የተጓዳኝ ትምህርት ከክፍል ውጭ በተማሪዎችና በመምህራን ፈቃደኝነት ላይ ተመስርቶ ከመደበኛው የትምህርት ፕሮግራም ወይንም የክፍል ውስጥ የመማር ማስተማር ሂደት ውጭ ባለው ሰዓት የሚፈፀም ነው። የተጓዳኝ ትምህርት ምንጭ ከማህበራዊ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ተፈጥሮ ሳይንስ፣ ባህልና ስነጥበብ፣ ስፖርትና ቱሪዝም፣ ወዘተ የተገኘ ነው። መሠረታዊ ሀሳቡ በክፍል ውስጥ ሊሰጥ ከተዘጋጀውና ከዚያም ውጭ ባሉ ማህበረሰባዊ ጉዳዮች የሚወሰድ በመሆኑ ወደ ተግባር የሚለወጥና ጠቀሜታ ያለው አሰራር ሲሆን በማንኛውም የትምህርት ቤት ደረጃና የመማር ማስተማር ስራ አጋዥ እንቅስቃሴ ነው።
ትምህርት ቤቶች እንደ ራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ ስርዓተ ትምህርቱን ወደ ተግባር ይለውጡታል ተብሎ የሚታመንባቸውን ጉዳዮች በመለየት በተጓዳኝ ትምህርት አደረጃጀቶች እንዲታቀፉ ያደርጋሉ። አደረጃጀቱ ለአመራር እንዲመችና የነበረውን የክበባት ያለ ልክ መለጠጥ ለማስቀረት በትምህርት ቤት ደረጃ የተጓዳኝ ትምህርት አደረጃጀት ቅርፅ በዚህ መምሪያ /ማንዋል/ ላይ ለማስቀመጥ ተሞክሯል። በየአደረጃጀቱ ስር ተያያዥነት ያላቸው ተጨማሪ ተግባራትንና ክበባትን ማዋቀር የሚቻል ሲሆን በመምሪያው የቀረበው መነሻ ሃሳብ መሆኑም ሊታወቅ ይገባል።
በተጓዳኝ ትምህርት ውስጥ የሚገኘው የማህበራዊ አገልግሎት ክበብ የበጎ አድራጐት፣ የትራፊክ፣ የፖስታ፣ የስካውት ወዘተ አገልግሎቶችን የሚያካትት ሲሆኑ፣ የክበቡ ዓላማ በተማሪዎች የሚከሰቱ የተለያዩ ማህበራዊ ችግሮችን በመቅረፍ የመማር ማስተማር ሂደቱን ውጤታማ እንዲሆን ማድረግ ነው። የማህበራዊ አገልግሎት ክበብ አበይት ተግባራት ተማሪዎችን በክበቡ ተሳታፊ እንዲሆኑ ምዝገባ ማካሄድ፣ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ያለባቸውን ተማሪዎች በመለየት ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ ማመቻቸት፣ የትራፊክ ደንቦችን በማስተዋወቅ አደጋዎችን መከላከል፣ ተማሪዎች የፖስታ አገልግሎት የሚያገኙበትን ሁኔታ ማመቻቸት እና የስካውት አገልግሎት የሚስፋፋበት ሁኔታ ማመቻቸት ይገኝበታል።
ለዛሬ የምንመለከተው በሸዋሮቢት ከተማ ውስጥ የሚገኘውን የሸዋሮቢት አጠቃላይ ሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤት የአርአያ ሰብ የበጎ አድራጎትና የደም ልገሳ ክበብ ነው። ክበቡ የተመሰረተው በቅርቡ ቢሆንም በትምህርት ቤት ውስጥ የሚገኙ ችግረኛ ተማሪዎችን ከመደገፍ አልፎ ለአረጋውያን የቤት ኪራይ እየከፈለ ይገኛል። ስለ ክበቡ አመሰራረትና የስራ እንቅስቃሴ ከአባል ተማሪና ከክበቡ ተጠሪ መምህር ጋር ቆይታ አድርገናል። መልካም ንባብ።
የክበቡ አመሰራረትና ያከናወናቸው ስራዎች
የበጎ አድራጎቱ ክበብ ከተጀመረ የቆየ ቢሆንም በመደበኛነት ወደ ስራ የገባው ግን 2012 ዓ.ም ላይ መሆኑን የክበቡ ተጠሪ መምህር ሰለሞን ጌታሁን ይናገራሉ። የበጎ አድራጎት ስራው ከተማሪዎችና ከመምህራን ገንዘብ ተሰብስቦ ለችግረኛ ሰው ድጋፍ በማድረግ የተጀመረ ነው። አሁን ግን ክበቡ የራሱ እቅድና አላማ ይዞ እየሰራ ሲሆን ስራውንም አቅዶ በአግባቡ እንደሚገመግም ገልፀዋል።
ክበቡ በህጋዊ መንገድ መንቀሳቀስ ከጀመረ በኋላ የኮሮና ወረርሽኝ እስኪገባ ድረስ ስራዎች መከናወናቸውን በመጥቀስ፤ በትምህርት ቤት ውስጥ የሚገኙ ችግረኛ ተማሪዎችን በመለየት ለአስራ አንድ ተማሪዎች ድጋፍ መደረጉን አቶ ሰለሞን ያስታውሳሉ። ድጋፍ የተደረገላቸው ልጆች በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ እንደሚገኙ ይናገራሉ። ለተማሪዎቹ በየወሩ በባንክ አካውንታቸው ገንዘብ ገቢ ይደረጋል።
የበጎ አድራጎት ክበቡ በዚህ ሁኔታ እያደገ መጥቶ አንድ ተማሪ በወር አንድ ብር የሚያዋጣ ሲሆን በአመት አስር ብር ለክበቡ ገቢ ያደርጋል። በትምህርት ቤቱ ውስጥ የሚገኙ መምህራን በወር አስር ብር በዓመት መቶ ብር እያዋጡ ክበቡን እየደገፉ እንደሚገኙም አቶ ሰለሞን ያስረዳሉ። ይህ ከትምህርት ቤቱ ጋር በጋራ በመሆን የሚሰራ ስራ ሲሆን እስካሁንም እንደቀጠለ ይጠቅሳሉ።
በክበቡ አማካኝነት የደም ልገሳ ስራዎች የሚከናወኑ ሲሆን ለመጀመሪያ ጊዜ በደብረ ብርሃን ከተማ የደም ባንክ 2007 ዓ.ም ሲቋቋም ወደ ሸዋሮቢት መጥተው ደም አሰባስበው ነበር። በወቅቱ ደም ለመለገስ ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች በሚሰበሰቡበት ወቅት የመጀመሪያው ደም ለጋሽ እንደነበሩ አቶ ሰለሞን ይናገራሉ። የደም ልገሳው እንዲቀጥል ፈቃደኛ የሆኑ ተማሪዎችንና መምህራንን በማሰባሰብ ወደ ስራ መገባቱን ይጠቅሳሉ። አቶ ሰለሞን ከአስራ ስምንት ጊዜ በላይ ደም የለገሱ ሲሆን በተማሪ ደረጃ በቋሚነት ከአምስት ጊዜ በላይ ደም መለገሱን ያመለክታሉ።
ክበቡ በዋናነት ከትምህርት ቤት ውስጥ የሚገኙ ችግረኞችን የሚረዳ ሲሆን ድጋፍ የሚደረግላቸው ተማሪዎች ወላጅ የሌላቸው ልጆች ናቸው። አንዳንዶቹ በሰው ቤት ተጠግተው የሚኖሩ ናቸው። በተጨማሪም ልጆቻቸውን ለማስተማር አቅም የሌላቸውን ወላጆች የመደገፍ ስራ ይከናወናል። ለተማሪዎቹ የመማሪያ ቁሳቁስ በተሟላ መልኩ ድጋፍ እንደሚደረግ ይገልፃሉ።
ከትምህርት ቤቱ ውጪ በተደረገው ስራ ቢያንስ አስራ ሶስት ሰዎች ድጋፍ ማግኘታቸውን የሚናገሩት አቶ ሰለሞን፤ ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልል የተፈናቀሉ ችግረኛ ሰዎች ደብዳቤ ይዘው መጥተው ክበቡ ድጋፍ ማድረጉን ይጠቅሳሉ። ድጋፍ ለሚፈልጉት ሰዎች ከአንድ ሺህ ብር ጀምሮ እንደ ችግሮቻቸው ሁኔታ መደገፋቸውን ያብራራሉ። ህክምና የሚያስፈልጋቸው ሰዎችን ደግሞ ህክምና እንዲያገኙ ተደርጓል። በከተማው ለፀበል ብለው የሚመጡ ችግረኛ ሰዎችን ክበቡ በቻለው አቅም እየደገፈ መሆኑን ይጠቁማሉ።
በከተማ ውስጥ በአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የሚገኝ አንድ ተማሪ ከፍተኛ ህክምና የሚያስፈልው ስለነበር ክበቡ በቻለው አቅም በገንዘብ እየረዳ እንደሚገኝ ይናገራሉ። ጧሪ ቀባሪ ለሌላቸው አረጋውያን የቤት ኪራይና የምግብ ገንዘብ እየተሰጠ እንደሚገኝም ያመለክታሉ። በተጨማሪም ቤተሰብ ሳይኖራቸው በተለያዩ ቦታዎች ተጠግተው ለሚገኙ ዜጎች በቋሚነት የገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግ ይጠቁማሉ።
የክበቡ ተጠሪ ተማሪ ጌታባለው ማሞ እንደሚናገረው፤ በሸዋሮቢት ሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤት የበጎ አድራጎት ክበቡ በ2013 ዓ.ም የካቲት ወር ላይ ተመሰረተ። ክበቡ ከተመሰረተ በኋላ የትምህርት ቤቱን ግቢ ማስዋብ ስራ ተከናውኗል። በግቢ ውስጥ ችግኞች ተተክለዋል። በሌላ በኩል ለተወሰኑ አረጋውያን የቤት ኪራይ መክፈል ስራ ይከናወናል። በተጨማሪም ወላጅ ለሌላቸው ተማሪዎች የተለያዩ ድጋፎች ይደረጋሉ። የመማሪያ ቁሳቁስና በበዓላት ወቅት አስፈላጊ ድጋፎቸ ይደረጉላቸዋል። ክበቡ ሲመሰረት 34 አባላት የነበሩ ቢሆንም በስራዎች ላይ በተጠናከረ መልኩ ተሳትፎ አያደርጉም። ነገር ግን ክበቡን በቀጣይ ለሚመሩ ተማሪዎች ርክክብ ተደርጓል።
የህብረተሰቡ አቀባበል
ክበቡ በትምህርት ቤት ውስጥ የተመሰረተ እንደመሆኑ የአካባቢው ሰው በቻለው አቅም እገዛዎችን እያደረገ ይገኛል። በተወሰነ መልኩ ደግሞ ወጣ ያሉ ነገሮችን እንደሚያሳይ ተማሪ ጌታባለው ይናገራል። አብዛኛው በጥሩ ጎኑ የሚነሳ ነው። ክበቡ ደብዳቤ በመያዝ ከተማው ላይ እርዳታ የማሰባሰብ ስራ ያከናውናል። የተሰበሰበው ገንዘብ ድጋፍ ለሚደረግላቸው ተማሪዎች እንዲውል እንደሚደረግ ይጠቅሳል።
አቶ ሰለሞን እንደሚናገሩት፤ የሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር ምንም አይነት ድጋፍ እያደረገ ባይሆንም የሴቶችና ህፃናት ቢሮ የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ እያደረጉ ናቸው። በተጨማሪም የደም ልገሳ በሚኖርበት ጊዜ ወጣቱን በማስተባበር በኩል ቢሮው ከፍተኛ እገዛ እያደረገ ይገኛል።
ክበቡን ያጋጠመው ችግር
በክበብ ውስጥ የሚገኙ አባላት በቋሚነት በስራዎችና በስብሰባዎች ላይ አለመገኘትና የገንዘብ እጥረቶች ይስተዋላሉ። የተረጂዎች ቁጥር መጨመር ክበቡን እያሳሰበው መሆኑን የሚናገሩት አቶ ሰለሞን፤ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው የሚመጡ ሰዎች በመብዛታቸው ድጋፍ ለማድረግ እጥረት መግጠሙን አመልክተዋል። ተፈናቅለው የሚመጡ ተማሪዎች በትምህርት ቤት ውስጥ እንዲማሩ ለማድረግ የመማሪያ ቁሳቁስና ዩኒፎርም ተገዝቶላቸው መሆኑን ይገልፃሉ። አንዳንዴም የቤት ኪራይ እንደሚከፈልላቸው ይጠቅሳሉ።
ሌላው ክበቡን የገጠመው ችግር የገንዘብ እጥረት ሲሆን ስለ በጎ ስራ ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እንደሚያስፈልግ መጥቀስ፤ በተወሰኑ ሰዎች በሚደረግ ድጋፍ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ይናገራሉ። ነገር ግን በተረጂዎች ቁጥር ልክ ገንዘብ መሰብሰብ አለመቻሉን ይገልፃሉ። በ2013 ዓ.ም የተሰበሰበው ገንዘብ 59 ሺህ 953 ብር ከተማሪዎችና ከመምህራን መሰብሰብ ተችሏል። በተወሰነ መልኩ በከተማው ከሚገኙ ባለሀብቶች ገንዘብ እየተሰበሰበ ይገኛል። ከተሰበሰበው ገንዘብ ውስጥ 56 ሺህ 153 ብር ድጋፍ ተደርጓል። በተረፈውም ገንዘብ ለቀጣይ የትምህርት ዘመን እንደሚውል ይጠቅሳሉ።
የክበቡ ቀጣይ እቅድ
ክበቡ የተመሰረተበት የራሱ አላማ ያለው ሲሆን በዋነኝነት ድጋፍ ለሚፈልጉ ሰዎች መድረስ ነው። በክበቡ ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ደም የመለገስ ስራ ያከናውናሉ። ህብረተሰቡም ደም እንዲለግስ ቅስቀሳ ያደርጋል። በየሶስት ወሩ በደብረ ብርሃን የሚገኘው የደም ባንክ ወደ ትምህርት ቤቱ በመምጣት ደም ልገሳው እንዲከናወን እንደሚያደርግ ተማሪ ጌታባለው ይገልፃል። ሌላው የክበቡ እቅድ ትምህርት ቤቱ ውብና ፅዱ እንዲሆን የመስራት እቅድ አለው። የተቸገሩ ሰዎች ካሉ ችግራቸውን በመመልከት በክበቡ ውስጥ እንዲታቀፉ የማድረግ እቅድ አለ። ቀደም ብሎ በትምህርት ቤት ውስጥ ሀበሻ የደም ልገሳ የበጎ አድራጎት ክበብ በሚል በአንድ አስተማሪ አማካኝነት የተመሰረተ ነበር። አሁን ተሻሽሎ አርአያ ሰብ የደም ልገሳና የበጎ አድራጎት ክበብ በሚል እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል።
መምህር ሰለሞን እንደሚናገሩት፤ በቀጣይ ክበቡ ያስቀመጠውን እቅድ በመከለስ 50 ተማሪዎችን ለመደገፍ ታቅዷል። በውጪ ደግሞ ለአስራ አምስት ተማሪዎች ድጋፍ ለማድረግ ሀሳብ አለ። በተጨማሪም ለ35 ችግረኛ ሰዎች ድጋፍ ለማድረግ እቅድ ተቀምጧል። ይህን ለማከናወን የክበቡን አባላትና አስተባባሪዎች ስራዎችን እየሰሩ ናቸው። አባል ተማሪዎቹ የበጎ ፈቃድ አርዓያ ሆነው እየተንቀሳቀሱ ነው። በከተማ ውስጥ ገንዘብ ከመጠየቅ ጀምሮ ሊስትሮና ሌሎች ስራዎችን በማከናወን ገንዘብ የመሰብሰቡ ስራ እየተከናወነ ነው። የክበቡ አባላት የመኪና መንገዶችን የዜብራ ቀለም በመቀባት የማህበረሰብ አገልግሎት ግዴታውን እየተወጣ ይገኛል።
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/2013