የውሀ መገኛ የአርባ ምንጮች መፍለቂያ ናት አርባምንጭ ። አርባ ምንጭ ሲነሳ ውሀ ውሀ ሲነሳ ደግሞ አሳ የማይቀር ነው። አሣ ያከማቹት የአባያና ጫሞ ሀይቆች የአርባ ምንጭ ከተማ ፈርጦች ናቸው። ከስምጥ ሸለቆ ሀይቆች በስፋት ትልቁ የሆነው የአባያ ሀይቅ ጥልቀቱ 13 ሜትር መሆኑና ከ11 በላይ ከአለት የተዋቀሩ ደሴቶች መገኛ ነው። ማራኪ ተፈጥሮ የተቸረው ጫሞ ሀይቅ የአምስት ገባር ወንዞች ባለቤትና በእርዝማኔው በዓለም ሁለተኛ እንደሆነ ይነገርለታል። አዞን ጨምሮ ጉማሬና የተለያየ ዝርያ ያላቸው አሣዎችን አካቶ ይዟል።
አንድ ሺ 70 ስኩዬር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው አባያና 350 ስኩዬር ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ጫሞ ሀይቆች ጨለማው ተገፎ ማለዳው ሲተካም ሆነ ፀሐይዋ ስታዘቀዝቅ ከአድማስ ባሻገር ተፈጥሯቸውን እንዲመለከቱ የሚያስገድድ ልዩ መስህብ አላቸው። ቀትር ላይም ለሚያያቸው ከሰማይ ጋር የገጠሙ ታምራዊ ትዕይንት ይመስላሉ። 6 ዲግሪ ሴንትግሬድ 2 ሰሜን ኬክሮስና፤ 37 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ 33 ምስራቅ ኬንትሮስ የሆነ አቀማመጥ ያላት አርባ ምንጭ ከተማን የሚያደምቋት በርካታ ተፈጥሮአዊ ውበቶችን ተችራለች ።
አርባ ምንጭ ስያሜዋን ያገኘችው ከስምጥ ሸለቆ የደን አለት ንቃቃት ውስጥ በመፍለቅ እዛም፤ እዚህም ከሚንፎለፎሉ ምንጮች ነው። ምንጮቹ አርባ ይባሉ እንጂ ከአርባ በላይ መሆናቸው ይነገራል። ምንጮቹ ከተማዋን ከማስዋብ ባሻገር ለነዋሪዎቿም በአይሶ ሰርተፊኬት የተረጋገጠ ንፁህ የመጠጥ ውሀ አቅርቦት መሆን ችለዋል። በትልቅነቱ በዓለም ሁለተኛ የሆነው አዞና ብቸኛው እርባታ ማዕከልም መገኛ በመሆኗ ጭምር ዓይን የሚጣልባት ሳቢና ማራኪ፣ የቱሪስት መዳረሻ ከተማ ሆናለች። የእግዜር ድልድይን ጨምሮ ልምላሜ የተላበሰው ተራራማ መልክዓ ምድሯ ከደጋማውና ወይና ደጋው የአየር ንብረቷ ጋር ተዳምሮ ለቱሪስትም ሆነ ለነዋሪዋ እንቅስቃሴና ደህንነት ምቹ አድርጓታል።
ከተማዋ በረጅሙና ጣፋጩ ሙዝ እና በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ መመረት በጀመረው የአፕል ፍራፍሬ ምርቷ ትታወቃለች። ባልተዘመረላቸው ባህላዊ ምግቦችና መጠጦች ትጠቀሳለች። በአካባቢው አጠራር ሎኮ የሚሰኘው (ሽፈራው) ዛፍና ቦዬ ከምግብነት ባሻገር ለመድሀኒትነት እንደሚጠቅሙ ይነገራል። ምንም ያህል የኑሮ ውድነት ቢኖርና ገቢ ቢጠፋ አርባ ምንጭ ላይ ጦም አይታደርም። በከተማዋ ተወልደው ያደጉት ነዋሪዎቿ እንደሚናገሩላት በተፈጥሮ የተቸረቻቸውን አትክልትና ፍራፍሬዎች እንዲሁም አሣ እየበሉ ብቻ መኖር ይቻላል።
መሬቱ የሰጡትን ብቻ ሳይሆን ያልሰጡትንም ያፈራል። የኢኮኖሚ አቅሟ ጠንካራ፤ ተወላጆቿ ተቻችሎ የመኖር ተምሳሌቶችና ፍቅሮች፣ ፈጣሪን የሚፈሩ ናቸው። ወጣቶቿ ለአረጋውያን ታዛዥ፣ክብር የሚሰጡና ባህላቸውን የሚያከብሩ ናቸው። በዛ ላይ በሸማ ጥበብ የረቀቁ ጠንካራ ሰራተኞችም መሆናቸው መላው ኢትዮጵያዊ ያውቃቸዋል ። በብዙ ፀጋዋ ማደግ የምትችል ለነዋሪዎቿ ምቹ ብትሆንም ከተቆረቆረችበት ዘመን አንጻር ግን አሁንም እድገቷ ተፈጥሮ እንደቸረቻት የተሟላ አይደለም። ሆኖም በአንዳንድ የከተማዋ አካባቢዎች ብዙ መሻሻሎችና ለውጦች መኖራቸው ግን አይካድም ከሚሉት መካከል ወይዘሮ ሰርተሽኩሪ አስናቀ አንዷ ናቸው።
ወይዘሮ ሰርተሽኩሪ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ ይኑሩ እንጂ ተወልደው ያደጉት በአርባምንጭ ከተማ ነው። የአርባ ምንጭ መጠሪያ የሆኑትን ምንጮች ደጋግመው በመቁጠር ልጅነታቸውን አሳልፈዋል። ጣፋጩ የአሣ ቁርጥና ጥብስ ከህሊናቸው የሚጠፋ አይደለም።
የአካባቢውን ለምነት ሲገልጹም‹‹መሬቱ ለም ከመሆኑ የተነሳ ሙዝ ሳይተከል በየግቢው ይበቅላል:: አፕል፣ ሎሚ፣ አቡካዶም እንዲሁ በቅሎ ይታያል።›› ሲሉ ያደንቃሉ። ከተማዋ በባህላዊ ምግብ ትታወቃለች። በውጪ ዜጎች ጭምር የሚወደድ ከበቆሎና ቦሎቄ ተዘጋጅቶ በዘይት ተጠብሶ በጎመን የሚሰራው ፖሰሴ ይጠቀሳል። በበቆሎ፣ ድንች ከሚመስለውና ውስጡ እንደ ወተት ከነጣው ቦዬና ከአሣ የሚሰራ ጣፋጭ ባህላዊ ምግብም አለ። የአካባቢው ነዋሪዎች ሎኮ የሚሉትና ሽፈራው የተሰኘው ዛፍ ቅጠል የአርባ ምንጭ ሴቶች በሽንኩርትና በዘይት ከሽነው ሲሰሩት ልዩ ጣዕም አለው።
ከጠጅ ሣር የሚሰራውን ጭማቂ (ጁስ)ና ቦርዴን ጨምሮ ሌሎች መጠጦችም የአርባ ምንጭ መገለጫ ናቸው ። የአርባ ምንጭ ሙዝ እና አሣ፣ የአዞ እርባታ ማዕከል፣ ሀይቆቹና የከተማዋ መልክዓ ምድር ከቱሪስት መስህብነታቸው ባሻገር የገቢ ምንጭ ናቸው። ሴቻና ሲቀላ በሚል በሁለት የተከፈለ ነው ከተማው። ሲቀላ አካባቢ የሚገኙት ቤቶች ዛሬም እንደ ፊቱ ከጭቃ እንደተገነቡ፣ እንደፈራረሱና በእርጅና እንደ ተጎሳቆሉ ይገኛሉ። የአብዛኞቹ የቀርከሀ አጥሮች አሁንም አልተለወጡም። በከተማው ልማት እንደሚጠበቀው አልተሰራም።
በዚሁ ከተማ ተወልደው ያደጉት ወይዘሮ ቢሆኖ ቦልጫም ከላይ የተጠቀሱትን ሀሳቦች ይጋሩታል። የጎረቤቶቻቸውን ያረጀ መኖሪያ ቤትም ለማሳያነት ይጠቅሳሉ። የሥራ ቦታቸው ጭምር የሆነ ቤታቸውን እራሳቸው ማስዋባቸውንም ይናገራሉ። ዕድሜቸው 80ውን ቢያልፍም ገጽታቸው ከስድሳ የዘለሉ የማያስመስላቸው ወይዘሮዋ የሚተዳደሩት ባህላዊ ምግብና መጠጦች እንዲሁም አልባሳትን በማዘጋጀትና በመሸጥ ነው። ዛሬም ጉልበታቸው እንዳይነጥፍ ያደረገው የአመጋገብ ባህላቸውና የከተማዋ ምቹ የአየር ፀባይ መሆኑን ሳይጠቅሱ አላለፉም። አሣ መረቅ፣ በአሣ ጥብስና በአሣ ቁርጥ ይነግዳሉ ። የጀበና ቡናም አላቸው። አብዛኞቹ ደንበኞቻቸው ቱሪስቶች ናቸው። በእነሱ ዘንድ ሁሉም ባህላዊ ምግቦች ተወዳጅ እንደሆኑና በተለይ ጥሬው የአሣ ቁርጥ መድሃኒት ነው በሚል ጭምር እንደሚፈለግ ይናገራሉ። ከኮቪድ 19 በኋላም ቢሆን ጥሬው አሣ መመገብ የሚፈልግ ቢኖርም ጥሬውን መሸጥ በከተማው ማዘጋጃ ቤት በመከልከሉ እንደማያቀርቡ አጫውተውናል።
ሌላዋ ወጣት የብቻዬ መካሻ ደግሞ ሴቻ ከበፊቱ በተሻለ መልማቷን ትናገራለች። የተለያዩ ህንፃዎችና መንገዶች ባለቤት ሆናለች። የማህበረሰቡ አኗኗርም ዘምኗል። ከተማዋ የመብራት ተጠቃሚ በመሆኗ እናቶች እንደ ፊቱ እንጀራና ዳቦ ለመጋገር በእንጨት አይጨናበሱም። በኤሌክትሪክ ምጣድና ምድጃ ያበስላሉ። በተለይ በመንግስት የሚሰጡ ማናቸውም አገልግሎቶች ፈጣንና ቀልጣፋ ሆነዋል። ቀድሞ ብዙ የሚያመላልሰው መታወቂያና የልደት ሰርተፊኬት የሚወጣው በአምስት ደቂቃ ውስጥ ሆኗል። ከተማዋ በቅርቡ የዲጂታል ፖርታል ቴክኖሎጂ ከተላለፈላት ጀምሮ ማናቸውንም የከተማዋን መረጃዎች ማግኘት ቀሏል። የቱሪስት መዳረሻ እንደመሆኗ በተለይም ቴክኖሎጂው መረጃን ለቱሪስት ተደራሽ በማድረግ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ስለመሆኑ ትገምታለች።
መምህር አስናቀ ብዙነህ ከዕድሜያቸው ግማሹን በከተማዋ አስተምረዋል። በከተማዋ ከመንገድ መብራት ጀምሮ እጅግ የሚበረታታ ለውጥ እየታየ መሆኑን ይገልፃሉ። እንደሚያስታውሱት ሲቀላ ላይ ለረጅም ጊዜ የሚያውቋቸው ቱሪስት ሆቴልና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብቻ ነበሩ። ብቸኛው ባንክ ረጅም መንገድ ተጉዘው ከሲቻ በመጡ ተገልጋዮች መጨናነቁንና ትንፋሽ ማሳጣቱንም አይዘነጉትም። አሁን ከተማዋ ውስጥ በርካታ የግል ባንኮችም አሉ። የጋራ መኖሪያ ቤት፤ ለውጪና ለሀገር ውስጥ ቱሪስት የሚመጥኑ ሆቴሎች ተገንብተዋል። በሲቻና በሲቀላ መካከል ያለው ኃይሌ ሪዞርትና ፓራዳይስ ሎጂን ለማሳያነት ይጠቅሳሉ።
በመምህርነት በቆዩበት ወቅት እንደተገነዘቡት የቱሪስት መዳረሻ ከመሆኗ ጋር ተያይዞ ታዳጊና ወጣቶች ፈጥነው ትምህርት ይቀበላሉ። በተለይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ጎበዞች ናቸው። የተማረው ማህበረሰብ ትምህርታቸው ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ መፈለጉ እንደተጠበቀ ሆኖ የማስተርጎም የገቢ ማግኛ ምንጭ የሚያደርጉት ገና ትምህርት ቤት ሆነው ነው። ከትምህርታቸው ጎን ለጎን ፍራፍሬዎችን ለገበያ በማቅረብ ከመሳተፋቸው ጋር ተዳምሮ ፈጥነው ከወላጆቻቸው ጥገኝነት በመላቀቅ ራሳቸውን ችለው ለከተማዋ ኢኮኖሚ ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉና በትምህርታቸው እስከ ከፍተኛ ደረጃ እንዲደርሱ ያግዛቸዋል።
በስነምግባር በኩልም ስብዕናቸው የተወደደ ነው። አረጋውያንን በማክበር፣ ምክር በመስማት፣ በመታዘዝና በመታገስ ይታወቃሉ። በከፋ ግጭት በገቡበት ወቅት ሣር ይዞ ለለመናቸው ሽማግሌ ይንበረከካሉ። ልመናውን ተቀብለው ቁጣቸው ፈጥኖ ይበርዳል። ከበቀልም ይመለሳሉ። ለዚህ በቡራዩ ግጭት በከተማዋ የተፈፀመው እርቅ ማሳያ ነው። ይሄን የሕዝቡን ተቻችሎ መኖርና የከተማዋን ሰላማዊ ቀጣናነት የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ መንግስቱ ማላም ይመሰክራሉ። ከተማዋ ላይ የተገኘውን ተካፍሎ ከመብላት ልምድ ባሻገር ከየትም ይምጣ ከየት ማነህ ተብሎ አይጠየቅም።
በመሰረተ ልማቱም የጎለበተ አቅም አላት። በቅርቡም ከ149ሚሊየን ብር በላይ ወጪ 31 የጌጠኛ ምንጣፍ ድንጋይ፣ 12 የቦይ ፣ አራት መለስተኛ ድልድይ፣ አንድ የውሀ መስመር ዝርጋታ፣ 55 የፕሮጀክቶች ግንባታ ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ሆኗል። በአጠቃላይ አሁን ላይ የከተማዋ አስፋልት መንገድ ሽፋን 64 ሺ 522 ኪሎ ሜትር፣ ኮብል መንገድ ሽፋን 99 ነጥብ 75፣ መብራት አገልግሎት 24 ሰዓት፣ ውሃ አገልግሎት 90 በመቶ፣ የውስጥ ለውስጥ አስፋልት ዘጠኝ ኪሎ ሜትር ደርሷል።
‹‹በአጠቃላይ ከተማችን በማያቋርጥ ለውጥና መሻሻል ላይ ነች›› ያሉት የአርባ ምንጭ ከንቲባ አቶ ሰብስቤ ምናቤ ፤ ከተማዋ በብዙ ነገር ትታወቃለች:: ሀይቆቿ አንድ መታወቂያዋ ሲሆኑ፣ የአሣ ሀብቱን ጨምሮ አፕልና ሙዝ መለያ ናቸው። በ20 ሜትር ርቀት የሚገኘውና “የእግዜርድልድይ” የሚባለው ብቻ የተለያዩ ቀለምና ይዘት ያላቸው አባያና ጫሞ ሀይቆች ተገናኝተው ፀብ እንዳይፈጥሩ ረጅም ከፍታ ላይ ለግልግል የቆመ የሚመስል ትልቅ መስህብ ነው።
ፓራዳይዝ ሎጂና ኃይሌ ሪዞርት ከፍታ ላይ በመሆን ስትታይ አረንጓዴ ሰልፈኛ ወታደር መስሎ ቀጥ ብሎ በቆመ ዛፍ ጥቅጥቅ ደን የተከበበች እጅግ ውብ ከተማ ነች። ምንጮቿ የከተማውን ነዋሪ የመጠጥ ውሀ አቅርቦት ሸፍነዋል። ውሃው ንፁህና ለጤና ተስማሚ በመሆኑ በሀገር ውስጥና በዓለም መስፈርት ተረጋግጧል። ከተማዋ ያሏት መስህቦች ጥምር መሆናቸው ከሌሎች ከተሞች ይለያታል። ለምሳሌ፦ ሐይቅ ያላቸው ከተሞች አሉ። ሀይቅ ሳይኖራቸው ምንጭ ያላቸው ከተሞች አሉ። ሁለቱም ሳይኖራቸው ጥሩ አቀማመጥ ያላቸው ከተሞች ይኖራሉ። ወይም ደግሞ እጅግ ውብና ማራኪ ህንፃዎች ብቻ ያሏቸው ከተሞች ሊኖሩ ይችላሉ።
‹‹አርባ ምንጭ ከተማ ግን በተፈጥሮ ሁሉንም ያሟላች ከተማ ነች›› ሲሉም ያሞካሿታል። እንደ ከንቲባው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታዋም ከፍተኛ ነው። ሀይቆቿ ከቱሪስት መስህብነታቸው በተጨማሪ ለጀልባ አገልግሎት ይውላሉ። ከፍተኛ መጠን ያለው የአሣ ክምችት ባለቤት ናት። የተለያዩ አእዋፋት፣ ጉማሬዎች፣ በእርዝማኔው በዓለም ሁለተኛ የሚባለው አዞ በራሱ በሀገር ብቸኛው ከሆነው የእርባታ ማዕከሉ ጋር ከፍተኛ ገቢ ያስገኛል። ይሄን ለመጎብኘት ከሚመጡ የውጪና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎች የሚገኝ ገቢ አለ። ጎብኚዎቹ ከተማዋ ላይ ውለው፣ አድረው፣ ሰንብተውና ተመግበው፣ ጠጥተውና፣ ተዝናንተው ወደ መጡበት ይመለሳሉ።
ይህም ለነዋሪው ከሚፈጥረው የሥራ ዕድል ባሻገር ለከተማዋ ዕድገት አስተዋጽኦ አለው። በኢትዮጵያ ፈጥነው እያደጉና እየሰፉ፤ የሕዝብ ክምችት እየተፈጠረባቸው ካሉት ከተሞች መካከል እንድትመደብ አስችሏል። ከዛሬ አራት ዓመት በፊት የነበረው መዋቅራዊ ፕላኗ ከተማዋ ያረፈችው በ5 ሺ 557 ሄክታር እንደነበር ይጠቅሳል። የዛሬ 10 ዓመት የነበራት የሕዝብ ብዛት 189 ሺ ነበር። የነዋሪው ቁጥር 300 ሺ እንደሚደርስ አንድ ጥናት ጠቁሟል።
ይዞታዋም ከ13 ሺ ሄክታር በላይ እንደሚሰፋ ይጠቅሳል። ይሄ ስፋቷና ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥሯ ካሏት የተፈጥሮ ሀብቶች ጋር ተዳምሮ ደረጃዋ በቀድሞ ፈርጅ አንድ ቢሆንም በቅርቡ ሪጅኦ ፖሊታን ከተማ ያደርጋታል ብለው ያስባሉ። የከተማዋ የገቢ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል። በዚህም ከራሷ አልፋ ለፌዴራል መንግስት ገቢ ታስገባለች። በቅርቡ ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ለከተማዋ የተላለፈው የመረጃ ቋት ከቱሪስት የሚገኘውን ገቢ በማሳለጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 1/2013