
ወጣት አለኸኝ ይመኑ እና ወጣት ግርማ ብሩ በሥጋ ከአንድ ማህጸን የተወለዱ ወንድማማቾች ናቸው። ውልደትና እድገታቸው ደግሞ በአዳማ አቅራቢያ በሚገኘው ልዩ ስሙ ቆቃ በተባለው አካባቢ ነው። ከልባዊ የእናትነት ፍቅር በላይ የሆነውን እናት ልጆቿን በምንም ምክንያት ለማንም አሳልፎ ያለመስጠት ተፈጥሯዊ ኃይል ያሸነፈውን የእናት አገር ጥሪ ተቀብለው ዛሬ ላይ በጦላይ መሰረታዊ የወትድርና ማሰልጠኛ ተቋም ተገኝተዋል።
ምንም እንኳን ከአንድ ቤት ሁለት ሰው ቤተሰብ ጥሎ መውጣቱ የሚከብድ ቢሆንም፤ በሠላም መኖር የሚቻለው አገር ስትኖር ነውና ሁለቱ ወንድማማቾች ወደ ዘመቻ ከመሄድ ወደ ኋላ አላሉም። ለዚህ ደግሞ አገር ጥሪ ባቀረበች ጊዜ ከሰንደቅዓላማዋ የሚበልጥ የለምና ኢትዮጵያን ከጠላት እንዲታደጉ እናታቸው መርቃ በደስታ ለውትድርና እንደላከቻቸው፤ እነርሱም ጁንታውን በሚገባው ቋንቋ ለማናገርና ድል ለማድረግ እንዲሁም ከወንድሙ ጋር ትልቅ ታሪክ ለመሥራት መዘጋጀታቸውን ሁለቱም ወንድማማቾች ይናገራሉ።
በዚህ መልኩ ወንድማማቾቹ ለእናት አገር ጥሪ መልስ ሲሰጡ፤ ቤተሰቦቻቸውም ሆኑ የአካባቢው ሰዎች ልጆቻቸው ለአገር መከታ ይሆኑ ዘንድ መርቀው በደስታ እንደሸኟቸው፤ ከሌሎች ወገኖቻቸው ጋር በመሆን ድልን እንዲቀዳጁ ፈጣሪን በጸሎት እንደሚለምኑላቸውም ቃል ገብተውላቸው በድል ተመለሱ ብለው እንደላኳቸውም ነው የሚገልጹት።
ከሁለቱ ወንድማማቾች ውሳኔ ባለፈ የእነ ግርማ እናት የአገር ፍቅር ስሜት ፍቅር ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ ለመረዳት ደግሞ ያላቸውን ሁለት ወጣቶች ሳይሰስቱ ለእናት አገርአሳልፈው መስጠታቸውን መመልከቱ በቂ ነው። የአገርን ጥሪ በደስታ የተቀበሉት ሁለቱ ወንድማማቾችም በአሁኑ ወቅት ከሌሎች ወጣቶች ጋር በጦላይ ማሰልጠኛ ማእከል ወታደራዊ ስልጠና በመውሰድ ላይ ይገኛሉ።
ብርጌድ ሁለት ሻለቃ አንድ ሻምበል አራት ውስጥ ሆኖ ወደ ሠራዊቱ ለመቀላቀል ወታደራዊ ሥልጠና እየወሰደ የሚገኘው የግርማ ታናሽ ወንድም አለኸኝ አንደሚናገረው፤ እስከዛሬ በቤታቸው ሆነው ሲሰሙ የነበረውና ጁንታው በወንድሞቻቸው ላይ ያደረሰውን ድርጊት በመኮነን ብሶታቸውን ለመወጣት ሲሉ ነው ወደ ሠራዊቱ ለመቀላቀል የወሰኑት። ወደ ሥልጠናው ሲቀላቀሉም በቆራጥነት መንፈስ ነው።
ለዘመቻው ጥሪ ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው ያማከረው ታናሽየው አለኸኝ ሲሆን፤ በወቅቱ ታላቅ ወንድሙም ጉዳዩን ሳያቅማማ በደስታ ተቀበለው። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የሚሰሙት ነገር አላስችል ስላላቸው እንደሆነ ይናገራል።
አለኸኝ እንደሚለው፤ ከመከላከያ ሠራዊቱ ጎን መሆን እንዳለባቸው ባመኑ ጊዜ ለአስር ዓመታት ያህል ሲሰራ የነበረውን የግል ሥራ ለመተው ተገደደ። ቅድሚያ ለአገሩ በመስጠት ሥራውንም ቤተሰቡንም እርግፍ አድርጎ በመተው ከታላቅ ወንድሙ ጋር ወደ ውትድርናው ዘመቻ አቀና።
ወጣት ግርማ በበኩሉ፤ ከዚህ በፊት ዘመቻ እንደነበረና ዳግም ከታናሽ ወንድሙ ጋር አገርን ለማገልገል በወታደር ቤት መገኘቱ እንዳስደሰተው ይናገራል። እርሱም እንደ ወንድሙ ሥራውን ትቶ ነው ሠራዊቱን ለመቀለቀል ስልጠና እየወሰደ ያለው። ዳግም ወደ ውትድርና እንዲመለስ ያደረገውም ከዚህ ቀደም ከአሸባሪው ይመነጩ የነበሩ ብልሹ አሰራሮች በአሁን ወቅት ስለተቀረፉና በተለይም «ከኔ ሌላ ለአሳር» የሚለውንና በማን አለብኝነት የሚፎክረውን ጁንታ ለመቅጣት በእልህ መነሳሳቱ እንደሆነ ይገልጻል።
በችግር ምክንያት ቤተሰብ ሊጎዳ ይችላል እንጂ አገሬ በፍጹም ልትነካ አይገባትም የሚለው ግርማ፤ አሁን ላይ ጥሎ የመጣው ቤተሰቡ ሳይሆን የሚያሳስበው የአገርና የሰንደቅዓላማ ጉዳይ እንደሆነ ይናገራል። ቤተሰብም ከአገር አይበልጥም ይላል። በመሆኑም አዝሎ ካሳደገው ታናሽ ወንድሙ ጋር በአንድ ላይ ወታደራዊ ሥልጠና እየወሰደ ለውትድርና ዝግጅት ማድረጉ «ክብር እንዲሰማን አድርጓል» ሲል ይገልጻል። ጁንታውን በሚገባው ቋንቋ ለማናገርና ድል ለማድረግ እንዲሁም ከወንድሙ ጋር ትልቅ ታሪክ ለመሥራትም ነው እየተዘጋጁ ያሉት። ይህ አንደሚሆንም ሙሉ እምነት አለኝ ብሏል።
ጭቃ እያቦኩና ብይ እየተጫወቱ አብረው ያደጉ ሁለቱ ወንድማማቾች እስከ መጨረሻው ከሠራዊቱ ጋር በመሆን የአገርን ሉዓላዊነት እንደሚያስጠብቁም ነው የገለጹት። የእነርሱን ብርታት ያዩ ሌሎች ወጣቶችም እንዲህ ዓይነቱን አገራዊ ጥሪ ተቀብለው አገርን የመጠበቅ ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል። ከሀሰተኛ ወሬ ራሳቸውን ጠብቀው ለአገር ሰንደቅ ኩራት እንዲሆኑ፤ እንዲሁም ሌሎች ወደ ዘመቻ ያልሄዱ ወጣቶችም አካባቢያቸውን በንቃት እንዲከታተሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም