
አሸባሪነት ከማህበረሰብና ከሀገር ባለፈ ለዓለም ሰላምና ደህንነት ስጋት ከሆነ ውሎ አድሯል። ይህንን ስጋት ለመቀልበስም ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ሰፊ ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል። ክተት ብሎ ሠራዊት ከማዝመት አንስቶ የአሸባሪ ቡድኖችን ሕልውና ለማሳጠር በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር መድቦ ተንቀሳቅሷል። ከፍያለ የህይወት መስዋእትነት የሚጠይቁ ወታደራዊ ዘመቻዎችንም ለማድረግ ተገዷል።
አሸባሪነት ጽንፈኛ በሆኑ መርዘኛ አስተሳሰቦች የሚመራ ፣ተስፋ በመቁረጥ ላይ የተመሰረተ እና ከዚህ በሚመነጭ የጭካኔና የክፋት ተግባር የሚገለጥ ነው። ከዚህ የተነሳም በየትኛውም የዓለም ክፍል የተነሱ አሸባሪዎች አጠቃላይ ለሆነው የሰው ልጅ የልብ ስብራት የሚሆኑ ተግባራትን ሲፈጽሙ ማየት የተለመደ ሆኗል።
ባለፉት አስርና ሃያ ዓመታት ውስጥ በዓለማችን የተለያዩ አካባቢዎች የተፈጠሩ አሸባሪ ቡድኖች የተፈጠሩበትን ማህበረሰብ ከዚያም አልፈው ዓለም አቀፉን ህብረተሰብ በአንድ ይሁን በሌላ ከፍ ያለ ዋጋ አስከፍለዋል። ጥለውት ያለፉት የሰቆቃ ጠባሳም ዓለም በቀላሉ ሊዘነጋው የሚችል አይደለም።
በአፍሪካ እንደ አልሸባብና ሎርድ ኦፍ ሪዚዝታንስ፤ በመካከለለኛው ምሥራቅ እንደ አልቃይዳ ዓይነት በጽንፈኛ አስተሳሰቦች የተቃኙ የአሸባሪ ቡድኖች ከተፈጠሩበት ማህበረሰብና አካባቢ ወጥተው ለዓለም ሰላም እና ደህንነት የስጋት ምንጭ ሆነዋል። ለዚህም ዋነኛው ምክንያት ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ገና ከጅምሩ ለቡድኖቹ ተገቢውን ትኩረት መስጠት ባለመቻሉ እንደነበር ብዙ አሳማኝ መረጃዎች ማቅረብ ይቻላል።
ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ የቡድኖቹን ውልደትና እድገት ማህበረሰባዊና አካባቢያዊ አድርጎ የመመልከቱ እና በቡድኖቹ የተፈጠሩ ስጋቶችና አቅልሎ የማየቱ እውነታ ቡድኖቹ ሆኑ የቡድኖቹ አክራሪ አስተሳሰቦች በማህበረሰቡ ውስጥ ከዚያም አልፈው አካባቢያዊና ዓለም አቀፍ እውቅና እንዲያገኙ በዚህም ለዓለም ስጋት እንዲሆኑ የተሻለ ዕድል እንደፈጠረላቸው ይታመናል።
እስከአሁን ባለው ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ለሽብርና ለአሸባሪነት አንድ ዓይነት ብይን ለመስጠት የተቸገረበት ሁኔታ ባይኖርም፤ ከብይን ባለፈ ተጨባጭ የሆኑ እውነታዎችን በፍትሐዊነት፤ ከዚያም በላይ በሰብዓዊ እሴቶች በመመዘን አሸባሪን አሸባሪ ለማለት በሚያስችል ቁመና ላይ ግን አይደለም።
በአንድ በኩል ከተገለጹ የሽብርተኝነት ተግባሮች በስተጀርባ ያሉ ቡድኖች ከሚፈጥሯቸው ችግሮችና ስጋቶች ውጪ በሆኑ መመዘኛዎች በመመዘን ተግባሮቹን ከማውገዝ ይልቅ ሁኔታዎችን አይቶ እንዳላየ መሆኑ በሌላ በኩል የቡድኖችን እኩይ ዓላማና ተግባር ለሌላ ስውር ተልእኮ ማስፈጸሚያ አቅም አድርጎ መውሰድ እየተለመደ ከመጣም ውሎ አድሯል።
ራስን በችግሩ ሰለባ በሆኑ ህዝቦች ተክቶ በማየት እንደ ሰብዓዊ ፍጡር ችግሩ ሊፈጥር የሚችለውን ስሜት ለመስማት ከመሞከር ይልቅ በራስ ወዳድነትና በስግብግብነት በደነደነ ልብ ለችግሩ የሚሰጡ ምላሾች ከዋናው ችግር የበለጠ ለችግሩ ሰለባዎች የልብ ስብራት እየሆኑም ነው።
በኛም ሀገር እየሆነ ያለው ከዚህ የተለየ አይደለም ከውልደቱ ጀምሮ በዘመኑ ሁሉ ሕዝባችንን በአንድም ይሁን በሌላ ከፍ ያለ ዋጋ ሲያስከፍል የኖረው አሻባሪው ህወሓት በሀገሪቱ የተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ከተፈረጀ ወራቶች አልፈዋል። ፍረጃው በተጨባጭ ማስረጃዎች ላይ የተመሰረተ በመርህ ደረጃ መላው ዓለም የሚስማማበትም እንደሆነ ይታመናል።
ቡድኑ በህዝባችን ማህበራዊ ፣ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ከዛም አልፎ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች ላይ ከፍ ያሉ ወንጀሎችን ከመፈጸሙም በላይ የህዝባችንን አብሮ የመኖር ባህል በተለያዩ ትርክቶች በማፋለስ ዜጎችን ከፍ ላሉ የደህንነት ስጋቶች የዳረገ ነው። በዚህም በሚሊዮን የሚቆጠሩት ዜጎቻችንን ለመፈናቀል፣ ለሞትና ለአካል ጉዳት ዳርጓል።
ከለውጡ ማግስት ጀምሮም በተለያዩ የሽብር ተግባራት ውስጥ በአደባባይ በመሳተፍ ሀገረቱ ውስጥ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ አለመረጋጋቶች እንዲፈጠሩ በሃሳብ በገንዘብና በተግባርም ጭምር የተደገፉ የሽብር ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል። ከዚያም አልፎ በሀገሪቱ የመከላከያ ኃይል ላይ አሰቃቂ የክህደት ጥቃት በመፈጸም ሀገርንና ህዝብን አደጋ ውስጥ የከተተ ተግባር ፈጽሟል።
ከዚህም ባለፈ የህዝባችን የሞራል አሴቶች በከፍተኛ ሁኔታ በሚፈታተን መልኩ ፣ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሊያስበው ቀርቶ ሲያስበው የሚቀፈውንና የሚጨንቀውን የዘር ማጥፋት ወንጀል በማይካድራ ፈጽሟል። ከዚህም በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሐን ዜጎች ማንነታቸውን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በአሰቃቂ ሁኔታ በአደባባይ በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል።
ቡድኑ በጦር ወንጀለኝነት በሚያስጠይቅ መልኩ ሕፃናትን የጦር መሳሪያ በማሸከም በግጭት አካባቢዎች አሰልፎ በሕፃናት ደም የፖለቲካ ቁመራ ውስጥ ነው። በርግጥ ለቡድኑ ይህ አዲስ ባይሆንም፣ በቀደመው ዘመኑ በዚሁ ሁኔታ ብዙዎችን ገብሮ ወደ ስልጣን የመጣበት እውነታ መኖሩ ግልጽ ነው ፣ ቡድኑ በዚሁ የሽብርና የጭካኔ ተግባሩ እንደቀጠለበት ነው።
ይህን ሁሉ በአለም አቀፍ ህግና በሰብዓዊ የሞራል አሴቶች በብዙ መልኩ ሊወገዙ የሚገቡ ፍጹም ኢሰብዓዊ ተግባራትን በማን አለብኝነት በአደባባይ ሲፈጽም ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ እያየና እየሰማ ዝምታን መምረጡ ግን ለአሸባሪው ህወሓት የልብ ልብ እየሰጠው በወንጀል ላይ ወንጀል እንዲፈጽም አቅም እየሆነው ይገኛል።
ቡድኑ መንግሥት የደረሰበትን የተናጠል የተኩስ አቁም ባለመቀበል በአማራና በአፋር ክልሎች ጥቃት እየፈጸመ ሲሆን፤ ሰሞኑን በአፋር ክልል በሚገኙ ንፁሐን ዜጎች ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ አካሄዷል። በጥቃቱም 170 ሕፃናትን ጨምሮ 240 ንፁሐን ዜጎችን ገድሏል፤ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች አፈናቅሏል።
ይህን ሁሉ ጭካኔ የተሞላበት የግፍ እና የሽብር ተግባር ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ለማውገዝ የወሰደበት ጊዜ በየትኛውም ሰብዓዊና ዓለም አቀፋዊ መመዘኛ የሚያስወቅሰው ነው። ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ የቱን ያህል እራሱን ከሰብዓዊ እሴቶች እያራቀ ባልተገቡ ምክንያቶች በራሱ ለዓለም ስጋት እና ለህዝቦች አለመረጋጋት ምክንያት እየሆነ እንዳለ የሚያመላክት ነው።
ችግሩ ዛሬ ላይ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን ታሳቢ ያደረገና ከፍ ያለ ዋጋ እያስከፈላቸው ቢሆንም ውሎ ሲያድር ዓለም አቀፉን ህብረተሰብ በተመሳሳይ ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል ከወዲሁ በአግባቡ ማሰብ አስተዋይነት ነው።
ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ላስቀመጣቸው የሞራል እሴቶች ራሱን ተገዥ በማድረግ የቡድኑን የሽብር ተግባር በአደባባይ ማውገዝና በቃህ ማለት ይኖርበታል። ለዚህ ደግሞ ሊያቀርባቸው የሚገቡ ምክንያቶች ሊኖሩ አይገባም ፤ የሚያባክናቸው ደቂቃዎችም መኖር የለባቸውም!አዲስ ዘመን ነሐሴ 4/2013