መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፤ የፋሽን ኢንዱ ስትሪው በአውሮፓ እና በአሜሪካ የተወለደ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪው በከፍተኛ ደረጃ አለም አቀፍ መልክ ያለው ሆኗል፡፡ የአልባሳቱ ዲዛይን በአንድ ሀገር ፣ አልባሳቱ ደግሞ በሌላ ሀገር እየተመረቱ ወደ ሌላ ሶስተኛ ሀገር እየተወሰዱ የሚቸበቸቡበት ኢንዱስትሪ እየሆነም ይገኛል፡፡
ኢንዱስትሪው ሰፊ ትስስር ወይም ሰንሰለት ያለውም ነው፡፡ ለአብነትም አንድ የአሜሪካ የፋሽን ኩባንያ ጨርቁን ከቻይና ሊገዛ፣ ልብሶቹን ደግሞ በቬትናም ሊያመርት፣ የአልባሳቱን የመጨረሻ ምእራፍ ደግሞ በጣልያን አካሂዶ መልሶ ወደ አሜሪካ መጋዘኑ የሚወስድበት አሰራር የሚከትልበት ሁኔታ ይታያል፡፡
ኢንዱስትሪው የመካከለኛው ዘመን ውጤት ነው።ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ቀድም ብሎ ሁሉም አልባሳት በእጅ የሚመረቱ ነበሩ፡፡ በ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ ደግሞ እንደ የልብስ ስፌት መሳሪያ፣ ፋብሪካዎች ያሉ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች መምጣትን ተከትሎ እንዲሁም ከካፒታሊዝም ስርአት መምጣት ጋር ተያይዞ አልባሳት የማምረት ስራው ደረጃንና ዋጋን መሰረት ባደረገ መልኩ ለህዝብ ወደ ማምረት ተሸጋግሯል፡፡
ኢንዲስትሪው በአለም ቢሊየኖች ዶላሮች የሚንቀሳቀሱበት ሲሆን፣ ኢንዱስትሪው ለአልባሳት ዲዛይን በማውጣት ፣ አልባሳትን በማምረትና ለገበያ በማቅረብ ላይ በስፋት ይሰራል፡፡ የፋሽን ኢንዱስትሪው የፋሽን ዲዛይን ማውጣት፣ ፋሽኖችን ማምረት፣ማከፋፈል፣ መቸርቸር ማስተዋወቅን ያጠቃላል፡፡ እነዚህ ብቻም ሳይሆኑ የትኛውንም አይነት የሴቶች የወንዶችና የህጻናት የአልባሳት ማስታወቂያ ስራዎች ጭምር በፋሽን ኢንዱስትሪው ስር ይጠቃለላሉ፡፡
በተዋቂ ዲዛይነሮች እየተፈጠሩ በፓርስና ኒውዮርክ ገበያ ላይ በውድ ዋጋ እየቀረቡ ከሚለበሱት አልባሳት እንስቶ በተለያዩ የአለም ክፍሎች በሚገኙ ግዙፍ የገበያ ማእከላት/ ሞሎች/ የሚቸበቸቡት ለህዝብ አገልግሎት እስከሚመረቱት ድረስ ያሉት እንደ ስፖርት አልባሳትና የአዘቦት አልባሳት የመሳሰሉት ሁሉ በዚሁ ኢንዱስትሪ የሚመረቱ ሆነዋል፡፡
ኢንዱስትሪው በሀገራችን ምን መልክ ይኖረው ይሆን፡፡ አቶ ቃልኪዳን ሾቤ በኔክስት ፋሽን ዲዛይን ኮሌጅ የክርኤቲቭ ዲዛይን መምህር ናቸው፡፡ እሳቸውም የፋሽን ኢንዱስትሪው በዓለም ገበያን በማነቃቃትና በመምራት ረገድ ትልቁን ቦታ ከያዙት ነገሮች መካከል አንዱ ነው ይላሉ፡፡
ምክንያቱንም ሲያብራሩ እንደገለጹት፤ የሰው ልጅ ይለብሳል ፤ ተመሳሳይ ልብስ ሠፊ ጊዜ ካደረገ ይሰለቻል፡፡ ለበዓላትም ሆነ የሚሄድበትን ቦታ ዐውድና ድባብ ጠብቆ የሚለብሰው አለ፤ የዕለት ተዕለት ፣ መደበኛ፣ የሥራና የደንብ ልብስ አለ፤በዚያም ሆነ በዚህ ሁለትን ሦስት ልብስ ሊኖረው ይችላል፡፡ ከሥራና ከደንብ ልብስ ውጪ ሌሎቹ ፋሽኑ ሊመራቸው የሚችሉ ናቸው ሲሉ የክርኤቲቭ ዲዛይን መምህሩ ያስረዳሉ፡፡
የሰው አስተሳሰብ፣የኑሮ ቦታና ሁኔታ ሲቀየር የሚለብሰው የሚቀየርበት ግዴታም ይኖራል፡፡ የመልበስ ሂደቱና ፍላጎቱ አይቆምም፤ ሰው ራሱን ጥሩ አድርጎ ማቅረብ፤ራሱን ዘና ፈታ ማድረግ ይፈልጋል፤ ስለዚህ መልበሱን ካላቆመ ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልልቅ ለውጦች አሉ፤ የተለያዩ ለልብስ እና ለፋሽን የሚረዱ አዳዲስ ቁሶች ይገባሉ፡፡ አዳዲስ ነገሮች በሰዎች ይፈጠራሉ፤ቴክኖሎጂዎች እያደጉ ነው፤ በቀላሉ ልብሶች ገበያ ላይ የሚወጡበት ሁኔታ ተፈጥሯል፤ ያለ ስፌት ልብስ መስፋት ይቻላል እየተባለ ያለበት ጊዜ ነው ያለነው፡፡
ልብስን በቀላሉ ገበያ ላይ ለማዋል የሚቻልባቸው መንገዶች መፈጠራቸውንም አቶ ቃልኪዳን ይጠቁማሉ። ይህም በፋሽን ኢንዱስትሪው ላይ በጣም እየተሠራ መሆኑን ያሳያል ነው የሚሉት፡፡
እኛ ሀገር ሲመጣ ግን የመሥሪያ ዕቃዎች፣ የሽመና ቁሶቹ አልዘመኑም ፤በዚህ የተነሳም የማምረቱ ስራ ጊዜና ጉልበት ይፈጃል፤ ውሱንነት አለው፡፡ ሸማዎቹን ለመሥራትና በሚፈለገው መልኩ ገበያ ላይ ለማቅረብ የግብአት እጥረት እና የዋጋ ንረት አለ ሲሉ ያመለክታሉ። አሠራሩ ቢከብድም ፋሽኑ ሲታከል ግን ገበያ እያገኘ በሰዎች ሆነ በነጋዴዎች እየተወደደ ነው፡፡ በጣም ለውጥ ዕድገት አለ ሲሉም ይጠቁማሉ፡፡
በሀገሪቱ በዘመናዊ ልብሶች በኩል በኢንዱስትሪዎች ጥሩ ጥሩ ጨርቆች ማምረት ተጀምሯል የሚሉት የክርኤቲቭ ዲዛይን መምህሩ፣ ምርቶቹ በጣም ጥሩ ጥራት እና ውበት ያላቸው ለዶላር ምንዛሪ ሲባል ወደ ውጪ የሚሸጡ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ እኛ ሀገር ተመርተው ለእኛ ሀገር ገበያ ብዙም እንደማይቀርቡ ጠቅሰው፣ በማምረቱ ስራ ግን ለዲዛይነሮቹ ጥሩ ሥራ የተፈጠረላቸው አጋጣሚዎች እንዳሉ ይጠቅሳሉ፡፡
«በሀገራችን የሚሠራ የሰው ኃይል እና የልብስ ገበያ ፍላት ሠፊ ነው፤ለባሽ አለ ፋሽን ኢንዱስትሪውም እያደገ ነው ፤ዲዛይነሮች በተለያየ ቦታ በገበያው ይፈለጋሉ ፤ ይህ ትልቅ ነገር ነው ፤ያስደስታል ሲሉ ያብራራሉ፡፡ እነዚህ ዜጎች የሚፈለጉት ለፋሽኑ ሲባል መሆኑንም ይጠቁማሉ። ልብስ ሠፊዎቹ እጃቸውን ሰብስበው በቀድሞው ስልት መስፋት እንደሚችሉም ጠቅሰው፣ ዲዛይነር የሚፈልጉት ግን ገበያውን ለመያዝ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ዲዛይነር አሁን እንደ ትልቅ ሙያ እየተቆጠረ በገበያው እየተፈለገ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ፤ በፋሽኑ እና ዲዛይን ዙሪያ ለውጦች አሉ፤ባህላዊ አልባሳት በተለያየ መልኩ እየተሠሩ ገበያውን እንደአዲስ እየሳቡት ነው፡፡ ለወንዶችም ለሴቶችም ምቹ የሆኑ ልብሶች በጥሩ ዲዛይን ተጠልፈው ተሠርተው ፋሽን ሆነው ሲመጡ ይታያል ፡፡ ይሄ ሁሉ ታዲያ የፋሽንና ዲዛይን ባለሙያዎች አሻራ አለበት፡፡ አንዳንዱ የባህል ጥበብ የአዘቦት ልብስ ሆኖም ጭምር የሚለበስ ሆኖም እየመጣ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ባህላዊ ልብስ ፋሽን ሆኖ ገበያ እያገኘ እና ተወዳጅ እየሆነ ነው ሲሉ የኔክስት ፋሽን እና ዲዛይን መምህሩ ያስረዳሉ፡፡
ጥበብ ልብሶች ላይ ብቻ ሳይሆን ዲዛይነሮቹ በሀገሪቱ ከዳር እስከ ዳር አዲስ ነገር እየፈለጉ የፋሽን ግብአት እየተደረገ ፋሽኑ ጎልቶ እንዲወጣ እየተሰራ ነው፡፡ እናም በፋሽንና ዲዛይን ላይ የዘርፉ ባለሙያዎችና ነጋዴዎች ትኩረት እየሠጡ ነው፤ይህ ደግሞ ገበያውን ያነቃቃዋል ሲሉ ያብራራሉ፡፡
ለፋሽንና ዲዛይን ያለው ዕውቀት እየሰፋ መምጣቱን ጠቅሰው፣ ይህን ተክትሎም የፋሽንም አልባሳትም ፍላጎት እየጨመረ ነው ሲሉ አቶ ቃልኪዳን በሙያው የመሰልጠን ፍላጎቱም በጣም ከፍተኛ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡
«ኔክስት ዲዛይን ሲቋቋም ሰዎች ለፋሽን ምንም የሚሰጡት ትኩረትም ሆነ ግንዛቤ አልነበረም የሚሉት አቶ ቃልኪዳን፣ ፋሽን እና ዲዛይን እንደ ሙያ በማይቆጠርበት ወቅት ፋሽን ዲዛይነር ማሰልጠኛ አቋቁማለሁ ብሎ ማሰቡ ዕብደት ነበረ ሲሉም ያስታውሳሉ፡፡ እየተሠራ የተመጣበት ሁኔታ ለድርጅቱ ዋጋ እንዳሰጠውም ያመለክታሉ፡፡
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 3 ቀን 2013 ዓ.ም