በዛሬው አዲስ ዘመን ድሮ ዓምዳችን ወደ 1969 ዓ.ም እንመልሳችኋለን።ይህ ዓመት ሶማሊያ በምስራቅ በኩል ኢትዮጵያን የወረረችበት እና ኢትዮጵያውያን ይህን ወረራ ለመመከት ሆ ብለው የተነሱበት ነበር።ያኔ ህዝቡ ወራሪውን የሶማሊያን ጦር ከሀገሪቱ ጠራርጎ ለማስወጣት ያደርግ የነበረውን እንቅስቃሴ አዲስ ዘመን ይዘገብ ነበር።ከሀገር ህልውና ጋር የተያያዙ ተመሳሳይ ዘገባዎች በአሁኑ ወቅትም እየተሰሩ እንደመሆናቸው ከዚያን ዘመኖቹ ዘገባዎች ጥቂቱን ዛሬ ይዘን ቀርበናል ።መልካም ንባብ።
የፖሊስ የሙዚቃ ክፍል ለዘመቻው 6ሺ ብር ሰጠ
ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
የፖሊስ ሠራዊት የሙዚቃና የቲያትር ክፍል የውይይት ክበብ አባሎች በመተሐራ፣ በአሰላ፣ በወንጂ፣ በሸዋ ስኳር ፋብሪካና በናዝሬት ከተሞች ለሚኖረው ሕዝብ አብዮታዊ ቲያትር በማሳየት ያገኙትን ስድስት ሺህ ብር በግንባር ቀደምትነት ለሚዘምተው ሕዝባዊ ሠራዊት ዝግጅት እንዲውል ባለፈው ሳምንት አስረክበዋል፡፡
ሻለቃ ደበላ ዲንሳ የደርግ አባልና የአዲስ አበባ ከተማ የአብዮትና ልማት ኮሚቴ ሊቀመንበር ፤የሠራዊቱ የቲያትርና የሙዚቃ ጓድ አባሎች የእናት ሀገር ጥሪ ለመቀበል የሰበሰቡትን ይህን ገንዘብ በተረከቡበት ወቅት ባደረጉት ንግግር የተደረገው ርዳታ ታላቅ አርአያነት ያለው መሆኑን ጠቅሰው አመስግነዋል፡፡
በዚሁ አጋጣሚ የሻለቃ ደበላ በአሁኑ ጊዜ ስላለው የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ፤ለአባሎቹ በመዘርዘር ካስረዱ በኋላ ፤ማንኛውም ግለሰብ በዕውቀቱ፣ በጉልበቱ፣ በገንዘቡ እና በሕይወቱ ጭምር መሥዋዕት በመሆን የእናት ሀገሩን አንድነትንና አብዮቱን ለመንከባከብ በቆራጥነት መነሳቱን ገልጠዋል፡፡
ከዚህ ቀደም ሲል ርዳታውን ካስረከቡት የሠራዊቱ የቲያትርና የሙዚቃ አባሎች መካከል የ፲ አለቃ አበበ ኃይሉ ባደረጉት ንግግር አባሎቹ ፫ ሺ፫፻፳፰ ብር ፫ ሳንቲም ከደመወዛቸው ተቆራጭ ሆኖ በፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ዋና መምሪያ ሒሳብ ክፍል በኩል ለዚሁ በተቋቋመው ኮሚቴ እንዲደርስ ማድረጋቸውን ገልጠዋል፡፡
የሠራዊቱ የቲያትርና የሙዚቃ ጓድ አባሎች ያለ እረፍት አምስት ቀን ሙሉ በማከታተል በአምስቱም ከተሞች ተገኝተው አብዮታዊ ቴያትር በማሳየት ያገኙትን ስድስት ሺህ ብር ለዘመቻው እንዲውል ያደረጉት ርዳታ የመጀመሪያውን እንጂ የመጨረሻው አለመሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡
ሰኔ 4 ቀን 1969 ዓ.ም
ታክሲ ነጂው በግንባር ቀደምትነት ለመዝመት ተዘጋጅተዋል
(በአዲስ ዘመን ጋዜጠኛ)
የእናት ሀገር ጥሪን የተቀበሉና ከአገር የሚበልጥ ነገር አለመኖሩን የተረዱ የታክሲ ሹፌር በግንባር ቀደምትነት ከሚዘምተው ሠራዊት ጋር አብረው ለመዝመት ባላቸው ቁርጠኝነት አስቸኳይ የንቅናቄ ትዕዛዝ እንዲሰጣቸው ከመጠየቃቸውም በላይ ዘማቹን ሠራዊት የሚመሩ አዛማቾች የሚጠቀሙበት አንድ የሸራ ድንኳን በዕርዳታ ሰጥተዋል፡፡
አቶ በየነ ተመስገን የተባሉት እኝሁ አገር ወዳድ ከዘማቹ ሠራዊት ጋር በግንባር ቀደምትነት ዘምተው
በዘመቻው ሥፍራ ስድስት ወር ያለ ደመወዝ በነፃ በከባድ መኪና ሾፌርነት አገራቸውንና ወገናቸውን ለማገልገል ቃል የገቡ ሲሆን፤በሁለተኛና በሦስተኛ ተራ ሳይባል በአስቸኳይ በግንባር ቀደምትነት እንዲዘምቱ ወስነው የዘመቻውን ትዕዛዝ በመጠባበቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ስድስት ወር በነፃ በሹፌርነት ለማገልገል ቆርጠው ከመነሳታቸውም በላይ በ፩ሺ፫፻ ብር የገዙትን ውሃ የማያስገባና ፲ ሰው የሚይዝ የግላቸው የሆነ ድንኳን ለእናት ሀገር ጥሪ በቅርቡ መስጠታቸውን ገልጸዋል፡፡
የቀድሞ የክቡር ዘበኛ ባልደረባ የነበሩት አቶ በየነ ለአገራቸውና ለወገናቸው መሥራት የጀመሩት ዛሬ ብቻ ሳይሆን ከአሁን በፊትም በሻሸመኔ ከተማ የግላቸው የነበረውንና በወር ፩፻፶ ብር የሚከራየውን ለድርቅ ርዳታ ማቋቋሚያና ማተባበሪያ ኮሚሽን ለአንድ ዓመት የእህል ማከማቻ እንዲሆን ሰጥተው በረሀብ የተጠቁትን ወገኖቻቸውን መርዳታቸው በማስረጃ ተረጋግጧል። እንዲሁም በግል ሀብታቸው የገዙትን ልዩ ልዩ የጦር መሣሪያዎች ቀድሞ አርሲ ለነበረው ንዑስ ደርግ ሲያስረክቡ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ በከፍተኛ ፳ ቀበሌ ፶፩ ልዩ ልዩ ዕርዳታና አገልግሎት በማበርከት ወገናቸውን ረድተዋል፡፡
ከዚህም በቀር የሀገሪቱ የዱር አራዊት ሀብት እንዳይባክን፤በተለይም በዓለም የማይገኙ ብርቅና ድንቅ የሆኑ አራዊቶች እንዳይጠፉ በራሳቸው ወጪ መንገድ በማሠራት፤ አራዊቱን ከአዳኞች በመጠበቅና ሕገ ወጥ አዳኞችን በማስቀጣት በሥራው መተባበራቸውን አስረድተዋል፡፡አቶ በየነ በአሁኑ ጊዜ በታክሲ ሹፌርነት ተቀጥረው የሚሠሩ የስምንት ቤተሰብ አስተዳዳሪ አገር ወዳድ ናቸው፡፡
ሰኔ 24 ቀን 1969 ዓ.ም
አንድ ሚሊዮን ውሸት
ውሸት ያለቀባቸው የሞቃዲሾ መሪዎች ያሻሻሉት ብሔራዊ ልማት ቢኖር የውሸት ት/ቤት ከፍተው በሬዲዮ
ጣቢያቸው የሀሰት ድቤ መደወል ነው፡፡
ግንቦት ፲፫ ቀን ፲፱፻፷፱ ዓም ነፃ አውጪው ከአዲስ አበባ በስተቀር የኢትዮጵያን ክፍለ ሀገሮች በሙሉ ይዞ በቁጥጥር ሥር አድርጓል በማለት አንድ ሚሊዮን ውሸት ዋሽተዋል፡፡ይህ የሞቃዲሾ መሪዎች መላምት የሕፃን ፖለቲካ ስለሆነ ያስቃል፡፡
ከዚህ በፊት የኤርትራ ክፍለሀገርና የሰሜንና የበጌምድር ክፍለሀገር በቁጥጥሩ ሥር ሆነዋል፤ ነገ ወይም ማታ አስመራና ጎንደር ይገባሉ ብለው እንደነበር በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ ተረትና ምሳሌ ከመሆኑም ሌላ በቀልድና ጨዋታ ጊዜ አሁንስ የሞቃዲሾ ድቤ ሆንህ በማለት መሳቂያና መዘባበቻ ሆነዋል፡፡
የሚገርመን ነገር ቢኖር አስቂኙ የሞቃዲሾ ሬዲዮ ጣቢያ ያበሻው መንግሥት ሀበሻ ያልሆኑትን ሀገሮች ለሶማሊያ ማስረከብ አለበት ይላል፡፡እኛም ኢትዮጵያውያን ለሞቃዲሾ መሪዎች የምናሳስባቸው ከኢትዮጵያ መሬት እንወስዳለን ከማለት ይልቅ ሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ ትመለሳለች ማለቱ ይቀላል፤ የሶማሌ ሕዝብ ምኞቱ ነውና፡፡
ስለዚህ ነው እኛ ኢትዮጵያውያን የሥጋችን ቁራጭ፤ የአጥንታችን ፍላጭ የሆኑት ነፃነታቸውን አግኝተው ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ከቅኝ ገዥዎች ስንታገል ብልጡ የእንግሊዝ መንግሥት በኢትዮጵያ መሬት ላይ ለመኖር የማያዋጣው መሆኑን ስለተረዳ ኢትዮጵያን ለማዳከምና ለመከፋፈል ከኢጣሊያ ተሻርከው ለሞቃዲሾ መሪዎች ሸጦ የሄደው፤ አሁንም ቢሆን ለሰው ልጆች ዕኩል እንደምናስብ ሁሉ የሞቃዲሾ ቅኝ ግዛት የሆነች የበርበራ ባለንብረት ሀርጌሳ ከቅኝ ግዛት ተላቃ የራስዋን ብሔራዊ መብት እንድትመሠርት ምኞታችን ነው፡፡
እዝራ ኑርልኝ
ሰኔ 26 ቀን 1969 ዓ.ም
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2013