ፖለቲከኛው አቶ ሙሼ ሰሙ ሰሞኑን በፌስቡክ ገጻቸው ስለአምስተኛ ረድፈኞች አንድ ጽሁፍ አስፍረው ነበር። አቶ ሙሼ እንዲህ አሉ “ጀነራል ኢሚሊዮ ሞላ ቪዳል በስፓኒሽ የርስ በርስ ጦርነት ወቅት አራቱን የአርሚው ረድፈኞች እየመራ ወደ ማድሪድ ሲተም፣ በከተማዋ ውስጥ ተሰግስገውና በስውር ተደራጅተው አሉባልታ በመንዛት፣ ስነ ልቦናዊ ቀውስ በመፍጠር፣ ኢኮኖሚያዊ አሻጥር በማስፋፋት፣ መረጃ በማቀበልና ግጭት በመቀስቀስ ደጀኑን ያዳክሙለት የነበሩትን ሃይሎች “አምስተኛ ረድፈኞች” ያላቸው መሆኑን ይጠቅሳሉ።
ዛሬ ይህ እጣ ፈንታ ሀገራችንን ገጥሟታል። ከጦር ግንባር እልፍ ኪሎ ሜትር ርቀው በማህበረሰባችን እቅፍ ውስጥ በሰላም እየኖሩ ሰላም እንዲሰፍን ከመትጋት ይልቅ ሕዝብን በአሉባልታ በማሸበር፣ ኢኮኖሚያችንን በአሻጥር በማመሰቃቀል፣ ጥላቻና ልዩነትን በመዝራት የደጀንነት ሚናችንን በአግባቡ እንዳንወጣና ሀገራችን እንድትበተን የውስጥ ዓርበኞች አዳዲስ ግንባር እየከፈቱብን ነው።
እውነታቸውን ነው ፤ ሀገራችን ዛሬ በአምስተኛ ረድፈኞች ጥቃት እየደረሰባት ነው። መሀል ከተማ ላይ ተቀምጠው ወሬ ሲፈበርኩ እና ሲያሰራጩ የሚውሉ ብዙ ናቸው። አንዱ ይነሳና መከላከያው እየሸሸ ነው ሲል፣ ሌላኛው መከላከያው ሀዝቡን ክዶታል ይላል ፤ ሌላው ደግሞ አሸባሪው ህወሓት እንዲህ አይነት መሳሪያ ይዟል ለካ ሲል ይገልጻል፤ ልዩ ሀይሉ እየሸሸ የሚልም አለ፤ ሌላው ደግሞ ጁንታው ወደ እገሌ ከተማ እየገሰገሰ ነው ይልሀል ፣ወዘተ.። እንዲህ እንዲህ እያለ በየማህበራዊ ሚዲያው ወሬ ሲያቀባብል የሚኖረው ብዙ ነው።
የሚገርመው ደግሞ አብዛኛው በማያውቀው ጉዳይ ነው ወሬ ሲያቀባብል መኖሩ ነው። ነገር ግን ጥቂቶች አሉ የሚሰሩትን አውቀው የሚሰሩ። እነዚህ ናቸው አምስተኛ ረድፈኞች።
የእነዚህ ሰዎች አላማ አንድ ነው ፤ እሱም ወገንን ከውስጥ ማወክ እና የተቀናጀ መልስ እንዳይሰጥ ማድረግ ነው። እነዚህ የወሬ አቀባባዮች ጠላት በሚሉት ወገን መሀል ሆነው ሁከት በመፍጠር ወገን ለሚሉት አካል የውስጥ አርበኛ ሆኖ ያገለግላሉ። ስለዚህም ጠላት የሚሉትን ወገን ወሬ እየፈጠሩ ማወክ እና እንዲተራመስ ማድረግ ቋሚ ስራቸው ነው። በዚህም ጦር ከፈታው ወሬ የፈታው የሚባለውን ብሂል በተግባር እንዲውል ያደርጉታል።
የምንኖርበት ዘመን ጦርነት በጠመንጃ ብቻ የሚካሄድበት አይደለም። ከጠመንጃ ጦርነቱ ባለፈ ፕሮፓጋንዳ እና የመረጃ ቅብብል ለአሸናፊነት ከፍተኛ ድርሻ አላቸው። የመረጃ ፍሰቱን መቆጣጠር ያልቻለ ሀይል ተሸናፊ መሆኑ የማይቀር ነው።
ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ይህን ስልት ተጠቅማ ጠላትን ድባቅ መምታት ችላለች። ይህም የሆነው በአድዋ ጦርነት ወቅት ነው። በወቅቱ ባሻ አውአሎም የተባሉ ጀግና ኢትዮጵያዊ ለፋሽስት የጦር መሪዎች የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ወራሪው ሀይል ሰተት ብሎ የወገን ወጥመድ ውስጥ እንዲገባ አድርገዋል።
ነገሩን ለማስታወስ ያህል በአድዋ ጦርነት ወቅት የሐገር ባለውለታና ጀግና ሰላይ የነበሩት ባሻ አውአሎም ለእነ ጀነራል አልቤርቶኒ ከሰጧቸው የሐሰት መረጃዎች መካከል፤ ‘ኢትዮጵያኖች በእለተ እሁድ ቤተክርስቲያን የመሳለም ልማድ ስላላቸው፤ የካቲት 23 ሰንበትም ብዙው ወታደር አክሱም ፅዮን ለመሳለም ስለሚያቀና የቀረውም ምግብ ፍለጋ በመበተኑ ንጉሠ ነገሥቱ ብቻቸውን ይሆናሉ፤ በጠዋት ማጥቃቱ ቢጀመር ድሉ ያለምንም ጥርጣሬ የጣሊያን ይሆናል” ብሎ አሳመኑ።
በዚህም የጠላት ጦር ንጉሠ ነገሥቱን ብቻቸውን ሊወጋ ቋምጦ ሲገሰግስ ከዓድዋ ሠፈር ተቃረበና ጠዋት በአሥራ አንድ ሰዓት ርችት አሰማ። የምኒልክም ሠራዊት አድፍጦ ሲጠባበቅ አድሯልና አፀፋውን መለሰ። በዚህ ጊዜ አፄ ምኒልክ የዓድዋን ጦርነት ከፈቱ። ጦርነቱ ሲፋፋም አውአሎምና ጓደኛው ወደ ወገናቸው ጦር ሲቀላቀሉ ያየና ነገሩ የገባው ጄነራል “አውዓሎም አውዓሎም” እያለ ሲጣራ አውዓሎም ሰምተው “ዘወአልካዩ እያውዕለኒ” ብለው አፌዙበት። (በዋልክበት አያውለኝ እንደማለት ነው) ዉጊያውም በሰዓታት ተጠናቆ ቀኑን ሙሉ ምርኮና አስክሬን ሲሰበሰብ ውሎ ከምሽቱ በአሥራ ሁለት ሰዓት ድሉ የኢትዮጵያ መሆኑ ታወቀ።
የዛሬዎቹ ባሻ አውአሎሞች ይህን ብልሀት እየተጠቀሙበት ያለው በገዛ ሀገራቸው ላይ ነው። ግማሾቹ ሆን ብለው የተሳሳተ መረጃ ለገዛ ወገናቸው ሲሰጡ እና አቅጣጫ ሲያስቱ፣ ሌሎቹ ደግሞ በህዝብ መሀል የማደናገሪያ ወሬ በማሰራጨት ከውስጥ የመገዝገዝ ስራ እየሰሩ ነው። ሆን ብሎ በመከላከያ ሠራዊቱ እና በመንግሥት መካከል ፤ በልዩ ሀይሉ እና በመከላከያው መካከል ፤ በፌዴራል መንግስቱ እና በክልሎች መካከል ፤ በአንዱ ክልል እና በሌላው ክልል ፤ በአንድ ከተማ እና በሌላው ከተማ ነዋሪ መካከል ስንጥቅ ለመፍጠር የሚወራው ወሬ ብዛት ስፍር ቁጥር የለውም።
ብዙ ሰውም ይህን ወሬ ሳያላምጥ ይውጠዋል። አላማው ምን እንደሆነ አይገነዘብም። አላማው ግን አንድ ነው ፤ እሱም የወገንን ሀይል ከውስጥ በወሬ በመፍታት ከደጅ የሚመጣው ጠላት ሰተት ብሎ እንዲገባ መንገድ ማስከፈት ነው።
የዋሆቹ ሳይገባቸው በሩን በመክፈት አብረው አጋዥ ይሆናሉ። መከላከያ ሰራዊቱ ደጀን ወደ ሆነው ህዝብ ተመልሶ አረፍ ከማለቱ ይህን ደጀን የሆነ ህዝብ ሀሰተኛ ወሬ በመዝራት ለመናድ ከሚጥሩ ጠላቶች ጋር አብረው ይሰራሉ። የዋሆች!
በዚያኛው ወገን ያለው ሀይል በየከተማው በሆነ ጊዜ ቆሞ የተነሳውን ወይም በ‹‹ፎቶ ሾፕ›› የሰራውን ሁሉ እየለጠፈ እዚህ ጋ ደርሰናል ፤ በዚያ ልንመጣ ነው ወዘተ… እያለ የስነ ልቦና ጦርነት ሲሰራ ፤ በዚህ በኩል ከውስጥ ሆነው የአምስተኛ ረድፈኝነት ስራቸውን እየሰሩ ያሉት ደግሞ ይህን በማስተጋባት የስነ ልቡና ጦርነቱን ያጠናክሩለታል። በዚህኛው ወገን ያለው ሰው የአምስተኛ ረድፈኞቹን አላማ ተረድቶ ከመከላከል እና ተመጣጣኝ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ጭራሹን የመከላከያ ሠራዊቱን እንቅስቃሴ በፎቶ እና በቪዲዮ እየዘገበ እና በማህበራዊ ሚዲያ እየለጠፈ ለጠላት ሌላ የጥቃት መሳሪያ ያቀብላል።
አሸባሪው ህወሓት በመደበኛ ጦርነት እንደማያሸንፍ አውቋል። ስለዚህም ያለው አማራጭ በአንድ ጎን ያገኘውን ህዝብ ያህል እያፈሰ ወደ ጦርሜዳ መላክ ሲሆን፣ ሁለተኛው እና ዋነኛው ስልት ግን ግዙፍ የሆነችውን ኢትዮጵያ ለመጣል የወሬ ዘመቻ እና የስነ ልቦና ጦርነት ማካሄድ ነው። ለዚያ ደግሞ ዋነኛ ተልእኮ የተሰጣቸው ሰላማዊው ቀጠና ላይ የተሰገሰጉት አምስተኛ ረድፈኞች ናቸው።
እና ምን እናርግ ነው? ዋናው ጥያቄ ። መፍትሄው አንደኛ አምስተኛ ረድፈኞች በመካከላችን እንዳሉ መገንዘብ ነው። ሁለተኛው እነዚህን አምስተኛ ረድፈኞች በየዋህነት የግርግር መረጃ ከሚያስተላልፉት መለየት ነው። ሶስተኛ በስህተት የገቡበትን መምከር እና ራስም በዚህ ላለመጠለፍ መጠንቀቅ ነው። አራተኛው ደግሞ አምስተኛ ረድፈኞቹ በሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ክትትል እንዲደረግባቸው ለዚህ አካል ማሳወቅ ነው።
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ነሐሴ 4/2013