በ2013/14 የመኸር ምርት ዘመን 12 ነጥብ 78 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማረስና 374 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ እቅድ መያዙን ከግብርና ሚኒስቴር የወጡ መረጃዎች ያሳያሉ :: በተመሳሳይ በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮው የመኸር እርሻ ከሚታረስ 6 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ውስጥ 3 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታሩን በክላስተር ዘዴ በመጠቀም አርሶ አደሮችን ምርትና ምርታማነትን እንዲያሳድጉ እየተሰራ ስለመሆኑ ከኦሮሚያ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የወጡ መረጃዎች ይጠቁማሉ:: በቅርቡ በምስራቅ ሸዋ ዞን አዳሚ ቱሉ ኮምቦልቻ ወረዳ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት አርሶ አደሮች በክላስተር ተደራጅተውና በሜካናይዜሽን ተደግፈው የስንዴ እርሻ ስራ ጀምረዋል ::
አቶ ጌታሁን በጋዋቄ በምስራቅ ሸዋ ዞን የአዳሚ ቱሉ ጂዱ ኮምቦልቻ ወጬሳ አካባቢ ሞዴል አርሶ አደር ናቸው:: የዞኑ አስተዳደር ባመቻቸው እድል ከሌሎች ሞዴል አርሶ አደሮች ጋር በክላስተር እንደተደራጁ ይናገራሉ :: በዚሁ መሰረት በአካባቢያቸው በኢንቨስትመንት ስም ረጅም ዓመታት ታጥሮ በቆየ መሬት ላይ በሜካናይዝድ የተደገፈ የስንዴ እርሻ መጀመራቸውን ይጠቅሳሉ ::
ከዚህ በፊት ስንዴን ሲያመርቱ የነበረው በበሬ በማረስ እንደነበርም ተናግረው ፤ይሁንና በአሁኑ ወቅት በክላስተር ተደራጅተው በትራክተር በማረስ በማሽን ስንዴ መዝራት በመጀመራቸው የምርት መጠን ከማሳደግ በዘለለ ጥራት ያለው ምርት ለማምረት እንደሚያስችል ይጠቁማሉ:: ምርታማነት የሚያድግ ከሆነ ደግሞ ገቢያቸውም እንደሚሻሻል ያምናሉ:: የአዳሚ ቱሉ ጂዱ ኮምቦልቻ እርሻ ቢሮ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች ከእርሻ ጀምሮ የኪራይ ማሽን እስከማፈላለግና ሃሳብ እስከማምጣት ድረስ ለእርሳቸውና መሰል አርሶ አደሮች ሙያዊ ድጋፍ እንዳደረጉላቸውም ያስረዳሉ::
በስድስት መቶ ሄክታር መሬት ላይ በክላስተር በመደራጀት ስንዴን በማሽን ከዘሩት ውስጥ እርሳቸው አንዱ መሆናቸውንም ጠቅሰው፤ በዚህ መልኩ ተደራጅቶና ተባብሮ ስንዴ ማምረት እኩል ምርት በማግኘት እኩል ተጠቃሚ እንደሚያደርግም ይናገራሉ:: በግላቸው በሄክታር ስልሳ ኩንታል የስንዴ ምርት የማግኘት ግምት እንዳላቸውና ይህም ከራሳቸው አልፎ ሌሎችንም ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ይጠቁማሉ:: የዞኑ አስተዳደር በዘንድሮው የመኸር ዘመን ብቻ ምርት እንዲያመርቱ መፍቀዱንም የሚገልፁት አቶ ጌታሁን በቀጣይ በበጋው ወቅትም እንዲያመርቱ ከፈቀደ ከዚህም በላይ ምርት የማምረት እቅድ እንዳላቸው ያመለክታሉ::
ልክ እንደ አቶ ጌታሁን ሁሉ አቶ ወርቁ ኤደውም የአዳሚ ቱሉ ጂዱ ኮምቦልቻ ወረዳ አካባቢ በዘንድሮው የመኸር ዘመን መንግስት በክላስተር አደራጅቶ ስንዴን በማሽን ተደግፈው እንዲያመርቱ ካደረጓቸው አርሶ አደሮች ውስጥ አንዱ ናቸው:: ከዚህ በፊት እርሳቸውን ጨምሮ በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮች እርሻን የሚያከናውኑት በበሬ እንደነበርም ያስታውሳሉ:: ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት የወረዳው አስተዳደር ባደረገው ጥረት ቀደም ሲል ለኢንቨስትመንት በሚል ተወስዶ በነበረው መሬት ላይ ከሌሎች ሞዴል አርሶ አደሮች ጋር በክላስተር በመደራጀት በማሽን የተደገፈ የስንዴ እርሻ መጀመራቸውን ያስረዳሉ::
በዚህ መልኩ የተጀመረው የስንዴ እርሻ ምርታማነትን የሚጨምር በመሆኑ ከራስ አልፎ ለአገር እንደሚጠቅም ይናገራሉ:: እርሻው ገና ጅምር በመሆኑና እንዲህ አይነቱ ዘዴም ወጥ በሆነና ባልተቆራረጠ መልኩ የሚካሄድ በመሆኑ ሌሎች የአካባቢው አርሶ አደሮችም ይህን ልምድ አይተው ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚያስችላቸውም ይጠቅሳሉ:: ምርት በጨመረ ቁጥር ደግሞ የአገሪቱ የምግብ ዋስትና እንደሚረጋገጥም ይጠቁማሉ::
ከስድስት መቶ ሄክታር መሬት ውስጥ አንድ ክላስተር ወይም ሃያ ሄክታር መሬት እንዳላቸውም አቶ ወርቁ ጠቅሰው፤ ከዚህ በፊት በሄክታር የሚያገኙት ምርት ዝቅተኛ እንደነበር ነገር ግን በዚህ የክላስተር ዘዴ ተጠቅመው በዘንድሮው የመኸር ዘመን በሄክታር ከሃምሳ ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁ ይገልፃሉ:: ይህም የእርሳቸው ብቻ ሳይሆን የሌሎች እርሳቸውን መሰል አርሶ አደሮች ገቢ እንዲሻሻል አገርም እንድትጠቀም አስተዋፅኦ እንደሚደርግ ይናገራሉ::
ወረዳው መሬቱን ያመቻቸው አርሶ አደሮች ለአንድ ዙር ብቻ እንዲዘሩበት መሆኑንም የሚናገሩት አቶ ወርቁ፤ ከተቻለ መሬቱ ለበጋው ወቅትም የሚፈቀድ ቢሆን የአካባቢውን ወንዝ በመጠቀም ስንዴን በመስኖ በማልማት ተጨማሪ ምርት ለማምጣት እቅድ አላቸው::
የአዳሚ ቱሉ ወረዳ አስተዳደር አቶ መሀሙድ በሪሶ እንደሚሉት ግብርናን ለማዘመን በርካታ ማሽነሪዎች ጥቅም ላይ እየዋሉ የሚገኝ ሲሆን ማሽኖቹን ብቻ መጠቀም በቂ ባለመሆኑ አርሶ አደሩ በክላስተር ተደራጅቶ እንዲያርስ እየተደረገ ይገኛል:: መንግስት ‹‹አንድም መሬት ፆም ማደር የለበትም›› በሚል ያስቀመጠውን አቅጣጫ መሰረት በማድረግ ወረዳው ቀደም ሲል በኢንቨስትመንት ታጥሮ የቆየ 600 ሄክታር ቦታን በማስለቀቅ 122 አርሶ አደሮች በ39 ክላስተር ተደራጅተው በሜካናይዝድ የተደገፈ የስንዴ እርሻ እንዲጀምሩ አድርጓል:: ተጨማሪ 40 ወጣቶችም ከአርሶ አደሮቹ ጋር ተቀላቅለው በክላስተር ተደራጅተዋል::
አካባቢው ስንዴ በስፋት የማይዘራበት ከመሆኑ አኳያ በዘንድሮው የመኸር ዘመን በክላስተር በተደራጁ አርሶ አደሮች ሙሉ ቴክኖሎጂን ሥራ ላይ በማዋል ስንዴ እንዲዘራ በመደረጉ ከሰባ እስከ ሰማኒያ ኩንታል ምርት በሄክታር ይገኛል ተብሎ ይገመታል:: የወረዳው አስተዳደርም አርሶ አደሮችን በክላስተር ከማደራጀት አንስቶ የእህል ማዳበሪያ እንዲዘጋጅ ብሎም በግብርና ባለሙያዎች በኩል አስፈላጊው ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል::
እንደ አስተዳደሩ ማብራሪያ አርሶ አደሩ በክላስተር ተደራጅቶና በቴክኖሎጂ ተደግፎ የስንዴ እርሻ መጀመሩ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ከማሻሻል በዘለለ የሀገር ኢኮኖሚን ከማሳደግ አኳያ ጉልህ ድርሻ ይኖረዋል:: በጋራ ተቀናጅቶ የማልማት ትልቅ ልምድ እንዲያዳብርም ያደርገዋል:: በጋራ ሰርቶ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥም ያስችለዋል::
በቀጣይም በኢንቨስትመንት ስም ታጥረው የተቀመጡ መሬቶች ወደ መሬት ባንክ እንዲገቡና አርሶ አደሮች በክላስተር ተደራጅተው በሜካናይዝድ የተደግፈው እርሻ እንዲያከናውኑ ተመሳሳይ ስራዎች ይከናወናሉ:: ከዚህ በፊትም በተመሳሳይ በዚሁ ወረዳ አነኖ ሺሾ በተባለ ቀበሌ ሰባ ሄክታር የሚሆን በኢንቨስትመንት ስም የታጠረ መሬት ለልማት እንዲውል በማድረግ በዚሁ ዘዴ አርሶ አደሮች ተደራጅተው ስንዴ እንዲያመርቱበት ተደርጓል::
የምስራቅ ሸዋ ዞን ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ መስፍን ተሾመ በበኩላቸው እንደሚገልፁት፤ በ2013/14 የምርት ዘመን እንደዞኑ ግብርና ቢሮ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ:: ከዚህ ውስጥ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አሕመድ ያስቀመጡትን ማንኛውም መሬት ሳይታረስ እንዳያድር የሚለውን መርህ በመከተል በዞን ደረጃ 439 ሺ 120 ሄክታር መሬት እየታረሰ ይገኛል:: ከዚህ ውስጥም 60 ከመቶ ያህሉ በኩታ ገጠም እርሻ /በክላስተር/ የሚታረስ ነው:: በምስራቅ ሸዋ ዞን በአዳሚ ቱሉ ወረዳ ጂዳ ኮምቦልቻ ወረዳ እየታረሰ ያለው 600 ሄክታር መሬት የስንዴ እርሻም የዚሁ አካል ሲሆን እርሻውም በሙሉ ሜካናይዜሽን ተከናውኗል:: እንዲህ አይነቱ የአስተራረስ ዘዴም ምርትና ምርታማነትን ይጨምራል፤ የገበያ ትስስሩንም በስፋት ለአርሶ አደሩ ያቀርባል::
ኃላፊው እንደሚሉት ፤እንደ ዞን 286 ሺ ሄክታር ማሳ በኩታ ገጠም /በክላስተር/ ለማረስ እየተሰራ ሲሆን በአዳሚ ቱሉ ወረዳ ጂዳ ኮምቦልቻ ወረዳ የሚገኘውና የስንዴ ኩታ ገጠም እርሻ ከዚህ በፊት ሳይታረስ የሚያድር ነበር:: ይሁንና በአሁኑ ወቅት በቦታው ላይ አርሶ አደሮችን በክላስተር በማደራጀት በሜካናይዜሽን ተደግፈው የስንዴ እርሻ እንዲያከናውኑ ተደርጓል:: ከዚህ 600 ሄክታር ማሳም ምን ያህል ምርት እንደሚገኝ የአዋጭነት ጥናት ተከናውኗል:: የግብአትና የማሽን ወጪ ከተሰራ በኋላ ትርፉ ባለው የገበያ ሁኔታ ተጠንቶ የሚሰላ ይሆናል::
የኩታ ገጠም እርሻ በሚመለከት በቅድሚያ ለአርሶ አደሩ ግንዛቤ መስጠት አስፈላጊ በመሆኑ ይህንን ታሳቢ በማድረግ የበልግና የክረምት የእርሻ ወቅት ከመድረሱ በፊት ቢሮው ይህን የአስተራረስ ዘዴ በሚመለከት ሰፊ ንቅናቄዎችን በማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫዎችን ሰጥቷል:: ቀደም ሲልም በአርሶ አደሮች በኩል አቀባበሉ ላይ ውጣውረዶች አጋጥመዋል:: ይሁንና በሂደት አርሶ አደሩ ወደ አንድ እየመጣ ይገኛል::
አርሶ አደሮች በኢንቨስትመንት ታጥረው በቆዩ ቦታዎች ላይ በክላስተር ተደራጅተው እንዲሰሩ የሚደረገው ከኢንቨስትመንት ቢሮ፣ ከግብርና ቢሮና መሬት አስተዳደር በጋራ በቅንጅት ሲሆን አስርና አስራ አምስት ዓመታት ሙሉ መሬት ወስደው የማያርሱ ባለሀብቶች ላይ እንደዞን እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል::
ይህን የመሰለ መሬት ደግሞ ፆሙን ማደር ስለሌለበትና አርሶ አደሩም መራብ ስለማይኖርበት በነዚህ አልሚዎች ላይ አስተዳደራዊ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል:: በዞኑ የተለያዩ ቦታዎች ላይ በኢንቨስትመንት ሥም በታጠሩ ሌሎች ቦታዎች ላይ አርሶ አደሮች በክላስተር ተደራጅተው እንዲያርሱባቸው ለማድረግ ስራዎች እየተሰሩም ይገኛሉ:: የኢንቨስትመንት ውል እንዲቋረጥም ተደርጓል::
የምስራቅ ሸዋ ዞን አስተዳደር አቶ አባቡ ዋቆ እንደሚገልፁት፤ መንግስት አርሶ አደሩ በሙሉ በክላስተር ተደራጅቶና ተመሳሳይ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ምርትና ምርታማነትን እንዲጨምር ባስቀመጠው የኩታገጠም አቅጣጫ መሰረት ዞኑ በአዳሚ ቱሉ ኮምቦልቻ ጂዳ ወረዳ በቴክኖሎጂ በተደገፈ የክላስተር እርሻ አስጀምሯል:: አርሶ አደሮቹ በክላስተር ተደራጅተው ምርታቸውን ካመረቱ በኋላ ለፋብሪካዎች ሲያቀርቡ በተዘዋዋሪ ከ140 በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድል ይፈጥራሉ:: እስካሁን ድረስም እንደ ዞን ከ ሰባት ሺ 940 በላይ ሄክታር መሬት ወደዚሁ የክላስተር ዘዴ እንዲገባ ተደርጓል::
በክላስተር ዘዴ ተደራጅተው ስንዴ መዝራት የጀመሩ አርሶ አደሮች ከአንድ ሄክታር ማሳ እስከ ሰማንያ ኩንታል ምርት ያገኛሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን አርሶ አደሮቹ በክላስተር ተደራጅተው ሲያመርቱ የገበያ ትስስር ችግራቸውን ከመቅረፍ በዘለለ ምርትና ምርታማነታቸውን ያሳድጋሉ::
አስናቀ ፀጋዬ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 29/2013