ይህን ያለው ዝነኛው የፈረንሳይ ጄነራል ቻርለስ ደጎል ሀገሩ ፈረንሳይ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት በተረታችበት ወቅት ‹‹ ፈረንሳይ በውጊያው ተሸንፋለች፤ ጦርነቱን ግን ገና አልተሸነፈችም››/‘France has lost a battle! But France hasn’t lost the war!’ / ሲል መናገሩ ይጠቀስለታል:: የጀርመን ጉልበት እያየለ ሲመጣ እና ጀርመን ፓሪስን ስትቆጣጠር የፈረንሳይ ዜጎችን ለማበርታት የተናገረው ሲሆን፣ ከዚህም ባለፈ ትልቁን ምስል ስለማየት አስፈላጊነትም ያስረዳል::
ይህን ያነሳንበት ዋነኛ ምክንያት በዚህ ሰሞን ብዙ ሰዎች ትልቁን ምስል ማየት ሲቸገሩ በመመልከቴ ነው:: በዚህም የተነሳ ብዙሃኑ በጥቃቅን ነገሮች ሲበሳጩ እና ሲደሰቱ አይቼና ሰምቼም ነው::
እስኪ በመጀመሪያ ከጦርነቱ እንነሳ:: ይህ ጦርነት በማን እና በማን መካከል ነው የሚካሄደው በሚለው ላይ ብዙዎች በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ነገሩን ሲያቃልሉት እና ትልቁን ምስል ሲዘነጉ ይታያል:: አንዳንዱ ጦርነቱ በዶ/ር ዐብይ አሕመድ እና ደብረጽዮን መካከል የሚካሄድ ግለሰባዊ ጉዳይ ነው ይላል:: ሌላው ደግሞ ጦርነቱ በብልጽግና እና በህወሓት መካከል የሚካሄድ የተለመደ የስልጣን ሽኩቻ ነው ይላል:: ሌላው ደግሞ ጦርነቱ በአማራ እና በትግራይ መካከል የሚካሄድ የመሬት ይገባኛል ጉዳይ አርጎ ይመለከተዋል:: ነገር ግን እነዚህ ሁሉ ነገሮች በአንድ ጎን ሆን ተብለው ጦርነቱን ለማቃለል እና ህዝብን ለማዘናጋት የሚነገሩ ነገሮች ሲሆኑ ፣በሌላ መልኩ ደግሞ ያለማወቅም ውጤቶች ናቸው::
ይህ ጦርነት በትልቁ እና በትክክለኛው መነጽር መታየት አለበት:: ጦርነቱ የሁለት ግለሰቦች ፤ የሁለት ፓርቲዎች ወይም የሁለት ክልሎች አይደለም:: ከዚያ ይሰፋል:: የሁለት እሳቤዎች እና የሁለት ተግባራት ጦርነት ነው:: እሳቤዎቹ የአንድነት እሳቤ እና የመከፋፈል እሳቤ ናቸው ፤ ተግባሩ ደግሞ ሀገርን የማዳን እና የማፍረስ ተግባር ነው:: ጦርነቱ በእነዚህ መካከል የሚካሄድ ነው::
ከዚህም አስፍቶ ማየት ያስፈልጋል:: ጦርነቱ የሚካሄደው ከሀገር ደረጃም ከፍ ብሎ ነው:: በአንድ ጎን ኒዎ ሊበራሊስቶች አሉ ፤ በሌላኛው ጎን ደግሞ የኒዎ ሊበራልን የሚቃወም ኃይል አለ:: ሁለቱም ወገኖች ባላቸው አቅም እና በቻሉት መንገድ ጦርነቱ ውስጥ ተሳትፎ ለማድረግ እየሞከሩ ነው::
ኢትዮጵያ ነገ ጉልበተኛ ሀገር ሆና ከተነሳች እንጎዳለን ብለው የሚያስቡ እንደ ሱዳን ዓይነት መንግሥታት ፤ እንዲሁም የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ወዳጅነት የቀይ ባህር ቀጠናን ችግር ውስጥ ይከትብናል ብለው የሚሰጉ የባህረ ሰላጤው እና የአውሮፓ ሀገራት ሁሉ በዚህ ጦርነት ላይ ባለድርሻ ናቸው:: ስለዚህም ጦርነቱን የሁለት ግለሰቦች ፤ ፓርቲዎች እና ክልሎች ጦርነት አድርጎ ማየት አደገኛ ነው::
ይህ በእንዲህ እንዳለ አሁን ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላ ደግሞ ብዙዎች ጦርነቱ የሆነ ከተማን የመቆጣጠር እና ያለመቆጣጠር ይመስላቸዋል:: ነገር ግን ይህ ስህተት ነው:: ጦርነቱ አንዲት ከተማን የመያዝ አይደለም:: አንድ ክልልንም የመያዝ አይደለም:: አንድን አደገኛ የሆነ የከፋፋይነት እና የባንዳነት አስተሳሰብ የመደቆስ እና የማድረግ አቅሙን የማሳጣት እንጂ::
ስለዚህም አንድ ቦታ ላይ የሚደረግ ጦርነት እና በዚያ የሚገኝ ድል እና ሽንፈት የጠቅላላ ጦርነቱን አሸናፊ አይወስንም:: ለዚህም ነው ቻርለስ ደጎል ከላይ የጠቀስነውን ንግግር የተናገረው:: ፈረንሳይ በፓሪስ የተደረገውን ፍልሚያ ብትሸነፍም፣ ጦርነቱን በሙሉ እንዳልተሸነፈች ደጎል ያምን ነበር:: ደግሞም አልተሳሳተም ፤ የመጨረሻዋ ሳቅ የፈረንሳይ ሆናለች::
እኛም ልናውቀው የሚገባ ነገር የመጨረሻዋ ሳቅ የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን እንደሚሆን ነው:: ለዚያ ደግሞ ከትንንሽ የጦር ሜዳ ጀብዶች እና ችግሮች አሻግረን ማየት ይገባናል::
ጦርነቱ በጦር ሜዳ ብቻ ሳይሆን ፤ በዲፕሎማሲ ፤ በኢኮኖሚ ፤ በፕሮፓጋንዳ እና ሌሎች ዘርፎች እንደሚካሄድ ማወቅ አለብን:: በጦር ሜዳ ላይ የሚካሄደው ዘመቻ በራሱ መንገድ በጥሩ ሁኔታ እየተመራ ነው:: ጁንታው የትግራይ ሕፃናት እና ወጣቶችን በገፍ ወደማይመለሱበት ጦርነት እየማገደ ነው:: መጪዋ ትግራይ ላይ እንኳን ለህወሓት የሚዋጋ ለእርሻ የሚሆን እንኳን ትውልድ እያስቀረ አይደለም::
በኢኮኖሚ ዘርፍስ በዚያም ቢሆን የጁንታው ኢኮኖሚ አቅም ለማገገም በማይችል መልኩ እየተመታ ነው:: በአንድ ወቅት ባንኩንም ታንኩንም ይዞ የነበረው አሸባሪው ህወሓት፤ አሁን ባንኩ ከእጁ አምልጦታል:: ልዩ ድጋፊው የሆኑ በሙሉ አሁን ያላቸውን ሀብት እየሸጡ እየፈረጠጡ ነው:: አወጣጣቸው በትርምስ የተሞላ በመሆኑ መንግሥት ችግር እንዳይፈጥሩ ለጊዜው የባንክ ብድርንም ሆነ የመሬት ነክ አገልግሎቶችን አስቁሟል::
በዲፕሎማሲው ረገድስ ቢሆን ፤ ፀረ ኢትዮጵያ የሆኑ መንግሥታት ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ የሚሰጡት አሸባሪው ህወሓት፣ በተደጋጋሚ በአጃቢዎቹ በኩል የኢትዮጵያ መንግሥትን ወንጀለኛ ለማድረግ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት ቢጓዝም ዓላማው በተደጋጋሚ ከሽፏል:: መንግሥት ጦሩን ከትግራይ በማውጣትም የምዕራቡን ኃይል የመጫወቻ ካርድ አስጥሎታል::
የአሸባሪው ደጋፊዎች የኢትዮጵያ መንግሥት እንደፈለጉት እጁ እንደማይጠመዘዝ ሲገባቸው የአካሄድ ለውጥ ወደማድረግ ገብተው ማባበል እና ማስፈራራትን አጣምረው እየሄዱ ነው:: እሱም ቢሆን አልተሳካም::
ከሳምንታት በፊት ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የዋሽንግተን ባለስልጣን ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሆነ ምክትላቸውን ለማግኘት ያደረጉት ሙከራ መክሸፉ አሁን ያለው መንግሥት ትዕዛዝ ለመቀበል ዝግጁ አንዳልሆነ አመላካች ነው:: በተቃራኒው እስከአሁን እንደተበዳይ አድርገው በሚዲያዎቻቸው ሲስሉት የነበረው አሸባሪው ህወሓት አማራ እና አፋር ክልሎችን በመውረር ፣ ዜጎችን በማፈናቀል፣ በመዝረፍ እና በመድፈር አዋርዷቸዋል::
በፖለቲካ ረገድም ቢሆን መቀሌ ገብቶ በመደበቅ እና ራሱን ከብልጽግና ውህደት በማውጣት በራሱ ላይ ጎል ያስቆጠረው ይህ አሸባሪ፣ በጦርነቱ ዋና የፖለቲካ መሪዎቹን አጥቷል:: አሁን በቀሩት የጦር እና የወታደራዊ ክንፍ መሪዎች መካከል አለመግባባት እንደተፈጠረም ይነገራል:: ወደ አማራ እና ወደ አፋር ያደረገው ዘመቻ እንዳሰበው ስኬት በማስገኘት ፈንታ ከአማራ እና አፋር ክልል ህዝብ የቁጣ ምላሽ እንዲጠብቀው ነው ያደረገው:: የተመኘውን የመደራደሪያ ካርድም አላገኘም:: እንዲያውም ሌሎች ክልሎችም ልዩ ኃይላቸውን ወደ ቦታው እንዲልኩ ነው ያስደረገው::
ህወሓት ወደ አፋር ክልል የገባው የጅቡቲ ኮርደርን ለመያዝ ቢሆንም፣ ዓላማው ጭፍጨፋ ነውና ማሳካት የቻለው ከሁለት መቶ በላይ ንጹሐንን መጨፍጨፍ ብቻ ነው/ በእሱ እይታ ለማለት ነው/::
የአፋር ጀግኖች በተቃራኒው የህወሓትን ሠራዊት ከባድ ቅጣት ቀጥተው መልሰውታል:: ወደ አማራ ክልል የመግባቱ ዓላማ የሱዳን ኮሪደርን ለማስከፈት ቢሆንም መንግሥት ግን የኮሪደሩን ጉዳይ ጥርቅም አድርጎ በመዝጋት ህወሓት የተመኘውን የድርድር ዕድልም አልሰጥም ብሎታል:: በተቃራኒው አማራው እንዲደራጅ እና እንዲነሳ በማድረግ ህወሓት ያላሰበውን የቁጣ ምላሽ አምጥቶበታል::
በፕሮፓጋንዳ ዘመቻውም ቢሆን አሁን ላይ የኢትዮጵያ ህዝብ የጁንታው ዋነኛ ጉልበት ቅጥፈት እንደሆነ ተረድቷል:: ለጁንታው የተበዳይነት ዘገባ ሲሠሩለት የከረሙት ሚዲያዎች ቀስ በቀስ ድምፃቸውን እያጠፉ ሲሆን፣ በተቃራኒው እነ አልጀዚራ ጁንታው በአፋር እና አማራ ክልል ያደረገውን ነውር በመዘገብ አዋርደውታል:: ጌታቸው ረዳ ከቢቢሰው ስቴፈን ሳከር ጋር ያደረገው ቃለመጠይቅ ደግሞ ጁንታው ሀገር የማፍረስ እና የተገንጣይነት ዓላማ ብቻ እንዳለው ዓለም እንዲያውቅ የሆነበት አጋጣሚ ፈጥሯል::
አሁን ጁንታው አቅጣጫው ጠፍቶታል:: ነገር ግን ይህን ለመረዳት ከጊዜያዊ መንገጫገጭ አሻግረን ትልቁን ምስል ማየት ያስፈልጋል:: ትልቁ ምስልም ኢትዮጵያ እያሸነፈች መሆኑ ነው::
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ነሃሴ 16/2013