አካባቢው ሰላም ከራቀው ቀናት ተቆጥሯል:: አካባቢው ባሩድ ብቻ ነው የሚሸተው :: ልክ እንደ ፈንዲሻ የሚንጣጣ የጥይት ድምፅ ይሰማል:: ከባድ መሳሪያ ሲተኮስና ለጥቃት የታሰበው አካባቢ ደርሶ ሲወድቅ መሬቱ ይርዳል:: ኮሎኔል ሳህሉ ከስሩ ያሉ ወታደሮችን በጥበብ እና በልዩ የውጊያ ስልት በመምራት ጠላትን ያጠቁ ዘንድ በወኔ ተሞልቶ ትዕዛዝ ይሰጣል::
ጦር ሜዳ ሳይሆን ልዩ ትርዒት ማሳያ ያሉ ይመስል የጠላትን ወረዳ በድፍረት በመግባት ጀብዱ እየፈፀሙ ባሉ ወታደሮች ላይ ጥልቅ የሆነ የአገር ፍቅር ስሜትን ያሳድራል:: በደረታቸው ላይ በእንግሊዝኛ “ኢትዮጵያን አርሚ” ተብሎ የተፃፈበት የወታደር ልብስ የለበሱ ወታደሮች ጠላትን እያጠቁ ወደፊት እየሄዱ ናቸው:: የገጠሙት ብርቱ ፊልሚያ ነውና እያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው ጥንቃቄ የተሞላበትና መሰዋዕትነትን የሚቀንስ ነው::
የውጊያው ስልት በጥልቅ ወታደራዊ ስትራቴጂ የሚመራና እያንዳንዱ እንቅስቃሴ በታለመው እና በታቀደው መልኩ የሚመራ ነው:: ካልሆነ በጠላት በቀላሉ ለመጠቃት ምቼ ሁኔታን ይፈጥራል:: መጀመሪያ ቀድመው ቦታ የያዙ ወታደሮች ከኋላ በሚከተሏው ወታደሮች ላይ ከተቃራኒ አቅጣጫ ጥቃት እንዳይፈፀምባቸው ሽፋን ይሰጣሉ:: ውጊያው በቅርብ ርቀትና ፊት ለፊት ስለሆነ ወታደሮቹ ለጠላት እንዳይጋለጡ በደረታቸው ወደፊት በመሳብ አመቺ ቦታ ከያዙ በኋላ ከፊት የሚመጣውን የጠላት ሀይልን እየተከታተሉ ያጠቃሉ::
ኮሎኔል ሳህሉ በላይ የመከላከያ ሰራዊቱ የአንድ ክፍለ ጦር ብርጌድ አዛዥ ነው:: በውጊያ ስልትና በአመራር ብቃቱ ብዙዎች ያውቁታል:: በዚህ ግንባር ጦሩን ድል ያስገኙለታል ተብለው ከተመረጡና ለወሳኙ ውጊያ አመራርነት እንዲሰጥ ከተመለመሉ መካከል አንዱ ነው:: ጥሩ የአመራር ስልት በመንደፍና በወኔ በማዋጋት የጠላትንም ሴራ ቀድሞ በመረዳት ችሎታው የሚታወቅና በውትድርና ህይወት ውስጥ ፈጣን መሻሻል በማሳየት ማእረጎችን በአጭር ጊዜ ውስጥ የደራረበ ታታሪ ወታደር ነው::
በጦርነት ወቅት የጠላትን ወታደራዊ አቅም ፣የሎጀስቲክ እና የውጊያ ስልት በተለያየ መንገድ ማወቅ አልያም ቅርብ የሆነ ግምት ከሌለ በማያውቁት ውጊያ ውስጥ ገብቶ እጅ እንደ መስጠት ይቆጠራል:: ስለዚህ የጠላትን አቅም አስቀድሞ መገንዘብ ግድ ይላል:: ኮሎኔል ሳህሉ በወታደራዊ ስልት እውቀቱ በብዙዎች ይደነቃል:: በውሳኔው ፈጣንና ለጠላት ጊዜ የማይሰጥ ብርቱ የጦር አዛዥ መሆኑ ይታወቃል::
በዚህ ውጊያ “35 ነብሮ ይሰማል” የሬድዮ መገናኛ ድምፅ ነው:: ኮሎኔል ሳህሉ መገናኛ ሬድዮኑን ወደ ጆሮው አስጠግቶ መስማት ጀመረ:: “ነብሮ ወደ ኋላ ሳበው፤ ጠላት ቆርጦ ለመግባት ሙከራ እያደረገ ነው:: በግራ በኩል ለሚመጣው የወገን ጦር ሽፋን ስጥ” ከሌላኛው የመገናኛ ሬድዮኑ ጫፍ የሚሰማ ድምፅ ነው:: ኮሎኔል ሳህሉ ወዲያው ከስሩ ያለ ጋንታ መሪ ማድረግ ያለበትን ትዕዛዝ አስተላለፈ:: ውሳኔዎች በፍጥነት የሚሰጥበት በቅፅበት የበዙ እርምጃዎች የሚወሰድበት ፍልሚያ ነው:: እያንዳንዷ ነገር ያለ ስህተት መከወን ይኖርባታል::
በውጊያው የመከላከያ ሰራዊቱ ለወታደራዊ እንቅስቃሴ ወሳኝ የተባሉ አካባቢዎችና ከተሞች እየተቆጣጠረ ወደፊት ቢሄድም የእነ ኮሎኔል ሳህሉ ደብዛ መጥፋት ግራ አጋባው:: ለካስ ቆርጦ በገባ የጠላት ጦር ተማርከው ነበር:: ኮሎኔል ሳህሉ ከስሩ ካሉ 7 ወታደሮች ጋር በጠላት እጅ ወድቋል:: ጠላት ለስውር ዓላማው ይሆነው ዘንድ የተቃጣበትን ጥቃት መቋቋም ሲያቅተው ቆርጦ ገብቶ ውስን ወታደሮችን ይዞ ወጣ:: ከዚያ መሀል የተገኘው ኮሎኔል ሳህሉ ነበር::
የጠላት ጦር ወታደሮች ፊትም የኮሎኔል ሳህሉን ዝና ያውቁ ነበርና የማረኩት እሱን መሆኑን ሲያውቁ ላጡት ድል ማካካሻ እንደሚሆናቸው አስበው ፈነደቁ:: በጦር ሜዳ ተራ ወታደር መማረክና የውጊያ አዛዥ መማረክ እጅጉን ይለያያል:: የጦርነቱ ህግ የሚመራው በዕቅድና በተጠና መረጃ ነውና፤ ከጠላት የሚገኘው መረጃ በተጠናከረ መልኩ አዛዦች ዘንድ መገኘቱ ይታወቃል:: ስለዚህም ነበር የጠላት ጦር ኮሎኔል ሳህሉን መያዙ ያስደሰተው::
የጠላት ሀይል የማረከውን ኮሎኔል ሳህሉን በተለያየ ስልት ስለ መከላከያ ሰራዊት አጠቃላይ መረጃ እንዲሰጥ ቢያግባባውም የፈለገውን ማግኘት ግን አልቻለም:: በመጨረሻም በሀይል የፍላጎታቸውን ለማድረግ ወስነው አካላዊ ቅጣትና ስቃይ ያደርሱበት ጀመር፤ ይሁንና በፍጹም ምንም የተለየ ነገር ማግኘት አልቻሉም:: ለእነሱ ከኮሎኔል ሳህሉ መረጃ ማግኘት እያጡ ያሉትን ድል ለመመለስ ይጠቅማል ብለው እጅጉን ተስፋ አድርገው ነበርና መረጃውን እንዲሰጣቸው ሌላ ስልት ቀየሱ::
ይህ ስልት ካተሳካ ግን በውጊያው ላይ ብዙ ጥቃት ያደረሰባቸውንና ስሙ የገነነውን አሁን እጃቸው ላይ የሚገኘውን ኮሎኔል ሳህሉን እንደሚገሉት ያውቃሉ:: በእርግጥ ኮሎኔል ሳህሉም መረጃውን አላወጣ ሲላቸው እንደሚገሉት ገብቶታል::
አሁን ያቀረቡት ወጥመድ ግን ከውጊያና ከመረጃ ለቀናት ርቆ ለቆየው ኮሎኔሉ ፈታኝ ነበር:: የጠላት ጦር ያቀረበለት አማራጭ ከተሳሳተ መረጃ ጋር ነበር:: መከላከያ በብዙ ግንባር ድል እየተነሳ መሆኑንና የእነሱ ጦር በውጊያው አንፀባራቂ ድሎችን እያገኘ መሆኑን ነገር ግን የተቀረውንና የመጨረሻውን ድል በፍጥነት ማረጋገጥ እንዲችሉ መረጃ እንዲሰጣቸው ለመጠየቅና ከአገር ወጥቶ ተንደላቆ መኖር የሚችልበት ረብጣ ዶላር በሳምሶናይት ይዘውለት ቀረቡ::
ያቀረቡለት አማራጭ በሳቅ ቢያፈርሰውም፣ የሚያቀርቡለት የተሳሳተ መረጃ ግን ፈታኝ ሆነበት:: ኮሎኔል ሳህሉ ብዙ አሰበ:: መከላከያ ውጊያው ሲጀምር በጠላት በሎጀስቲክ እንደሚበልጥ ያውቅ ነበርና ያቀረቡለትን መረጃ እየተጠራጠረም ቢሆን ወደማመኑ ደረሰ:: በመጨረሻም ድርድር ውስጥ ገባ:: መረጃውን የሚሰጠው ግን ለእሱ አስተማማኝ ያለው ቦታ ሲደርስና ከኢትዮጵያ መውጣት የሚችልበት ምቹ ሁኔታ ሲመቻችለት መሆኑን ተናገረ::
ያን ሁሉ ሊያደርጉለት ወስነው በ3ኛው ቀን መረጃውን ተቀብለውት በሱዳን በኩል ቃል ከገቡለት ዶላር ጋር ሸኙት:: ኮሎኔል ሳህሉ ድንበር መሻገሩን ካረጋገጠ በኋላ በሳምሶናይት ውስጥ የታጨቀውን የአሜሪካ ዶላር ባለማመን ክፍቶ አስሬ ያየዋል:: የተሰጠው ዶላር በሽፍቶች እንዳይወሰድበት ከሳምሶናይት አውጥቶ መንገድ ላይ ባገኘው አንዲት ጨርቅ ልክ እንደ ስልቻ ጠቅልሎ በእጁ አንጠልጥሎ ብዙ ተጓዘ::
በእግር አንድ ቀን ከተጓዘ በኋላ ሱዳን ውስጥ እንዲት የገጠር ከተማ ደርሶ ወደፊት የሚያደርገውና ለመኖሪያ የሚሆነውን አገር ማሰብ ጀመረ:: የያዘው እስከ አለም ጫፍ ለመድረስ እና ምቹ ኑሮ መኖር የሚስችል ገንዘብ ለዚያውም ዶላር መሆኑን ያውቃል:: አገሩን መካዱ ወደፊት ከሚገጥመው እድልና ድሎት ጋር ፈፅሞ የሚያወዳድረው አልሆነበትምና በውሳኔው ደስ ተሰኘ::
የደረሰበት ከተማ ላይ አንድ መለስተኛ ሆቴል ውስጥ ገብቶ ከተመገበ በኋላ ማረፊያ ጠይቆ አንዳለ ተነገረው:: ራሱን ለማሳረፍ ወደ አልጋ ክፍሉ ሄደ:: ብዙም ሳይቆይ ከያዘው አልጋ ክፍል ወጣና ወደ አውሮፓ የሚያሻግሩ ደላሎችን ማጠያየቅ ጀመረ:: በቀላሉ ሰዎች አገናኙት:: ደላሎቹ የጠየቁትን ገንዘብ መክፈል እንደሚችል ሲያውቁ ተሯሩጠው ብዙ አማራጮችን ነገሩት:: በኮንትራት ላንድክሮዘር መኪና እስከ ሊቢያ ጫፍ ከሚያደርሰው ሰው ጋር ተስማማ:: ማለዳ ፀሀይ ሳትወጣ ካረፈበት ከተማ ለመውጣት ተስማሙ::
ለማረፊያ የተከራየው ሆቴል ገብቶ ወዳልጋው ያመራው ወዲያው ነበር:: የእግር ጉዞው በጣም አድክሞታል:: ክፍሉ እንደገባ ቴሌቪዥን ከፈተ:: ከቴሌቪዥኑ ላይ የሚያየው መረጃ ፈፅሞ ያልጠበቀው ነበር:: ዜናው መከላከያ የጠላት መቀመጫ የነበረችውን ከተማ በመያዝ ድል ማድረጉን የሚያውጅ ነበር:: ፈፅሞ ከጠበቀውና ከተነገረው የተለየ ነበር:: ግራ ተጋባ:: እሱ መከላከያ መሸነፉን ነበር የሚጠብቀው ፤ የተነገረውም ያ ነበርና::
ወዲያው የተከራየው ክፍል በር ተንኳኳ:: የፀጥታ ሀይሎች ነበሩ::በሚያየው ነገር ተደናገጠ:: በሆቴሉ አስተናጋጆች የታጀቡት የሱዳን የፀጥታ ሀይል ባልደረቦች ገብተው መበርበር ጀመሩ:: ለሆቴል አገልግሎት ክፍያ ዶላር አውጥቶ መስጠቱ ቆጨው:: ኮሎኔል ሳህሉ አገሩን አሳልፎ የሰጠበትን ገንዘብ ሊዘርፉት የመጡ መስሎት መታገል ጀመረ:: ፖሊሶቹ መሳሪያ ሲያቀባብሉበት እጁን ወደላይ አንስቶ ቆመ:: ፖሊስ ጣቢያ ይዘውት ሄዱ:: የያዘው ዶላር ሀሰተኛ ኖት መሆኑንና በማጭበርበር ወንጀል መከሰሱ ተነገረው:: ተፈፀመ::
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 14/2013