አሜሪካ የታሪፍ ስምምነቱን “በከፍተኛ ሁኔታ ጥሳለች” ስትል ቻይና ከሰሰች

ቻይና አሜሪካ የገባችውን የንግድ ስምምነት “በአደገኛ ሁኔታ መጣሷን” አስታውቃ ጥቅሞቿን ለመከላከል ጠንካራ ርምጃዎችን እንደምትወስድ አስታወቀች። የቻይና ንግድ ሚኒስቴር እንዳለው ዋሺንግተን ባለፈው ወር በጄኔቫ ሁለቱም ሀገራት ወደ ሀገራቸው በሚያስገቧቸው ምርቶች ላይ የጣሉትን ታሪፍ ዝቅ ለማድረግ ከስምምነት ቢደርሱም፤ አሜሪካ ግን ይህንን ስምምነት “በአደገኛ ሁኔታ ዝቅ የሚያደርግ” ርምጃዎች መውሰዷን አስታውቋል።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አክለውም የአሜሪካ ርምጃዎች በጥር ወር በቻይና መሪ ዢ ጂንፒንግ እና በፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ መካከል በተደረገ የስልክ ውይይት ወቅት የተደረሰውን ስምምነት በእጅጉ ጥሷል ብለዋል። የቻይና መንግሥት አቋም የተሰማው ባለፈው አርብ ትራምፕ ቻይና “ከእኛ ጋር የገባችውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ ጥሳለች” ሲሉ ከተናገሩ በኋላ ነው።

በወቅቱ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዝርዝር መረጃን ያልሰጡ ቢሆንም የንግድ ተወካይ ጄሚሰን ግሬር እንደተናገሩት ግን ቻይና በስምምነቱ መሠረት ከታሪፍ ውጪ የሆኑትን ተግዳሮቶች እያነሳች እንዳልሆነ ተናግረዋል። በግንቦት ወር በጄኔቫ በተካሄደው ስብሰባ ላይ በተካሄደው የንግድ ስምምነት አሜሪካ ከቻይና የሚመጡ ሸቀጦች ላይ የጣለችውን ቀረጥ ከ145 በመቶ ወደ 30 በመቶ ዝቅ አድርጋለች።

ቻይና በበኩሏ በአሜሪካ ምርቶች ላይ የጣለችውን ታሪፍ ከ125 በመቶ ወደ 10 በመቶ አውርዳለች። ሰኞ ዕለት ቤይጂንግ አሜሪካ በስምምነቱ ላይ የጣሰችውን ስትዘረዝር የኮምፒዩተር ቺፕ ዲዛይን ሶፍትዌር ለቻይና ኩባንያዎች መሸጥ ማቆም፣ በቻይናው ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያ ሁዋዌ የተሠሩ ቺፖችን በሀገሯ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ማስጠንቀቅ እና የቻይናውያን ተማሪዎች ቪዛ መሰረዝን ያጠቃልላል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁለት ከፍተኛ የዋይት ሐውስ ባለሥልጣናት ትራምፕ እና ዢ በቅርቡ ሊነጋገሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል። የግምጃ ቤት ዋና ፀሐፊ ቤሴንት በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ለሲቢኤስ ኒውስ እንደተናገሩት የንግዱ ዝርዝር ሁኔታ ዢ እና ትራምፕ ከተነጋገሩ በኋላ “ይፈታል” ብለው፤ ነገር ግን ይህ ውይይት መቼ እንደሚሆን የሰጡት ማረጋገጫ የለም።

የብሔራዊ ኢኮኖሚ ካውንስል ዳይሬክተር ኬቨን ሃሴት ለኤቢሲ እንደተናገሩት ሁለቱ መሪዎች በዚህ ሳምንት ውይይት እንደሚያደርጉ እና “ለመነጋገር ፈቃደኛ ናቸው” ብለዋል።”ዋናው ነገር ሁኔታዎች እኛ በምንፈልገው መንገድ ካልሄዱ ዝግጁ መሆን አለብን” ሲሉ ሃሴት ስለሚጠበቀው ንግግር ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት ትራምፕ አሜሪካ በብረት እና በአሉሚኒየም ላይ የምትጥለውን ታሪፍ ከ25 በመቶ ወደ 50 በመቶ እንደምታሳድግ አስታውቋል። አርብ ዕለት በፒትስበርግ ፔንስልቬንያ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ትራምፕ እንደተናገሩት ርምጃው በቻይና ላይ ያለውን ጥገኝነት በመቀነስ የአካባቢውን የብረታ ብረት ኢንዱስትሪ እና ብሔራዊ አቅርቦትን ለማሳደግ ይረዳል ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።

አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2017 ዓ.ም

Recommended For You