ድንገት ሰዎች በተሰበሰቡበት አካባቢ ይደርስና “ቁም” ይላል፤ ሴት ከሆነች ደግሞ “ቁሚ”:: ለመጀመሪያ ጊዜ ድርጊቱን የታዘበ ሰው ደንግጦ ምላሽ ይሰጣል:: አካባቢዎችን እየቀያየረ ይህንኑ መልእክቱን ያቀርባል:: ግለሰቡን የሚያውቁ ሰዎች “አውቆ አበድ” ይሉታል:: አውቆ ያበደ ሰው ለማለት ነው:: የቀድሞ ስራውን አቁሞ አሁን የሚተዳደረው በልመና ነው:: ቁም ብሎ አስቁሞ መልእክቱን አቅርቦ የሚለምን ለየት ያለ የልምና መንገድን የሚከተል ሰው:: አውቆ አበዱን ግለሰብ ለመምከር የሞከሩ ሰዎች “ኧረ ተመከር እንዲህ አይነት ልመና የለም” ይሉታል:: ለእርሱ ልመና ሥራ ብቻም አይደለም፤ የውስጥን ጥሪ የማዳመጫ መንገድ ነው::
ቀድሞ የሚያውቁትን ጎደኞቹን ሲያገኛቸው የተለመደውን ጥያቄ ያቀርብላቸዋል። “ዛሬም ህዝቡ እየዋሸ ሲኖር አይታችሁ እንዳለየ ሆናችሁ ትኖራላችሁ አይደል?” በማለት:: የእነርሱ የተለመደ ምላሽ ደግሞ “አውቆ አበድ አሁንም ይህ ፍልስፍናህ አልተወህም?” አይደል የሚል ነው:: ከጓደኞቹ ጋር የሚተዋወቁት የመቃብር ጉድጓድ በመቆፈር ስራቸው ነው:: ዘወትር ከእርሱ ጋር የሚገጥማቸው ከሥራ ጋር የተገናኘ ቅይማት እርሱን ወደ አደባባይ አውጥቶታል:: እነርሱ ግን ስራቸውን ቀጥለው አሁንም ኑሯቸውን በስራቸው ይመራሉ::
የቅይማቱ ምክንያቶች በዋናነት ሁለት ናቸው፤ ከቀብር ጋር የተገናኘ ምክንያት:: የመጀመሪያው አውቆ አበድን የሚያበሳጨው ጉዳይ አብሬ ካልተቀበርኩ ብለው የሚያስቸግሩ ሰዎች ናቸው:: ሁለተኛው ደግሞ በሟቹ መቃብር ላይ ቤተሰብ “ሩጫዬን ጨርሻለሁ” ሃውልት ላይ የሚጽፈው ጥቅስ ነው::
“ምን እያላችሁ ነው በስንት ድካም ለአንድ ሰው መቀበሪያ የተዘጋጀ ጉድጓድ ውስጥ እኔም አብሬ ካልተቀበርኩ ብሎ ማስቸገር ምን የሚሉት ነው?” ይላል:: ከምሩም ጉዳዩን አስቦበት ያዝናል:: አስመሳይነት የበዛበት ህይወት ብሎ ያስባል:: ሟች ተቀብሮ የሚቀመጠው ማስታወሻ ላይ ደግሞ “ሩዬጫን ጨርሻለሁ” እና ሌሎችም መሰል መልእክቶች ሲቀመጡ እንዲሁ ይሞገታል:: “እውነት ማን ነው ሩጫውን በቅጡ ጨርሶ የሞተ? ሁላችንም ከአንድ ስራ ወደ ሌላ ከሆነ ጭንቀት ወደ ሌላ እየተፈራረቅን የምንኖር፣ ሞትን ከዙሪያችን አርቀን የምንመላለስ እንጂ ሩጫን ጨረስን ብለን ተዘጋጅተን እንሞታለን? ጳውሎስ ሞቱን አስቀድሞ አውቆ ለእዚያም ተዘጋጅቶ የጻፈውን ደብዳቤ የእኛ አድርገን ራሳችንን መደለሉ ምን የሚሉት ነው?” ይላል አውቆ አበድ::
አውቆ አበድ የሚረዳው ቢያጣ “በመቃብር ሰፈር እየኖርኩ ምን ጨጓራዬን አቃጠለኝ፣ ይህን ህዝብ ቁም እያልኩ እያስተማርኩ፤ ላስተማርኩበትም ክፍያ እየለመንኩ አልኖርም?” ብሎ ወደ ልመና ተሰማራ:: በአጭሩ የአውቆ አበድ ስራው የመንገድ ላይ አስተማሪ፤ ስፖንሰር የሚያደርገው ደግሞ የሚለምነው ህዝብ ብለን ልንገልጸው እንችላለን:: በጓደኞቹ ዘንድ አውቆ አበድ፤ ለእርሱ ደግሞ የሚሰማውን የሚኖር ሰው:: ቁም! ቁሚ!
በዛሬው ጽሁፍ በህይወት ውስጥ ጥቅም ስላለው “መቆም” እንመለከታለን::
የሚቆመው ጉዞ ላይ ያለነው
የተገነዘን፣ የሞተን ሬሳ ቁም ብትለው አይሰማህም:: በጠና ህመም በድጋፍ ያለን ሰው ቁም ብትለው እንዲሁ ሊቸገር ይችላል:: እንደ ትእዛዝ “ቁም!” የምትለው በጉዞ ላይ ያለን ሰው ነው:: ዛሬ ይህን አንብቦ መረዳት የሚችል ሰው ሁሉ ቁም የተሰኘው መልእክት ሊደርሰው ይገባል ብሎ ጸሃፊው ያምናል፤ ራሱን በህይወት እንዳለ ስለሚያውቅ::
በህይወት መኖራችን ውስጥ ብቻ ተስፋ አለ:: ዙሪያችን የቱንም ያህል በጨለማ የተሞላ ቢመስል በመቆም ውስጥ መውጫ መንገድ እንዳለ መመልከት እንችላለን:: የመቆምን አስፈላጊነት ከመመልከታችን በፊት በጉዞ ላይ በመሆናችን ውስጥ እያገኘነው ያለነውን ማወቅ እውቅና መስጠት ይገባል::
ለውጥን መፈለግ አንድ ነገር ሆኖ የምንፈልገው ላይ ለመድረስ ዛሬ ለቆምንበት እውቅና መስጠት ሌላ ጉዳይ ነው:: የሚቆመው ጉዞ ላይ ያለነው በምንልበት ጊዜ፤ ዛሬ እየሆነ ላለው ነገር ስፍራን ቦታን መስጠት ይገባል እያልን ነው:: ዛሬ ላይ የካፍቴሪያ አስተናጋጅ የሆነች ወጣት መዳረሻዋ እዚያው ካፍቴሪያ ነው ማለት አንችልም:: ነገን አሻግራ ስታይ የራሷ ካፍቴሪያ እያየች ይሆናል:: ነገን አሻግራ የተመለከተቸው እውን ይሆን ዘንድ ራእይ አንድ ነገር ሆኖ ሳለ ከዛሬ የምትማረው ሌላ ነገር ነው:: ዛሬ እያደረግነው ላለነው ጉዞ ቦታን ሳንሰጥ የተሻለው መሰላል ላይመጣ ይችላልና::
በማህበረሰባችን ውስጥ ያልንን የማጣጣል አባዜ በሰፊው የተንሰራፋ ይመስላል:: ሻይ ቡና ለማለት በተሰባሰብን ቁጥር የሰዎች ድካም፤ ጥረትን ማጣጣል፤ ጨለምተኝነትን መመልከት ወዘተ ላይ ካተኮርን ለውጥ ማድረግ አስቸጋሪ ይሆናል:: ለውጥ የአመለካከት ውጤት መሆኑን መዘንጋት አይገባም:: አመለካከት ደግሞ ነገሮችን የምናይበት መንገድ:: ዛሬያችንን የምናይበት መንገድ በተጣመመ ልክ ነጋችንን በአግባቡ ልናይ አንችልም::
ለዛሬ እውቅና በመስጠት፤ ዛሬን በማጣጣም መራመድ አስፈላጊ ነው:: የምስራቁ የኢትዮጵያ አካባቢ በተለይም የድሬድዋ አካባቢ ሰዎች ነገሮችን ቀለል አድርጎ የመመልከትና ለመጨናነቅ ቦታን ሳይሰጡት እናያለን:: አስተዳደግ ነገሮችን የምናይበትን መንገድ እንደሚወስን ከእነርሱ እንማራለን:: ዛሬ በሚያጨናንቁ ነገሮችም ሳይሆን ከመጨናነቅ መፍትሄን መፈለግ ላይ ማተኮረን ከድሬዎች መማር እንችላለን:: በመቀጠል ለመቆም ቦታ ለመስጠት የመቆምን አስፈላጊነት እንመልከት::
የመቆም አስፈላጊነቱ
መቆምን ማን ይፈልጋል? ማንም:: ሁላችንም እንድንቆም የሚያስገድደን ነገር ባይገጥመን እንወዳለን:: ሾፌር መኪናው ተበላሽቶበት ሲቆም ደስ ሊለው አይችልም:: ትራፊክ አስቁሞ የሚወስድብን ጊዜም ሳትቀር ስሜታችንን ትረብሻለች:: በአጭሩ ማንም መቆምን አይፈልግም፤ ከህይወት በስተቀር::
የህይወት ጉዞ ግን ማቆምን የግድ የሚልበት ፌርማታ አለ:: ህይወት አስገድዳ ማቆምን ታለማምደናለች:: የመጨረሻው መቆም ከእዚህ ቀደም ስሜቱ ምን ይሁን ምን ከማናውቀው ሞት ጋር ማገናኘት ነው::
ይህ መጣጥፍ የሚመለከተው “ቁም” ግን ተገደን ስለምንገባበት ሳይሆን ወደን በመደበኛነት ልናደርግ ስለሚገባው፤ ራስን በራስ አስገድዶ ስለማቆምና ውስጠ ፍተሻ ስለማድረግ ነው:: “ውስጠ-ፍተሻ” የሚለውን ቃል በተለየ ቦታ ላይ አስቀምጠን፤ አንድንስራ ለመስራት ስንነሳ ልናሟላ ስለሚገቡን መስፈርቶች እያሰብን እንቀጥል::
ንግድ ፈቃድ እንዲሁ ያለምንም መስፈርት ማውጣት አንችልም፤ የሆነ ኮሌጅ ዝም ብለን ገብተን ተማሪ ልንሆን አንችልም፤ መስፈርቶች ስላሉ:: በአንድ ተቋም ውስጥ መስራት ስለፈለግን ብቻ ዘው ብለን ገብተን ሰራተኛ ሆኛለሁ ብለን አናውጅም። ውስጠ-ፍተሻም እንዲሁም የራስን የውስጥ ጤንነትን በመስፈርቶች በመመልከት ለቀጣይ ህይወት ራስን የማጠንከር ግብዓት ነው:: በመቆም ውስጥ ሲሆን ደግሞ የበለጠ ውጤታማ የሚያደርግ:: ሦስት ነጥቦችን እናንሳ::
1. እውነታን መረዳትና መስማት፡- ቀዳሚው የመቆም አስፈላጊነት እውነታን ለመረዳት እድል የሚሰጥ መሆኑ ነው:: በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን ውስጥ በተጨባጭ የሆንነው ነባራዊ እውነታ አለ:: እውነታን መቀበልና ከእውነታው ጋር ራስን አስማምቶ መገኘት አትራፊነት ነው:: በግል ህይወታችን የምናደርገው ጥረታችን ወደ ውጤት እንዲቀየር ቆም ብለን ያለንበትን ሁኔታ ማየት መቻል አስፈላጊ ነው::
2. የእረፍት ህይወትን መለማመድ፡- ሌላው የመቆም አስፈላጊነት የእረፍት ህይወትን መለማመድ ነው:: ከሰኞ እስከ ቅዳሜ በስራ ወከባ ውስጥ የቆየ ሰው እሁድ ቀን የሚቆምበት ቀን ቢያደርገው የእረፍት ህይወትን በሳምንት አንዴ መኖር ቻለ ማለት ነው:: አቅማችንም ቢሆን የበለጠ ምርታማ የሚሆነው በመታደስ ውስጥ ስለሆነ:: በመቆም ውስጥ ያለንበትን እውነታ ለመመርመር እድል እንደምናገኘው ሁሉ በመቆም ውስጥ እረፍትን ማጣጣም እንችላለን:: ከሳምንት እስከ ሳምንት በሞባይላችን፣ በቲቪ፣ በኮምፒውተሮቻችን ወዘተ ላይ ሰፊ ጊዜ የምናጠፋ ከሆነ ከሳምንት አንዱን ቀን መርጠን በመቆም እረፍትን ለአካላችን እንዲሁም ለአዕምሮችን ማድረግ አለብን::
3. ስለነገ ከመጨነቅ ወጥቶ ማሰብ መቻል፡- ሦስተኛው የመቆም አስፈላጊነት ለነገ ለማሰብ ነው:: ነገ በእጃችን ያልገባ ቀን ነው:: ስለነገ መጨነቅ የለብንም:: ስለነገ መጨነቅ ባይገባንም ስለነገ ማሰብ ግን ተገቢ ነው:: ነገን እንዴት ባለ አካሄድ ልንቀበለው እንደሚገባ ማሰብ ተገቢነት የሚኖረው፤ በመቆም ውስጥ ስንመለከተው ነውና::
የመቆም ፈተናው
የመቆም ፈተና የሚመነጨው ለመቆም ካለን ግንዛቤ ነው:: መቆም ማለት ማቋረጥ አድርገን መረዳት የለብንም:: የጀመርነውን ነገር እስከመጨረሻው ይዞ ለመሄድ የሚደረገው ጥረት እርሱ የጽናት ውጤት ነውና ይበረታታል:: ተስፋ በመቁረጥ እጅ ለመስጠት መቸኮል አስፈላጊ አይደለም:: ጉዞን ማቆረጥ እና ጉዞን ማቆም ግን ፈጽሞውኑ ይለያያሉ:: በመንገድ ላይ የምናየው “ቁም” የሚለው የመንገድ ላይ ምልክት ቆመህ ቅር ማለት አይደለም::
የመቆም አስፈላጊነቱ ያለንበትን እውነታ ለመረዳት፣ እረፍት ለማድረግ፤ እንዲሁም ነገን አሻግረን ለመተለም እንዲውል ነው:: ስለ መቆም ካለው የግንዛቤ ፈተና መነሻነት የሚመነጩ ሌሎችም ፈተናዎች አሉ:: በመቆም ጊዜ የሚሆኑትን ፈተናዎችን መርምረን ልንፈታቸው ይገባል:: ስለ በአላት እናንሳ፤
በዓላት ሃይማኖታዊ፣ ሀገራዊና ፖለቲካዊ ይዘት አላቸው:: አከባበራቸውን ስንመለከት በጋራ በመሆን አብሮ በመብላት በመጠጣት፣ አብሮ ሰልፍ በመውጣት ወይንም የሆነን መርሃግብር አብሮ በማድረግ ውስጥ የሚገለፅ ነው::
እንደ ግለሰብ እያንዳንዱ ሰው ከማንም በላይ ለራሱ አሳቢ መሆን አለበት:: እንደ ግለሰብ በማህበረሰብ ውስጥ መኖር እንዳለ ሆኖ ራስን ግን በአግባቡ መርምሮ መምራት መቻል መኖርም አለበት:: አንዱ የመቆም ፈተና ይህ ነው፤ በራስ ከመቆም በብዙሃን ውስጥ መደበቅ:: ለዚህ ደግሞ ማህበራዊ ሚዲያው አንድ ራሱን የቻለ ጫካ ሆኖ እያገለገለ ይገኛልና ቆም ብሎ ማሰብን ይጠይቃል።
በሚጠጡ ሰዎች መካከል የተገኘ አንድ የማይጠጣ ሰው “አታስደብረን” ተብሎ ወደ ቡድኑ እንዲቀላቀል ግፊት ሊደረግበት ይችላል። ይህን ቆም ብሎ በማሰብ መቋቋም የእሱ ፋንታ ነውና ሊያደርገው ይገባል። ይህ በተለይም በአስገዳጅ ሁኔታዎች የተፈጠረ ማቆም የወለደው መቆም ስለሆነ ለውጣት ያበቃል::
አስገዳጅ ሁኔታዎች የሚፈጥሩት መቆም
“ለረጀም አመታት ተቀጥሬ እየሰራሁ የሰራተኛ ቅነሳ ሲደረግ ተሰናበትኩ:: በወቅቱ ሰማይ ምድር የተገለበጠብኝ መሰለኝ:: በመጨረሻ አዲሱን ህይወት ለመጋፈጥ ወሰንኩ። የራሴን ስራም ጀመርኩ:: ይኸው ዛሬ ሚሊዬነር ሆኛለሁ::” የሚሉ ሰዎች በዙሪያችን የለም?
በተወሰነ እርቀት ላይ በአስገዳጅ ሁኔታ በተፈጠረ መቆም ውስጥ የስኬትን በር ያገኙ ሰዎችን ታሪክ እናገኛለን:: ከውጤታማ ሰዎች ጀርባ ሄደን እናጥና::
ዛሬ በሀገራችን በጦርነት፣ ኮቪድን ተክትሎ በሚመጣ የንግድ መክሰር እንዲሁም ከስራ መፈናቀል እንዲሁም በሌሎች ምክንያቶች አስገዳጅነት መቆም የገጠማቸው ሰዎችን በዙሪያችን አሉ:: ለእነዚህ ሰዎች የምንሰጣቸው ተስፋ ምንድን ነው? የምናቀርብላቸው የማበረታቻ ቃልስ? አስገዳጅ ሁኔታዎቹ የሚያመጡልንን መቆም እንደበጎ እድል ለመውሰድ በማሰብ መንቀሳቀስን ጸሃፊው ያምናል::
ከአስገዳጅ መቆሞች መካከል ሥነ-ልቦናዊ ጠባሳቸው ከፍተኛ የሆኑ መቆሞች የሚፈጥሩት የመቆም ባህሪ አቅደን ከምናደርገው ይለያል:: ባለንበት ቦታ ቆመን መቅረት እና በመቆም ውስጥ ነገርን ኢላማ ውስጥ ማስገባት ይለያያሉ:: የምናየውና የምንሰማው ሳይሆን በእኛ ላይ እንደግለሰብም ሆነ እንደቤተሰብ የሚደርስብን ነገር ሥነ-ልቦናዊ አቅማችንን የመፈተን እድሉ ይለያያል:: ከፍተኛ ሥነ-ልቦናዊ ጠባሳ ጥሎ በሚያልፍ የህይወት አጋጣሚ ውስጥ ስንገኝ ምናልባትም ሞት መታደል ሆኖ ይሰማንም ይሆናል::
ህይወት በየአቅጫው በማይመቹ ዜናዎች የተሞላች ሆናለች:: ነገር ግን ዛሬም ታሳቢ ማድረግ የሚኖርብን በህይወት መኖራችን ተስፋ መኖሩን አመላካች ነውና፤ ተስፋን ከመቆም ውስጥ መፈለግን ነው::
የመነሻ ታሪካችን ላይ ያነሳነው ጓደኞቹ “አውቆ አበድ” ያሉት ግለሰብ በማህበረሰቡ ላይ ያለን ቅይማት ያሳያል:: ማህበረሰቡ ራሱን እያታለለ እንደሆነም ግለሰቡ ያምናል:: ከሚቀበር ሰው ጋር “አብሬ ካልተቀበርኩ” ማለት፤ ሟች ያልሆኑትን በሟች መቃብር ላይ መጻፍም አላሳመነውም:: ሁለቱንም ነጥቦች ለመውጫነት እንጠቀምና በሰንበት እንሰነባበት::
ስትቆም እምትወስነው
ቆሞ የሚነሳ ሰው ከሚወስናቸው ውሳኔዎች መካከል የመነሻ ታሪካችንን መነሻ በማድረግ ሁለት ነጥቦችን እንመልከት:: አውቆ አበድ የተባለው ሰው እያቀረበው ያለው መልእክት ‘ሰው ሲቀበር አብሬ ልቀበር አትብሉ፤ እርሱ ከእውነታ ጋር የተፋታ ህይወት ነው፤ የወደድነውን ብናጣም ህይወት ግን መቀጠል አለባት ብለን ልናምን ነው የሚገባን፤ ጉድጓድ የተቆፈረው ለአንድ ሰው ነው::’ የሚል ነው:: ለአንድ ሰው መቀበሪያ የሚሆን ጉድጉድ ቁፋሮ ተነጋግሮና ቀብድ ከፍሎ በቀብሩ ቅጽበት ጉድጓድ ውስጥ አብሬ ካልተቀበርኩ ማንን ወንጀለኛ ለማድረግና ደግሞስ ለምን ከእውነታ የተፋታ ህይወትን እንኖራለን የሚል ነው:: እውነታን ተቀብሎ ወደፊት ለመሄድ ራስን ዝግጁ ማድረግ እንደሚገባን ያስገነዝበናል:: ሁለተኛው ደግሞ በመቃብር ላይ የሚለጠፈውን እውነተኛ ስለማድረግ ነው:: ስለዓላማ ትምህርት የሚሰጡ አስተማሪዎች በመደበኛነት የሚጠይቁት ነገር አለ፤ “በእለተ ሞትህ ሰዎች በምን ቢያስታውሱህ ደስ ይልሃል?” የሚል ጥያቄ:: ሰው ሁሉ በአንድ ጉዳይ አንድን ሰው ማስታወስ ሊቸግረው ቢችልም ህይወታችንን ስንመራ በህይወታችን የመጨረሻ ቀን ላይ ሆነን የምንገኘውን እያሰቡ መራመድ የተሻለ ነው::
ዛሬ ቆም ብለን ራሳችንን ፈትነን ለነገ ትልም ዝግጅት አድርገን መራመድ እንዳለብን ግልጽ ግንዛቤን ይሰጠናል:: በአጠቃላይ በሆነ ፌርማታ ቆም ብሎ ለራስ እረፍት በመስጠት ያለውን ፋይዳ በሚገባ ከተረዳን እንዴት በመደበኛነት በህይወታችን ውስጥ እንተግብረው የሚለውን እንደመውጫ እናንሳ:: የሰንበትን መንገድ::
ሰንበትን ስንረዳ
በቀደምት አይሁድ እምነት ውስጥ ሰንበት ያለው ባህል እጅግ ጥብቅና ስር የሰደደ ነበር:: በሀገራችንም በተመሳሳይ ሁኔታ ለሰንበት የተሰጠው ከፍተኛ ስፍራ አለ:: ሰንበት የእብራይሰጥ ቀጥተኛ ትርጉሙ መቆም ማለት ነው:: በመደበኛነት ከምናደርገው እንቅስቃሴ መቆም:: በመቆም ደግሞ እረፍት ማድረግ፣ ከመደበኛ ስራችን ውጭ ሆነን እረፍት ማድረግ፣ ለራሳችን ተረጋግቶ ለነገ ማለም እንዲችል እድል መስጠት:: በሰንበት ቀን ምንም አይነት የስራ ከባቢ ውስጥ ላለመሆኑ የሰንበት ዝግጅቱ ቀድሞ ይደረጋል:: በሰባት አመት አንድ ጊዜ ደግሞ የሚታረሰው መሬትም ሰንበት እንዲሆንለት ይደረጋል::
ዛሬ ከስራ ባህሪያችን አንጻር ጊዜ እንደሌለን የምናስብ ሰዎች ከስራችን ጋር በተስማማ ሁኔታ ቆም የምንልበትን ቀን ሊኖረን ይገባል:: ቆሞ ከራስ ጋር መሆን፣ ቆሞ ከሌሎችም ጋር መሆን፣ አብሮ ማረፍ፣ ወደፊት አሻግሮ ማየት፣ ከስልክ፣ ከቴሌግራም፣ ከፌስቡክ ወዘተ እርቆ መቆም:: መቆም ከራስ ጋር ለመሆን፤ መቆም ከሌሎች ጋርም ለመሆን:: መቆም ውስጥ ያለውን ትርፍ እየተገበሩ የበለጠ መረዳት ይቻላል:: ለዛሬው በአጭሩ ቁም! ቁሚ! ተባብለን እንለያይ:: ሰላም::
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 1/2013