“የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር በፌዴራል መንግስት ሰዎች ሲታይ “ጁንታ” ነው። በትግራይ ክልል ሰዎች እይታ “ባንዳ” ነው። ስለዚህ ፎርሙላው ጊዜያዊ አስተዳደር = ጁንታ + ባንዳ = “ጁንዳ” “….. ይህን ያለው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ሹመኛ የነበረው የአረናው ሊቀመንበር አብርሃ ደስታ ነበር::
ዶ/ር አረጋዊ በርሄ እና ሌሎች አካላትም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ውጤታማ አለመሆኑን በአደባባይ ተናግረዋል:: ነገር ግን አስተዳደሩ የከሸፈው ከሌሎች ችግሮች ይሁን በውስጡ ጁንታ ኖሮበት ፈጣሪ ይወቀው:: በፌዴራል መንግስት ደረጃ ግን ጊዜያዊ አስተዳደሩ ጁንታ መሆኑን ሲነገር አልሰማንም::
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ባንዳ ስለመሆኑ ግን በጁንታው እና በደጋፊዎቹ በአደባባይ ሲነገር ከርሟል:: ነገሩ ማንኛውም ትግርኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሆኖ የህወሓት ደጋፊ ባልሆነ ሰው ላይ የሚደርሰው ጥቃት አይነት ነው:: ህወሓቶችን መደገፍ ትግራይን መደገፍ ነው ብለው ህወሓቶች ደምድመዋል:: ከዚህ በተቃራኒ የሆነ ሁሉ ባንዳ የሚል ታፔላ እንዲሰጠውም ወስነዋል:: ይህ ደግሞ ዛሬ ሳይሆን ቀድሞ የተጀመረ ነው:: የህወሀት አምባገነንት ምልክት ነው::
የሆነ ሆኖ ባንዳ ምንድን ነው? ባንዳስ ማን ነው? የሚለውን ማወቅ ነገሩን ለማጥራት ይጠቅማልና ከሱ እንጀምር:: ባንዳ ለሚለው ቃል ብያኔ ስንሰጥ በአጭሩ ለጠላት ሀይል እየሰራ ወገኑን የሚያስጠቃ ማለት ነው:: ይህ ደግሞ ወደ ሌላኛው የብያኔ ጥያቄ ይወስደናል:: ጠላት ማነው? ወገንስ ማነው? ወደሚል ጥያቄ…::
እንግዲህ የምናወራው ስለ ትግራይ ህዝብ ከሆነ ወገን የሚባለው የአማራ ህዝብ ፤ የኦሮሞ ህዝብ ፤ የአፋር ህዝብ ወዘተ…በጥቅሉ የኢትዮጵያ ህዝብ ማለት ነው:: ቋንቋ ፣ ባህል. ታሪክ እና መልክአ ምድርን ካየን ደግሞ የኤርትራ ህዝብም ለትግራይ ህዝብ ወገን ነው:: ህወሀሓትም ሆነ ሌላ ድርጅት በዚህ ዘመናትን ባለፈ የወገን ትስስር ውስጥ ብቅ ያሉ ጊዜያዊ ክስተት እንጂ ሌላ አይደለም::
እስኪ ጠላት እና ወዳጅን በታሪክ መነጽር በደንብ እንያቸው:: ጠላት ማነው? ጠላትማ የኢትዮጵያን አንድነት የሚጻረር ፤ ኢትዮጵያ ሰላም ስትሆን የሚጨንቀው ፤ ልማት ሲያይ አይኑ የሚቀላ ማለት ነው:: የኢትዮጵያ ጠላት ሲለው መንግስት ሆኖ ፤ ሲለው አለምአቀፍ ድርጅት ሆነ ፤ ሲለው ሚዲያ ሆኖ ብቅ የሚል ሀይል ነው::
ታዲያ ዛሬ ከዚህ ሀይል ጋር የዚህን ሀይል አጀንዳ እያስፈጸመ ያለው ማን ነው? ግልጽ ነው:: ማነው ኢትዮጵያ በ1969 አ.ም በምስራቅ በኩል በዚያድባሬ ተወርራ ባለችበት ወቅት በሰሜን በኩል ሲወጋት የነበረው? ማነው ለተራበ ህዝብ የተሰጠን እርዳታ ሸጦ መሳሪያ የገዛበት? ማነው የገዛ ህዝቡን በደርግ አውሮፕላኖች እንዲደበደብ ያመቻቸው? ማነው የወገን ሀብትን ከፈለጉ ግመሎቻቸውን ያጠጡበት ብሎ ወደብን የሚያህል ሀብት ያለ ውይይት አሳልፎ የሰጠው?
ማነው የገዛ ወገንን ነጻነት ወይስ ባርነት ብሎ ያስመረጠው? ማነው በአለም የሌለ የመገንጠል መብትን ህገ መንግስት ውስጥ የጨመረው? ማነው በሀገር ስም 30 ቢሊየን ዶላር ተበድሮ 30 ቢሊየን ዶላር በሙስና የዘረፈው? ማነው ወገንን ነፍጠኛ እና ጠባብ ብሎ የከፋፈለው? ማነው የህዝብን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ሽሮ ፌደራላዊ ስርአቱ እንዲመክን ያደረገው? 20 አመት የጠበቀውን ጦር ከጀርባ የወጋው?… እነዚህን ጥያቄዎች ስንመልስ የዚያን አካል ማንነት እናውቀዋለን::
ወገንስ? ወገንማ የትግራይ መሬት የኔ መሬት ነው ብሎ በየተራራው ነፍሱን የገበረው ነው :: ወገንማ 20 አመት ድንበር ለመጠበቅ ቤቱን ትቶ በምሽግ ያረጀው ነው:: ወገንማ የአንድ ብሄር የበላይነት ቢንሰራፋም ችግሩ የፓርቲው እንጂ የህዝቡ አይደለም ብሎ በማስተዋል የኖረው ነው:: ወገንማ የአክሱም ሀውልት ምንህ ናት ቢባልም አክሱም የኔ ናት ብሎ በየአመቱ ደጇን የሚሳለመው ነው:: ወገንማ ህወሓት እና የትግራይ ህዝብ ይለያያሉ ብሎ በጥበብ የህወሓትን ወንጀል ከህዝብ ያራቀው ነው:: ወገንማ በትግራይ ክልል በየጊዜው ድርቅ ሲከሰትና ህዝበ ሲጎዳ የሚለግሰው ነው:: ወገንማ የትግራይ ሀዝብ በመላው ኢትዮጵያ ሲኖር አንድም ቀን የባዳነት ስሜት እንዳይሰማው አድርጎ ያኖረ ነው ….
ታዲያ ከማን ጋር መሰለፍ ነው ባንዳ ሊያስብል የሚገባው? ግልጽ ነው:: እነ አብርሀ ደስታም ሊያሳስባቸው የሚገባው በጁንታው የተሰጣቸው ስም ሳይሆን እውነታው ነው:: በታሪክ የቀኝ ገጽ በኩል ለተሰለፈ ሰው ዛሬ ማንም ባንዳ ቢለው ሊጨንቀው አይገባም::
በታሪክ በግራ ገጽ ለተሰለፈ ግን ወዮለት:: ምክንያቱም ጊዜ ሁሉን ያሳያልና ነው:: ባንዳነት እንደማይፈለግ ሽበት ነው:: የፈለገ ቀለም ቢቀባቡት መታየቱ አይቀርም:: ባንዳ የሆነ ሰው በጊዜው ማንነቱ መታወቁ አይቀርም፤ ያልሆነም እንደዚያው:: ለዚህ ደግሞ ታሪክ ምስክር ነው::
ከዚህ ቀደም በዘመናቸው ባንዳ ተብለው መከራን የተቀበሉ በኋላ ግን ጀግንነታቸው ታውቆ ክብራቸው ከነሱ አልፎ ለልጅ ልጃቸው የተዳረሰ ብዙዎች አሉ:: በተቃራኒው በጊዜው ጀግና ተብለው በኋላ ነውራቸው በአደባባይ የታወቀም አሉ::
ዛሬ በህወሓት ጀግና የተባሉ ነገ ባንዳነታቸው እንደሚታወቅ እርግጥ ነው:: ዛሬ ባንዳ የተባሉ ደግሞ ነገ ጀግና እንደሚባሉ የታወቀ ነው:: ለዚህ አንድ ምሳሌ መጥቀስ ካስፈለገ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ጀግናው አርበኛ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ ነው::
በላይ ዘለቀ ባንዶች ሀገር ምድሩን በተቆጣጠሩበት ዘመን የኖረ ጀግና ነው:: በድህረ ጣልያን ወረራ አርበኞች ተገፍተው ባንዶች በየቦታው በተሾሙበት ዘመን የሞራል ልእልናው እና ጀግንነቱ እረፍት የነሳቸው ባለጊዜዎቹ ባንዶች በላይን ባንዳ ነው ብለው ከሰሱት፤ አስፈረዱበትም:: እሱም ወደ መቃብር እነሱም ወደ ሹመት ተምዘገዘጉ:: ግን ጊዜ ጌታ ነውና በጊዜው የበላይ እውነት ተገለጠች:: እነማን ባንዳ እንደነበሩም ታየ:: ዛሬ በላይ በጀግንነቱ የሚታወስ ፤ የበላይ ዘር ነኝ ማለትም የሚያኮራ ነው:: በላይን ባንዳ ያሉት ግን ከታሪክ መዝገብ ተረስተዋል::
ስለዚህ ዛሬ ጁንታው ማንንም እየተነሳ ባንዳ ሲል ስንሰማ ትዝ ሊለን የሚገባው ይህ የበላይ ዘለቀ ታሪክ ነው:: ዋናው ቁምነገሩ መባሉ አይደለም፤ ተግባሩ እንጂ:: ተግባሩ ደግሞ በታሪክ መዝገብ በቀኝ ወይም በግራ በኩል የማረፍ ነው:: በቀኝ በኩል ማረፍ ማለት ደግሞ በእውነት እና በኢትዮጵያ በኩል መሰለፍ ማለት ነው:: እውነት እና ኢትዮጵያ እንደሚያሸንፉ የተረጋገጠ ሀቅ ነው::
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ነሃሴ 16/2013