ጋዜጠኛ መሳይ ወንድሜነህ የመጀመሪያ ዲግሪውን የተመረቀው በጤናው መስክ ነው። መሳይ ከልጅነቱ ጀምሮ ምኞቱ ጋዜጠኛ መሆን ነበር። በወቅቱ የሚመድበው ትምህርት ሚኒስቴር ስለነበር መሳይ የሚፈልገውን ሙያ ሳይሆን የተመደበበትን ተማረ። ግን ፍላጎቱ ያለው ጋዜጠኝነት ላይ ነበር።
አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለ የሚያደርገውን የጋዜጠኝነት ሙያ እንቅስቃሴ ዩኒቨርሲቲ ሲገባም ቀጠለበት። በሚኒ ሚዲያና በአማተር የጋዜጠኝነት ክበባት እየሰራ ከዩኒቨርሲቲ ተመርቆ ወጣ። ከዚያም ሥራ ተቀጠረ። ግን ጋዜጠኝነት ከልቡ አልራቀም። የተመደበበትን ሥራ ከስድስት ወራት በላይ ሊቆይበት አልቻለም። በዚህም ከተመደበበት አካባቢ ትቶት ወደ አዲስ አበባ መጣ።
ጋዜጠኝነትን ለማግኘት ትክክል ነው ብሎ የወሰነው ውሳኔ ይሄው ነበር። አዲስ አበባ ውስጥ ያለምንም ሥራ ተቀመጠ። ሥራው የጋዜጠኝነት ሥራ መፈለግ ነበር። ምኞትህ ይሳካ ሲለው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ለኤፍ ኤም አዲስ 97 ነጥብ1 ማስታወቂያ አወጣ። ጋዜጠኛ መሳይ ተወዳድሮ ፈተናውን አለፈ። ጋዜጠኛም ሆነ።
በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ለበርካታ ዓመታት በጋዜጠኝነት ያገለገለው ጋዜጠኛ መሳይ ወንድሜነህ አሁን የ‹‹ጊዜ መልቲ ሚዲያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር›› መስራችና ሥራ አስኪያጅ ሲሆን፤ በኢቢኤስ ቴሌቪዥን የሚተላለፈው ‹‹ማን ከማን›› ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ ነው።
ጋዜጠኛ መሳይ ወንድሜነህ ‹‹ጋዜጠኝነት ሙያ ነው›› ይላል። ‹‹ጋዜጠኝነት ሙያ ነው ሙያ አይደለም›› የሚለውን ክርክር አይቀበልም። ጋዜጠኝነት ፍላጎት ብቻ ሳይሆን ሙያ ነው ብሎ ስለሚያምንም የጋዜጠኝነት ሥራን በያዘ በዓመቱ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ተምሯል። ፍላጎቱና ተሰጥዖው ቢኖረውም ሳይንሱን መማር እንዳለበት ያምን ነበር። ትምህርቱን ከተማረ በኋላም ጋዜጠኝነት በትክክል ሙያ መሆኑን አይቷል።
በጋዜጠኝነት ሥራ ውስጥ የሚገባ ሰው ሙያው የሚፈልገውን ትምህርት መማር አለበት። የጋዜጠኝነት አዘጋገብ መርሆዎችና መንገዶች አሉት፤ ዜና የራሱ ሳይንስ አለው። ይህ በሌለበት የድምጽ ማማርና ፍላጎት ብቻውን ጋዜጠኛ ሊያሰኝ አይችልም ይላል።
ጋዜጠኝነትን ሳይማሩ ተወዳጅ የነበሩ ጋዜጠኞችን እንደ ምሳሌ ለሚጠቅሱት ጋዜጠኛ መሳይ ሌላ መልስ ያስቀምጣል። እነዚያ ሰዎች በወቅቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ትምህርት ክፍሉ ባይኖር እንኳን ውጭ አገር ሄደው የተማሩ ናቸው። የጋዜጠኝነትን ሳይንስ ያወቁ ነበሩ። ግን ‹‹የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት ባይኖርስ?›› እስከማለት ደርሷል። በውጭው ዓለም ጋዜጠኝነት ሙያ ነው። እንዲያውም እየተከፋፈለ ወደ ልዩ ልዩ ሙያዎችም እያደገ ነው። በአንድ ጉዳይ ላይ እንኳን ተለይቶ ነው የሚሰራበት። ስለዚህም ሙያ መሆኑን መቀበል ይገባል ይላል።
ጋዜጠኝነት ከ1980ቹ በፊትና በኋላ የተለያየ ገጽታ እንዳለውም ጋዜጠኛ መሳይ ይናገራል። ከ1980ቹ በፊት የግል መገናኛ ብዙኃን ስላልነበሩ ጋዜጠኝነት የሚወሰነው በመንግስት ሥር ባሉት ተቋማት ብቻ ነው። ከ1980ዎቹ ወዲህ ግን ብዙ የህትመት ውጤቶችና የኤፍ ኤም ጣቢያዎች በመከፈታቸው ጋዜጠኝነት መልኩን ቀይሯል። ሙያውን በሚገባ የሚያውቁትና ችሎታው ላላቸው ሰዎች የመስራት ዕድል መስጠቱና የጋዜጠኝነት ሳይንስን ማስፋቱ አንዱ ሲሆን፤ ጋዜጠኝነት የተማረውም ያልተማረውም እንደፈለገ የሚሰራበት መሆኑ ሌላው እንደሆነ ያስረዳል።
የአሐዱ ኤፍ ኤም 94ነጥብ3 ሥራአስኪያጅ ጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ‹‹ጋዜጠኝነት ሙያ ነው›› በሚለው ሃሳብ አይስማማም። ምክንያቱም ጋዜጠኝነት ፕሮጀክት ስለሆነ ነው። ይሄውም በተለያየ ጉዳይ ላይ የሚሰራ መሆኑ ነው። የሰሞኑን የአቶ ክንፈ ዳኜው መያዝ እንደ ምሳሌነት ያነሳል። ይህን ጉዳይ የሚሰራ ጋዜጠኛ የህግ ጉዳዮችን ያነባል፤ ስለብረታብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ታሪካዊ ዳራዎችን ያሰባስባል፤ በዚህ ዙሪያ የሆኑ መረጃዎችን ካሰባሰበ በኋላ የአቶ ክንፈን ጉዳይ ይጨርሳል። ሌላ ቀን ደግሞ ስለኢንዱስትሪ ፓርክ ሊሰራ ይችላል፤ አሁንም ሌላ ቀን የጤና ጉዳይ ወይም የግብርና ጉዳይ ይሰራል። ስለዚህ ጋዜጠኝነት እንደየሁኔታው የሚቀያየር ፕሮጀክት መሆኑን ነው የሚገልጸው።
ሙያ የሚባለው በአንድ ጉዳይ ላይ ያጠና እና በዚያ ጉዳይ ላይ ብቻ የሚሰራ እንደሆነ የሚናገረው ጋዜጠኛ ጥበቡ፤ የጋዜጠኝነት መርሆዎች የሚባሉት በሥልጠናና በማንበብ ይገኛሉ። ጋዜጠኝነት ማንበብና ነገሮችን ማወቅ ነው። ለዚህም የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት ሳይገቡ ብዙ የምርመራ ዘገባዎችን የሚሰሩ ጋዜጠኞች ምስክር ናቸው ይላል።
የጋዜጠኛ ጥበቡ የሥራ አጋር ጋዜጠኛ ጌጥዬ ያለው ግን በዚህ አይስማማም። ጋዜጠኝነት ሙሉ በሙሉ ሙያ መሆኑን ነው የሚናገረው። ሙያውንም ከህክምና፣ ከህግ ባለሙያ እና ከኪነ ሕንጻ ባለሙያ ጋር ያነጻጽረዋል። እያንዳንዱ ሙያ ፍላጎትና ተሰጥዖ አለው። ጋዜጠኝነት በፍላጎትና በተሰጥዖ ብቻ የሚሰራ ነው የሚለው ትክክል እንዳይደለም ያስረዳል።
አንድ የኪነ ሕንጻ ባለሙያ(አርክቴክት) ከልጅነቱ ጀምሮ ሥዕል የመሳልና ቅርጻቅርጽ የማውጣት ፍቅር ቢኖረውም ትምህርቱ ካልታከለበት ግን ህንጻና ሌሎች የጥበብ ሥራዎችን ሊያከናውን አይችልም። ስለዚህም ጋዜጠኝነትም ይህ ነው ይላል።
ጋዜጠኛ ጌጥዬ እንደሚለው፤ ጋዜጠኝነት የሚለካው በዜና ነው። ዜና ደግሞ እንደማንኛውም የሳይንስ ትምህርት ቀመር ያስፈልገዋል። የራሱ የአቀማመጥ ሥርዓት፤ የምንጭ አጠቃቀምና ለህትመትና ለብሮድካስት የሚሰራ ዜናም እንዲሁ የየራሱ ባህሪ አለው። ይህ ደግሞ ሳይንስ ነው። የጋራ መግባቢያ ቋንቋ ያለው እንደሆነም ያስረዳል።
እንደ ጋዜጠኛ ጌጥዬ ገለጻ፤ ማራኪ የሆነ የስነ ጽሑፍ አቀራረብ የዜና ባህሪ አይደለም። ለምሳሌ አንድን ግጥም ለአንድ ሃያሲ ቢሰጥ ጥሩ አይደለም ሊል ይችላል። ያንኑ ግጥም ሌላ ሰው ብናስነብበው በጣም ሊያደንቀውና የተለየ ቅኔ ሊያወጣለት ይችላል። በዜና ግን ይሄ ባህሪው አይሆንም። አንድ በትክክል ያልተጻፈን ዜና ለአሥር አርታዒ ብንሰጠው አሥሩም ሊጥሉት ይችላሉ፤ ምክንያቱም የጋራ መግባቢያ ቋንቋ አላቸው፤ ሳንይንስም ነው።
በባህዳር ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ዶክተር አደም ጫኔ ለጋዜጠኛ ጥበቡ በለጠ ሀሳብ መልስ አላቸው። ጋዜጠኝነት በባህሪው ብዙ ነገሮችን ይነካል። ህክምናን፣ ህግን፣ ግብርናን ወዘተ። ነገር ግን ይህንን ሁሉ ሲያደርግ ወደራሱ አምጥቶ በጋዜጠኝነት ቀመር ብቻ መሆኑን ያስረዳሉ። ስለምህንድስና ሲዘግብ ከራሱ ቀለበት ሳይወጣ ነው። ዲዛይኑ እንዲህ ነው መሰራት ያለበት ሊል አይችልም። መገናኛ ብዙኃን ሲባልም ብዙሀኑን ለማገናኘት የሚችል በዜና አውታሩ መሆኑን ለመግለጥ እንደሆነ ይናገራሉ። ስለዚህም የጋዜጠኛ ብቃት የሚለካው በዜና መሆኑን ያስረዳሉ።
አንድ ሙያ ‹‹ሙያ›› የሚባለው የራሱ የሆነ ሙያዊ ቃላትና መለኪያዎች ሲኖሩት እንደሆነ የሚያስረዱት ዶክተር አደም፤ ጋዜጠኝነት ደግሞ ይህ ባህሪ አለው። ማንም ሰው ጋዜጠኛ መሆን ይችላል የሚለው ትክክል አይደለም። ፈቃድ የሌለው ስለሆነ ግን ማንም ሰው የሚሰራው መስሏል ይላሉ።
እንደ ዶክተር አደም ገለጻ፤ አንድ የህግ ባለሙያ የህግ ምሩቅ መሆኑን የሚገልጽ ማስረጃ ከሌለው አይሰራም፤ በጋዜጠኝነት ግን ይህ ስለማይደረግ ማንም መሥራት የሚችለው ሙያ እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል። በውጭ አገራት ግን ፈቃድ እየተሰጠው ነው የሚሰራው። እንደ ቻይና እና ህንድ ያሉ አገራት ጋዜጠኝነትን እንደ ሙያ ነው የሚያዩት። የጋዜጠኝነት ትምህርት የሌለው በዘርፉ ተሰማርቶ አይሰራም። ስለዚህ ሙያ መሆኑ አጠያያቂ ሊሆን አይገባም ይላሉ።
ወደ እውነታው ስንመጣ ደግሞ በሀገራችን የጋዜጠኝነት ሙያ በፈተና ውስጥ መሆኑን የሚናገሩ በርክተዋል። ምክንያቱም ማንም በሚዲያ ላይ ለመስራት የፈለገ ሰው ሁሉ ካለምንም ገደብ መሰማራት ይችላል። ፈቃድ ለማውጣትም ቢሆን ፍላጎት ብቻ በቂ ሆኗል። ማውራት የሚችል ሁሉ በኤፍ ኤም ጣቢያዎች፤ መፃፍ የሚችለው ደግሞ በህትመት ሚዲያዎች፤ አንዲሁም የአየር ሰዓት ገዝቶ በቴሌቪዥን መስራት የፈለገም ካልምንም የሙያ ፈቃድ በመስራት ላይ ይገኛል። ይሁን አንጅ ከሙያው ሰነ ምግባር አንፃር ሲመዘን ደግሞ ይህ ተገቢ አለመሆኑን ብዙዎች የተዛቡ ዘገባዎችንና የግል አመለካከቶች መንፀባረቃቸውን በዋቢነት በመጥቀስ እንደመከራከሪያ ያነሳሉ።
ዋለልኝ አየለ