ሆድ ይዞ የሚያንቆራጥጥ፣ ቁጭ እድርጎ የሚያንቀጠቅጥ፣ አንዳንዱን ደግሞ መሬት ላይ እያንከባለለ የሚያንፈራፍር ሳቅ ግን የት ሄደ? እኔምለው ሰዎቹ እሱንም ሰርቀውን ነው እንዴ የሄዱት? ልክ ነው፤ እነሱ ስንቱን ጥሩ ጥሩ ነገር ወሰዱብን? የተዉልን አስለቃሹን ነው:: ግን ቆይ ጎበዝ እነሱ መሳቅ አይችሉ፤ ሴራ ላይ ናቸው፤ ሳቁ ምን ይሰራላቸዋልና ነው ይዘውብን የሄዱት?
እያስመለስናቸው እንዳሉት ብዙ ነገሮቻችን ሳቃችንንም ማስመለስ አለብን:: እዚህም ላይ መስራት አለብን:: በእርግጥ ውዶቼ ሙሉ ሳቃችን በቅርቡ ይመለሳል፤አትጠራጠሩ:: እናስመልሳቸዋለን:: እያመማቸውም ቢሆን ይመልሷታል::
እውነቴን ነው የምላችሁ፤ እኔ ካካካካካ….ቂቂቂቂቂቂ ሃሃሃሀሃሃ የሚሉት አንከትካች ሳቆች አይደለም በዚህ መልክ የሚስቅ ሰው ካየሁ ስንት ጊዜ ሆነኝ መሰላችሁ:: በዚህ መልክ የሚስቅ ሰው አገኘሁ ስል ወዲያው አቀሞ ይቆዝማል:: ወይ ጉድ!
ደግነቱ ግን እንዲሁ መለስ ያለ ሳቅ እዚህ እዚያም በምንመለከተው ጉዳይ አልራቀንም:: ባይሆንማ ህይወት በራስዋ ትፀልምብን ነበር:: አሁን ላይ ደግሞ ሳቆቻችን ከምሬት ውስጥ የሚፈልቁ ሳንወድ በግድ የሚያስፈግጉን ሆነዋል:: እነዚያ ሳቃችን የሰረቁት የሚቀልዱት መራር ቀልድ በእነሱ ላይ እንድንስቅ እያደረገን ነው:: ከዚያ መንደር ያሉት ባለማፈር የሚናገሩትን ባለማስተዋል የሚቀባጥሩት ሁሉ ሳንወድ በግድ እንድንስቅ ፣ሳንፈልግ እንድናስካካ እያደረጉን ነው::
ሰውዬው ለካስ “ወደው አይስቁ” ያለው ይህን አይቶ ነው:: የመረረ ጫዋታው የሚያስቃችሁ ሰው የለም:: እየሳቃችሁ የምትገምቱት እየሳቃችሁበት ጉዳዩ ቁብ የሌለው መሆኑን የምትገልፁለት አይነት ሰው:: የሳቃችን ምንጩ ሰዎቹ አልያም የሚያነሱት ርዕሰ ጉዳይ ነው:: ታዲያ በዚህ መልኩ ሳቅ የሚፈጥሩብን ሰዎች ፈፅሞ ውስጣችን ላይ አንዳች ደስ የሚል ስሜት አይፈጥሩብንም:: እንዲሁ በሳቃችን ውስጥ ለእነሱ ያለንን ምልከታ በብዙ ብናሳይ እንጂ::
አለ አይደል፤ ህፃናት በምናጫውትበት አልያም በምናባብልበት ጊዜ ህፃናቱ እኛ በምንፈጥረው ማታለል ሲታለሉና ሲስቁ እያየን እኛም የምንስቀው ሳቅ::ይሄንንም እንደዛ በሉት:: ልዩነቱ እነዚህ ሳቅ የሚፈጥሩብን ሰዎች የሚያነሱት ጉዳይ የመረረ መሆኑንና እኛ በእነሱ ንግግርና ተግባር መሳቃችን ብቻ ነው::
እኔ ምለው እነዚያ ሳቃችን የሰረቁት እነሱ ይስቁበት ይሆን እንዴ? አይመስለኝም፤ የእኛን ሳቅ ቀምተው ቢያለቅሱ እንጂ አይስቁም፤ መሳቅ አይችሉምና:: በእርግጥም እያለቀሱ ነው::
ምን እነዚህ ነጣቂዎች ስንቱን ቀምተውናል መሰላችሁ:: ግድ የለም አሁን ላይ የቀሙንን ሳቅ ሁሉ ወደራሳችን በራሳችን እንመልሰዋለን:: በዚህ እርግጠኛ ሁኑ:: በነገራችን ላይ በሴራቸው የቀሙን ሳቅ እንዳይጎልብን አስበው መሰለኝ አልፎ አልፎ በመራር ቀልዳቸው እንድንስቅባቸው እያደረጉን ነው:: አንዳንድ ብርቱ የሆኑ መራር ቀልደኛ ጥራዝ ነጠቅ ኮሜዲያን አላቸው::
አንዳንዴ ሰዎች ባላቸው ጠባብ ምልከታ ሰፊ እና ጥልቅ የሆኑ ውስብስብ ጉዳዮችን ያቀላሉ:: እነዚህ ሳቅ የሚፈጥሩብንና በሳቃችን የምንታዘባቸው ብሎም የምንስቅባቸው ሰዎች የምር ሳቅ አይፈጥሩብንም:: ይልቅ ስራና ተግባራቸው መራር ሳቅ ይፈጥርብናል:: ጥርሳችንን ከፍተን ምን አልባትም ካካካ ወይም ቂቂቂ ብለን ሳቃችንን በድምፅ ልናጅበው እንችል ይሆናል::
ከሳቆቻችን ነጣቂዎች አንዱ በነፃነት ሰውን ይዘልፋል፤ ያለ ልክ ማህበረሰብን ያንቋሽሻል:: አንድ ወቅት ስለ ባህላዊ ጨዋታ ሲያወራ ብዙዎች ፈግግ ብለውበት ነበር:: በቀልዱ ሳይሆን በቀላጁ ነው ፈገግ ያሉት::
ስሙ አሉላ ነው:: አሉላ የሚለው ስም ለእሱ ፈጽሞ አይመጥነውም:: ግን ምን ይደረግ፤ ራስ አሉላን በእጅጉ ይቃረናቸዋል:: እሳቸው ለአገራቸው የተዋደቁ ጀግና ፤ለኢትዮጵያ የታገሉ ታላቅ ሰው ሲሆኑ እሱ አገሩን ለማዋረድ የተፈጠረበትን ለማፍረስ የሚጥር የመንደር ቧልተኛ ነው:: ትልቅነትና ትንሽነት በሁለቱ መካከል ያለ ልዩነት ነው:: እናም የዚህን ጉደኛ ቧልተኛ ጉዳይ እያነሳሁ መራር በሆኑ ቀልዶቹ እጅግ ያጠረና ያላገናዘበ ምልከታውን ላሳያችሁማ፤ ቆዩኝ:: የምር በሳቅ ፍርስ ያሰኛል፤ ተግባርና ንግግሩ:: በአገር ላይ ለመቀለድ መሞከሩ ይመራል እንጂ::
ያኔ ትዝ ይላችኋል፤ ይህቺን አገር ለማፍረስ ዱብ ዱብ በይፋ የጀመሩ ሰሞን:: አዎ ያኔ ነው ፤ይህ ወገኛ መራር ቀልዱን ጀምሮ የነበረው:: “ጦርነት ለኛ ባህላዊ ጨዋታችን ነው…ከፈለጉ መጥተው ይግጠሙን” እያለ በይፋ የሰው ልጅን ያህል ክቡር ፍጡር ለመስዋዕትነት የሚያቀርብ ጦርነትን ሲቀሰቅስ ነበር:: ልብ አድርግ ወገን ፤“ ጦርነት ባህላዊ ጨዋታችን ነው” ነበር ያለው:: ምን ዋጋ አለው ይህ ቧልተኛ የሚጋጠመው ከኢትዮጵያ ልጆች ጋር መሆኑን ረስቶት ባህላዊ ጨዋታው ከ15 ቀን ባልበለጠ ጊዜ ሲከተከት ጨዋታውን ቀየረ::
መልሶም በሌላ ጨዋታው ትንሽ ፈገግ አስብሎን ብዙ ሳቅንበት:: ይሄ ልጅ ባህላዊ ነገር ይመቸዋል መሰለኝ:: ያኔ እሱ ባህላዊ ጨዋታችን ነው ባለው ወገቡ ከተሰበረ በኋላ ሌላ ባህላዊ ጉዳይን አነሳ:: “ወገኖቼ በፍፁም ከኢትዮጵያዊ በርበሬ፣ሽሮ፣እንጀራ ባህላዊ ምግብ እንዳትገዙ፤ እንዳትጠቀሙ” ብሎ አንድ ብቻውን እየቀባጠረ በሚውልበት ገፁ ላይ አሳዛኝ የሆነ ገፅታውን ይዞ ሲናዘዝ ሰምተንም ስቀንበታል:: ምን እንዲበሉ አስቦ ይሆን? እኔ ምለው ይሄንን ቀልድ ግን ከየት ለምዶት ይሆን እባካችሁ:: አሁን ላይ በጠፋ ቀልድና ሳቅ እሱ ባይኖር በምን እንስቅ ነበር ፤ማለቴ ማን ላይ እንስቅ ነበር:: ምን ዋጋ አለው ?ሊያስቀን የሚነግረን ሁሉ ስለሱ እያሰብን መሳቀቃችን በዛ እንጂ::
ይሄ ጉደኛ ሰሞኑን በሌላ መራር ቀልድ ብቅ ብሏል:: እኛ ያልመራናት ኢትዮጵያ ብትንትንዋ ይውጣ:: እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ ህልውናዋ ምን ሊረባ ብሎ በድፍረት ሲናገር ተሰምቷል:: አይገርምም ውዶቼ አንድ ተራ ቧልተኛ ኢትዮጵያን የምታክል ግዙፍ አገር በጠባብ መነፅሩ ተመልክቶ እኔና የኔ ቢጤ ብቻ ካልተጠቀመ እንደፈለገ ካላዘዘና ካልሰረቃት አታስፈልግም ብሎ ሲደነፋ:: በእርግጥ ልኬታውን የማያውቅ የኢትዮጵያን ትልቅነት በምን እሳቤ ሊረዳ ይችላል::
ለምስረታዋ አንዲት ጠጠር ያልወረወረ፣ ስትፈጠር ለመፈጠር አይደለም ያልታሰበ አንድ ተራ ቧልተኛ ነው እንግዲህ ቀዳሚ የሆነ ታሪክ የተጎናፀፈች፣ህዝቦችዋ በፍቅር ተሳስረው የሚኖሩባትና በአንድነት ጠብቀዋት የቆይዋትን እምዬ ኢትዮጵያን ብትንትንዋ ይውጣ የሚል::
ደፋርና ደንባራ መነሻውን እንጂ መድረሻውን አያስብም ይባላል:: የሚገርመው ግን ይሄ ጉደኛ መነሻውም መድረሻውም በፍፁም ያለየ ነው:: ማስረጃ አለኝ መነሻው ዛሬ እኔ ካልመራኋት ትፍረስ እኔ እንዳሻኝ ካልዘርፈኳት ትውደም የሚላት ኢትዮጵያ ጡት ነካሽ ሆኖባት እንጂ ከአመዳማነት ወደ ወዛማነት ቀይራው ነበር::
ኢትዮጵያ እናት ናትና እሱንም ልጄ ብላ አቅፋ አሳድጋ ከሌላት ላይ ቀንሳ ከፍ አድርጋው ነበር:: ከሀዲነቱ በርትቶ ዝቅታ ላይ ተገኘባት እንጂ:: እናም መነሻውን ነው ትውደም የሚለው:: ምክንያቱም መነሻውን አያውቅማ::
መድረሻውንም አያውቅም ያልኩትም በምክንያት ነው:: የኢትጵያን ግዙፍነት፣ የኢትዮጵያዊያን ፅኑነትና አገር ወዳድነት፣የህዝቦችዋን አንድነት ጠንቅቆ አያውቅምና ዛሬን እንደምትሻገር ነገ መፍረስ ሳይሆን መጠንከር የእስዋ መገለጫና ከፍታ መገኛዋ መሆኑን አያውቅም:: እሱና ሴረኛ ሀሳቡ ከመሰል ጋሻጃግሬዎቹ ጋር መድረሻ እንደማያገኙ መገኛቸውም ተራ ቦታ እንደሆነ አይረዳም:: ስለዚህ ይህ ጉደኛ መነሻውንም መድረሻውንም አያውቅም::
እሱ ብቻ አይደሉም በእድሜ ዘመናቸው ምላስና ሰንበር ብቻ መተዳደሪያቸው፣ውሸትና ቅጥፈት የስራ ዘርፋቸው የሆኑ መሰሎቹ እንደሱው መራር ቀልድ እየቀለዱ እንድንስቅባቸው ደጋግመው ግብዣ ያቀርቡልናል:: እኔ የምለው ሰው ስብዕናን የሚያህል አካል ተሸክሞ፤ ሰው መምሰልን መስሎ እንዴት ርካሽ ነገርን ከራሱ ጋር ያዋህዳል:: ኢትዮጵያን ከመሰለ ውድና ክቡር ማንነት ረከስ ብዬ ልገኝ እንደምን ይላል? አበቃሁ፤ ቸር ይግጠመን::
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 14/2013