት አምላክ ከኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ጋር ነበሩና እንኳን ማስቆም ማዘግየትም ሳይችሉ ጥረታቸው ሁሉ ከንቱ ሆኖ ቀርቷል። ይልቁኑ የእነዚህ አገራት ያልተገባ ድፍረት ለኢትጵያውያን ወኔ ሆኗቸው የግድቡን ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ለፍጻሜ አብቅተው የሀብታቸውን የመጀመሪያ ፍሬ ለመቋደስ በዋዜማው ላይ ይገኛሉ። ከላይ በዝርዝር የተመለከትናቸው እነዚህ እውነቶች ኢትዮጵያ ለክብሯና ለሉዓላዊነቷ ያላትን ክብር እንዲሁም እውነትን የያዘ ሁሌም አሸናፊ መሆኑን የሚያመላክቱ ናቸው።
በጣም የሚያኮራውና መልካሙ ነገር ደግሞ የኢትዮጵያን ሉዓላዊ አንድነትና ክብር ሁሌም የሚያከብሩና ከአውነትና ከፍትህ ጋር አብረው የቆሙ ብዙ ወዳጆች ኢትዮጵያ ያሏት መሆኑ ነው። እነዚህ አገራት ኢትዮጵያ ችግር ባጋጠማት ጊዜ ሁሉ በሚችሉት አቅም ከጎኗ በመቆም በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ገድላቸውን በወርቃማ ቀለም ጽፈዋል። ጉዳዮች ከፍትህ አደባባይ ለፍርድ በቆሙበት ወቅትም ከእውነት ጋር ብቻ በመወገን ታላቅነታቸውን አስመስክረዋል። በጣልያን ወረራ ወቅት ኢትዮጵያ በዚያኔው ሊግ ኦፍ ኔሽን ባቀረበችው አቤቱታ አውነቱን ተገንዝብው ከኢትዮጵያ ጋር የቆሙ አገራት ለዚህ ሰናይ ምሳሌዎች ናቸው።
ተስፋፊዋ ሶማልያ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ችግር እንደምቹ ዕድል ተጠቅማ አገራችንን በወረርችበትና በዜጎቻችን ላይ ግፍ በፈጸመችበት ወቅት ከጎናችን ተሰልፈው የህይወትና የአካል መስዋዕትነት የከፈሉ እንደ ሩሲያ፣ ኩባና የመን ያሉ አገራት የኢትዮጵያ እውነተኛ ወዳጅነታውን በወሳኝ ወቅት በደምና ህይወት ዋጋ አረጋግጠዋልና ኢትዮጵያውያን መልካም ተግባሮቻቸውን ለዘላለም ሲዘክሩት ይኖራሉ።
ታሪክ የማይቆም ሂደት ነውና ዛሬም ኢትዮጵያውያን እውነተኛ ወዳጅና ጠላታቸው ማን እንደሆነ በሚመዝኑበት ወቅት ላይ እንገኛለን። ለማንም ግልጽ እንደሆነው አሸባሪው ህወሓት አገር የማፍረስ ተልዕኮን አንግቦ በኢትጵያውያን ላይ ሊነገር የማይችል ገፍ እየፈጸመ ይገኛል። ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር በማበርም ኢትዮጵያን ለማፍረስ ሲዖል ድረስ እሄዳለሁ በሚል መፈክር አለኝ ያለውን የጥፋት ጥይት ሁሉ በኢትዮጵያ ላይ እየወረወረ ይገኛል። ይህንን ተከትሎም መላ ኢትዮጵያውያን ከጫፍ ጫፍ በአንድነት ተሰልፈው አገራቸውን ከጥፋት ኃይል ለመታደግ በክተት ላይ ናቸው።
በዚህ ወሳኝ ወቅት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብም በሁለት ጎራ ተከፍሎ ይታያል። ከፊሉ የአሸባሪውና የጥፋት ኃይሉ ጋሻ ጃግሬ ሆኖና የተዳከመች ኢትዮጵያን አውን ማድረግን አልሞ በማስፈራሪያና ዛቻ ኢትዮጵያ ራሷን እንዳትከላከል ብሎም ይህን አጋጣሚ በመጠቀምም ተላላኪ መንግሥት በኢትዮጵያ ለመትከል እንቅልፍ አጥቶ እየሠራ ነው።
የቁርጥ ቀን ወዳጆቻችን ደግሞ የኢትዮጵያ ሉኣላዊ አንድነትና ግዛት ፈጽሞ መደፈር የለበትም በሚል መርህ የኢትዮጵያን ጉዳይ ለኢትዮጵያውያን እንተው የሚል አቋም በግልጽ በማራመድ ላይ ይገኛሉ። ከዚህ አንጻር ለማንም ግልጽ ሊሆን የሚገባው ጉዳይ ኢትዮጵያውን ለልማትና ለኢኮኖሚ ትብብር ትልቅ ቦታ የሚሰጡ ቢሆንም ነፃነታቸውን በዳቦ የመለወጥ ታሪክ የሌላቸው መሆኑ ነው!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 17/2013