የዝግጅት ክፍላችን እሁድ እሁድ ይዞት በሚቀረበው ሳምንቱን በታሪኩ አምድ በዘመን ትዝታ ውስጥ አይን የሚሞሉ ትውስታዎችን ይዞ ይቀርባል። በመዝገባችን ላይ ደጋግመን ብንከትባቸው ልንማርባቸው እንጂ ሊሰለቹን የማይችሉ በርካታ ክስተቶች አሉ። በየአመቱ ብናሞግሳቸው ቢያንስባቸው እንጂ የማይበዛባቸው ታላላቅ የአገር ባለውለታዎች ሞልተዋል። የዚያኑም ያህል ሁሌም ቢዘከሩ የማይሰለቹ ታላላቅ ክንውኖችም አሉ፡፡ ለዚህም ነው የታሪክ ዶሴዎችን በየሳምንቱ እየገለጥን ወደእናንተ አንባቢዎቻችን ፊት ልናቀርባቸው የወደድነው።
እየተገባደደ ባለው የነሐሴ ወር በዚህ ሳምንት አያሌ ሊታወሱ የሚገባቸው ታሪካዊ ክስተቶች ተፈጸመዋል፡፡ ከእነዚህ ሁነቶችና ታሪካዊ ክስተቶች መካከል ለዛሬ በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ግዙፍ ስፍራ ያላቸውን “የንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ” ታሪክን ቀንጨብ አርገን አቅርበናል፡፡ ለእዚህ መነሻ የሆነን ደግሞ ንጉሰ ነገስቱ የተወለዱት በዚህ ሳምንት መሆኑ ነው፡፡ ዳግማዊ አፄ ምኒሊክ ከአባታቸው ንጉስ ኃይለመለኮት እና ከእናታቸው ወይዘሮ እጅጋየሁ ነሐሴ 12 ቀን 1836 ዓ.ም በዕለተ ቅዳሜ በሰሜን ሸዋ ዞን አንጎለላ ቀበሌ ልዩ ስሟ እንቁላል ኮሶ በምትባል ቦታ ነው የተወለዱት፡፡
የኢትዮጵያውያን የኩራት ምንጭ የሆኑትን እኚህን ታላቅ ንጉስ ስናስብ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው የጥቁር ህዝብ ድል ያጎናፀፈውን “የአድዋ ድል” በተመሳሳይ ልንዘክር ግድ ይለናል። ምክንያቱም አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀራመት ባደረጉት ዘመቻ ጣልያን ኢትዮጵያን ለመያዝ የፈጸመችውን ወረራ ድል በማድረግ ሉአላዊነትን ማስከበር የተቻለው እኚህ ብልህ ጥቁር አፍሪካዊ መሪ መላ ኢትዮጵያውያን አስተባብረው በፈጸሙት ገድል ነው።
ከዚህ ባሻገር መላው ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር አንድነታቸውን ጠብቀው እንዲኖሩና የውስጥ ባንዳም ሆነ የውጪ ጠላት አገራቸውን ሊያጠቃ ቢሞክር ቀፎው እንደተነካ ንብ ተምመው ሉአላዊነታቸውን አንዲያስከብሩ ማድረግ ችለዋል። ስለዚህ ጉዳይ ስናነሳ የንጉሱን የሚከተለውን ንግግር እናስታውሳለን፦
«እናንተ አንድ ልብ ከሆናችሁ በምቀኝነት እርስ በርሳችሁ ተዋግታችሁ ካላለቃችሁ በቀር ኢትዮጵያ አገራችንን ለሌላ ባእድ አትሰጧትም፤ ክፉም ነገር አገራችንን አያገኛትም። ነፋስ እንዳይገባባችሁ አገራችሁን በያላችሁበት በርትታችሁ ጠብቁ፤ ወንድሜ ወንድሜ እየተባባላችሁ ተደጋገፉ፤ የኢትዮጵያን ጠላት ተጋግዛችሁ ተድንበር መልሱ።
የኢትዮጵያ ጠላት ባንዱ ወገን ትቶ ባንድ ወገን ቢሄድና ድንበር ቢገፋ፤ በኔ ወገን ታልመጣ ምን ቸገረኝ ብላችሁ ዝም አትበሉ፤ ያ ጠላት በመጣበት በኩል ሁላችሁም ሄዳችሁ በአንድነት ተጋግዛችሁ ጠላታችሁን መልሱ፤ እስከ እየቤታችሁ እስኪመጣ ዝም ብላችሁ አትቆዩ» የሚል ታሪካዊ መልእክት ከማስተላለፋቸውም ባሻገር፣ በዚህ መንገድ ኢትዮጵያውያንን በማስተባበር ሀገሪቱን ከውጪ ወራሪ በመጠበቅ “አድዋ” ላይ ጣሊያንን ድል አድርገው ዓለም ሲዘክረው የሚኖረው ታሪክ ሰርተው አልፈዋል። ለመሆኑ ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ ዳግማዊ አፄ ሚኒሊክ አመራርና ብልሃት ምን ይመስላል? የሚከተለው ዳሰሳ ይህንን ለመመለስ ይሞክራል።
አርቆ አስተዋይነት
ታሪካቸውን ከምናውቀው የኢትዮጵያ ነገሥታት ውስጥ አፄ ምኒልክን በአርቆ አስተዋይነት የሚወዳደራቸው እንደሌለ በርካታ የውጪና የአገር ውስጥ የታሪክ ተመራማሪዎችና ምሁራን በመፅሃፎቻቸው ላይ አስፍረዋል። ትልቁ የዚህ ስጦታቸው ምክንያት በመቅደላ የአፄ ቴዎድሮስ እስረኛ በነበሩበት ጊዜ ከሀገር ሊቃውንትና ከውጭ ሀገር እስረኞች ጋር መቆየታቸው ሳይሆን አይቀርም ሲሉ ብዙዎች በመላምታቸው ያስቀምጣሉ። መላው ኢትዮጵያውያን “እምየ ምኒልክ” እያለ እንዲጠራቸው ያስቻለውም ይሄው የአስተዋይነትና የአመራር ጥበብ ጥበባቸው ነው ይባላል።
አፄ ምኒልክ ዘውድ የደፉ ዕለት ከንጉሥ ሱስንዮስ ጀምሮ የተሠራውን ሠላሳ አምስት ሹመት ለጦር አበጋዞቻቸው መስጠታቸውን መረጃዎች ያሳያሉ። አፄ ዮሐንስም እንደ ባህሉ አድርገዋል። ሹመቱን የሰጡት ግን ለትግራይ ተወላጆች ብቻ ነበር። አፄ ምኒልክ ግን ከሌላ አካባቢ ለመጡት ጭምር እንጂ ለሸዋዎች ብቻ አልነበረም የሰጡት።
ቅድመ አድዋ ኢትዮጵያ እንደ ቴዎድሮስና እንደ ዮሐንስ ያሉ ታላላቅ ነገሥታት አግኝታ ነበር፤ ጀግንነትን፥ ሃይማኖታዊነትን፥ ብልሃተኝነትን ጎንጒኖ በመያዝ የታጠቀ ግን ምኒልክ ብቻ ነበሩ። ሪቻርድ ካውልክ ፤ ‹‹ከጅቦች መንጋጋ ውስጥ- የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ታሪክ ›› (Richard Caulk, Between the Jaws of Hyenas: A Diplomatic History of Ethiopia [1876-1896]) በሚል ርእስ በጻፈው መጽሀፉ፥ ንጉሰ ነገስቱ ከምዕራባውያን መንጋጋ ገብተው ያመለጡ መሆናቸውን አስፍሯል፡፡
ሌላው ታሪክ ጸሐፊያቸው (ጸሐፍ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ) ደግሞ ፤ ጥፋት የተገኘበት ሰው ገንዘቡን ተወርሶ እጁን ታስሮ መሬቱ ይሸጥ ነበር። ነፍስ የገደለ ሰውም ራሱ ቢያመልጥ ዘመዱ እስከ ሦስት ትውልድ መሬቱ ይነቀል ነበር። ንጉሠ ነገሥቱ ግን “ከዋያት በመለስ አዋሽ” ድረስ ያለውን የጋሻ መሬት ሁሉ እንደመንዝ ርስት አድርጌልሃለሁ። ምንም ብታጠፋ በገንዘብህ ተቀጣ እንጂ መሬትህ አይነቀል ብለው አዋጅ ነገሩ ሲሉ ጽፈዋል።
የኢየሩሳሌሙ የኢትዮጵያ ገዳም ታሪክም አፄ ምኒልክን የሚያስከብር ድርጊት እንዲህ ሲል መዝግቧል፤
ጥንት የክርስቲያን ሀገሮች በቅድስት ሀገር በኢየሩሳሌም ቦታ ሲይዙ ኢትዮጵያም ይዛ ነበር። ግን እዚያ የሚኖሩ መነኮሳት ሕይወት ነገሥታቱን ሁል ጊዜ ያስቸግር ነበር። በተለየ መንገዱ በሙስሊሞች ኃይል ስለተያዘ እንኳን ገንዘብ ሊላክላቸው ጳጳስ ከግብጽ የሚመጣው እንኳን በስንት ጭንቅ ነበር። አርቆ አስተዋዩ አፄ ምኒልክ መነኮሳቱን በወለዱ ሊያኖራቸው የሚችል ገንዘብ ኢየሩሳሌም በሚገኝ ባንክ አስቀመጡላቸው። መኳንንቶቻቸውም እዚያ ቤት እንዲያሠሩ መክረዋቸው፥ የሠሯቸው ቤቶች እስከዛሬ ይከራያሉ።
የአፄ ምኒልክና ስልተኛነትና የአድዋ ድል፤
አፄ ምኒልክ ስልተኛ መሪ መሆናቸውን ታሪካቸው ሲያሳየን፥ እውነትም እኮ አድዋ ላይ ለተገኘው ድል የንጉሡ የጦር አቅድ አውጪነት ትልቅ ስፍራ እንደሚሰጠው ይነገራል። ለምሳሌ ያህል፦ በንጉሠ ነገሥት አፄ ምኒልክ በኩል ኢትዮጵያ አዋጭ ያለችውን ዝግጅት ለአይቀሬው ጦርነት እያዘጋጀች ነው። ሃገራዊ ዝግጅቱ በንጉሠ ነገሥቱ በአፄ ምኒልክ የዘመቻና የጦርነት አዋጅ ይጀምራል። የአዋጁ ይዘት የዘመቻ ጥሪን ለኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ነዋሪዎችና ለሹማምንቶች ኢትዮጵያ በጠላት ጥርስ ውስጥ መግባቷንና የቅኝ ተገዥነት ዕጣፋንታዋ መቃረቡን፣በሕዝቦች የተባበረ ክንድ ግን ጠላትን መመከት እንደሚቻልና በቅኝ መገዛት እንደማይቻል የተገነዘቡት ንጉሠ ነገሥቱ፣ ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝቦች ይህን ታላቅ የጦር ክተት አዋጅ አወጁ።
ከታሪክ መረጃ ምንጮች የምንገነዘበው የምንረዳውም የሩቁንም ሆነ የቅርቡን የዘማች ሠራዊት ኃይል በማደረጀት ከሸዋና ከአካባቢው የተነሳው ዘማች ኃይል ወሎ ወረ ኢሉ ላይ እንዲከት፣ ከጎጃም፣ ከደምቢያ፣ ከቋራ፣ ከበጌምድር እና ከጨጨሆ በላይ ያለው ሀገር ሁሉ አሸንጌ ላይ እንዲከት፣ የሰሜኑንና የወልቃይት ጠገዴንም ሰው መቀሌ ላይ እንዲከት፣ የሐረር ዘማች በአዲስ አበባ በኩል ገና የጥቅምቱ ዘመቻ ሳይጀምር አዲስ አበባ ገብቶ ወረ ኢሉ እንዲከት፣ የወለጋው ሠራዊት መግባት የቻለው ገብቶ ክረምቱ በመስከረም ስለሚበረታ በውሃ ሙላት እንዲቆይ ተደርጓል።
ዋናው ቁም ነገር ግን አዋጁ ሀገራዊ ንቅናቄን መፍጠሩና መተግበሩ ስለነበር በትክክል ተተግብሯል ለማለት ይቻላል። ታላቁ ንጉሠ ነገሥት ሐይማኖትህን እና ሚስትህን የሚሉ ታላላቅ ጉዳዮችን ማካተታቸውን ስንመረምር ምን ያህል አርቆ አሳቢ መሆናቸውን እንረዳለን። ሰው በሚስቱ እና በሃይማኖቱ ከመጡበት ቀናኢ ነውና !
የዘመተው ሠራዊት ፍጹም ሕብረ ብሔራዊ ነበር። እገሌ እና እገሌ ሳይባባሉ ፈቃደኝነት ላይ በተመሠረተ የንጉሠ ነገሥቱን አዋጅ ተቀብለው በሀገራዊ፣ በወገናዊና በባሕላዊ ጉዳዮች የጋራ ትስስር፣ የጋራ መግባባትና በኢትዮጵያዊነት ወኔ ተሞልተው ታሪክ ለመሥራት የተሠባሰቡ ዜጎች እንጂ ግዴታ፣ ኃይልና በወቅቱ ሕግ አስገዳጅነት የዘመቱ አልነበሩም።
በኢትዮጵያዊ ማንነታቸውና በሀገራቸው የነፃነትና የሉዓላዊነት ጉዳይ ላይ ያተኮሩ እንጂ በትናንሽ ቁርሾዎች ልዩነት ፈጥረው ከዋናው ሀገር የመጠበቅ ተልዕኮ ያፈነገጡም አልነበሩም። በዘመቻው ሂደት የታየው የጋራ ክተት ጥሪ፣የታየው የጋራ ዓላማ ፅናት የተሞላበት ረዥሙ የዘመቻ ጉዞ፣ ሳይቸኩሉ ሁሉንም በልባቸው አድርገው የጋራ ድል ማስመዝገባቸው የዚያ የአድዋ ዘመቻ የጦር አመራር የጥበብ የምክክር ብስለትና ብቃት ውጤት ነበር። ይህ ባይሆን ኖሮ የዓድዋን ድል ማስመዝገቡ አስችጋሪ በሆነ ነበር።
የታሪክ ምሁሩ ዶክተር ሹመት ሲሻኝ እንደጻፉት፥ አፄ ምኒልክ የአድዋ ጦርነት እንደሚነሣ ቀደም ብለው ስላወቁት፥ ሠራዊታቸው ከአዲስ አበባ እስከ አድዋ ድረስ ሲጓዝ እንዳይቸገር በሚሰፍሩበት ቦታ ሁሉ አስፈላጊውን ስንቅ ቀደም ብለው አከማችተው ነበር። አድዋ ላይ የኢጣልያን የጦር ሠራዊት ከምሽጉ ውስጥ እንዳለ ሊገጥሙት ፈልጎ ነበር፤ ንጉሡ ግን አልፈለጉም። የመሸገን ጠላት ለማሸነፍ እንደማይቻል በሰሐጢ በአፄ ዮሐንስ ላይ ከደረሰው ሽንፈት ስለተማሩ፥ በዘዴ አስወጡት። “የምኒልክ ጦር ተዳክሟል” የሚል ሰላይ ላኩበት። እውነት መስሎት ከምሽጉ ወጣ፤ ሲወጣላቸው ልብ- ራሱን አሉት።
አፄ ምኒልክ የአፍሪካውያን ጦርነት እንደ ቼዝ ጨዋታ መሆኑን ያውቁ ነበር። በቼዝ ጨዋታ ንጉሡ ከሞተ፥ ሠራዊቱ እንዳለ ቢሆንም፥ ንጉሡ የሞተበት ተጫዋች ተሸናፊ ይሆናል። ኢትዮጵያ ከሱዳን ደርቡሾች ጋር መተማ ላይ ባደረገችው ጦርነት ያገኘችውን ድል ያጣችው ንጉሣችን አፄ ዮሐንስ ጦሩን ስለመሩት ነው።
የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም የአድዋ ጦርነት ተካሂዶ፥ ኢጣሊያ የኢትዮጵያ እጅ ያደቆሳት ሽንፈት ደረሰባት። ይህም ሌሎች ሕዝቦችን የሚነካ ሁለት ውጤቶች አስከተለ፤ አንደኛ፥ ሰሜን አፍሪካ ላይ አውሮፓዊ ክብርን ትልቅ ምች መታው። ሁለተኛ፥ በአውሮፓ ፖለቲካ ማንነት ረገድ የኢጣልያ ዋጋ ቁልቁል ወረደ።
አፍሪካ በአጠቃላይ በአውሮፓውያን ቅኝ ግዛት ቀንበር ውስጥ በወደቀችበት ዘመን ኢትዮጵያ በጀግኖች አርበኞቿ ተጋድሎ ነጻነት እና ሉዓላዊነቷን ያስጠበቀችበት ልዩ ቀን ነው። የአድዋ ድል፦ ኢትዮጵያውያንን በአንድነት አሰባስቦ ለታላቅ ድል ማብቃቱ በአውሮጳውያን የታሪክ ተመራማሪዎች እና ሀገር አሳሾች ጭምር በተለያየ ጊዜያት ተመስክሮለታል።
ጥቁር ከሰው በታች ነው የሚል አስተሳሰብ በነገሰበት ዘመን፤ ጥቁር የማይታሰበውን ማድረግ እንደሚችል ያሳየበት ድል የዓለምን ታሪክ በሚደንቅ ሁኔታ ቀይሮታል። ኢትዮጵያውያን እንደ ሌሎች በቅኝ ግዛት ስር የተላቀቁበትን ቀን «ነጻ የወጣንበት» ብለው እንደሚያከብሩት ሳይሆን በኩራት የድል ቀናችን እያሉ በልዩ ሁኔታ የሚያከብሩት ታላቅ ቀን ነው።
የአድዋ ድል ኢትዮጵያውያን ከዳር እስከ ዳር ቀፎው እንደተነካበት ንብ ተምመው በንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ አጻ ምንሊክና በእቴጌ ጣይቱ ስር በአንድ ጥላ እንዲሰባሰቡ ያደረገ ታሪካዊ ክስተት ነው። ይህን ታሪካዊ ክስተት እንድንመለከት የንጉሰ ነገስት ዳግማዊ አጼ ምኒለክ ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡
ዳግም ከበደ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 16/2013