ባለፈው ሳምንት ማክሰኞ በዚህ አምድ ‹‹ትምህርት ቤቶች ሆይ! የክፍያ ጭማሪውን እያስተዋላችሁ!›› በሚል ርእስ የወጣውን ዘገባ አንብቤዋለሁ:: ዘገባው የበርካታ ወላጆች ስጋት የሆነውን የግል ትምህርት ቤቶች የክፍያ ጭማሪ ጉዳይ ማንሳቱ ተገቢና ወቅታዊ ነው እላለሁ:: ጸሀፊው የግል ትምህርት ቤቶች የትምህርቱን ዘርፍ በመደገፍ እያበረከቱ ስላለው ሚና ጠቆም በማድረግ ፣ ባለፈው ዓመት በኮቪድ የተነሳ ጭማሪ ሳያደርጉ ተማሪዎችን በማስተናገድ ለተወጡት ማህበራዊ ሃላፊነት ምስጋና አቅርበዋል:: በመቀጠልም የግል ትምህርት ቤቶቹ የኢንቨስትመንት ተቋማት መሆናቸውንና ለጽድቅ እንደማይሰሩ አስታውቀዋል:: ማትረፍ እንዳለባቸውም በመጠቆም፣ ጭማሪያቸው ግን የተጋነነ መሆን እንደሌለበት ለማሳሰብ ሞክሯል:: የህብረተሰቡን የመክፈል አቅም አሁን ያለውን የኑሮ ውድነትም በመጥቀስ የመተሳሰብን አስፈላጊነት አመልክተዋል:: ትክክል ነው::
እንደሚታወቀው በሀገራችን የግሉ ዘርፍ በትምህርቱ መስክ በተለይ እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች እተጫወተ ያለው ሚና ከፍተኛ ነው:: ከአዲስ አበባ ተማሪዎች አብዛኞቹም የሚማሩት በግል እና በድርጅት/የእምነት ተቋማት ትምህርት ቤቶችና የመሳሰሉት/ ትምህርት ቤቶች መሆኑም ይገለጻል:: ከ50 በመቶው በላይ የትምህርት ሽፋን በግሉ ዘርፍ የተያዘ ነው ሲባል የሰማሁ መሰለኝ:: የግሉ ዘርፍ የትምህርት ቤት ተፈላጊነት አለ ባለበት አካባቢ ሁሉ ትምህርት ቤቶችን ይከፍታል:: ይህ ትልቅ ነገር ነው::
ትምህርት ቤቶቹ በተለያየ ቁመና ላይ ቢሆኑም፣ በህዝብ ዘንድ በከፍተኛ መጠን ይፈለጋሉ:: የክፍል ተማሪ ጥምርታቸው ጥሩ የሚባል መሆኑ፣ በአቅራቢያ እንደልብ መገኘታቸው፣ የቁጥጥር ሥርዓታቸው፣ ተማሪዎች በነጻነት የሚማሩበትን ሁኔታ መፍጠራቸው ተመራጭ እንደሚያደርጋቸው ወላጆች ሲገልጹ ይደመጣል::
ማህበረሰባችን ለትምህርት ትልቅ ዋጋ ይሰጣል፤ ሳይማር ያስተማረንን… እየተባለ የሚነገረውም ለእዚህ አይደል:: ወላጅ እሱ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ተምሮ፣ ወይም ጥሮ ግሮ ሰው እንደሆነ በማሰብም ልጆቹ ተምረው ሰው እንዲሆኑለት ይፈልጋል:: በተለይ በእዚህ ዘመን ለልጆቻችን የምናወርሰው እውቀት መሆን አለበት እያሉ ክፍያው እየጎዳቸውም ልጆቻቸውን በግል ትምህርት ቤት ያስተምራሉ:: ክፍያቸው እየከበደ መጥቶ እንጂ የግል ትምህርት ቤቶችን የማይመርጥ ያለ አይመስለኝም:: ይህም ሁኔታው ለግሉ ዘርፍ ጥሩ ገበያ መሆኑን ይጠቁማል::
የግል ትምህርት ቤቶችና ወላጆች በዚህ ደረጃ ቢፈላለጉም የክፍያ ጭማሪ ሁሌም ሲያወዛግባቸው ቀጥሏል:: ዘንድሮም የጭማሪው ጉዳይ ትልቅ አጀንዳ ሆኗል:: አንዳንድ ወላጆች በጉዳዩ ተማረው ሲያለቅሱም፣ ተቋማቱን ሲያማርሩ፣ ቅሬታቸውን ለመገናኛ ብዙሃንና ለሚመለከታቸው አካላት ሲያቀርቡም ይሰማል::
የህብረተሰቡ ስጋት ባለፈው ዓመት በኮቪድ የተነሳ ጭማሪ ስላልተደረገ ያን የሚያካክስ እንዲሁም በዚህ ዓመት የታየውን የኑሮ ውድነት ታሳቢ ያላደረገ ጭማሪ ሊደረግብን ይችላል የሚል ነው::
አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች ህንጻ ተከራይተው የሚሰሩ እንደመሆናቸው የቤት ኪራይ ዋጋ ጭማሪ እንዲያደርጉ ሊያስገድዳቸው ይችላል፤ መምህራንን ለማቆየት ፣ ሌሎች መምህራንን ተወዳድረው ለመቅጠር ገንዘብ ያስፈልጋቸዋልና ጭማሪ ሊጠይቁ ይችላሉ:: ጭማሪ ለመጠየቅ የሚያስገድዱ ሌሎች በርካታ ምክንያቶችም ሊኖሩ ይችላሉ::
ትምህርት ቤቶቹ ጭማሪውን ማድረጋቸው ላይ ቅሬታ ያለው ያለ አይመስለኝም:: ትምህርት ቤትን ያህል ተቋም ቀርቶ በየቤቱ የኑሮ ውድነቱ ያስከተለው ፈተና ከባድ እንደመሆኑ ጭማሪው አይደለም ያሳሰበው፣ ጭማሪው የተጋነነ አይሁን የሚሉት እንጂ::
ባለፉት ጊዜያት ይደረጉ በነበሩ ጭማሪዎች ብዙ ወላጆች ተማረዋል:: ባለፉት አመታት ልጆቻቸው አነስ ያለ ክፍያ ትምህርት ቤት የወሰዱ፣ ወደ መንግስት ትምህርት ቤት ያስገቡ ጥቂት እንዳልሆኑ ይነገራል:: አሁንም ስጋቱ እውነት ከሆነ ጥርሳቸውን ነክሰው የሚያስቀጥሉ ሊኖሩ የሚችሉትን ያህል ትምህርት ቤት የሚቀይሩ ይኖራሉ::
ባለፈው ሳምንት በዚህ አምድ የጻፈው ወንድሜ እንዳለው መተሳሰቡ አስፈላጊ ነው :: ትምህርት ቤቶቹ ተማሪዎቹ ልጆቻቸው ናቸው::እናም ልጆቻቸውንም፣ የልጆቻቸውን ቤተሰቦች እነሱም በማይጎዱበት አግባብ ጭማሪ ቢያደርጉ ጥሩ ነው::
ከዚህ ውጪ ግን ከሆነ እነሱም ሊጎዱ እንደሚችሉ ማሰብ አለባቸው:: ከተጋነነ የክፍያ ጭማሪ ቢወጡ ጥሩ ነው:: ሁሉኑም ነገር ባንዴ መፈጸም ይከብዳል:: እንደ ቤት ኪራይና የመምህራን ቅጥር ያለውን ታሳቢ በማድረግ ጭማሪውን ቢያደርጉ ብዙም ከወላጆች ጋር የሚጣሉ አይመስለኝም::
ወላጆችም ማስተዋል አለባችሁ:: ወላጆች ትምህርት ቤቶቹን ፈልጋችሁ ነው የሄዳችሁት:: ትምህርት አሰጣጡን ቅርበታቸውን፣ ክፍያውን እችለዋለሁ ብላችሁ ነው የሄዳችሁት:: እንደ እኔ እንደ እኔ ይህ ውል እንደመግባት ይቆጠራል:: ውል እንደሚገባ ሁሉ ሊፈርስም ይችላል፤ ካልተስማማችሁ ውል አፍርሳችሁ ሌላ አማራጭ መፈልግ ይኖርባችኋል::
ክፍያው ኑሯችንን ሊያናጋ ነው ማስተማር እንችልም የምትሉ ከሆነ አማራጮችን መፈለግ ነው የሚያስፈልጋችሁ:: ለመጠነኛ የክፍያ ጭማሪ ይህን ያህል ትቆጣላችሁ ብዬ አላስብም:: የሚያስቆጣ ጭማሪ ካለም በጉዳዩ ላይ በወኪሎቻችሁ በኩል መምከር አለበለዚያ ግን አማራጭ መፈልግ ይገባችኋል:: እንደ እኔ በአዲስ አበባ አሁን ጥሩ አማራጭ ያለ ይመስለኛል:: ከግሉ ትምህርት ቤት አንወጣም ከሆነ አቋማቸው ብዙም ያልተነጋነነ ክፍየ የሚጠይቁ ትምህርት ቤቶችን መማተር ይገባችኋል::
ትምህርት ቤቶቹን እያማረሩ ከመኖር ወደ መንግስት ትምህርት ቤት መማተርም ሌላው አማራጭ ነው:: አሁን በአዲስ አበባ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ልጆችን ለማስተማር ምቹ ሁኔታ ያለ ይመስለኛል:: ጥሩ ማኩረፊያ ተፈጥሯል::
መንግስት ለተማሪዎች ምግብ ፣ ዩኒፎርምና ጫማ ጭምር እያቀረበ ነው:: ትምህርት ቤቶች በጥሩ ሁኔታ እየታደሱና እየተስፋፉም ናቸው:: ለመምህራንም የመኖሪያ ቤት በኪራይ /አሁን ደግሞ እንዲገዙት ተፈቅዷል/ ተመቻችቷል:: ትምህርት ቤቶችን የማስፋፋት አዳዲስ ትምህርት ቤቶችን የመክፈት ሁኔታም ይታያል:: ይህ ሁሉ በትምህርት ቤቶቹ የትምህርት አሰጣጥ ላይ ለውጥ እንደሚያመጣ ይታመናል:: እናም የመንግስት ትምህርት ቤቶች ጥሩ ማኩረፊያ ናቸው:: ይህን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ከጫና መገላገል ይገባል::
እናም ወላጆች ሆይ የግል ትምህርት ቤት የክፍያ ጭማሪ ችግር ብላችሁ ብዙም አዳባባይ ባትወጡ እመክራችኋለሁ:: አማራጮች ባሉበት ሁኔታ ማልቀስ ፣ግራ መጋባት ራስን መጉዳት ነው:: እርግጥ ነው ጨክኖ መውጣት ሊያስቸግር ይችላል:: ዓመቱን ሙሉ ከማልቀስ ከመቸገር ጨክኖ ልጆችን ወደ መንግስት ትምህርት ቤት ማስገባት የሚሻል ይመስለኛል:: እናም አሁን የተፈጠረውን ማኩረፊያ በሚገባ ተጠቀሙበት ነው::
ትምህርት ቤቶቹም አርቀው ማሰቡን ትተው የተጋነነ ጭማሪ የሚያደርጉ ከሆነ እነሱም ሊጎዱ እንደሚችሉ ማሰብ አለባቸው:: ዘንድሮ ዱሮ አይደለም፤ ፌንጣ ብትቆጣ ክንፏን ታጣ የሚል አባባል አለ:: በእኔ እይታ ትምህርት ቤቶቹ ጭማሪውን ሃላፊነት በሚሰማው መልኩ የማያደርጉ ከሆነ እርግጠኛ ነኝ እነሱም ይጎዳሉ:: አንድ ተማሪ ማጣት በዓመት ብዙ ሺ ብር ማጣት ነው:: ቤተሰብ በአብዛኛው ከትራንስፖርት ጋር በተያያዘ ልጆቹን አንድ ትምሀርት ቤት ነው የሚያስተምረው:: አንድ ቤተሰብ ሁለት ልጅ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ሊያስተምር ይችላል:: በተጋነነ የክፍያ ጭማሪ እናም ልታጡ የምትችሉትን አስቡ::
በአዲስ አበባ ዙሪያ ባለ አንድ ከተማ የግል ትምህርት ቤት ያላቸው አንድ ግለሰብ ያሉትን ልጠቅስላችሁ:: በመንግሰት ትምህርት ቤቶች ለተማሪዎች የተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎችን ተክትሎ ወደ 20 ተማሪዎች እንደለቀቁባቸው ሲናገሩም ሰምቻለሁ:: የግል ትምህርት ቤቶች ሆይ! ይህ ትምህርት ይሁናችሁ::
ዘካሪያስ ዶቢ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 27/2013