የአገር ፍቅር ከውስጥ የመነጨ ስሜትን የሚገዛ አንዳች ኃይል ያለው ነው። ስለ አገር ፍቅር ከመግለጽም ሆነ ከመናገር የሚቀድመው በሲቃ የታፈነ፣ በእንባ የታጀበ የተለያዩ ስሜቶች የሚንጸባረቁበት ንግግር እና ስሜት ነው። ከአገሩ ወጥቶ በባዕድ አገር ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ከዚህም እጅግ የላቀ ስሜት ያለው ነው።
በዓለማችን የተለያዩ ክፍሎች የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ደግሞ ለዚህ ምስክር ናቸው። እትብታቸው ስለተቀበረበት፤ የዘር ሐረጋቸው ስለተመዘዘበት፤ ዞሮ መግቢያው ቤታቸው ቀን ከሌሊት የሚጨነቁ እና ተቆርቆሪ መሆናቸው በተደጋጋሚ በዓለም አደባባይ አስመስክረዋል።
የዲያስፖራ ማህበረሰብ የአገሩ ናፍቆት ሰቅዞ ይዞት ከነገ ዛሬ አገሬ እመለሳለሁ የዘወትር ምኞቱ በመሆኑ የአገሩን ጉዳይ ችላ ሳይል በንቃት ይከታተላል። ኢትዮጵያ አድጋና በልጽጋ የማየት ህልምና ፍላጎት ስላለው ከዓላማዋ የሚያደናቅፍ እንቅፍት እንዲገጥማት አይፈልግም። በሩቅ እየኖረ አይኑን ከአገሩ ላይ ሳይነቅል ለአገሩ ዘብ ሆኖ ይቆማል ። አገሩ በምንም ሁኔታና ምክንያት እንድትነካ አይፈቅድም።
በውጭ የሚኖረው ዲያስፖራ ማህበረሰብ ምንም እንኳን የተለያየ አመለካከትና ፍላጎት ቢኖረውም በአገር ጉዳይ አንድ ከመሆን ቦዝኖ አያውቅም ። በእርግጥ ነው ባለፉት ጊዜያት ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ በብሔርና በሃይማኖት በመከፋፈል እንዳይግባቡ ለማድረግ የተሰራው ሴራ ቀላል አልነበረም። ከዚህም አልፎ ተርፎም በአገር ውስጥም ሆነ በአገር ውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን አንድነት እንዳይኖራቸው፤ ተባብረው ለአገር እድገት በጋራ እንዳይሰሩ ለማድረግ ያልተቧጠጠ ዳገት ፤ ያልተቆፈረ ድንጋይ አልነበርም። ሆኖም ግን ኢትዮጵያ በማፍረስ ፤ ሕዝቦቿ ለመበታተን የተሴረው ሴራ ከሽፏል።
እንደ ድርና ማግ የተገመደውን አንድነት ለመበተን እና ለመበጠስ የቆመው የእኩይ ተግባር ባለቤት ለአሸባሪው ህወሓት እጅ ሳይሰጡ ቆይተዋል። ኢትዮጵያውያኑ ይህን እንዲሆን አልፈቀዱምና ጊዜው ደርሶ ኢትዮጵያውያን ተከፋፍለውና ተለያይተው ማየት የሚሹ አካላት ሴራቸው እንደ ጤዛ ተኖ፤ እንደ ጉም በኖ ጠፍቷል ። ታዲያ የተበታተነ እና የተፍረከረከ የመሰለው አንድነት በማይበጠስ መልኩ ጠንክሮና ተጋምዶ የእኩይ ተግባር ባለቤቶችን አንገት አስደፍቶ ለማሳፈር አልዘገየም ። ሊያውም በጽኑ የአንድነት መሠረት ላይ የተገነባ ለአገር ተቆርቋሪና አለኝታ የሚሆን፤ አንድነትና ህብረት ከመቼው ጊዜ በላይ እንደ ብረት የተጠናከረበት ሊጋፉ የማይችሉት ሆነ እንጂ ።
በአንድነት የጠነከረ ስሜት ውስጥ ሆነው የሚጠበቅባቸው ለአገራቸውን ለማበርከት የሚሹ በርካቶች ናቸው ። በተቃራኒው ጽንፍ ይዘው የቆሙ ዶላራቸውን እየመዠረጡ አሸባሪውን ህወሓት ሳይቀር በመደገፍ ለወገኖቻቸው ስቃይና መከራ በመደገስ ወገኖቻቸውን እያስጨረሱ የሚገኙም አልታጡም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰልችቶት የተፋውን አሸባሪው ህወሓት ደጋፊ መሆናቸውን በአገራቸው ላይ ጫና እንዲደረግ በዓለም አደባባይ እየጮሁ የሚገኙ የታሪክ ተወቃሾች እንዳሉም የምናየውንና የምንመለከተው ጉዳይ ነው።
የማይነጋ የለምና ጨለማው ተገፎ ነግቷል። አሁን ላይ በኢትዮጵያ ሰማይ ሥር የኢትዮጵያውያን ከልብ የመነጭ የአገር ፍቅር ገንፍሎ አሸባሪውን ህወሓት አደብ እያስገዛው ይገኛል። ለአገሩ ዘብ የቆመው ዲያስፖራው ደግሞ ከሀገሩና ከወገኖቹ ጎን ቆሞ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርገውን ጫና በመቃወም ለአገሩ ከለላ እየሆነ ይገኛል። ዲያስፖራው የነበረውን ልዩነት ወደ ጎን በመተው ለአገርና ለወገን ደራሽ አለኝታነቱ ከማሳየቱም ባሻገር በዲፕሎማሲ ረገድ የተለያዩ ሥራዎች እየሰራ ይገኛል።
በተለይ አሁን ላይ ምዕራባውያኑ አይናቸውን ኢትዮጵያ ላይ ተክለው በአይነቁራኛ እየተከታተሉ ባሉበት እና ሚዲያዎቹም የተዛባ መረጃዎችን በሚያስተላልፉበት ወቅት ከሀገራቸው ጎኑ መቆም የቁርጥ ቀን ልጅነታቸውን ያስመሰከሩበት ነው።
ከዚህም ባሻገር ከአሜሪካ የመጡት ዲያስፖራው ማህበረሰብ በአገር ውስጥ እየተካሄደ ያለውን ነባራዊ እውነታ በመመልከት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እና ለዲያስፖራው ለማስረዳት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸው ደግሞ ለአገራቸውን ያላቸውን ፍቅር ኃያልነት የሚያሳይ ነው ። በዚህም የዓለም አቀፉ ሚዲያዎች ስለኢትዮጵያ የሚያራግቡት የተሳሳተና የተዛቡ አመለካከቶች መሆናቸውን በአካል ተገኝተው አረጋግጠዋል። ወደ ሚኖሩበት አሜሪካም ሲመለሱ በአገር ውስጥ ስላለው ነባራዊ ሁኔታ የሚያስረዱ መሆኑን ተናግረው እንደነበር የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያውያኑ በኢትዮጵያ ላይ የተቃጡ የተዛቡ መረጃዎችን እና አመለካካቶች ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማሳወቅ በእጅጉ ጥረት አድርገዋል ። ጥረታቸውና ልፋታቸው መና አልቀረም ። በተባበሩት መንግሥታት እንዲታየ የቀረበው የህዳሴ ግድብ ድርድር ወደ አፍሪካ ህብረት እንዲመለስ ለማድረግ ከፍተኛ ጫና የፈጠረ ነበር። በተመሳሳይ በተለይ አሜሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት እንዳሻት እና እንደፈለገች የምታሽከረክረው መንግስትና አገር ስለምትፈልግ ለአሸባሪው ህወሓት መደገፍ አገራችን ላይ ማዕቀብ እንዲጣል ለማድረግ የምታደርገውን ጥረት ተቃውመዋል። በዚህም የአሸባሪው የህወሓት ደጋፊዎች ኢትዮጵያን በውሸት በማጠልሸት ተጨማሪ ጫና ለማሳደር የሄዱበትን እኩይ ተግባር አክሸፈዋል።
የአሜሪካ አካሄድ ያልተዋጠላቸው የኢትዮጵያ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላት እና ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች በጋራ የተቀናጀ መልኩ ባደረጉት ዘመቻ ነው የአሜሪካን እቅድ ያስቀየሱት።
በዚህም አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ በተሳሳቱ መረጃዎች ላይ ተመስርታ በምክር ቤቷ በማቅረብ ልታስወስነው የነበረውን የ”ኤችአር445” ረቂቅ እንድታዘገይ በማድረግ መክቷል።
ዲያስፖራው ስለኢትዮጵያ ያለውን ትክክለኛ መረጃ በሴናተሮቹ እና በኮንግረንስ አባላት ለማሳውቅ በተደጋጋሚ ጥረት አድርገዋል። ጥረታቸው የልፋታቸውን ያህል ባይሆንም ለኮንግረስ አባልዋ ካረን ባስ እውነታውን ማስረዳት ችለዋል ። በዚህም ምክንያት የኮንግረስ አባል የሆኑት ካረን ባስ ለአሜሪካ ኮንግረንስ ሊቀርብ የነበረውና የሰብዓዊ መብት ጥሰትን የተመለከተው ኤችአር 445 (HR 445) የተሰኘው ሰነድ ከመጽደቁ በፊት እውነታውን ማጣራት እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በጀርመን የሚኖሩ የኢትዮጵያና የኤርትራ ማህበረሰብ አባላት ‘ሰላምና መረጋጋት ለምስራቅ አፍሪካ’ በሚል ርዕስ ሰላማዊ ስልፍ አካሄደዋል። በሰልፉም የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት በሚዳፈሩ እና በውስጥ ገዳይ ጣልቃ መግባት እንደሌለባቸው ያሳወቁበት እና የአሸባሪውን የህወሓት ተግባር ያወገዙበት እንደነበር ከኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያሳያል።
አሁን ላይ ኢትዮጵያ እየገጠማት ካለው ውስብሰብ ችግር በተጨማሪ በውጭ ሀገራት የሚደረግ ጫና ለመመከት ዲያስፖራው ያላሰለሰ ጥረት እያደረገ ይገኛል። በዲፕሎማሲው መስክ እያደረገ ካለው ጥረት በተጨማሪም በዲጂታል ሚዲያው በኩል ከፍተኛ ሥራ እየተሰራ ነው። የቲውተር ዘመቻን በማቀላጠፍ ስለኢትዮጵያ ትክክለኛው መረጃ በማሳወቅ የሚተላለፉ የተዛቡ እና የተሳሳቱ መረጃዎች በመመከት ጠንካራ ሥራ እየሰራ ይገኛል። አሁን ላይ አገሩን በከፍተኛ ደረጃ እየጠቀመ ያለው ዲያስፖራ ያለው ቁርጠኝነት ሊበረታታና ሊደገፍ የሚገባው ተግባር ነው።
በአገራዊ አንድነት ላይ የማይደራደረው ዲያስፖራ በኢትዮጵያ ለሚካሄድ ለህዳሴው ግድብ ግንባታ እና ለፕሮጀክቶች ቀዳሚ በመሆኑ በሀብቱ፣ እውቀቱ እና በዲፕሎማሲው ሥራ አስፈላጊውን እገዛ ሁሉ ሲያደርግ እያደረገ ይገኛል።
ወርቅነሽ ደምሰው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 28/2013