ዛሬ ዛሬ አለማችንን ቀስፈው ከያዟት ተግዳሮቶች መካከል አንዱ የስራ እድል ጉዳይ ሲሆን፣ የዚህ እድል ያለመኖር የፈጠረው የስራ አጥ ቁጥር በብርሀን ፍጥነት እያደገ መሄዱ ነው።
ይህ ከህዝብ ቁጥር እድገት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያለው ስራ፣ ስራ ፈጠራና የስራ እድል ካለው ፍላጎት ጋር አብሮ ሊሄድ ያልቻለ በመሆኑ በየአገሩ ችግሩ አሳሳቢ እየሆነ ነው። በተለይም በማደግ ላይ ባሉት አገራት ችግሩ በሁሉም ገፅታው እየሰፋና እየተወሳሰበ የሚገኝ ሲሆን አሳዛኙ ነገር መንግስታት ከችግሩ ግዝፈት አኳያ ለመፍትሄው በሚፈለገው ፍጥነት ሲንቀሳቀሱ አለመታየታቸው፤ ይህም በየጊዜው ሲጎዳቸው፤ ስልጣናቸውን እስከማጣት ድረስ ሲወስዳቸው፤ አገርና ህዝብንም ላልተፈለገ ቀውስ ሲዳርግ ይታያል።
ለዚህ ምሳሌ ይሆነን ዘንድ አዲስ አበባን ማዬት ይቻላል። በከተማዋ ምንም አይነት የአገልግሎት ዘርፍ ወደ ፊት ፈቀቅ ሳይል የህዝብ ቁጥሩ አናቱ ላይ በመውጣቱ ምክንያት ብቻ የከተማው አገልግሎት ዜሮ ገብቷል። ይህም ከመፀዳጃ ቤት ጀምሮ ጠቅላላ የአገልግሎት ዘርፉን ሰልፍ በሰልፍ ከማድረጉም በላይ አጠቃላይ የነዋሪውን “ኑሮ እንዴት ነው ኑሮ ቢለው፤ ምን ኑሮ አለ ልፊያ ነው ያለው” አለ እንደተባለው፤ ሁሉም ነገር ልፊያና ግፊያ ሆኖ እርፍ ብሏል።
በዚህ ሁሉ መሀል ይህንን ሁሉ ችግር ተቋቁመው፣ የማህበረሰቡን አመለካከት ችላ ብለው (“ሰው ምን ይለኛል” ገመድን በጣጥሰው) ህይወትን እየገፉ ያሉ መኖራቸው የሚያስገርም ሲሆን፤ ይህንን በማድረጋቸውም በአርአያነታቸው ይጠቀሳሉ፣ ተከታይ ያፈራሉ፣ እራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ይደጉማሉ (ያኖራሉ)። ከእነዚህም አንዱ የዛሬው እንግዳችን ዘሪሁን አያና ነው።
ሕይወትን የተለያዩ ስራዎችን በመስራት ሲመሩ የነበሩና እየመሩም ያሉ በርካታ ሰዎች አሉ። ከእነዚህም ጥቂቶቹ ከሊስትሮነት ተነስተው እዚህ የደረሱ ናቸው። ለምሳሌ ድምፃዊ መሀሙድ አህመድ ቀዳሚ ተጠቃሽ ነው። የዛሬ እንግዳቸንም የነገው “ሌላ ሰው” እንደሚሆን በመተማመን ለዛሬ ያለበትን ሁኔታና የመጣበትን መንገድ፤ እንዲሁም ለሌሎች የሚተርፍ ልምዱን እንዲያጋራን እንግዳችን አድርገነዋልና አብረን እንዝለቅ።
ወላይታ ተወልዶ ያደገው፣ ባለ ትዳርና የልጆች አባቱ ዘሪሁን እንደነገረን ከሆነ ህይወት በጣም ፈትናዋለች። አባታቸው በልጅነታቸው፣ ገና የአራተኛ ክፍል ተማሪ እያለ መሞታቸውንና እናታቸውም ጥለዋቸው መሄዳቸውን ተከትሎ በእሱና በታናሽ እህቱ ላይ ነበር ሀላፊነቱ የወደቀው። በተለይ እህቱን ሌላ ዘመድ በመውሰዱ ምክንያት እሱ ላይ ሁሉም ነገር የበረታ ነበር። እንደዛም ሆኖ ትምህርቱን ሳያቋርጥ እስከ 10ኛ ክፍል (2006 ዓ/ም) ድረስ ተምሮ ማትሪክ ተፈተነ። ምን ያደርጋል መግቢያው 2.71 ስለነበር እሱ ለአንድ ነጥብ ወደቀ። ይሁንና ወደቅሁ ብሎ አልቦዘነም። እንደገና ተፈትኖ በማሻሻል ብራይት ኮሌጅ በመግባት ለሶስት አመት አካውንቲንግ የጥናት መስክን በመከታተል በዲፕሎማ ተመረቀ። አሁን በዚሁ ሙያ የዲፕሎማ ባለቤት ሲሆን እየሰራ ያለው ግን በሊስትሮነት ነው። ለምን? ኃይሉ ገብረዮሀንስ (ጎሞራው) “አልሳካ ብሎ ነገሩ ሲጠጥር / ጠጣሩ እንዲላላ የላላውን ወጥር” እንዳለው በአንድ በኩል አልሳካ ሲል በዛው በኩል ክችች ማለት ሳይሆን ሌሎች አማራጮችን እየሞከሩ ኑሮን የማሻሻል ጥረትን መቀጠሉ ስለሚመረጥ ነው፤ ወይም የተሻለ በመሆኑ።
ከልጅነቴ ጀምሮ ከፍተኛ የትምህርት ፍቅር ነበረኝ የሚለው ዘሪሁን እንደነገረን ከሆነ ሁሌም ከስራው ጎን ለጎን ማስታወቂያ እየተከታተለ በወጣበት ሁሉ ያመለክታል። ይሁን እንጂ የመቀጠር እድሉን አያገኝም። ይህ ደግ ሁሌም እንቆቅልሽ እንደሆነበት የቆየ ሲሆን በኋላ ግን ደረሰበት።
በትምህርት ደረጃው ኮሌጅን የበጠሰው ዘሪሁን አያና እሱን ተከትሎ የሚመጣውን የብቃት ማረጋገጫ ፈተና (ሶኦሲ)ም ተፈትኖ በማለፍ ብቃቱን ያረጋገጠው ዘሪሁን በእሱ የጥናት መስክና የሙያ አይነት የስራ መደብ ያወጡ መስሪያ ቤቶችን በር ሳያሰልፍ አንኳኮታል። ያንኳኳ እንጂ አንዱም በር አልተከፈተለትም።
ዘሪሁን ይህንን ተወዳድሮ ያለማለፍ ችግርን በተመለከተ “ዋናውና ቁልፍ ችግር የስራ ልምድ የሚሉት ነው” እሚለው ላይ ደርሷል። “መስሪያ ቤቶች ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያ ሲያወጡ የስራ ልምድ ይጠይቃሉ። ከተቋማት ተመርቆ የወጣ ግን ይህ የስራ ልምድ የሚባለው ነገር የለውም። በዚህም ምክንያት ስራ አያገኝም ማለት ነው።” የሚለው የዛሬው ሊስትሮ ዘሪሁን “ይህ ችግር ካልተወገደ ከንቱ ልፋት እንጂ ምንም ዋጋ የለውም” ሲልም ይናገራል።
“አመለክታለሁ፤ ግን አላገኝም። ለምን?” ለሚለው የራሱ ለራሱ ጥያቄ “አዲስ አበባ ውስጥ ከፍተኛ ውድድር መኖሩ አንድ ነገር ሆኖ፤ ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያ የሚያወጡ መስሪያ ቤቶች የስራ ልምድን የግድ ማለታቸውና ዜሮ አመት ያለውን ምሩቅ ለማስተናገድ ፍላጎት የሌላቸው መሆኑ”ን ደርሶበታል። ይህ ብቻም አይደለም፤ “በአሁኑ ሰአት ስራ ለመቀጠር በቢሮ አካባቢ ሰው (ባለስልጣን) ያስፈልጋል። እኔ ደግሞ ምንም የማውቀውም ሆነ የቅርብ ሰው የለኝም። አንዱ ችግር እሱ ነው።” የሚለው ዘሪሁን ያለ ሰው ወይም ዘመድ (በግልፅ ቋንቋ ያለ ሙስና ማለቱ ነው) ስራ ማግኘት አስቸጋሪ መሆኑንም ይናገራል።
የሊስትሮ ስራና ገቢውን በተመለከተም “በፊት የቁርስ፣ ምሳና እራት ውጪን ችለን በቀን 50 ብር ይዘን መግባት እንችል ነበር። አሁን ግን ሰዉ ኑሮ ከብዶት ሊሆን ይችላል ስራችን ተቀዟቅዟል።” በማለት የነገረን ሲሆን፤ በተለይ ቤተሰብ ለሚያስተዳድሩት ሊስትሮዎች ኑሮ ከባድ እንደሆነ ይናገራል። “በተለይ የቤት ኪራይ ውድ ነው። ከጓደኞቼ ጋር አራትና አምስት ሆነን ባንኖር ኖሮ መኖርም አንችልም ነበር።” ሲልም ከችግር እላቀቃለሁ ሲል የተማረው ትምህርት ምንም እንዳልጠቀመው ይናገራል።
ሌላው የዘሪሁን ጠንካራ ጎን አሁንም የሚያስተምረው፣ የሚያግዘው ቢያገኝ በዲግሪ ደረጃ ትምህርቱን መቀጠል የመፈለጉ ጉዳይ ነው። “አሁንም አጋዥ ባገኝ ትምህርቴን መቀጠል እፈልጋለሁ።” ሲል ፊቱ ላይ ብርሀን እየፈነጠቀ ነው።
ከሌሎች ጋር በመደራጀት ሃና ማሪያም አካባቢ የኮብልስቶን መንገድ ስራን ሰርቶ እንደነበር፤ ጥሩ ገንዘብ በማግኘቱም ወደ ኋላ፤ ወደ ትውልድ ስፍራው በመመለስ አነስተኛና ጥሩ የሆነ መኖሪያ ቤት መስራቱን፣ ትዳርም መመስረቱን፤ ከዛም እንደገና ወደ አዲስ አበባ በመመለስና እንደገናም በመደራጀት ይህንን አሁን እየሰራ ያለውን የጫማ ማሳመር ስራ መስሪያ ቦታ (አራት ኪሎ) ማግኘቱን ወጣት ዘሪሁን ይናገራል፡፡ የመጀመሪያ ልጁን የሚያስመዘግብበት ትምህርት ቤት በማፈላለግ ላይ ሲሆን (ልጁንም በአጋጣሚ አጠገቡ አድርጎት አይተነዋል) ምንም ያህል ኑሮ ቢወደድ ልጁን በሚገባ ማስተማሩ ላይ እንደማይደራደር ይናገራል።
ዘሪሁንን “ለሌሎች ወጣቶች የምታስተላልፈው መልእክት ካለህ?” ብለነው ነበር። ሲመልስልንም “እኔ የማስተላልፈው መልእክት አንድ ሲሆን፤ እሱም ስራ ክቡር ነው፤ ወጣቱ ስራ መምረጥ የለበትም፤ መንገድ ላይ መዞር፣ ሺሻ ቤት መዋል፣ ሌላም ሌላም ምንም ጥቅም የለውም፤ ቤተሰብ ላይም ሸክም መሆን ተገቢ አይደለም። ወጣቱ ያገኘውን መስራት ነው ያለበት፤ ያገኘውን እየሰራ ያሰበበት ቦታ መድረስ ይችላል። በስራ እንጂ በሰው እጅ መተማመን የለበትም። ስራን ባህሉ ማድረግ ነው ያለበት። የሰው እጅ ከማየት፣ ከመለመን፣ ሰፈር ውስጥ ቆሞ ከመዋል ስራ ሳይመርጡ ያገኙትን መስራት ነው ተገቢ የሚሆነው። የቤተሰብ ትከሻ ላይ መሆንም አይገባም። የሚገባው ለአገርም፣ ለህብረተሰብም ፀር ሳይሆኑ ሰርቶ መኖር ነው።”
“የወደፊት እቅድህስ?” ላልነውም “የወደፊት እቅዴና አላማዬ ብዙ ነው። እውቀት ይዥ ነው ቁጭ ያልኩት። እኔ ብዙ አይነት ሙያና ችሎታ አለኝ። በሂሳብ ስራ ልምድ አለኝ። አቅም ቢኖረኝ፣ ረዳት ባገኝ በርካታ ስራዎችን በመስራት፣ የተለያዩ የስራ እድሎችን በመፍጠር ፍላጎት ያላቸውን ወጣቶች ተጠቃሚ ማድረግ እፈልጋለሁ።”
የስራ እድል ፈጠራ ጉዳይ በተነሳ ቁጥር የተለያዩ ምክንያቶች አብረው የሚነሱ ሲሆን በፖለቲካው አለመረጋጋት ምክንያት የመንግሥት ትኩረት ወደ ፖለቲካ መዞሩ፤ ክፍት የሥራ ቦታዎች በዝምድና መያዛቸው እና ያሉት የሥራ ዕድሎች እና የተመራቂዎች ቁጥር አለመጣጣምን እና የመሳሰሉት ቀዳሚ ተጠቃሽ ሲሆኑ ዘሪሁንም አንዱ ማሳያ ነው።
በተለይ የፖለቲካው ጡዘት ያለውን በማፍረስ ላይ የተመሰረተ ከመሆኑ አኳያ ለስራ አጥ ዜጎች መብዛት እያደረገ ያለው አስተዋፅኦ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ የሚናገሩ በርካቶች ሲሆኑ በተለይ ፖለቲካው አካባቢና ብሄር ተኮር መሆኑ ደግሞ ችግሩን የበለጠ አወሳስቦታልም ነው የሚሉት። ዘሪሁንም “እኔ ሰው የለኝም …” ሲለን በራሱ መንገድ ይህንን እየነገረን ነውና ጉዳዩ ያሳስባል።
የምእራቡ አለም ስልጣኔ (Western civilization) አካል ተደርጎ የሚወሰደው፤ በአለም ሁሉ የሚገኘው ሊስትሮና ሊስትሮነት በጥናት እንደ ተረጋገጠውና ከታዋቂ ድምፃዊያን እስከ ስመጥር አገር መሪዎች ድረስ ያሉ እውቃን ከዚሁ በሊስትሮ ስራ ስራቸውን “ሀ” ብለው የጀመሩ ስለመኖራቸው ተገልጿል።
ባጭሩ፣ ሊስትሮነት ከሰለጠነው አለም ጀምሮ፣ እንደ አንዳንዶቻችን አስተያየት ዝቅተኛ ስራ ሳይሆን እንደ አንድ የስራ መነሻና ወደ ተሻለ የህይወት ክፍል መስፈንጠሪያ ተደርጎ የሚወሰድ (ጎሞራው “አልሳካ ብሎ ነገሩ ሲጠጥር / ጠጣሩ እንዲላላ የላላውን ወጥር” እንዳለው) አለም አቀፍ የሙያ ዘርፍ ነው። በመሆኑም ዘርፉን ማዘመን እንጂ ማጣጣሉ ወይም ዝቅተኛው የስራ መስክ አድርጎ መቁጠሩ ሊወገድ ይገባል እንላለን። ለዚህ ደግሞ በአንድ ወቅት ከጀርመን መንግስት በተገኘ ገንዘብ እዚህ አዲስ አበባ (ምኒልክ ትምህርት ቤት) ውስጥ በአሉን በደማቅ ሁኔታ ካከበረውና የሊስትሮ ሙያን ለማዘመን ቃል ገብቶ ከነበረው “የሊስትሮዎች ማህበር” (ካለ) ብዙ ይጠበቃልና ወደ ፊት ሙያው ስራ አጥ የሚሰማራበት ሳይሆን የሰለጠነ የሰው ኃይል የሚሰማራበት እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን። ዘሪሁንም ያሰበው እንዲሳካለት እንመኛለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 15/2013