ሀገራት ሁለት ዓይነት የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ሊከተሉ ይችላሉ። አንደኛው በገበያ ፍላጎት የሚመራ ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ስርዓት (ፍሎቲንግ ካረንሲ ኤክስቼንጅ ሬት) ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ቋሚ የውጭ ምንዛሪ ተመን ይባላል። ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሪ ተመን ማለት የውጭ ምንዛሪ መጠን በገበያ የሚወሰንበት (ፊክስድ ካረንሲ ኤክስቼንጅ ሬት) ሲሆን ይህም ማለት የምንዛሪ ተመኑ በፍላጎት እና አቅርቦት የሚወሰንበት ማለት ነው። ቋሚ የምንዛሪ ተመን ደግሞ የአንድ ሀገር ማዕከላዊ ባንክ የምንዛሪ ተመን የሚወሰንበት ነው። አብዛኞቹ ነጻ ገበያ መርህ የሚከተሉ ሀገራት ተለዋዋጭ የውጭ ምንዛሪ ተመንን ተግባራዊ የሚያደርጉ ሲሆን ነጻ ገበያን የማይከተሉ ሀገራት ደግሞ ቋሚ የምንዛሪ ግብይት ስርዓትን ተግባራዊ ያደርጋሉ።
ኢትዮጵያ ከደርግ ውድቀት ማግስት ጀምሮ ነጻ ገበያን እንደምትከተል ይፋ ያደረገች ቢሆንም የውጭ ምንዛሪ ተመን ግን በገበያ ሲወሰን አልነበረም። የምንዛሪ የግብይት ተመን በአቅርቦትና ፍላጎት እንዲወሰን አልተወችም። ይልቁኑ በብሄራዊ ባንክ ነው ሲወሰን የነበረው። ብሄራዊ ባንኩ የውጭ ሀገራት ገንዘቦች በምን ያህል ዋጋ መሸጥ እንዳለበት ገደብ ሲያስቀምጥ ቆይቷል። በዚህም ምክንያት ከዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ከፍተኛ ጫና እና ትችት ስታስተናግድ ቆይታለች። ከዚያ አለፍ ብሎም የብር የመግዛት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ ስታወርድ ቆይታለች። በዚህም ምክንያት የብር የመግዛት አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወረደ ዛሬ ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል።
ብሔራዊ ባንክ የብር የውጭ ምንዛሪ ፍላጎትን መሰረት በማድረግ የብር ዋጋ በገበያ ተመን እንዲወሰን ማድረግ ተገቢ ነው ከሚል ድምዳሜ በመድረሱ፤ ኢትዮጵያ በቀጣይ ጥቂት ዓመታት ውስጥ ብርን ወደ ፍሎቲንግ ካረንሲ ስርዓት (የገንዘብን ተመን በገበያ ዋጋ ላይ መመስረት) እንደምትሸጋገር ይፋ አድርጋለች። በዚህም ምክንያት የተለያዩ አካላት የተለያዩ አስተያየቶችን ሲሰነዝሩ ቆይተዋል። የዘርፉ ምሁራን የኢኮኖሚ መደላድል ባልተፈጠረበት ሁኔታ ሀገሪቱ ተለዋዋጭ ወይም ፍሎቲንግ ካረንሲ ኤክስቼንጅ ሬት ለመጠቀም መወሰኗ ከጥቅሙ ጉዳት እንደሚበዛ በመግለጽ ላይ ይገኛሉ። በተለይም በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ውስጥ ከእለት ወደ እለት እየተባባሰ የመጠው የዋጋ ንረት ጣሪያ ሊነካ ይችላል የሚል ስጋታቸውን ይገልጻሉ።
በዲላ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶክተር ጣሰው ታደሰ እንደሚሉት፤ አሁን እየታየ ያለው የብር የመግዛት አቅም ከዕለት ወደ ዕለት እያሽቆለቆለ ነው። ሀገሪቱ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የዋጋ ንረት የሚስተዋልባት ሀገር ናት። ኢትዮጵያ በርካታ ነገሮችን ከውጭ ሀገራት ነው የምታስገባው። ከጥቃቅን ነገሮች አንስቶ እስከ ትላልቅ ማሽነሪዎች ከውጭ ሀገራት ነው የምታስገባው። የገቢ ንግድ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የተደገፈ ኢኮኖሚ ላይ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመን ሙሉ በሙሉ በገበያ እንዲወሰን ማድረግ በአጭር ጊዜ መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ የዋጋ ንረት የበለጠ ሊያባብስ ይችላል።
ሀገሪቱ ለዶላር ያላት ፍላጎት በጣም ከፍተኛ ሲሆን፤ ከወጪ ንግድ የሚገኘው ዶላር ደግሞ በጣም ውስን ነው የሚሉት ዶክተር ጣሰው፤ ስለዚህ ከፍተኛ የዶላር እጥረት ባለበት ኢኮኖሚ ውስጥ የውጭ ምንዛሪ ተመን ሙሉ በሙሉ በገበያ እንዲወሰን የሚለቀቅ ከሆነ የዋጋ ንረቱ እየጨመረ ሄዶ የብር የመግዛት አቅም የበለጠ እየተዳከመ እንዲሄድ የሚያደርግ ነው።
እንደ ዶክተር ጣሰው ማብራሪያ፤ የውጭ ምንዛሪ ተመን በአቅርቦት እና ፍላጎት እንዲወሰን ከተተወ በተለይም ኢምፖርትድ ኢንፍሌሽን እንዲባባስ ምክንያት ይሆናል። ኢምፖርትድ ኢንፍሌሽን መባባስ ደግሞ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች ዋጋም እንዲንር ያደርጋል። ከምንም በላይ ችግሩን አሳሳቢ የሚያደርገው ደግሞ የብር የመግዛት አቅም እየወረደ በሄደ ቁጥር በሀገር ውስጥ አነስተኛ ገቢ ያለው ሸማች ላይ ያለው ጫና እየበረታ ይሄዳል።
ከለውጡ በፊት የነበረው መንግሥት ብዙ ጫናዎች በመቋቋም የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመን በብሄራዊ ባንክ እንዲወሰን መወሰኑ የዋጋ ንረትን በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ጋብ እንዲል እገዛ አድርጓል የሚሉት ዶክተር ጣሰው፤ አሁንም ቢሆን ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት የሚመጡ ጫናዎችን በመቋቋም ብሄራዊ ባንክ ቁጥጥሩን መቀጠል አለበት። የምንዛሪ ግብይት ተመን በብሄራዊ ባንክ በሚወሰነው የግብይት ተመን ማስቀጠል ከፍ ያለ ፋይዳ እንዳለው ያነሳሉ።
“ፍሌክስብል ኤክስቼንጅ ሬት” ፖሊሲ ውጤታማ ሊሆን የሚችለው የወጪ ንግድ ዘርፉ ጠንካራ ሲሆን ነው የሚሉት ዶክተር ጣሰው፤ በአሁኑ ወቅት ግን የሀገሪቱ የወጪ ንግድ እጅግ ደካማ ነው ይላሉ። ወደ ውጭ ሀገራት የሚላኩ ምርቶችም የግብርና ምርቶች መሆናቸውን ያነሳሉ። ሀገሪቱ ምርቶችን በብዛት አምርታ እና እሴት ጨምራ ወደ ውጭ ሀገራት መላክ እስክትጀምር ሀገሪቱ ቋሚ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ስርዓት መከተሏን መቀጠል አለባት ብለዋል። ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ስለሚችል መንግሥት ውሳኔውን ቢያጤነው መልካም ነው።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 7/2013