በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን ወደ 1969 ዓ.ም ክረምት ወቅት ይወስደናል። ወቅቱ ኢትዮጵያ በሶማሊያ ሰርጎገቦች የተወረረችበት ሲሆን፣ መንግስትም ይህን ወረራ ለመቀልበስ ክተት አውጆ ነበር። ኢትዮጵያውያንም ይህን ጥሪ ተቀብለው በተለያየ መልኩ ያደርጉ የነበረውን ተሳትፎ፣ የውጭ ሀይሎች ከሶማሊያ ጋር በማበር ያደርጉ የነበረውን ድጋፍ አስመልክቶ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የወጡ ዘገባዎችን ይዘን ቀርበናል። ዘገባዎቹ በአሁኑ ወቅት አሸባሪው ሕወሓት እና የውጭ ሀይሎች በሀገራችን ላይ የጋረጡትን አደጋ ለመቀልበስ ኢትዮጵያውያን እያከናወኑ ካሉት ተግባር ጋር በእጅጉ የሚመሳሰሉ ጉዳዮች የቀረቡባቸው ናቸው። መልካም ንባብ።
ግብፅ ለሶማሊያ ዋና የጦር አቀባይ ሆናለችዋሽንግተን (ከዜና ወኪሎች)፡- በርከት ያሉ የዓረብ አገሮች በተለይም ግብፅ ለሶማሊያ የጦር መሣሪያዎችን በማቀበል ረገድ ዋነኛይቱ እንደሆነች ውስጥ አዋቂ ምንጮች መግለጣቸው ከዋሽንግተን የደረሰው ዜና ያስረዳል።
ሶማሊያ ከእነዚህ አገሮች የጦር መሣሪያ ለማግኘት በመቻሏ ከሌሎች የውጪ ኃያላን መንግሥታት መሣሪያ ማግኘት አይጠቅማትም ባይባልም ለጊዜው ከኃያላን መንግሥታት መሣሪያ የማግኘቱን አጣዳፊነት የቀነሰላት መሆኑን የዜና ምንጮች ጨምረው ገልጠዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ የሐያ አንድ የአረብ ሊግ አባል ሀገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በዛሬው ዕለት ካይሮ ከተማ ስብሰባ እንደሚያደርጉና በዚህም ስብሰባቸው በመካከለኛው ምሥራቅና በቀይ ባሕር አካባቢ የተቀነባበረ የዓረቦች እስትራቴጂ ለማውጣት እንደሚነጋገሩ በካይሮ የተላለፈው ዜና ገልጧል።
̎በቀይ ባህር አካባቢ ፀጥታን ለማስከበር̎ በሚል ሰበብ የዓረብ አገሮች ስለሚያደርጉት ጥረት ስብሰባው ከሚነጋገርባቸው ዋና ነጥቦች አንዱ እንደሚሆን የውስጥ አዋቂ ምንጮች መግለጣቸውን ዜናው ጨምሮ ገልጧል።
ቀደም ሲል በዚህ ዓመት በቀይ ባሕር ጠረፍ አካባቢ የሚገኙ የዓረብ አገሮች መሪዎች በእነሱ አባባል ̎ ስለ ቀይ ባህር ሰላም ̎ ለመነጋገር በሱዳንና በሰሜንና የመን ስብሰባ አድርገው እንደነበር ይታወሳል።
የዓረብ ሀገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በማኅበሩ ምክር ቤት ትእዛዝ የሚንቀሳቀስ ስድስት ሺህ ወታደሮች የሚገኙበት ጦር እንዲቋቋም እንደሚስማሙ የዓረብ ሊግ ዋና ጸሐፊ ተስፋ ማድረጉን ለሪፖርተሮች መግለጡ ታውቋል።
ሌሎች የስብሰባው መወያያ አርስቶች ለአረብ ሊግ አባልነት በጅቡቲና በኮሞሮስ ደሴቶች የቀረቡት ማመልከቻዎች እንደሚሆኑና ስብሰባው ከሁለት እስከ ሦስት ቀን እንደሚቆይ ዜናው ጨምሮ ገልጧል።
ነሀሴ 28 ቀን 1969 ዓ.ም
ትንሹ ጐሻ ህዝባዊ ሠራዊት አባሎች ተመርቀው ታጠቁ
ጅማ (ኢ-ዜ-አ-) በከፋ አውራጃ በትንሹ ጐሻ ወረዳ በማኅበር ከተደራጁት አርሶአደሮች ተመልምለው ለ፫ወራት የተሰጠውን የውትድርና ትምህርት የተከታተሉ ፹፯ የሕዝባዊ ሠራዊት አባሎች ባለፈው ሐሙስ እጅግ ደማቅ በሆነ ሥነ ሥርዓት ተመርቀው የምስክር ወረቀት ተቀብለዋል።
ከነዚህ የአርሶ አደሩ ሕዝባዊ ሠራዊት መካከል ፮ቱ ሴቶች ናቸው። በዚህ የምረቃ በዓል ላይ የወረዳው አስተዳዳሪና የወረዳው የህዝብ ድርጅት ኃላፊ በየተራ ስለ ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ተጨባጭ ሁኔታ፤ ስለ አብዮቱ ሂደት፤ ስለ አዲሱ ብሔራዊ ዴሞክራሲያዊ አብዮት መለስተኛ ፕሮግራምና አባላቱ በተማሩት የውትድርና ተጠቅመው አንዳንድ ሰርጎ ገብ አድኃሪያንን መደምሰስ ስለሚችሉበት መንገድ በመተንተን ማብራሪያና ገለጣ አድርገውላቸዋል።
የሕዝባዊ ሠራዊት አባላትም የተማሩትን የውትድርና ትምህርት በትርእይት መልክ ለሕዝብ አሳይተው ከፍተኛአድናቆትን አትርፈዋል።
በመጨረሻም የጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ሀቀኛ አብዮታውያንን ለማስታጠቅ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ለነዚህ ህዝባዊ ሠራዊት አባላት የጦር መሣሪያ አስታጥቋል።
ይህንኑ ትጥቅ በስፍራው ተገኝተው ለአርሶ አደሩ ሠራዊት ያስታጠቁት የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ ደመቀ ወልደ ማርያም መሆናቸውን ከወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት የደረሰን ዜና አረጋግጧል።
ሰኔ 6 ቀን 1969 ዓ.ም
በወበራ
38 ሠርጎ ገቦች ተደመሰሱ
በርከት ያሉ ቆስለው ተማረኩ
ሐረር፤ (ኢ/ዜ/አ-) በሐረርጌ ክፍለ ሀገር በወበራ አውራጃ በተለያዩ ሥፍራዎች ውስጥ ተሽለኩሉከው ከገቡት ሠርጎ ገብ ወንበዴዎች መካከል ሰሞኑን ፴፰ ሲደመሰሱ፤ ሌሎች በርከት ያሉ ወንበዴዎች ደግሞ ቆስለው መማረካቸው ተገለጠ።
ከእነዚህ መካከል ስምንቱ ወንበዴዎች የተገደሉት በደደር ወረዳ በሰቃ ም/ወረዳ ልዩ ስሙ ራሚስ በተባለው ሸለቆ ውስጥ ሲሆን፤ የቀሩት ፴ ዎቹ ደግሞ የተደመሰሱት በመልካበሎ ወረዳ ልዩ ስሙ ሸዋ በር በተባለው ሥፍራ መሆኑን ታውቋል።
በእነዚህ ሥፍራዎች ውስጥ በተለያዩ ቀናት ለ፫ኛ ጊዜ አሰሳ አድርጎ ይህን ከፍተኛ ውጤት ያገኘው ከመለዮ ለባሹ ጋር የተባበረው የአውራጃው ሕዝባዊ ሠራዊት መሆኑ ተገልጧል።
ሰኔ 3 ቀን 1969 ዓ.ም
የንግድ ባንክ ሠራተኞች ለእናት ሀገር ጥሪ 525 ሺህ ብር ሰጡ
(ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት)
የእናት ሀገሩን ዳር ድንበርና አብዮቱን ለማስከበር በግንባር ቀደምትነት ለሚዘምተው ሕዝባዊ ሠራዊት ስንቅ መሰናዶ የሚሆን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሠራተኞች ከዚህ
ቀደም ካዋጡት ሌላ በትናንትናው ዕለት የአንድ ወር ደመወዛቸውን አምስት መቶ ሃያ አምስት ሺህ ብር በቼክ ለሻለቃ ደበላ ዲንሳ የአዲስ አበባ አጠቃላይ የአብዮትና ልማት ኮሚቴ ሊቀመንበር አስረክበዋል።
የንግድ ባንክ ሠራተኞች የእናት ሀገር ጥሪን በመደገፍ ከዚህ ቀደም ፪፻፲፪ ሺህ ፭፻ ብር የረዱ ሲሆን፤ ወደፊትም የሚያገኙትን የልዩ ልዩ አበል ገቢ ሰማንያ ስድስት ሺህ ብር ያህል ለዘማቹ ሠራዊት የስንቅ መሰናዶ ለመስጠት መወሰናቸውን የሠራተኞች ማኅበር ጊዜያዊ የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ ሊቀመንበር አስታውቀዋል።
ከዚህ በቀር ዘመቻው በድል እስከሚፈጸም ድረስ ለዘማች ሠራዊቱ የሚደረገው እርዳታ መቀጠል ያለበት መሆኑን በመገንዘብ፤ የባንኩ ሠራተኞች አምስት አባላት የሚገኙበት አንድ የሰብሳቢ ኮሚቴ ያቋቋሙ መሆናቸውን ሊቀመንበሩ ጨምረው ገልጠዋል።
ቀደም ሲል ሻለቃ ደበላ ዲንሳ ለሠራተኞቹ ባደረጉት ሰፊ ማብራሪያ አድኃሪያንንና ኢምፔሪያሊስቶች በመተባበር በኢትዮጵያ ሕዝብና አብዮት ላይ የሚያካሂዱት ሴራ በጭቁኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተባበረ ክንድ የሚከሽፍ መሆኑን አመልክተው፤ አብዮታዊው መለዮ ለባሽና ሕዝባዊ ሠራዊት ጠላቱን ሳይደመስስ ወደ ኋላ እንደማይል አረጋግጠዋል።
ይህ አብዮታዊ ሠራዊት የሚቀዳጀው የማያዳግም ድል ዛሬ የኋላ ደጀን በመሆን ከፍተኛ የስንቅና የሞራል ድጋፍ የሚሰጡት ተራማጅና አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ የሚያኰራ እንደሚሆን ሻለቃ ደበላ ዲንሳ ጨምረው አስረድተዋል።
በመጨረሻም የንግድ ባንክ ሠራተኞች ለእናት አገር ጥሪ ስላደረጉት ከፍተኛ መዋጮ ከልብ አመስግነው፤ ይህም የባንኩ ሠራተኞች ለአብዮታዊት እናት አገራቸው መስዋዕት ለመሆን መዘጋጀታቸውን የሚያረጋግጥ ነው ብለዋል።
ሀምሌ 9 ቀን 1969 ዓ.ም
ሀይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 10/2013