በምዕራቡ ዓለም ከሚደገፈው የአፍጋኒስታን መንግሥት ጋር በተደረገው ያልተሳካ ውይይት እና የአሜሪካ ወታደሮች ከሀገሪቱ መውጣታቸውን ተከትሎ ታሊባኖች በዚህ ዓመት ግንቦት ወር ላይ ጥቃታቸውን ከጀመሩ ወዲህ በፍጥነት ወደፊት እየገሰገሱ ናቸው።
የመንግሥት ኃይሎች ተቃውሞ እየከሸፈ እና በመዲናይቱ ካቡል ላይ ጥቃት ሊደረግ ቀናት ሊቀር ይችላል የሚል ስጋት እየጨመረ በመምጣቱ የታሊባን ታጣቂዎች አፍጋኒስታንን ሁለተኛ እና ሦስተኛ ትልልቅ ከተሞች በቁጥጥር ስር አውለዋል።
የታሊባን ታጣቂ ቡድን በአሁኑ ጊዜ 34 ከሚሆኑ የአፍጋኒስታን ግዛቶች መካከል የ14 የአፍጋኒስታን ጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማዎችን መቆጣጠራቸውን ዓለም አቀፍ ዘገባዎች አመልክተዋል።
ከእነዚህም መካከል ባለፈው ዕሁድ በታሊባን እጅ የወደቀችውና ለ270 ሺህ ሰዎች መኖሪያ የሆነችው ኩንዱዝ ከተማ አንዷ ስትሆን ከተማዋ በአገሪቱ በማዕድን የበለፀገ የሰሜናዊ ግዛቶች መግቢያ በር ተደርጋ ትወሰዳለች።
የታሊባን አማጺዎች ባለፈው ሳምንት ዓርብ ዕለት የአገሪቱን ሁለተኛውን ከተማ ካንዳሃርን ተቆጣጠረ። ካንዳርሃን በአንድ ወቅት የታሊባን ምሽግ የነበረ ሲሆን፤ እንደ በንግድ ማዕከልነት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያለው ነው።
የአካባቢው ባለስልጣናት ዋቀቢ አድርጎ ቢቢሲ እንደዘገበው የታሊባን አማጺዎች የሎጋር ግዛት ዋና ከተማ ፑል-አላምን ተቆጣጠሩ። ሎጋር ከካቡል አውራጃ ጋር የሚዋሰን ሲሆን፤ ከ ፑል-አላም ወደ አፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል ቀጥተኛ አገናኝ መንገድ አለው።
የተባበሩት መንግሥታት ጠቅሶ ቢቢሲ እንደዘገበው ባለፉት – እ.ኤ.አ ከ2001 ዓ.ም ጀምሮ ባለፉት 20 ዓመታት የአፍጋኒስታን ጦርነት በስታቲክሳዊ መረጃ እንደሚከተለው ተቀምጧል።
የተገደሉ የአሜሪካ የሰው ኃይል ብዛት- ሁለት ሺህ 312፤ የቆሰሉ የአሜሪካ የሰው ኃይል ብዛት 20 ሺህ 660፤ የአሜሪካ ይፋ ግምታዊ ኦፕራሽኑ የፈጀው 77 ቢሊየን የአሜሪካን ዶላር፤ የተገደሉ የእንግሊዛውያን የሰው ኃይል ብዛት- 456 ናቸው።
እንዲሁም የተገደሉ የአፍጋኒስታን ወታደራዊ ፖሊሶች ግምታዊ አኀዝ 64 ሺህ 100 ሲሆን፤ በጠቅላላ የተገደሉ ወይም የቆሰሉ ንጹሐን ዜጎች ቁጥር 111 ሺህ ያህል ናቸው።
ቴሌግራፍ ኢንዲያ እንደዘገበው የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ባለሥልጣን- እ.ኤ.አ. በመስከረም 11 2001 በዩናይትድ ስቴትስ ላይ ጥቃት ከደረሰ በኋላ ታሊባን ከስልጣን የተባረረ – ሲሆን፤ በቀናት ውስጥ በካቡል ላይ እርምጃ ሊወስድ ይችላል በማለት ስጋቱን ገልጿል።
የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ሐሙስ ዕለት የአሜሪካ ኤምባሲ ሠራተኞችን ለማስወጣት 3000 ተጨማሪ ወታደሮችን ለመላክ ማቀዱን አስታውቋል።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ
ጉተሬዝ “አፍጋኒስታን ከቁጥጥር ውጪ እየሆነች ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። በመሆኑም ሁሉም ወገኖች ንጹሐን ዜጎችን ከጥቃት ለመጠበቅ የተቻላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
ጉቴሬዝ በኒው ዮርክ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ “ጥቃቱን ለማስቆም የሚያስችል ጠንካራ ድርድር የሚጀመርበት ጊዜው አሁን ነው፤ ለረጅም ጊዜ የቆየውን የእርስ በእርስ ጦርነት ወይም የአፍጋኒስታን መገለል የሚወገድበት ጊዜ ነው” ብለዋል።
የአፍጋኒስታን ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት አምሩላህ ሳሌህ በፕሬዚዳንት አሽራፍ ጋኒ በተመራው የፀጥታ ስብሰባ በኋላ በጦር ኃይሎች እንደሚኮሩ እና መንግሥት ታሊባንን ለመመከት የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል ብለዋል።
የአሜሪካው ፕሬዚዳን ጆህ ባይደን በዚህ ሳምንት
ጦሩን ከአፍጋኒስታን መውጣቱን አስመልክቶ በውሳኔው አልተቆጨሁም ብሏል። ዋሽንግተን በ20 ዓመታት ጦርነት መካከል ከአንድ ትሪሊዮን ዶላር በላይ ማውጣቷን እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቿን እንዳጣች ጠቅሰው የአፍጋኒስታን ጦር እና መሪዎች እንዲጠናከሩ ጥሪ አቅርበዋል።
በአስተያየት መስጫ በተሰባሰቡ መልዕክቶች ላይ አብዛኛዎቹ አሜሪካውያን የባይደንን ውሳኔ ደግመዋል። ነገር ግን ሪፐብሊካኖች የዴሞክራቲክ ፕሬዚዳንቱን ተችተዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ሴኔት ሪፐብሊካን መሪ ሚች ማክኮኔል የአፍጋኒስታን ሁኔታ “ውድቀት” ቢሉትም ለአፍጋኒስታን ኃይሎች የአየር እና ሌሎች ድጋፎችን በመስጠት የታሊባን ወደ አፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡል መሻገር ለማስቆም ጊዜው አልረፈደም ብለዋል።
በሐይሉ አበራ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 10/2013