ትናንት ያለፈው ለዛሬ አንድ መሰረት ጥሎ ነውና ዛሬን ለማጠንከር ወደኋላ ማየት ተገቢ ነው።ዛሬ ላይ በመላው አገራችን “ኢትዮጵያን እናልብስ” በሚል የአረንጓዴ አብዮት ኢትዮጵያዊያን ሀገራቸውን አረንጓዴ በማልበስ ላይ ይገኛሉ።
ታዲያ ከዚህ ታላቅ ዘመቻ ጋር ተያይዞ ሁሌም የሚታወስ ሀያል ተግባር በታሪክ ሰነድ ላይ ሰፍሮ ይገኛልና በዛሬ ሳምንቱን በታሪክ አምዳችን ያንን ማንሳት ፈለግን።ታሪኩ የተፈጸመው ከሳምንት በፊት ቢሆንም ፣ ክንውኑ ክረምቱን በሙሉ የቀጠለ በመሆኑ ይህን ታላቅ ክንውን ለዛሬ ይዘነው ቀርበናል።
ኢትዮጵያ በደን መመናመን ክፉኛ የተጠቃች ሀገር ናት።መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ የኢትዮጵያ የደን ሽፋን ከነበረበት 35 በመቶ እያሸቆለቆለ ወርዶ 4 በመቶ ደርሶ ነበር።ኢትዮጵያ ይህን የደን መመናመን ለማስቆም ፣የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተጽእኖ ለመቋቋም፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ከደለል ለመታደግ በተፋሰስና ደን ልማት ላይ አተኩራ እየሰራች ትገኛለች።
በደን ልማቱ ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች መሆኑን ተከትሎም በደን ሽፋን ላይ ለውጥ እየታየ ይገኛል።በአሁኑ ወቅት የደን ሽፋኑ ወደ 17 በመቶ ማደጉን መረጃዎች ያመለክታሉ።ለእዚህ ሁሉ ታዲያ ኢትዮጵያ ባለፉት በርካታ አመታት ያካሄደቻቸው የችግኝ ተከላ መርሀ ግብሮች አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።
ኢትዮጵያ በተለይ ከ2000 ሚሌኒየም አንስቶ በችግኝ ተከላ ላይ ትኩረት ሰጥታ እየሰራች ነው።በሚሌኒየሙ ሁለት ችግኝ በሁለት ሺ በሚል መርሃ ግብር ኢትዮጵያውያን ሀገር በቀል ችግኞች እንዲተክሉ መደረጉ ይታወቃል።
ይህ ለደን ልማቷ የሰጠችው ትኩረት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ አነሳሽነት ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መጥቶ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ችግኞችን በየአመቱ መትከል ውስጥ ገብታለች።በእዚህ ታላቅ የደን ልማት ተግባርም ተጠቃሽ የሆነው ደግሞ በ2011 ክረምት ወቅት የተካሄደውን የችግኝ ተከላ ነው።
በዚህ የችግኝ ተከላ መላ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆኑ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ጭምር እንዲሳተፍ እየተደረገ ነው።እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ 40 ችግኞችን እንዲተክል በማድረግ 4 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል ታቅዶም ነው የተሰራው።የዚህ እቅድ አካል የሆነው በአንድ ጀንበር 200 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል ሀምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ቀጠሮ ተይዞለት፣ ሰፊ ዝግጅትም ተደርጎበት መላ ኢትዮጵያን በማነቃነቅ የችግኝ ተከላው ከማለዳ አንስቶ እስከ ምሽት ድረስ ተካሂዷል።
በዚህ የችግኝ ተከላም ታሪክ መስራት የተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል።ኢትዮጵያ በአንድ ጀንበር 200 ሚሊየን ችግኞችን ለመትከል አቅዳ ከ350 ሚሊየን በላይ ችግኞችን መትከል ችላለች።ይህ ከእቅድ በላይ የተመዘገበ የችግኝ ተከላ ብቻ አይደለም፤ ድሉ እአአ በ2017 ህንድ በአንድ ጀንበር 66 ሚሊየን ችግኞችን በመትከል ይዛው የቆየችውን ታላቅ ሪከርድም በብዙ እጥፍ የሰበረ ለመሆን ችሏል።
ኢትዮጵያውያን የፈፀሙት ይህ ታላቅ ተግባር ታላላቅ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኋን ዘግበውታል።የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማት ጭምር በአድናቆት ተመልክተውታል።
አልጀዚራ «ኢትዮጵያ 350 ሚሊየን ችግኞችን በአንድ ቀን ተከለች» ሲል የዘገበ ሲሆን፣ ቢቢሲ በበኩሉ ‹‹ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ባካሄደችው የችግኝ ተከላ ክብረ ወሰን ሰበረች›› ብሎ ዘግቧል።ሲኤንኤን፣ ‹‹ኢትዮጵያ በ12 ሰአታት ውስጥ 350 ሚሊየን ችግኞችን ተከለች›› ሲል ዘገቧል።ሌሎች በርካታ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃንና አለም አቀፍ ተቋማት ጭምር ዜናውን ተቀባብለውታል።
ይህ ታላቅ ቀንም የኢትዮጵያ ህዝብ አብሮነት የተንፀባረቀበት ሆኖ አልፏል። ኢትዮጵያ አረንጓዴ ልማት ለሕዝቧ የሕልውና እና የኑሮ መሠረት መሆኑን በመረዳት በ2011 ዓ.ም የችግኝ መትከያ ወቅት ከ4 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል ታላቅ ተግባር ፈጽማለች።
በዚህ “አረንጓዴ አሻራ” በሚል ተሰይሞ ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም በተካሄደው ታሪካዊ የችግኝ ተከላ ዘመቻ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት፣ ሕጻናት፣ አዛውንቶች፣ አካል ጉዳተኞች፣ ገበሬዎችና ግብርና ባለሙያዎች፣ የልማት ጣቢያ ሠራተኞችና ተማሪዎች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ አትሌቶች፣ ጋዜጠኞች የዲፕሎማቲኩ ማኅበረሰብ፣ በአጠቃላይ ከሰሜን እስከ ደቡብ፣ ከምዕራብ እስከ ምሥራቅ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በነቂስ ወጥቶ ተሳትፏል።
ኢትዮጵያዊያን ሩቅ በማሰብ ወጥነው በዚያን ወቅት በስፋት የጀመሩት የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋምና ዝቅተኛ የካርበን ልቀት መጠን እንዲኖር የሚያደርግ አብዮት መሆኑም በወቅቱ ተጠቁሟል።
ኢትዮጵያን በአረንጓዴ እፅዋት የማልበስ የአረንጓዴ አብዮት መርሀ ግብር ዘንድሮን ጨምሮ ለሶስት ተከታታይ ዓመታት ቀጥሏል።ይህ ተግባር በዓለም አቀፍ ደረጃም ተጠቃሽና በብዙዎች የሚወደስ ሆኗል።
በ2011 ብቻ ከ4 ቢሊዮን ችግኞች በላይ ተተክለዋል፤ በ2012 ደግሞ 5 ቢሊዮን ችግኞች የተተከሉ ሲሆን፣ ዘንድሮ ደግሞ በሀገር ውስጥ ስድስት ቢሊዮን ችግኞች ለመትከል እየተሰራ ነው ።ክልሎች የአንድ ጀንበር እቅድ ጭምር ይዘው ተከላውን አካሂደዋል።በኦሮሚያ ክልል ብቻ በአንድ ጀንበር ከእቅድ በላይ 390 ሚሊየን ችግኞች ተተክለዋል።
በተለይ በአንድ ጀንበር 200 ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ የነበረው መርሃ ግብር ሀምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም ሲካሄድ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ጭምር ይተላለፍ ነበር።ምሽት ጭምር ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚወጡ መረጃዎች እየተሰበሰቡ የተደረሰበት አሀዝም ይፋ ይደረግ የነበረበት እንደመሆኑ አይረሴ ክስተት ተብሎ የሚወሰድ ሆኖ አልፏል።
በዚህም ኢትዮጵያዊያን በአንድ ጀንበር ከ350 ሚሊየን በላይ ችግኞች ተክለዋል።ይህ የችግኝ መጠን 80 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን ነው፡ በዚሁ ዓመት የተተከለው አራት ቢሊየን ችግኝ፤ ሲታሰብ ደግሞ አንድ ሚሊየን ሄክታር መሬት የሸፈነ እንደነበር በወቅቱ ባለሙያዎች የሰጡት መረጃ አመልክቷል።
በአንድ ጀንበር ከ350 ሚሊዮን ችግኞች በላይ በመትከል ኢትዮጵያ የአለም ክብረ ወሰን ባስመዘገበችበት በዚህ ታሪካዊ ቀን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አሕመድ ህዝቡ በዘመቻው እንዲሳተፍ መልዕክት አስተላልፈዋል።መልዕክታቸው ተግባራዊ በሆነበት ማዕግስትም ‹‹የአረንጓዴ አሻራ ድላችሁ የተለየ ምስጋናዬን በፍቅሬ ሙዳይ ሞሽሬ እነሆ ልኬያለሁ።ሀገር ታመሰግናለች- እኔም አመሰግናለሁ።! …ይህ የተሳትፎ ማእበል እና የእምቢ ለሀገሬ ሆታም በታሪክ ማህደር ላይ መቼም አይረሳም።….”ሲሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በዚህ መርሃ ግብር የተተከለው ችግኝ ፀድቆ ደን መሆን ሲችል የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በአንድ በመቶ ሊያድግ እንደሚችል በወቅቱ በባለሙያዎች ስሌት መሰረት በመገናኛ ብዙኋን ተገልፆ ነበር።
አሁን ላይ እየተካሄደ ባለው ኢትዮጵያን አረንጓዴ የማልበስ ዘመቻ የአገሪቱን የደን ሽፋን ለማሳደግና ተፈጥሮን ለመጠበቅ እጅጉን ጠቃሚ መሆኑ የሚታዩ ለውጦች ምስክር ናቸውና ተጠናክሮ ይቀጥል መልዕክታችን ነው።
ኢትዮጵያ የተያያዘችውን የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር ዘንድሮ ወደ ጎረቤት ሀገሮች ለማስፋት እየተሰራ ነው።በዚህም አንድ ቢሊየን ችግኞች ለመትከል ታቅዷል።
ይህን ፅሁፍ ስናሰናዳ፤ በዘመቻው ወቅት መረጃውን ካዘጋጁ የአገር ውስጥና የውጪ መገናኛ ብዙኃን ገፆች ለመረጃው ምንጭ ሆነውናል።አበቃን ቸር ይግጠመን።
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 2/2013