በሐሰት የቱንም ያህል ትርክት መደርደር ቢቻል መቼም ቢሆን እውነት ሊሆን አይችልም፡፡ ለተወሰነ ጊዜ ውሎ ቢያድር እንጂ እውነቱ ራሱ ውሸቱን ይገልጠዋል፡፡ ባዶነቱንም በአደባባይም ያስጣጣዋል፡፡ የአሸባሪው ትርክት፣ የአይጥ ምስክር ድምቢጥ እንዲሉ በምዕራባውያኑም ጭምር የታገዘ በመሆኑ ለቅጽበት ያህል እውነት ሊመስል ይዳዳው ይሆናል፤ ነገር ግን ከእውነት ጎን ተስተካክሎ መቆም ስለማይችል እየተሸማቀቀ እንደ ጤዛ ይረግፋል፤ እየረገፈም ይገኛል፡፡
የትኛውም የኢትዮጵያ ጠላት የሆነ አካል የተቻለውን ያህል እውነት የመሰለ የሀሰት ትርክት ሲደረድር ውሎ ሲደረድር ቢያመሽ፣ ኢትዮጵያን ማፍረስ አይቻለውም፡፡ ይህን ማድረግ እንደማይቻለውም የኢትዮጵያ ታሪክ የማይደበዝዝ ደማቅ ማሳያ ሆኖ ዛሬም ድረስ የዘለቀ በመሆኑ እውነተኞች እሱኑ እየተገበሩ ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ያለፈ ታሪኳና ዛሬ የገጠማት ተግዳትን በማስተሳሰር እንዴት መሻገር እንደሚገባ የታሪክ ተመራማሪውን ፕሮፌሰር ላጲሶ ጌዴሌቦን አዲስ ዘመን አነጋግሮ እንደሚከተለው አጠናቅሮታል፡፡ መልካም ንባብ ይሁንልዎ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ታሪክ ያላት አገር መሆኗን ታሪክ ራሱ ይመሰክራል፤ ለመሆኑ የኢትዮጵያን ታሪክ ስናወሳ ከየትኛው ዘመን ነው መጀመር ያለብን?
ፕሮፌሰር ላጲሶ፡- ዛሬ ያለው መንግስት እንዲህ አይነት መልክ ይዞ ለመነሳቱ ጅማሬው ከታላቁ አጼ ምኒልክ ዘመነ መንግስት ነው ማለት እንችላለን። ይህን ስል ሁላችንም በእርሳቸው ዘመን የተሰራ ታላላቅ ነገር ስለመኖሩ ስለምናውቅም ጭምር ነው፡፡ በእርግጥ በ19ኛ ክፍለ ዘመን የውጭ ጠላቶች አፍሪካን ስለከበቡ አጼ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያ እንዳትጠፋ ሲሉ ህይወታቸው እስካለፈች ድረስ ኢትዮጵያን ማደስ የጀመሩ ንጉስ ናቸው፡፡
አባይ ውሃ በመለስ እና ህንድ ውቅያኖስ በመለስ ያለው ሁሉ የእኛ ነው የሚሉ እነዚህ ኢትዮጵያውያን ነገስታት ናቸው፡፡ በእርግጥም የተጠቀሰው ሁሉ የእኛ ነው፡፡ በዘመኑ እንደ ኢትዮጵያ የተነሳ ታላቅ መንግስት የለም፡፡ የቱንም ያህል ድክመት ቢኖርም ሁሉም ሲጠፋ ኢትዮጵያ ግን እስከዛሬ ድረስ አልጠፋችም፡፡ በወቅቱ የአጼዎችን መንግስት ማደስ ነው መድሃኒቱ በማለት የታገሉት አጼ ቴዎድሮስ ቢሆኑም ሰው አልተቀበላቸውም ነበር፡፡
ከዚህ በኋላ ደግሞ አጼ ዮሐንስ ይነሳሉ፡፡ እርሳቸውም ከአጼ ቴዎድሮስ የተማሩት ነገር ስለነበር እርሳቸውን ጨምሮ በወቅቱ የተነሱት መንግስታት ሁሉ ልክ እንደ አፄ ቴዎድሮስ ሁሉ ትልቋን ኢትዮጵያ ማንገስ ይፈልጋል፡፡
በዚያን ወቅት ኢምፔሪያሊዝም ግብጽ ደርሶ፤ ሱዳንን አቋርጦ ጎንደር ላይ ለመውረር ነበር የሞከረው።ጊዜው አጼ ቴዎድሮስ የንጉሰ ነገስት ግዛትን ህዳሴ የጀመሩበት ወቅት ነው፡፡ ይሁንና እንዳልኩት ከውስጥም ከውጪም ሰዎች አልተቀበሏቸውም ነበር። በወቅቱ ደግሞ እንግሊዞች ኃይል በመጨመር ነበር የተነሱት፡፡ በዚህ ጊዜ ግን አጼ ዮሐንስ ከትግራይ እንደተነሱ ይታወሳል፡፡
አጼ ዮሐንስም ልክ እንደእርሳቸው የጥንቷ ኢትዮጵያ ህንድ ውቅያኖስ፣ ቀይ ባህር እንዲሁም አባይ ሸለቆ በመለስ ነው የሚል እሳቤ ያላቸው ናቸው። አጼ ቴዎድሮስና ትግራይም ይህንኑ ጉዳይ አጠናከሩ። በዚሁ ትግል ውስጥ እያሉ ነው በጦር ሜዳ ግንባር የተሰውት።
ከእነዚህ ነገስታት በኋላ ታላቁ ሰው ብዬ የምጠራቸው አጼ ምኒልክ ናቸው፡፡ በጣም አስገራሚው ነገር ኢምፔሪያሊዝምን በጦር ሜዳ ደምስሰው ያልተሰራ ታሪክ የሰሩ ናቸው። ነጭን፣ አውሮፓንም ባለፉት ጊዜያት ውስጥ ያሸነፈ የለም።ኢትዮጵያ ናት በአደዋ ጦርነት ላይ ነጭን ያሸነፈች ታላቅ አገር በመሆን ስሟ ዘወትር የሚጠቀሰው፡፡ ስለዚህ ዛሬ አገሬ ኢትዮጵያ ብለን የምንጠራትን ታላቂቷን ኢትዮጵያ ያስወረሱን እነዚህ ታላላቅ ነጋስታት ናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ የታሪክ ምሁራን እና ፀሃፊዎች ኢትዮጵያ ቀደም ሲል እስከሩቅ ምስራቅ ድረስ፤ ከፊሎቹ ደግሞ እስከሰሜን አፍሪካ ትገዛ እንደነበር ይገልጻሉ፤ ከዚህም አልፎ የጥቁር ህዝቦች መጠሪያ እንደሆነች የሚገልጹ አሉ፤ ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ የግዛት ወሰን እስከምን ድረስ ይዘልቅ ነበር?
ፕሮፌሰር ላጲሶ፡- ሰዎች ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ የምትገኝበትን አካባቢ የአፍሪካ ቀንድ ሲሉ ይጠሩታል፡፡ ቀንድ የሚባል ነገር የለም፤ ያለው አገር ነው፡፡ አጼ ቴዎድሮስና ጎንድር፣ አጼ ዮሐንስና ትግራይ፣ አጼ ምኒልክና ሸዋ፤ ሰሜን ምስራቅ አፍሪካ ማለትም ኢትዮጵያ ራሷን ይዞ ሱዳን፣ ኬንያን ጨምሮ አንድ አራትና አምስት የሆኑ አገሮች በአንድ ላይ የእኔ ናቸው ይላሉ፡፡ እነዚህ ነገስታት ያንን አካባቢ አንድ ያደረጉ ሰዎች ናቸው፡፡ አጼ ምኒልክ የአደዋን ድል የተጎናጸፉት በአራት ሰዓት ውስጥ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ነጋስታት የእኛ ድንበር ብለው የሚሉት ከህንድ ውቅያኖስ በመለስ ያለውን አገር ሁሉ ነው፤ ነገስታቱ ስፍራዎቹ የአባቶቼ ነው የሚሉ ናቸው፡፡ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ሱማሊያ ድረስ የኢትዮጵያ ግዛት ነው በሚል ነው የሚያምኑት፡፡
አጼ ምኒልክ ካደረጉት ታላቅ ገድል ዋናው የአደዋ ጦርነት ስለመሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ በየትኛውም ኃይል ግዛቴን አላስደፍርም በሚል ነው ተጋድሎ ያደረጉት፡፡ ከአደዋ ጦርነት በኋላ የአውሮፓ መንግስታት ወዲያውኑ ነው የአጼ ምኒልክ መንግስትን በአግባቡ ያወቁት፡፡ ጣሊያን በጥቁር ተሸነፈ መባሉን በፍጹም ግን ማመን አልቻሉም ነበር፡፡
አዲስ ዘመን፡-ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው ከሚታወቁባቸው ነገሮች አንዱ የነፃነትና የአልደፈር ባይነት ተምሳሌት መሆናቸው ነው፡፡ ለመሆኑ የኢትዮጵያ የነፃነት የተጋድሎ ታሪክ ምን መልክ አለው?
ፕሮፌሰር ላጲሶ፡- የድል መልክ ነዋ ያለው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ በባህሪው መገዛትን አያውቅም፤ በመጀመሪያም ቢሆን ለማን ተገዝቶ ያውቅና ነው! በየትኛውም ዘመን ያለው የኢትዮጵያ መንግስት ለማንም ተገዝቶ አያውቅም፡፡ ይልቁኑ አፍሪካ በሙሉ የኢትዮጵያ ነው የሚል ጀግና ነው፡፡
ከአጼ ቴዎድሮስ በፊት በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ቱርኮች መካከለኛውን ምስራቅ ይዘው ነበር።የኢትዮጵያ ነገስታት ግን የኢትዮጵያ ድንበር ቀይ ባህር በመለስና ህንድ ውቅያኖስ በመለስ እንደሆነ ነው የሚገልጹት፡፡ እኔም ይህንኑ እነርሱ የሚሉትን ነው የማምነው፤ የምቀበለውም፡፡ ለምሳሌ ዛሬ ኤርትራ፣ ትግሬ፣ አማራ ወይም ሌላ ሌላ ሊባል ይችላል፤ ነገር ግን ሁሉ በእዛ ውስጥ ያለ ነው፡፡ በወቅቱ የነበረው ህዝብ የቋንቋ ብዛት ሳይለየው ነው ለሚመጣው ነገር ሁሉ የሚተባበረው፡፡
ወደ ዘመነ አጼ ኃይለስላሴ ሲመጣ ደግሞ አፍሪካን አንድ አድርገው የያዙ ንጉስ ናቸው፡፡ ለክፉም ሆነ ለደግ ሁሉም አፍሪካውያን የሚመጡት ወአገራችን ኢትዮጵያ ነው፡፡ እርሳቸው በጣሊያን ወረራ ጊዜ ለተወሰኑ ጊዜያት በውጭ ቢቆዩም በድል ወደ አገራቸው መመለስ ችለዋል፡፡ ሁሉም በወቅቱ የነበሩ ነገስታት በየትኛው መልክ ጠላት አገራችንን ለመውረር በመጣ ጊዜ የየራሳቸውን ተጋድሎ ፈጽመው የዛሬዋን
ኢትዮጵያ ለትውልድ ያቆዩልን ናቸው፡፡ እናም እኛ ኢትዮጵያውያን የማንም ተጽዕኖ ሳያንበረክከን እዚህ የደረስን ነን ማለት ይቻላል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በተለይ ከቅኝ ግዛት ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ቅኝ ባለመገዛት ለጥቁር ህዝቦች ሁሉ አርአያ የሆነች አገር ናት፤ ይህ ታሪክ ከምን የመነጨ ነው?
ፕሮፌሰር ላጲሶ፡- አጼ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ ተነሱ፤ ለእሱም ዓላማ መስዋዕት ሆኑ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን አንድ በጣም የሚያሳዝነኝ ነገር ቢኖር የትግራይ ተወላጅ ሆኖ እያለ ከኢትዮጵያ እለያለሁ መባሉ ነው፡፡ እንዲህ እያሉ ያሉት ደግሞ የአጼ ዮሐንስ ልጆች ናቸው፡፡ አጼ ዮሐንስ ብቻ ሳይሆኑ በኢትዮጵያ የተነሱ ነገስታት ሁሉ ዛሬ ላይ ከትግራይ ጉያ የወጡ ልጆች የሚባሉ ሰዎች ያነሱትን እንዲህ አይነቱን ሐሳብ ማንም አንስቶት አያውቅም፡፡
እንኳን ኢትዮጵያን እርስ በእርሷ እንድትከፋፈል ለማድረግ ቀርቶ አሁን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ እየተባለ የሚጠራውን አገር ሁሉ የእኔ ነው የሚል መሪ ነበር በኢትዮጵያ ስለመኖሩ የምናውቀው፡፡ አውሮፓውያኑ አፍሪካን ለእኔ ለእኔ በሚል ሲከፋፈሉ ኢትዮጵያ ግን ከራሷም አልፋ ድንበሬ እስከዚህ ድረስ ነው በሚል ነበር ቆራጥነቷን በተግባር ስታስመሰክር የነበረው፡፡
እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጣሊያን የዛሬ ኤርትራና ሱማሊያ የሆነውን ጠረፉን ያዙት፤ ከአጼ ቴዎድሮስ በኋላ በአጼ ምኒልክ ጊዜ ማለት ነው፡፡ አጼ ምኒልክ ከአደዋ ጦርነት በኋላ ድሉን በጦር ሜዳ ተጎናጽፈው እያለ፤ ኤርትራን አሳልፈው ሰጡ ተባለ፡፡ ነገር ጣሊያን ኢትዮጵያን ወሮ የነበረው ኤርትራን ይዞ ነው፡፡ እርሳቸውም ጣሊያን ኤርትራን ስለመያዙ ያውቃሉ። ይሁንና በኋላ ላይ አሸንፈው በወቅቱ የነበረችውን ኢትዮጵያ መሰርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት እኛ በድህረ አብዮትና ዘመነ ሪፐብሊክ ነው የምንኖረው፤ ይህ ታላቅ ነገር ነው፡፡ በአሁን ወቅት በዓለም አቀፍ ደረጃ አገራቱን ከእርሱ ጎን ያሰለፈ እንደ ኢትዮጵያ የለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያውያን ለነፃነታቸውና ለሉአላዊነታቸው የሚያደርጉት ተጋድሎ አሁን ባለበት ሁኔታ ምን ይመስላል፤ በተለይ ወረራን ባለመቀበል ያላቸው ስነልቦና እንዴት ይገለፃል?
ፕሮፌሰር ላጲሶ፡- የትግራይ ልጆች አማራን ወይም ኦሮሞን እንዲህ አደርጋለሁ ብለው አስበው አያውቁም፡፡ ቀደም ሲል ስልጣን ላይ ከመውጣታቸው በፊት አቶ መለስና ወያኔ ለ17 ዓመታት የኢትዮጵያን መንግስት ይዘው ነበር፡፡ ይህን ሲያደርጉ የነበረው ደግሞ በአሜሪካን መንግስት ድጋፍ ነው፡፡ አቶ መለስ ጫካ እያለ የአሜሪካን መንግስት ግባና ኢትዮጵያን ያዝ ሲለው ነበር፡፡ የአሜሪካ መንግስት ወታዳራዊ መንግስትን ስለጠላ መለስን ኢትዮጵያን ሂድና ያዝ ነው ያለው፡፡ መለስም የአሜሪካን ትዕዛዝ ተቀብሎ ነው የገባው እንጂ ወታደራዊ መንግስትን ታግሎ ስላሸነፈ አይደለም፡፡ በዚህ መልኩ ኢትዮጵያን ከውስጥም ከውጪም ለማጥፋት የሚሞክሩት በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ኢምፔሪያሊዝም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተሸንፎ አይታወቅም ነበር፤ ነገር ግን የተሸነፈው በኢትዮጵያ ነው፡፡
ሌሎች ቢያውቁት ወይም ሊያውቁት ባይፈልጉም የኢትዮጵያ መንግስት ምንም ጊዜ ቢሆን ኃያል መንግስት ነው፡፡ አሁንም ቢሆን ለብዙዎች አይመሰል እንጂ አፍሪካን እየመራች ያለች አገር ኢትዮጵያ ናት፡፡ ለምሳሌ አሜሪካ አሁን ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የኢትዮጵያ ጠላት ሆናለች፡፡ ምክንያቱም በኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ በማደረጉ በኩል ከልክ ያለፈ መንግስት ሆኗል፡፡ ይሁንና ተጽዕኖው በአሜሪካም ሆነ በሌላው በኩል ቢበረታም ኢኢዮጵያውያን ሸብረክ የማለት ባህሪ ዛሬም ሆነ ትናንት የላቸውም፤ አልነበራቸውምም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ላይ እየተቃጣ ያለው የውጭ ጫና እና የውስጥ ጫና ኢትዮጵያን የማፍረስ ሙከራ ነው፤ ይህ ከምን የመነጨ ነው ይላሉ?
ፕሮፌሰር ላጲሶ፡- ሌላ ምን ምክንያት ይኖራቸዋል? ዋናው ነገር ኢትዮጵያን የራሳቸው አገር አድርገው እንዳሻቸው ለማድረግ ነው፡፡ በተቻላቸው ሁሉ በኢትዮጵያ ታዛዥ መንግስት እንዲኖርም ስለሚፈልጉ ነው፡፡ የተባለውን ከመፈጸም ውጭ ጠያቂ የሆነ መንግስት ስለማይፈልጉም ጭምር ነው። ይሁንና ምንም እንኳ ፍላጎቱ ቢኖራቸውም አሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ ምንም አይነት ፍንጭ የማይሰጥ መሪ መሆኑን እያወቁ ነውና ተስፋ የቆረጡ ይመስለኛል፡፡
የግብጽ በር ክፍት ነው፤ የተከፈተ በር ካለ ደግሞ ሌባ ይገባል፡፡ የግብጽ በር ወለል ብሎ ለሌባ መከፈቱ ሌባው ወደ ኢትዮጵያ እንዲዘልቅ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ነው፡፡ ግብጽም፣ ኢትዮጵያ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ እንዳታከናውን የተቻላትን ሁሉ ብታደርግም ኢትዮጵያ ግን ውሃው ለሁላችንም ይበቃል በሚል መርህ መልካምነቷን ስታሳይ ቆይታለች፡፡
ዓለም የትግል ሜዳ ነው፡፡ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ አምስት ታላቅ መንግስታት ተነስተዋል። አንዷ እንግሊዝ ናት፤ እርግጥ አሁን ላይ እንግሊዝ የቀደመ ጥንካሬዋ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ሌላዋ ደግሞ አሜሪካ ናት፤ አሜሪካም በሽተኛ በመሆኗም እምብዛም ተቀባይነት የላትም፤ አፍሪካውያንም አይቀበሏትም፡፡ ሌሎች መንግስታት ደግሞ ፈረንሳይ፣ ራሽያ፣ እና ቻይና ናቸው፡፡
እነዚህ አምስት ታላላቅ መንግስታት ባሉበት ስፍራ ኢትዮጵያ ኃያል ሆና ማሸነፍ ችላለች፡፡ መቼ ብትዪ ደግሞ ባለፈው በህዳሴ ግድባችን ምክንያት የደረሰብንን ስሞታ ግልጽ ለማድረግ በተካሄደ መድረክ በኃያሉኑ ፊት ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆና መውጣት ችላለች፡፡ ስለዚህም ነው የቱንም ያህል ኢትዮጵያን ለማፍረስ የተለያየ ጫና በተለያዩ አካላት ቢደርስብንም ኢትዮጵያ ግን በአምስቱ ታላላቅ አገሮች ፊት አሸናፊ ሆና ታይታለች፡፡
እንደ እኔ እምነት ከዚህ በኋላ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ተጨማሪ ጫና ልታደረስ የምትችልበት መንገድ የለም፡፡ በአንድ ወቅት በሱማሊያ ጦርነት ጊዜ ኢትዮጵ መሳሪያ ለመግዛት ለአሜሪካ የከፈለችውን ገንዘብ አሜሪካ መሳሪያውን አልሳጥም ማለቷ የሚታወስ ነው፤ ታላቅነት ማለት ታዲያ በግብሩ መልካም ሆኖ ካልተገለጠ ምኑን ታላቅ መንግስት ሆነ፡፡
በነገራችን ላይ ፕሬዚዳንት መንግስቱ ኃለማርያም በወቅቱ አብዮቱን የመሩ እና ትልቅ ቦታ ያደረሱ መሪ ናቸው፡፡ የአሜሪካ መንግስት ክህደት ቢፈጽምም እርሳቸው ወደራሺያ ሄደው መሳሪያ በማምጣታቸው በዚያ መሳሪያ በወቅቱ ወርራን የነበረችውን የሱማሊያን ጦር መደምሰስ ተቻለ፡፡
እኔ ሁሉንም ትምህርት ማለት በሚያስደፍር መልኩ ያገኘሁት በአገረ አሜሪካ ነው፡፡ ለዚህም የአሜሪካንን ህዝብ በጣም እወዳለሁ፡፡ የአሜሪካን መንግስት ግን ከልክ ያለፈ ተግባር እየፈጸመ ያለ መንግስት ነው። ምክንያቱም በየጊዜው ኢትዮጵያን እያሳለፈ የሚሸጥ መንግስት ነው፡፡ አሁንም ደግሞ ኢትዮጵያን ያህል ታላቅ አገር ከወንበዴው ጋር ታረቁ በሚል ፍላጎት ማሳየቱ አግባብነት የሌለው አስተሳሰብ ነው፡፡
እንዲያም ሆኖ አሜሪካና መሰሎቿ ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር ቢጣጣሩም ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙ አገራት ደግሞ አሉ፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ ቱርክ ኢትዮጵያን እንደምትደግፍ ገልጻለች። ራሺያም እንዲሁ ኢትዮጵያን ስትደግፍ ተስተውሏል። በተመሳሳይ ቻይናን ብትወስጂ ደግሞ ከኢትዮጵያ ጎን ናት፡፡ ቻይና ኢትዮጵያን ደገፈች ማለት ደግሞ የዓለም ዋነኛዋ ኃያል አገር እንደመሆኗ ዓለምን እንደመቆጣጠር የሚቆጠር ነው፡፡
ስለዚህ አሁን እየታየ ያለ ጫናና መሰል ነገር ለታላቋ አገር ኢትዮጵያ ምንም እንዳልሆነ ነው የሚሰማኝ። ምክንያቱም ኢትዮጵያ የተሸናፊነት ታሪክ የላትም። እኛ ኢትዮጵያውያን ኢምፔሪያሊዝምን በዚያን በጨለማው ወቅት ምንም በሌለበት ጊዜ ያሸነፍን ህዝብ ነን፡፡ እኛ የቴዎድሮስን ስራ አርማ ይዘን የተነሳን ትውልድ ነን፡፡ ቴዎድሮስ አልሞቱም፤ ኢትዮጵያን አንድ የማድረግ ዓላማ ይዘው የተነሱ የታላቁ ንጉስ ዛሬም የእርሳቸው ትውልድ የሆንን ህዝብ በመሆናችን የማንም ጫና ኢትዮጵያዊነታችንን አይከፋፍለውም። ኢትዮጵያ ተራ አገር አይደለችም፡፡ የኢትዮጵያን መንግስት የዋሽንግተን መንግስት የሚያዘው አይደለም፤ በሌላ አገር መንገስት የመታዘዝ ባህሪ የለሌን፤ ይህ ሊሆንም አይችልም፡፡
አጼ ቴዎድሮስ በወቅቱ በአካባቢ ያቸው ያሉትን አንድ ለማድረግ ጣሩ፤ አጼ ዮሐንስ ደግሞ ቀጠሉ፤ አጼ ምኒልክ ደግሞ ይበልጥ አጠናከሩ፡፡ በጣሊያን ወረራ ጊዜ ዓለም አጭበርብሮ ኢትዮጵያን ሊያጠፋ ቢሞክርም ከሶስትና አራት ዓመት በኋላ ግን ኢትዮጵያ መልሳ ድል አደረገች፤ አጼ ኃይለስላሴም በድል ወደአገራቸው ገቡ፡፡
ስለዚህ ኢትዮጵያ በምንም በማንም አትደፈርም፡፡ የትግራይ ልጆች በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያን መንግስት የአሜሪካ መንግስት አንድ እንዲልለት በየቀኑ በአሜሪካ መንግስት ቤተ መንግስት በየቀኑ ደጅ እየጠኑ ነው፡፡ ይሁንና የአሜሪካ መንግስት የኢትዮጵያን መንግስት እንዳሻው ሊያዝ አይችልም። ምክንያቱም ኢትዮጵያ በጣም ትልቅ አገር ከመሆኗም በተጨማሪ የምታደርገውን ጠንቅቃ የምታውቅ አገር ነች፡፡
አዲስ ዘመን፡- ኢትዮጵያ ከግብጽም ሆነ ከሱዳን ጋር ባላት ግንኙነት በነዚህ አገራት የሚደረግባት ደባ ምን ይመስላል? በተለይ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ በየጊዜው ጫና ሲያደርጉ ነበርና የነዚህ አገራት ጫና እስከምን ድረስ የዘለቀ ነው?
ፕሮፌሰር ላጲሶ፡- ኢትዮጵያን መንካት ሁሉንም አፍሪካ እንደመንካት ይቆጠራል፡፡ ኢትዮጵያ አንድ አገር ብቻ አይደለችም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ አፍሪካን የምትመራ አገር ናትና ነው።ሱዳንና ግብጽ ኢትዮጵያ ላይ ተጽዕኖ ለማድረስ የሚያደርጉት ሩጫ አሁን ላይነሳ ወድቋል፡፡
በእርግጥ በአንድ ወቅት እነርሱ ጉዳዩን ወደ አሜሪካ አድርሰው የነበረ ሲሆን፣ የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ትራምፕ የሚሏቸው ሰውዬ ስለግድቡና ስለሁኔታው አንዳች ግንዛቤ ሳይኖራቸው የህዳሴ ግድቡን ማፍረስ ነው ማለታቸው ይታወሳል። ግራም ነፈሰ ቀኝ የአፍሪካን ጉዳይ መጀመሪያውኑ ወደዛ መውሰድ አግባብነት የሌለው ነበር፡፡
እንዲያም ሆኖ ጉዳዩ አሜሪካም ወጣ አፍሪካም ወረደ ኢትዮጵያ በየትኛውም ስፍራ አሸናፊነቷን አረጋግጣለች፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ መንግስትና ህዝብ ከኢትዮጵያ ላይና ከህዳሴ ግድባችን ላይ አሜሪካንን እጅሽን አንሺ ባለው መሰረት አስነስቷል። ከዚህ በኋላ በህዳሴ ግድባችን ላይ ማንም እንዳሻው ጣቱን መቀሰር አይችልም፡፡
በመጀመሪያ ደረጃ ግብጽ ማን ናት? ሱዳንስ ብትሆን ምንድን ነች? ወንበዴው ህወሃትስ ቢሆን ምንድን ነው? ኢትዮጵያ በየዘመኑ የተነሱባትን ጠላቶች አሳፍራ የመመለስ ባህሪ ያላት አገር እንጂ ለአፍታ እንኳ እጇን ሰጥታ የማታውቅ ነች፡፡ ለወንበዴው ህወሃት ደግሞ በአገሩ ጉዳይ ላይ ይህን መሰል ተግባር እየፈጸመ መገኘቱ ለእርሱ ትልቅ ውርደትም ቅሌትም ነው፡፡ የትኛውም አካል ኃያል ናቸው የሚላቸውን አካል ይዞ ኢትዮጵያን ማጥቃት በጭራሽ አይችልም፡፡ በፊትም ቢሆን ሆኖ አያውቅም፡፡
አዲስ ዘመን፡- አሁን አሸባሪው ህወሃት በኢትዮጵያ ላይ የከፈተው ጦርነት አለ፤ ይህ ድርጊት የባንዳ ተግባር ነው ልንል እችላለን?
ፕሮፌሰር ላጲሶ፡- ይህን ቡድን ማሸነፍ ብቻ ነው የሚያስፈልገው እንጂ መስደብ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ይህ ያልሽው ቡድን እኮ ለኢትዮጵያ ሰራዊት ለቁርስ እንኳን የሚሆን አይደለም፡፡ ይህን ቡድን አማራ ብቻውን ቢገጥመው አፍታም ሳይቆይ ወዲያውኑ ያሸንፈዋል፡፡
ነገር ግን ኢትዮጵያና ትግራይ ተዋጉ ብሎ ማሰብ በራሱ ከባድ ነው፤ አማራና ትግራይ ተዋጉ ማለት አሳፋሪ ነገር ነው፤ ይህ የኢትዮጵያ መገለጫ አይደለም።በእርግጥ ከኢትዮጵያ ጋር የሚዋጋ ሁሉ አያሸንፍም፤ ኢትዮጵያን ማንም ማሸነፍ አይችልም፡፡ ይሁንና ኢትዮጵያውያን እርስ በእርሳቸው ተዋጉ የሚለውን ለማሰብ ግን አሁንም ቢሆን እንደሚከብደኝ ነው ልገልጽልሽ የምፈልገው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአሁኑ ወቅት በውጭ ሃይ ሎችና በአሸባሪው የህወሃት ቡድን የተከፈተውን ጦርነትና ጫና ለመቋቋም ኢትዮጵያውያን በአንድነት ቆመዋል፤ ይህ ከታሪክ አንጻር እንዴት ይታያል?
ፕሮፌሰር ላጲሶ፡– የባለቤትነት ስሜት መኖሩን ነው የሚያሳየው፡፡ አማራ ወይም አፋር ተነካ ሲባል ሁሉም ኢትዮጵያዊ በመሆኑ አገሩን ሊያስከብር ነው በአንድነት ለመቆም የተመመው፤ ይህ ዛሬ የመጣ ፈሊጥ ሳይሆን ቀደም ሲልም ኢትዮጵያውያን አገራቸውን የማያስደፍሩ ስለመሆናቸው የሚያሳይ ነው፡፡ እየተካሄደ ያለው ጦርነት የአማራ ጦርነት አይደለም፤ የኢትዮጵያ ጦርነት ነው፡፡ ቢሆንም ደግሞ አማራ ብቻውን ቢሆንም እንኳ በዛ ቡድን የሚሸነፍ አይደለም፡፡
አዲስ ዘመን፡- በቀጣይ ኢትዮጵያ አሁን ከገባችበት ፈተና ለመውጣት ምን ማድረግ ይገባታል ይላሉ?
ፕሮፌሰር ላጲሶ፡- ኧረ ኢትዮጵያ ምንም ፈተና የለባትም፤ ዶክተር ዐብይ ሁሉን ነገር ያውቃል፤ እርሱ የሚሰራውን ጠንቅቆ የሚያውቅ መሪ ነው፡፡ የእኛ ጦር እኮ ከፈለገ ሱዳንን ወደ ኢትዮጵያ መቀላቀል የሚችል ነው፡፡ በሱዳን የተያዘውን ቦታ እንኳ ምንም ጋጋታ ሳይኖር በጥቂት ወታደር ማስመለስ ይቻላል፡፡
የትኛውም አካል ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን አፍሪካንም እንዳይነካ ማድረግ አገራችን ይቻላታል ነው የምለው፡፡ ጫና ፈጣሪ ነን የሚሉ አካላት ታሪክን በአግባቡ ባለማወቃቸው ነው እየሳቱ ያሉት። የኢትዮጵያ የአሸናፊነት ታሪክ ተረት አይደለም፤ ኢትዮጵያ ደግሞ ከጥንት ጀምሮ ያላት ታሪክ የድል ነሺ እንጂ የተሸናፊነት አይደለም፡፡ ይህን ያላወቁ ሊያውቁ ይገባል ባይ ነኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡– ፕሮፌሰር፣ ለሰጡን ማብራሪያ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ፕሮፌሰር ላጲሶ፡– እኔም አመሰግናለሁ፡፡
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11/2013