
በናይጄሪያዋ ሞካዋ ከተማ የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተፈጠረ ከባድ ጎርፍ አደጋ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ200 በላይ መሆኑ ሲገለጽ ቢቆይም ቁጥር እስከ 700 እንደሚደርስ ተነግሯል። በሀገሪቱ ማዕከላዊ ናጀር ግዛት ውስጥ በደረሰው አደጋ እስካሁን 500 ሰዎች የደረሱበት አለመታወቁን ተከትሎ የአካባቢው ባለሥልጣን እንደተናገሩት በሕይወት የሚገኝ ሰው ከዚህ በኋላ አይኖርም በሚል እምነት የነፍስ አድን ጥረቱ ተቋርጧል።
ባለፉት 60 ዓመታት ሀገሪቱ ካጋጠማት የጎርፍ አደጋ ሁሉ የከፋው ነው የተባለው ይህ ጎርፍ ቲፊን ማዛ እንዲሁም አንጉዋን ሃኡሳዋ የተባሉ ከተሞች ላይ ከባድ ውድመት አድርሷል። በአካባቢው ተላላፊ በሽታ እንዳይዛመት ለማድረግ በጎርፉ የተቀበሩ ግለሰቦችን ቆፍሮ በማውጣት ተገቢው የቀብር ሥነ ሥርዓት ማከናወን በቅርቡ እንደሚጀመር የሞካዋ አካባቢ አስተዳዳሪ ሙሐመዱ አሊዩ ተናግረዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ዓይናቸው እያየ ቤታቸው እና ቤተሰቦቻቸው በጎርፍ ሲወሰዱ መመልከታቸውን ተናግረዋል። ባለቤቱ እና ጨቅላ ልጁ በጎርፍ የተወሰዱበት አዳሙ ዩሱፍ የተባለው ግለሰብ “ቤተሰቤን ጎርፍ ሲወስድ ምንም ማድረግ ሳልችል ቆሜ ተመልክቻለሁ። እኔም መዋኘት በመቻሌ ነው የተረፍኩት” ብሏል ።
ሳሊኡ ሱሌይማን የተባለ ሌላ ግለሰብ ጎርፉ ቤት አልባ እንዳደረገው ገልጾ፤ ከንግድ ያገኘው ገንዘብ እና ንብረት አብሮ መወሰዱን ተናግሯል። “በጎርፉ የተነሳ 1500 ዶላር የሚያወጣ ንብረት ወድሞብኛል። ቀደም ብሎ ከሸጥኩት የግብርና ምርት ያገኘሁት ነበር። ከተቀመጠበት ቀጣይ ክፍል ሄጄ ማውጣት ፈልጌ ነበር፤ ነገር ግን የውሃው ግፊት አስፈራኝ።”
እሁድ ዕለት የሀገሪቱ ብሔራዊ የአደጋ ጊዜ አስተዳደር ኤጀንሲ በጎርፍ አደጋው ለተጠቁ ሰዎች የርዳታ አቅርቦት ማዳረስ እንደሚጀምር ተናግሯል። ኤጀንሲው በፌስቡክ ገጹ ላይ በለጠፈው መረጃ መሠረት በጎርፉ መንገዶች እና ድልድዮች ጉዳት ደርሶባቸዋል። ይህም በአካባቢው የኢኮኖሚ እና የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል።
የናይጄሪያ ቀይ መስቀል አርብ ዕለት ባወጣው መግለጫ በሀገሪቱ የጣለውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ የተከሰተው ጎርፍ “ከባድ የሕይወት መጥፋት እና ሰፊ ስጋት ፈጥሯል” ማለቱን የዘገበው ቢቢሲ ነው።
አዲስ ዘመን ማክሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2017 ዓ.ም