ራስጌ ያለው የቀጠሮ ደወል እሪታውን ሲያሰማ እጁን ከብርድ ልብስ ውስጥ የሞት ሞቱን አውጥቶ አጠፋው። ሿ… እያለ የሚወርደው ዝናብ የጠዋቱን ብርሀን አጨፍግጎታል። በእርግጥ እሁድ ነው። መክብብ አብዝቶ ቤቱ የሚውልበት ቀን። ዛሬ ብርቱ ጉዳይ ስለገጠመው ቅዝቃዜውን መቋቋም ያስችለኛል ያለውን ልብስ መርጦ ለበሰ። ወንድሙ ሳህሉ ያለበትን ክፍል ሲመለከት በሩ እንደተዘጋ ነው። ስለወንድሙ እያሰበ ከቤት ወጣ።
ከወንድሙ ሳህሉ ጋር አንድ ቤት ተከራይተው ነው የሚኖሩት። እሱ በአንድ የግል ባንክ ውስጥ በደህና ደመወዝ ተቀጥሮ የሚሰራ ሲሆን፣ ወንድሙ ሳህሉ ደግሞ በቅርቡ ከአንድ የግል ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አጠናቆ ስራ ከያዘ ገና 3ኛ ወሩ ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አጠናቆ ወደ መንግስት ዩኒቨርሲቲዎች መግቢያ ነጥብ ስላልሞላለት ክፍለ አገር ከሚኖሩ ቤተሰቦቹ ተነጥሎ አዲስ አበባ ከወንድሙ ጋር ሆኖ ነው የከፍተኛ ትምህርቱን ያጠናቀቀው። ሳህሉ በወንድሙ መክብብ ወጪ ነው የተማረው።
መክብብ ሰሞኑን የሳህሉ ባህሪ መቀየሩ አሳስቦታል። ለወትሮው በባህሪው ከሰዎች ጋር በቀላሉ መግባባት የሚችልና ህይወትን ማቅለል ልማዱ ሆኖ ሳለ ስለምን ከስራ መቅረትና ከሰዎች ተነጥሎ በቁዘማ እቤት መዋል አዘወተረ? ሊያወራው ሞክሮ “እንዲሁ ደብሮኝ ነው” ከማለት ውጪ የመለሰለት መልስ ባለመኖሩ ሁኔታው አሳስቦታል። መሳቅ መጫወት ማቆሙ ጭንቀት ፈጥሮበታል።
ደጋግሞ ሊያወራው ሞክሯል፤ ሳህሉ ግን ምንም ምላሽ አልሰጠውም። ምን ማድረግ እንዳለበት ብዙ አሰበ። ወትሮ ከሌላ በተለየ የሚቀርበውና ስለተለያዩ ጉዳዮች የሚያዋየው በተለይ ወሳኝ ጉዳዮች ላይ የሚያማክረው ወንድሙ ዛሬ ሁሉ ነገሩ ተቀይሮበታል። ይሄኔ ግራ የተጋባው መክብብ ስለ ወንድሙ ከጓደኞቹ መጠየቅ ፈልጎ ነው ደውሎ የሳህሉ ጓደኛ ደጀኔን የቀጠረው።
ስታዲየም ላሊበላ ሬስቶራንት ሲደርስ ቀድሞት የደረሰው የሳህሉ ጓደኛ ደጀኔ እጁን አነሳና ወደሱ እንዲቀርብ አመለከተው። የሚፈልጉትን አዘው ስለ ሳህሉ አወሩ። መክብብ ስለወንድሙ ሁናቴ መለወጥ ለጓደኛው ደጀኔ አዋየው፤ ምክንያቱን ያውቅ እንደሆን ጠየቀው። ደጀኔ የሚያውቀው ነገር እንዳለ ሲጠይቀው ትንሽ አቅማምቶ እውነቱን ነገረው።
“ሰሞኑን ከስራ መቅረት ሲያበዛ እኔም አናግሬው ነበር፤ ነገር ግን በቃ ብቻዬን መሆን ፈልጌ ነው” ነው የሚለው። ሳህሉ ከራሱ በላይ የሚወዳትና የሚያፈቅራት ልጅ አለች። ከእስዋ ጋር የሆነ ነገር ተፈጥሮ እንደሆነ ለማጣራት ሞከርኩ፤ ነገር ግን ምንም ሊነግረኝ አልፈለገም። እኔ የሚመስለኝ ከሷ ጋር ተጣልቶ አልያም አስቀይማው ይሆናል።” በማለት ጥርጣሬውን ገለፀለት። መክብብ በፍፁም የወንድሙ ጉዳይ ከፍቅር ጋር ይገናኛል ብሎ አላሰበም። መክብብ ለፍቅር ግንኙነት ገና አዲስና ከዚህ በፊት ምንም አይነት ግንኙነት እንዳለው አያውቅም ጠርጥሮ አያውቅም።
ወንድሙ ሳህሉ መክብብ እንዲያገባ ደጋግሞ ይጎተጉተዋል። የቤተሰቡ ምኞት ሁሉ መክብብ አግብቶ ማየት እንደሆነ ያዋየዋል። ነገር ግን አንድም ቀን ሳህሉ የፍቅር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው ጠርጥሮ አያውቅም።
ሁሌም አግባ እያለ ለሚጨቀጭቀው ታናሽ ወንድሙ ሳህሉ የፍቅር ግንኙነት መጀመሩን በቅርብ ነው ያሳወቀው። ከፍቅረኛው ጋር ከከተማ ወጥቶ ለ3 ቀናት መቆየት ነበረበትና የሚሄድበትን ለሳህሉ ሲነግረው ነበር በዚያውም የፍቅር ግንኙነት እንደ ጀመረና በቅርቡ አምላክ ከፈቀደ እንደሚያገባ የነገረው። በዚህ ሳህሉ እጅጉን ተደሰተ።
መክብብ ከፍቅር አጋሩ ጋር በደንብ ተግባብተው ስለጋብቻ ማውራት ቢጀምሩም ለሳህሉ ስለፍቅር ግንኙነቱ ቢነግረውም ከፍቅረኛው ጋር አላስተዋወቀውም። መክብብ ግን ሳህሉ የፍቅር ግንኙነት መጀመሩን አያውቅም ነበር። ለሚሰማው ወሬ አዲስ በመሆኑ ደጀኔን ደጋግሞ ጥያቄዎችን አበዛበት። “ማን ናት፣የት ነው የምትኖረው፣ ስምዋስ፤ ቆይ ከመቼ ጀምሮ ነው ግንኙነታቸው?” በማለት አከታትሎ ጠየቀው።
ደጀኔ የሚያውቀውን ነገረው።” አይ ግንኙነታቸው እንኳን ከሶስት ወር አይበልጥም፤ ልጅቷ እዚሁ አዲስ አበባ የኮሌጅ ተማሪ መሆንዋን ነው የነገረኝ። እኔ እንኳን አልተዋወኳትም። እሱ ስለ ልጅቷ ከነገረኝ ውጪ አላውቃትም።”በማለት አስረዳው። መክብብ ስለወንድሙ ይበልጥ አሰበ። ልጅቷን እንዴት አግኝቶ ሊያወራትና በመሀላቸው የተፈጠረውን በምን መንገድ ሊያውቅና ችግርም ካለ በውይይት ይፈቱት ዘንድ ለመምከር ፈልጓል ፤ ግን በምን መንገድ ፤ ምንም ሀሳብ አልመጣለትም።
የተጠቀሙበትን ሂሳብ ከፍሎ ደጀኔን ተሰናብቶ ከሬስቶራንቱ እየወጣ ስልኩን አንስቶ ደወለ። “ሄሎ ፍቅር እንዴት አደርሽልኝ።”ከወዲያኛው የስልክ ጫፍ ምላሽ የሰጠችው ሜላት ነበረች። የመክብብ ውድ ፍቅረኛ፤ የነገ ሚስቱ።“እንዴት ነህልኝ ማሬ፤ የት ሆነህ ነው ጫጫታው፤ በጠዋት ዛሬ እሁድ አይደል እንዴ፤በሰላም ነው” አለችው። “አዎ ሰላም ነው፤ አልተነሳሽም ፈልጌሽ ነው” ሲላት። “እኔ አላምንም፤ ዋው እቤትህ ልትጋብዘኝ ነው።” በቅርቡ ከወንድሜ ጋር አስተዋውቅሻለሁ ብሏት ስለነበር ለዚያ የፈለጋት ነበር የመሰላት።
የሚፈልጋት ለሌላ ጉዳይ መሆኑንና ከ1 ሰዓት በኋላ የሚገናኙበትን ካፌ ተነጋግረው ስልኩን ዘጋው። ሜላትን እስኪያገኛት በቀጥታ ያመራው ወደቤቱ ነበር። ቤት ሲደርስ ሳህሉ ልብሱን በአንድ ሻንጣ እያስገባ መንገደኛ ይመስል ሲሰናዳ አገኘው። ግራ ተጋባ ፤“ምንድነው? ምን እያደረክ ነው?” ሲለው ወደ ቤተሰብ ጋር ክፍለ ሀገር ሊሄድ እንደሆነ ነገረው። ለምንድነው ችግርህን የማትናገረው። በስንት መከራ የተማርከው ትምህርትና በአሳር ያገኘኸውን ስራስ ምን አድርገህ ነው ምትሄደው?” ሲል በንዴት ጦፎ ጠየቀው። ሳህሉ እንባ አንቆት ሳግ በተናነቀው ድምፀት ስራውን አልፈልግም፤ ቤተሰብ ጋ ሆኜ ሌላ ስራ እፈልጋለሁ፤እዚህ መስራትም መኖርም አልፈልግም ሲል መለሰለት።
ሳህሉ አንዴ ችክ ካለ እንደማይመለስና እልኸኛ መሆኑን መክብብ ያውቃል። የሚያደርገው ግራ ገባው። ለማስቆም አንድ ነገር አሰበና ስልኩን አውጥቶ መልዕክት ላከ። ሜላት ወደሱ ሰፈር እንድትመጣ ነበር የፃፈላት። ቤት ባትገባም ሰፈሩን በምልክት ነግሯታል፤ታውቀዋለች።
መልዕክቱን ልኮ ቀና ብሎ። “በቅርቡ ላገባ እንደሆነ ነግሬህ ነበር አይደል፤ አሁን ፍቅረኛዬ ሜላት ወደዚህ ትመጣለች። የግድ ልሂድ ካልክ ቢያንስ ተዋውቀሀት ትሄዳለህ።” ሲለው፣ ሳህሉ ይበልጥ ፊቱ ተለዋውጦ መቻኮል ሲጀምር መክብብ ግራ መጋባቱ ጨመረ። የወንድሙ የሁልጊዜ ጉትጎታ አግባ የሚል ስለሆነ እሱ ሲያሳውቀው ይረጋጋል፤ በዚያም ረጋ ብሎ በጉዳዩ ላይ ያወራኛል በሚል ነበር ይህን ያደረገው።
ሳህሉ እቃውን ሰብስቦ ጫማውን ማጥለቅ ሲጀምር መክብብ ፈጥኖ ወጥቶ የውጪውን በር ቆለፈና ሜላትን ይጠባበቅ ጀመር። ምን አልባት ሜላት ለምናው ማስቆም ከቻለች ብሎ። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሜላት ደርሳ መክብብ አጠቃላይ ሁኔታውን አስረዳት። ሜላት ምን አልባት እሺ ካላት ረጋ ብላ እንድታናግረው ነገሯት በሩን ከፍተው ተያይዘው ገቡ። ሻንጣውን ይዞ በረንዳ ላይ ቆሞ ተመለከቱት። ሜላት እጅጉን ደንግጣ ወደ ኋላ አፈገፈገች። ሳህሉ በረንዳው ላይ ቆሞ አይኑ ያነባል። መክብብ ግራ በመጋባት ስሜት እያፈራረቀ ያያቸዋል።
ሜላት ግቢውን ከፍታ ወጥታ ሮጠች፤ መክብብ ተከትሎ ሊያስቆማት አልቻለም። ምን ሆና ይሆን ብሎ ግራ ተጋባ። ሳህሉ በእንባ ተሞልቶ ሜላት የእሱም ፍቅረኛ እንደሆነችና ስልክዋ ላይ ከሳምንት በፊት ከወንድሙ ጋር ሆና የተነሳችውን ፎቶ አይቶ የወንድሙም ፍቅረኛና ሊያገባት ያሰባት ሴት መሆንዋን ማወቁ ሜላት ሁለቱ ወንድማማቾች መሆናቸውን ሳታውቅ አፍቃሪ መስላ እንደተጫወተችባቸው በእንባ ተሞልቶ ስቅስቅ ብሎ እያለቀሰ አረዳው። መክብብ በሰማው ነገር ሰማይ ምድሩ ተደበላለቀበት። ተፈፀመ::
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/2013