በጋዜጣው ሪፓርተር
በእዚህ ዘመን በኢንተርኔት መርብ ወይም በኮምፒውተር የሚካሄዱ ጨዋታዎች /ጌሞች/ ዘና ማድረግ ይችላሉ። በእነዚህ ጨዋታዎች ሲዝናኑ የሚታዩት በአብዛኛው ወጣቶች ናቸው። ጨዋታዎቹ የማዝናናታቸውን አዕምሮ ሰፋ አርጎ እንዲያስብ የማድረጋቸውን ያህል፣ ወጣቶችን እጅግ ሱሰኛ በማድረግም ይታወቃሉ። በዚህ የተነሳ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነው ጭምር ሲጫወቱ የሚገኙበት ሁኔታ ይታያል። በፊሊፒንስ አንድ መንደር በቅርቡ ከሆነው የምንረዳውም ይህንኑ ነው።
በቅርቡ በፊሊፒንስ ቻይነታ ከተማ ኃይለኛ ዝናብ ይጥላል። ዝናቡ ያስከተለው ጎርፍም ከተማዋን ከማጥለቅለቅ አልፎ በየመኖሪያና ንግድ ቤቶቹ ገብቶ ተንጣሎ ይተኛል። በርካታ ወጣቶች በተመስጦ ጌም እየተጫወቱ ካለበት አንድ ኢንተርኔት ካፌ የጌም ማጫወቻ ቤትም ይገባል።
ወጣቶቹ ግን በጨዋታው ክፉኛ በመመሰጣቸው ሳቢያ ጎርፍ መግባቱ አላሳሰባቸውም፤ ከጎርፉ ራሳቸውን ለመጠበቅ ከመሞከር ይልቅ ጨዋታውን ይቀጥላሉ። አንዳንዶቹ እግሮቻቸውና መቀመጫቸው ጭምር በጎርፍ ውስጥ ገብቷል፤ አንዳንዶቹ ደግሞ እግሮቻቸውን የሆነ ነገር ላይ ሰቅለው መጫወታቸውን ቀጥለዋል። ይህ ሁኔታም የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንን ትኩረት በእጅጉ መሳቡን የኦዲቲ ሴንትራል ድረገጽ አስነብቧል።
ወጣቶቹ በጎርፍ በተሞላ ክፍል ውስጥ ሆነው ሲጫወቱ በሚያሳየው ቪዲዮ ላይ እንደተመለከተውም የአንዳንዶቹ እግራቸው ብቻ ሳይሆን መቀመጫቸው ጭምር ውሃ ውስጥ ሆኖ ይታያል። አንዳንዶቹ ደግሞ የወንበሮቻቸው መቀመጫ በጎርፉ ሲሞላባቸው ወንበሮቹን እያራቁ ቆመው ጨዋታቸውን ቀጥለው ይታያሉ።
ግማሽ አካላቸው ደለል ጨምር ባለው የጎርፍ ውሃ ውስጥ ሆኖም ንቅንቅ ያላሉ ወጣቶች ነበሩ። ኮምፒውተር ስክሬናቸው ላይ አፍጥጠዋል፤ ሌላው ቀርቶ ጎርፉ የኤሌክትሪክ አደጋ ሊያስከትል ይችላል ብለውም አልሰጉም። የድርጅቱ ባለቤት መጥቶ ሁኔታው አሳሳቢ መሆኑን ተመልክቶ እነሱን አስወጥቶ ካፌውን እስከሚዘጋ ድረስ ንቅንቅ ለማለት አልፈለጉም። ካፌው ሲዘጋ ነው ጥለው የወጡት ይለናል ድረገጹ።
‹‹ ያን ዕለት የጎርፉ መጠን ይጨምራል ብለን አልገመትንም፤ ወጣቶቹ ጎርፉ ውስጥ ሆነው ሲጫወቱ እንደተመለከትኩ በአስቸኳይ ዕርምጃ ወሰድኩ፤ ቁሳቁሱን ወደ ከፍታ ቦታ ማዘዋወር ስላለብኝ ውጡልኝ አልኳቸው›› ያለው የድርጅቱ ባለቤት፣ ሁሉም ወጣቶች ይህን ሲሰሙ ጨዋታውን አቁመው ወጡ። የደረሰባቸው ምንም ዓይነት ጉዳት ግን የለም ሲል ባለቤቱ ሲይኦ ሳምሶን ተናግሯል።
ወጣቶቹ ጨዋታው ተቋረጦባቸው እንጂ ከካፌው ንቅንቅ የሚሉ ዓይነት አልነበሩም፤ ደግነቱ የካፌው የኤሌክትሪክ መስመሮች በሙሉ የጎርፍ ውሃው መጠን ከደረሰበት ከፍታ በላይ ነው የሚገኙት፤ አካባቢው ለጎርፍ ተጋላጭ መሆኑ ታስቦበት ሶኬቶች በሙሉ ከፍ ባለ ስፍራ ላይ ነው የተገጠሙት፤ ይህ ባይሆን ኑሮ የቪዲዮ ጌሙ ከባድ ትራጀዲ የሚያስከትል ነበር ሲል ባለቤቱ ተናግሯል።.
ሁኔታውን የተከታተሉ አንዳንድ አካላት ትክክለኛ ተጫዋቾች ምንም ዓይነት ችግር ቢያጋጥም ጨዋታ አያቋርጡም ይባላል፤ እነዚህ ወጣቶችም የእዚህ ምሳሌ ናቸው ብለው በአድናቆት እንደተመለከቷቸው ድረገጹ አያይዞ አስነብቧል። የቪዲዮ ጨዋታዎች ህይወትን ለአደጋ የሚያጋልጡ ዓይነት መሆን የለባቸውም ሲሉም የተቹ አካላት አሉ። በአንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ የኤሌክትሪክ አደጋ ሊከሰት የሚችልበት ዕድል ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል በመጥቀስም ሁኔታውን ክፉኛ ተችተውታል::
አዲስ ዘመን ነሃሴ 10/2013