የሽብር ድርጊት በሰው ልጆች ህይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ የሚገኝ ወንጀል ነው። ሽብርተኝነት ለዓለም ሕዝብ ሰላምና ደህንነት ከፍተኛ ስጋት ሲሆን፤ መንግሥትም የአገርና የሕዝብን ሰላምና ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነቱን ለመወጣት፤ ወንጀሉን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ባህሪውን ያማከለ ጠንካራ ቅድመ ጥንቃቄ የማድረግ ግዴታ አለበት። ወንጀሉ ከተፈፀመም አጥፊዎች ከድርጊታቸው ጋር ተመጣጣኝና አስተማሪ ቅጣት እንዲያገኙ ጠንካራ የሕግ ማዕቀፍ እንደሚያስፈልግ አያጠያይቅም።
ኢትዮጵያ የጸረ ሽብር አዋጅ ለመጀመሪያ ጊዜ ያጸደቀችው በ2001 ዓ.ም ነበር። ይህ አዋጅ የፀረ-ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 በይዘትና አፈጻጸም ክፍተቶች ነበሩበት። ይህ ሕግ በዜጎች መብት እና ነጻነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ በማሳደሩ እና የግለሰቦችን መብቶች እና ነፃነቶች በበቂ ሁኔታ ሊያስጠብቅ እና የሕግ አስፈጻሚ አካላትን ተጠያቂነት ማስፈን በሚያስችል ሕግ መተካት እንዳለበት ሲነገር ቆይቷል። በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 55 ንዑስ አንቀፅ (5) መሰረት ሌላ አዋጅ ታውጇል። አዋጁ የሽብር ወንጀልን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር የወጣ 1176/ 2012 ይባላል።
የሽብር ድርጊት ለመፈጸም የዛተ ሰው ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ በአዋጁ ተቀምጧል። ዛቻ የሚያስቀጣው የዛተው ሰው አድርጌዋለሁ ወይም አስደርጌዋለሁ ያለውን ድርጊት ለመፈጸም ያለበት ሁኔታ ወይም ያለው ዕድል ወይም ያደረገው መዛት በህብረተሰቡ ወይም በህብረተሰቡ የተወሰነ ክፍል ላይ የፈጠረውን ወይም ሊፈጥር የሚችለውን ሽብር በማገናዘብ ነው።
የሽብር ወንጀል ለመፈጸም ማቀድ እና መሰናዳትን በሚመለከትም በአዋጁ አንቀፅ 3 ላይ እንደተመለከተው፤ የሽብር ወንጀል ለመፈጸም የማቀድ ተግባር የፈፀመ ሰው ከሶስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እሥራት እንደሚቀጣ አስቀምጧል። የሽብር ድርጊት ለመፈጸም መሰናዳት ደግሞ ከአምስት ዓመት እስከ አስራ ሁለት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ያስቀጣል፡
የሽብር ወንጀል ለመፈጸም ማደም ወይም እንዲፈጸም ለማድረግ ያደመ ከአምስት ዓመት እስከ አስራ ሁለት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት ይቀጣል። የሽብር ድርጊት እንደተፈጸመ ወይም እየተፈጸመ እንደሆነ ወይም እንደሚፈጸም በሐሰት ገልፆ ማስፈራራት፤ በህብረተሰብ ወይም በተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል ውስጥ ድንጋጤን፣ ሽብርን፣ መረበሽን ወይም ስጋትን የፈጠረ እንደሆነ በቀላል እስራት ወይም ነገሩ ጉዳት ያስከተለ እንደሆነ ከሶስት ዓመት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣ በአዋጁ ተመላክቷል።
የሽብር ድርጊትን ከመፈፀም በተጨማሪ ማንኛውም ሰው የሽብር ወንጀል አፈጻጸምን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ያመቻቸ ወይም የረዳ ከሆነ፤ ሽብርተኛ ድርጅትን ለመርዳት በማሰብ ሰነድ ወይም መረጃ ካዘጋጀ፤ ካቀረበ፤ ከሰጠ፤ ወይም የክህሎት፣ የምክር ፣ የሙያ ድጋፍ ከሰጠ ተጠያቂ ይሆናል። እንዲሁም ማንኛውንም ፈንጂ፣ ድማሚት፣ ተቀጣጣይ ንጥረ ነገሮችን፣ የጦር መሳሪያ ወይም ሌላ ገዳይነት ያለው መሳሪያ ወይም መርዛማ ንጥረ ነገሮችን፣ ያዘጋጀ፣ ያቀረበ፣ የሰጠ፣ የሸጠ፤ በተጨማሪ ስልጠና የሰጠ ወይም አባላትን የመለመለ ከሰባት ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት በሚደርስ ፅኑ እስራት እንደሚቀጣ አዋጁ አስቀምጧል።
የንብረት ድጋፍ ማድረግን በሚመለከት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ እና በተጨማሪ ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር በወጣ አዋጅ መሰረት ይቀጣል። በሰብአዊ ተግባር ላይ የተሰማሩ ድርጅቶች የሚያደርጉት ሰብዓዊ እርዳታ ወይም ሌላውን ሰው የመርዳት የሕግ ኃላፊነት ያለበት ሰው ተግባርና ኃላፊነቱን ለመወጣት ብቻ የሚያደርገው ድጋፍ ግን እንደማያስቀጣ ተቀምጧል።
የሽብር ወንጀል እንዲፈጸም በንግግር፣ በጽሑፍ፣ በስዕል ወይም በሌላ ማንኛውም አድራጎት በግልጽ ሁኔታ ቅስቀሳ ያደረገ፣ ወይም እንደዚህ ዓይነት ይዘት ያለው ነገር መሆኑን እያወቀ ያተመ፣ ያሳተመ፣ ያስተላለፈ፣ ያሰራጨ፣ ያከማቸ፣ የሸጠ፣ ወይም በሌላ ማንኛውም መንገድ ለሕዝብ ተደራሽ ያደረገ እና ወንጀሉ የተፈጸመ ወይም የተሞከረ እንደሆነ ከሶስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል። የወንጀል ህጉ አንቀጽ 46 ንዑስ አንቀፅ 2 ቢኖርም፤ እንዲፈጸም የተፈለገው የሽብር ወንጀል ያልተሞከረ ወይም ያልተፈጸመ (ያልታተመ) ቢሆንም፤ ከአንድ ዓመት እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል።
ከሽብር ወንጀል ጋር የተገናኘ ንብረትን ስለመያዝም የሚያስጠይቅ እና የሚያስቀጣ መሆኑ በአዋጁ ተካትቷል። ከሽብር ወንጀል ጋር የተገናኘ ንብረት መሆኑን እያወቀ ንብረቱን ይዞ የተገኘ ወይም የተገለገለበት ማንኛውም ሰው የንብረቱ መወረስ እንደተጠበቀ ሆኖ ከሶስት ዓመት እስከ አስር ዓመት በሚደርስ ፅኑ እሥራት ይቀጣል። ድርጊቱ የተፈጸመው በቸልተኝነት እንደሆነ ቅጣቱ ከአንድ ዓመት እስከ ሶስት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይሆናል።
በጠቋሚ እና በምስክር ላይ የሚፈጸም ወንጀልንም በሚመለከት ወንጀል ጠቋሚ ወይም ምስክር ሊሆን የሚችል ወይም ማስረጃ ያለው ሰው፤ መረጃውን ወይም ማስረጃውን ለፍትሕ አካላት እንዳይሰጥ ወይም በምርመራ ወይም በክርክር ሂደት ምስክር ሆኖ እንዳይቀርብ በእርሱ ወይም ከእርሱ ጋር የቅርብ ግንኙነት ባለው ሰው ላይ የተንኮል፣ የኃይል ስራ፣ የማስፈራራት፣ የማይገባ ጥቅም በመስጠት ወይም በመደለል፣ በሌላ ማንኛውም መንገድ ጣልቃ በመግባት የከለከለ እንደሆነ እና ከሶስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚያስቀጣም በአዋጁ ተቀምጧል።
ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ የተመለከተ ወንጀልን አስመልክቶ ጥቆማ ወይም መረጃ የሰጠ፣ ወይም ምስክር ሆኖ የቀረበን ሰው መረጃ በመስጠቱ ወይም ምስክር ሆኖ በመቅረቡ ምክንያት፤ በእርሱ ላይ ወይም ከእርሱ ጋር የቅርብ ግንኙነት ባለው ሰው ላይ ጥቃት፣ ማስፈራራት፣ ወይም ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ ከሶስት ዓመት እስከ ሰባት ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት ይቀጣል። ወንጀሉ በተበዳይ ላይ ከባድ የአካል ወይም የጤና ጉዳትን ወይም ሞትን አስከትሎ እንደሆነ፤ እነዚህን ወንጀሎች በሚመለከት አግባብነት ያላቸው ሕጎች በተደራቢነት ተፈጻሚ እንደሚሆኑም ነው አዋጁ ያስቀመጠው።
በአዋጁ ሌሎችም ቅጣቶች የተካተቱ ሲሆን፤ ማስረጃ ማጥፋትን ጨምሮ በዳኝነት ወይም በህግ አስፈፃሚ አካላት ላይ ስለሚፈፀም ወንጀል እና ስለሚያስከትለው ቅጣት ተቀምጧል። ስለምስክሮች ጥበቃ እና ሌሎችም ጉዳዮች በአዋጁ ተካትተዋል።
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 30/2013