በጦርነት ወቅት አንዱ የጦር መሣሪያ ሆነው ከሚያገለግሉት እና አንዱ ባላንጣ ሌላኛውን ባላንጣ ለማዳከም ከሚጠቀምባቸው በጣም ውጤታማ ከሆኑት መሳሪያዎች አንዱ የኢኮኖሚ አሻጥር ነው:: የኢኮኖሚ አሻጥር አቅርቦትን፣ አምራቾች እንዲሁም የሎጂስቲክስ መስመሮችን ከጥቅም ውጭ ማድረግን ያካትታል::
ቁልፍ አቅርቦቶችን፣ አምራቾችን፣ ስትራቴጂካዊ ሥፍራዎችን እና የሎጂስቲክስ መስመሮች በአግባቡ ስራ እንዳይሰሩ ሽባ በማድረግ ባላንጣን ማዳከም ብሎም አቅም አልባ ማድረግ እንደሚቻል በዘርፉ የተሰሩት ጥናቶች ይጠቁማሉ:: የኢኮኖሚ አሻጥር የሚፈጽሙ አካላት ሁል ጊዜ ግልፅ እና የሚታዩ ላይሆኑ ይችላሉ። ብዙዎቹ ለአንዱ ባላንጣ ወኪል ሆነው ከባላንጣ አካል ጋር ያላቸውን ቁርኝት ለማወቅ እጅግ አዳጋች ነው::
ኢትዮጵያም በጦርነት ውስጥ መግባቷን ተከትሎ መንግስትን እና ሀገርን ለማዳከም የኢኮኖሚ አሻጥሮች ጥቅም ላይ እየዋሉ መሆኑን መንግስት እና የተለያዩ ምሁራን እየገለጹ ነው:: ይህ የኢኮኖሚ አሻጥርም በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ለሚታየው የዋጋ መናር እና የኑሮ ውድነት እንዲባባስ ምክንያት መሆኑን ያስረዳሉ::
የምጣኔ ሀብት ምሁራን እንደሚያብራሩት፤ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ተከትሎ የኢኮኖሚ አሻጥሮች እየተፈጸሙ ነው:: ከሶስት ዓመት በህዝባዊ እምቢተኝነት የማዕከላዊ መንግስት ስልጣንን አጥቶ መቀሌ የከተመው ሀይል የመንግስትን ስልጣን ተቆጣጥሮ በነበረበት ወቅት ከሚያስተዳድረው መንግስት እና ፓርቲ ጋር ግንኙነት ያላቸው የቢዝነስ ሰዎች እና ካምፓኒዎች ኢኮኖሚውን እንዲቆጣጠሩ አድርጎ ነበር:: ይህም አሁን ለሚታየው ኢኮኖሚ አሻጥሮች እና ውጥንቅጦች መነሻ ፈጥሯል ይላሉ::
በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በኮሜርስ ኮሌጅ የኢኮኖሚክስ መምህር የሆኑት አቶ ምትኩ ከበደ እንደሚሉት፤ ለ27 ዓመታት ሲቀነቀን የነበረውን ርዕዮት ሲያቀነቅኑ የነበሩ እና ታማኝነታቸውም ለቢዝነሳቸው ሳይሆን ለዚህ ርዕዮተ ዓለም እና ለፓርቲው የሆኑ ሰዎች ኢኮኖሚውን ተቆጣጥረው ቆይተዋል::
ሀገሪቱን ይመራ የነበረው ሀይል ከስልጣን ገሸሽ ቢደረግም ከነዚህ ሀይሎች ጋር እጅና ጓንት ሆነው ሲሰሩ የነበሩ ሀይሎች የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ተቆጣጥረው መቆየታቸውን የሚያነሱት አቶ ምትኩ፤ በእነዚህ ሀይሎች ካምፓኒዎች አሁን ሀገርን የሚጎዳ ተግባር ላይ በመሰማራት የኢኮኖሚ አሻጥሮችን እየፈጸሙ ነው የሚል እምነት እንዳላቸው ያብራራሉ::
ባለፉት 27 ዓመታት ጥቂት አቅራቢዎች ስለነበሩ እና እነዛም ከመንግስት እና ፓርቲ ጋር ቁርኝት የነበራቸው ስለሆኑ አሁን ላለው አሻጥር ምክንያት ሆኗል:: ዛሬም ኢኮኖሚውን ተቆጣጥሮ ያለው ሀይል በወቅቱ በኢኮኖሚው ውስጥ ትልቅ አቅም ያላቸው ሀይሎች ናቸው:: እነዚህ ሀይሎች በፈለጉበት ወቅት ኢኮኖሚውን ወደፈለጉበት አቅጣጫ የመጠምዘዝ አቅም ያላቸው ናቸው:: በዚህም ምክንያት አሁን እየሆነ ያለው እየሆነ ነው ብለዋል::
ይህም የሚያመላክተው ኢኮኖሚው አሁን ያለበትን ችግር እያስተናገደ ያለው በፖለቲካው ምክንያት መሆኑን ነው:: በመሆኑም ኢኮኖሚውን ለማስተካከል የሚደረገው ጥረት ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎችን ወይም የፖሊሲ እርምጃዎችን ብቻ በማካሄድ ሳይሆን የፖለቲካ ውሳኔዎችን ጭምር የሚጠይቅ ነው:: አሁን በሀገሪቱ የሚታየውን የኢኮኖሚ አሻጥሮችን ለማስቆም የፖለቲካ ቁርጠኝነትን ይጠይቃል:: የፖለቲካ ቁርጠኝነት ያልታከለበት የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ችግሩን ለመቅረፍ አያስችልም:: ከፖለቲካ ውሳኔ ውጪ አማራጭ የለም ይላሉ::
በኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የልማት ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህርር የሆኑት ዶክተር ተስፋዬ ጮፋና በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ ውስጥ ጦርነቱን ተከትሎ የምርት ዋጋ መጨመር በግልጽ እየታየ ነው:: በየቀኑ የእቃ ዋጋ እየጨመረ ነው:: የምርት ዋጋ መጨመሩ እውነትም እቃው ስለተወደደ የተፈጠረ ነው ወይ የሚለው አጠራጣሪ ነው:: የአሻጥሩ አካል የመሆን እድል ስላለው መንግስት ትኩረት ሰጥቶ ማየት አለበት::
በጦርነት ወቅት መንግስት በሌላ ጉዳይ ተጠምዷል፤ ምንም ሊያደርግ አይችልም ወንጀል ብንሰራ እንኳ ማንም አይደርስብንም በሚል እሳቤ የኢኮኖሚ አሻጥሮች ከጠላት እንዲሁም ወገን ተብሎ በሚታሰበው አካልም ሊፈጸም እንደሚችል የጠቆሙት ዶክተር ተስፋዬ፤ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ መሰል ምልክቶች መኖራቸውንም ያነሳሉ::
መንግስት አሸጥሮችን መቆጣጠር ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት ያሉት ዶክተር ተስፋዬ፤ መንግስት አሻጥር ለመቆጣጠር ከሰሞኑ እርማጃዎችን መውሰድ መጀመሩን እንደመልካም ጅምር ያነሱት ዶክተር ተስፋዬ ከነዚህ እርምጃዎች መካከል አንዱ ባንኮች ተለዋጭ መመርያ እስኪሰጣቸው ሕንፃና ቤቶችን መያዣ በማድረግ የሚሰጧቸውን ብድሮች እንዲያቆሙ የሚል ነው:: መሰል እርምጃዎች በኢኮኖሚው ላይ አሉታዊ ጫና በማያስከትል መልኩ መቀጠል አለበት ብለዋል::
በተጨማሪም መንግስት በየደረጃው ያሉ ተቋማት ምን እየሰሩ እንዳሉ፣ ሀላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን መንግስት ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ አለበት የሚሉት ምሁሩ መንግስት በየደረጃው ያለውን ሲቪል ሰርቫንት እና የመንግስት አመራሮችን በፊት ከነበረው በላይ መቆጣጠር እንዳለበት ጠቁመዋል::
እንደ ዶክተር ተስፋዬ ገለጻ፤ እያንዳንዱ ተቋም ስራውን በአግባቡ እየሰራ ነው ወይ የሚለው ከሚኒስቴር መስሪያ ቤት ጀምሮ እስከታችኛው መዋቅር ጥብቅ ቁጥጥር ከማድረግ ባሻገር፤ በፊት ከነበረው የተሻለ ተግባቦት መፍጠር እንዲሁም ከህዝቡ መረጃ መሰብሰብ ያስፈልጋል:: መንግስት ከሹመኞቹ ብቻ ሳይሆን ከህዝብም መረጃ መሰብብ አለበት:: ከተለያዩ አቅጣጫዎች መረጃዎችን መሰብሰብ ወሳኝ ነው:: ህዝቡ እያንዳንዱን ክስተቶች ስለሚያውቅ በተለይም ፖሊስ እና የጸጥታው ዘርፍ ከህዝቡ ጋር መስራት አለባቸው:: ሚዲያዎቹ በየቦታው የሚከሰቱ ነገሮችን ማነፍነፍ አለባቸው::
ህብረተሰቡ በከፍተኛ ንቃት ነገሮችን እየተከታተለ መሆኑን ከሁኔታዎች መረዳት እንደቻሉ የሚጠቁሙት ዶክተር ተስፋዬ ህብረተሰቡ ነገሮችን በንቃት የመከታተል እና ለሚመለከተው አካል የመጠቆም ልምዱን ሊያጠናክር ይገባልም ብለዋል::
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 14/2013