
በመዲናችን ከሚገኙ የጀበና ቡና ቤቶች አብዛኞቹን እየቃኘሁ ነው። ለምለም ቄጤማ በተጎዘጎዘበት ወለል ላይ በረጅሙ ረከቦት ላይ ለአይን የሚሞላ በርካታ ሲኒዎች ተደርድረዋል። ጥቁሩ የሸክላ ጀበና ማንደጃው ላይ ተሰይሟል። የዕጣኑ ጢስ እንደ ጢስ አባይ እንፋሎት ሳያቋርጥ ቦለል ይላል። የቡና ቁርሱ ፈንድሻ ስርዓቱን ደማቅ አድርጎታል።
እዚህ ጋር የተሰየሙት ሴቶች በአብዛኛው በባህላዊ አልባሳት ተውበዋል። የየራሳቸውን ስያሜም በሚገልጽ የደንብ ልብስ ያሸበረቁ አሉ። ቡና አቆላላቸውና አቀዳዳቸው ቄንጠኛ ነው። አብዛኛው ደንበኛ ወደ ጀበና ቡና ቤቶቹ የሚጎርፈው ዓይኑ በስርዓቱና በሴቶቹ ፣አፍንጫው እየተቆላና እየተፈላ ባለው ቡና ሽታ እየተሳበ ነው።
አራት ኪሎ፣ፒያሳ፣ ሜክሲኮና ካዛንቺስ ጎራ እያልን የቃኘናቸው የጀበና ቡና ቤቶችና የአጀባቸው ስርዓት በሙሉ ተመሳሳይ ነው። ቤቶቹ እረፍት የሚያጡበት ዋና ገበያቸው ምሳ ሰዓት ላይ ነው። በዚህ ሰአት ቡና አስተናጋጆቹ እዛም እዚህም ትዕዛዝ ስለሚበዛባቸው ይዋከባሉ። መቀመጫ እስኪ ጠፋ ቤቶቹ በሰው ይጨናነቃሉ። ቆሞ ወንበር እስኪለቀቅ የሚጠብቁም አልጠፉም። እንደ ምሳ ሰዓት ባይበዛም ረፋዱ አራት ሰዓት ላይም በተወሰኑ ደንበኞች ይጎበኛሉ። ከዚህ ውጪ ያለው ገበያ የሚንጠባጠቡ ደንበኞች የሚስተናገድበት ነው።
አብዛኞቹ ደንበኞች አሳምረው የቡና ጣእም ያውቃሉ። በሚያስገርም ሁኔታ በጣእሙ ቡናው የየት አካባቢ እንደሆነም ይለያሉ። ይሄን ቡና ሻጮችም ይጋሯቸዋል። ዋጋቸው እንደሚሸጡበት ቤት ይዘት ቢለያይም አማካኙ የአንድ ስኒ ቡና ዋጋ የብዙዎችን ቡና ጠጪዎች አቅም ያማከለ አምስት ብር ነው።
አራት ኪሎ የጀበና ቡና ባለቤት ወይዘሪት ገነት ደጀኔ ሥራውን መሥራት ከጀመረች ሁለተኛ ዓመት ሆኗታል። በአካባቢው በአምስት ብር ቡና የምትሸጠው እሷ ብቻ ነች። ሌሎቹ ከስድስት እስከ 15 ብር ነው የሚሸጡት። የእርሷ ሂሳብ የደንበኞቿን አቅም ታሳቢ ያደረገ ነው። ከደንበኞቿ አብዛኖቹ አምስት ብሩን እንኳን መክፈል የሚከብዳቸው ጡረተኞች ናቸው። የፌዴራል ፖሊስ፣የመከላከያ አባላት እና ገቢያቸው ዝቅተኛ የሆነ የህብረተሰብ ክፍሎች ደንበኞቿ ናቸው። ቢያንስ በቀን ሁለቴ ብቅ ብለው ይጠጣሉ።
በአሁኑ ወቅት የጥሬ ቡና ዋጋ ከፍ ማለቱን ትናገራለች። ሆኖም ግን በነበረው ዋጋ መሸጡን የቀጠለችው ደንበኞቼ ይሸሹኛል የሚል ፍራቻ አድሮባት ነው። እነሱስ ከየት ያመጡታል በሚል አዘኔታ ጭምር መሆኑን ትጠቅሳለች። እሷም ቡና ጠጪ መሆኗ ሱስ አስቸጋሪ መሆኑን እንድትረዳ አድርጓታል።
ገነት በምትሰራው የጀበና ቡና ከራሷም አልፋ ለሌሎችም የስራ ዕድል ፈጥራለች። የሥራ ዕድል ከፈጠረችላቸው አንዷ ወጣት ዘነበች ታደሰ ትባላለች። ቡና ማፍላት እና ማስተናገድ ነው የምትሰራው። ደም ግቡ የሆነው የፊቷ ገጽታ በፈገግታ የታጀበ ነው። በመስተንግዶው ሰዎችን በአክብሮት ተቀብላ ታስተናግዳለች። እንደፍላጎታቸው ታዝዛና አስደስታ ትሸኛለቸ። ይሄ ደግሞ ደንበኞች ተመልሰው እንዲመጡ ትልቅ እድል ፈጥሮላቸዋል። እኛም ያናገርናት ደንበኞቿን አስተናግዳ ከሸኘች በኋላ በድጋሚ ከስራ ውጪ አግኝተናት ነው።
በየአካባቢው የጀበና ቡና ከተለመደ ጀምሮ የቡና ጠጪዎች ቁጥር ተበራክቷል የሚል እምነት አላት። በቀን ሶስት ኪሎ ቡና ያልቃል። ይሄም እሷን ጨምሮ ለብዙ ዜጎች የሥራ ዕድልም እየፈጠረ ይገኛል። በዚህም ኢኮኖሚያዊ ችግሮቿ እየተቃለለ ነው። ለምሳሌ እሷ የአሰሪዋ መልካም ፈቃድ ተጨምሮበት ከምታገኘው 1ሺ500 ብር ደመወዝ ቤት ተከራይታ መኖር ችላለች። በችግር ምክንያት ከሰባተኛ ክፍል ያቋረጠችውን ትምህርትም እየተማረች ነው። ከዚህ አንፃር የቡና ሥራ አዋጪ ነው፤ ለብዙዎች የስራ ዕድልም ፈጥሯል ትላለች።
‹‹ቡናው ቀጠነ ወፈረ የሚል ደንበኛ ቢኖርም ተመጥኖ የሚፈላበት የራሱ የልኬት ደረጃ አለው›› ያለችን ደግሞ በዚሁ ቤት ተቆጣጣሪ ወጣት ቤተልሔም አራጌ ነች። በተፈጥሮ ውሀ የማያነሳ ቡና ዓይነት መኖሩንም ትናገራለች። ይሄ ቡና ለሽያጭ ሲቀርብ ቀጠነ በሚል የሚነሱ ቅሬታዎች ይኖራሉ። ሆኖም ውሀ ከሚያነሳው አንድ ኪሎ ቡና 96 ስኒ የተፈላ ቡና ይወጣዋል።
ወጣት አለማየሁ ጃለታን አራት ኪሎ ድንቅ ስራ ህንፃ ካሉት የጀበና ቡና መሸጫ ቤቶች ቡና ሲጠጣ ነው ያገኘነው። አለማየሁ እንደሚገልፀውም የቡና ዋጋ የአብዛኛው ደንበኛ ኪስ ማዕከል ያደረገ ነው ይላል። ሆኖም ግን እንደየቦታው የጀበና ቡና ዋጋው ይለያያል። አንዳንድ ቦታ ላይ 20 ብር ሲከፈልበት አስተውሏል።
በሾላ፣በመርካቶና በተለያዩ ሸቀጣሸቀጥ መደብሮች የቡና ዋጋ ጠይቀን ነበር።ሁሉም ጋር አንደኛ ደረጃ የሚባለው ኪሎ ቡና 240 ብር ነው የሚሸጠው። የሾላው ቡና ነጋዴ ነስሩ ከድርም በዚሁ ዋጋ መሸጡን ገልጾልናል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 3 ቀን 2013 ዓ.ም