የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ልማት ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ዋና ተልዕኮው በዘርፉ የሰው ኃይል ማብቃት ነው። ይህም በአጠቃላይ ዘርፉን የሚደግፉ የቴክኖሎጂ ዕውቀትና ክህሎት ያላቸው ባለሙያዎች እንዲፈጠሩ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ነው።ፋብሪካዎቹም በቂ ገበያ እንዲያገኙ ይደግፋል።
የኢንስቲትዩቱ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ባንቲሁን ገሰሰ ኢንስቲትዩቱ አጠቃላይ የማማከር አገልግሎት በመስጠት፤ በጨርቃ ጨርቅ አልባሳት በጥጥ ዘርፉ ዙሪያ የተሰማሩ ፋብሪካዎቹንም እርሻዎቹንም ሁሉ በማካተት ለባለሀብቶቹንና ለፋብሪካዎቹን ሙሉ ድጋፍ ይሰጣል።ድጋፎቹ ቴክኒካል እንዲሁም የኢንዱስትሪ ባህሉና አመራሩ ለማሳደግ የሚያስችሉ ረጅምና የአጭር ጊዜ የአመራር ሥልጠናዎችን ናቸው ሲሉ አቶ ባንቲሁን ያስረዳሉ።
አቶ ባንቲሁን እንደተናገሩት በጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪው የሚሰማሩ ኦፐሬተሮች ባለሙያዎች ሱፐርቫይዘሮች ሁሉ እንዴት ተቀናጅተው ፋብሪካውን መምራት እንዳለባቸው ዕውቀትና ክህሎት የማስጨበጥ ሥራዎችን ናቸው።ባለሙያዎቹም ሙሉ ዕውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው አጫጭር ሥልጠናዎች እያዘጋጀ ይሰጣል፡፡
በኢንስቲትዩቱ የስፌት፣ የሽመና አሠራር፣ የፊኒሺንግ ሥራዎች ቴክኖሎጂዎች፣ የምርመራና ላቦራቶሪ ሥራዎች እና የልብስ ስፌት የተለያዩ ዘመናዊ የሆኑ ቴክኖሎጂዎች መሣሪያዎቹን ተጠቅሞ በየጊዜው የዲዛይንና የፋሽን ሥራዎቹ ዘመናዊ እየሆኑ ከወቅቱ ጋር አብረው እንዲሄዱ የሚያደርጉ ሥልጠናዎችን እያዘጋጀ ለኢንዱስትሪ አመራሮች ባለሙያዎችና ለኦፕሬተሮች በኢንስቲትዩቱ ውስጥ ሥልጠናዎችን ያዘጋጃል።በፋብሪካዎቹም ሄዶ ክፍተታቸውን በማጥናትና ክፍተታቸውን ለመቀነስ የሚያስችል ሥልጠናዎችን ይሰጣቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ልማት ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ፋብሪካዎቹ ተወዳዳሪ ብቃት ጥራትና ብዛት ያለው ምርት እንዲያመርቱ የሚያስችል ዕውቀትና ክህሎት ባለሙያዎቹ እንዲታጠቁ የማድረግ እና ለፋብሪካዎቹ ደግሞ በቂ ድጋፍ እንዲያገኙ የማመቻቸት ሥልጠናዎችን የመስጠት ሥራዎችንም ይሠራሉ፡፡
በፋሽን ዘርፍ በጣም ብዙ ለውጦች ቢኖሩም ኢትዮጵያ ውስጥ ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ላይ የነበረው የሙያ ክህሎት በጣም ደካማና ከባህላዊነት አለመላቀቁን ብዙ ማሳያዎች መጥቀስ ይቻላል።በመሆኑም ባህላዊውን በጣም የማዘመንና ወደ ፋሽን የማሳደግ ሥራዎችና እነዚህን ባህላዊው ልብሶች ወደ ዘመናዊ የመቀየር፤ ባለሙያዎቹ በዚህ መንገድ ሥራቸውን እንዲሠሩና ድጋፍ እንዲያደርጉ ፋብሪካዎቹም ይህን የሚሠጣቸውን ሥልጠና ተጠቅመው ተወዳዳሪ የሆነ ምርት እንዲያመርቱ ዕውቀትና ክህሎት እንዲኖራቸው የሚያደርግ ሥራዎች በኢንስቲትዩቱ ተሰርተዋል።
የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎች ከንድፈ ሀሳብ በስተቀር በተግባር ብዙም ዕውቀቱ ስላልነበራቸው ለማብቃት የረጅም ጊዜ የጨርቃ ጨርቅና የአልባሳት ዘርፍ ልምድና ተሞክሮ ካላት ህንድ ጋር ቁርኝት በማድረግ በሦስተኛ (ዶክትሬት) እና በሁለተኛ ዲግሪ ወደ 70 የሚደርሱ ባለሙያዎችን በረጅም ጊዜ ሥልጠና መሰለጠናቸው በዘርፉ የሚሠሩ ሰዎችን ለማብቃት ሚና እንዳለው አቶ ባንቲሁን ይናገራሉ ። በተጨማሪም የድሬዳዋና ባህርዳር ዩኒቨርሲቲዎችን ጨምሮ ከ6 በላይ ከሆኑ የተለያየ ቴክኖሎጂ ካላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ ትምህርት እንዲስፋፋና በዩኒቨርሲቲዎች እንዲሰጥ የማድረግና በቂ ባለሙያዎች ለማፍራት የሚያስችል ሥራዎች መሠራታቸውን ነው አቶ ባቲሁን የሚያስረዱት፡፡
ከህንድ የሰለጠኑት የኢንስቲትዩቱ ሰዎች ከፋብሪካዎች ጋር በመቀናጀት ያለባቸውን ችግር እየለዩ በቂ የሆነ ሥልጠና እንዲያገኙ የማድረግ ሥራዎች በተከታታይ ይሠራሉ።በዚህም በጣም ሠፊ የሆነ ለውጥ መጥቷል፤ በረጅም ጊዜ ትምህርት በየኢንዱስትሪ ፓርኩ የተለያዩ የጨርቃ ጨርቅ ባለሙያዎች እየተፈጠሩ ነው ።ፋሽናዊ የሆነ በፋሽንም ባህላዊውን የማዘመን ወደ ፋሽን የመቀየር ከባህላዊ አሠራር በመውጣት ዘመናዊ አሠራርን እንዲከተሉ ተወዳዳሪና ምርታማ እንዲሆኑ ፋብሪካዎቹ ምርትን የማሳደግ እና ወደ ውጪ ሄዶ ሠፊ ገበያ የሚያገኙበት እና በዓለም ባለው ገበያ በስፋት እንዲሠማሩ በየጊዜው የተለያዩ ሥልጠናዎች ይሠጣሉ፡፡
የኢንስቲትዩቱ ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አሁን የተሻሉ ባለሙያዎች በዘርፉ እየተፈጠሩ መሆኑን ይጠቁማሉ። የኢንስቲትዩቱ ባለሙያዎችና በዩኒቨርሲቲዎችም በየጊዜው ጥናት እየተደረገ ሥልጠና ይዘጋጃል። በጥናቱ መሠረት ክፍተት እየተሞላ በየጊዜው የተሻለ ባለሙያ እየተፈጠረ ነው።በሀገሪቱ የሠራተኛው የመሥራት ክህሎቱና አመለካከቱ እንዲሁም ምርትና ምርታማነት እያደገ ነው።በዛም ኢንዱስትሪዎች የተሻለ አፈጻጸም እያስመዘገቡ መጥቷል፡፡
በኢንስቲትዩቱ የፋሽንና ዲዛይን ሥራዎች የሚመለከት የጋርመንት ልብስ ስፌት ቴክኖሎጂ ዲፓርትመንት አለ።ዲዛይኖቹ በኮምፒውተር ሲስተም በየጊዜው እየተዘጋጁ በጣም ተወዳዳሪ እና ፋሽን የሆኑ ጨርቆች እንዲመረቱ ከማድረግ አኳያ አልባሳቱን በየጊዜው በማሻሻልም ሥልጠና ይሰጣል።የሚሰጠው ለፋብሪካ ሠራተኞች አመራሮችና ሙያተኛዎች ብቻ አይደለም፤ በቴክኒክ ሙያ የተሠማሩ መምህራን ሱፐርቫይዘሮችና ርዕሳነ መምህራንም ጭምር ነው ፡፡በኢንስቲትዩቱ በጣም ዘመናዊ የሆኑ ቴክኖሎጂዎች ስላሉ ማለት ነው ሲሉ አቶ ባንቲሁን ያስረዳሉ፡፡
በኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ልማት ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ሙያተኛ መምህራን ቴክኖሎጂውም አለ።በኮምፒውተር እንዴት ሥራዎች መሥራት ምርቶችን እንዴት ማዘመንና ፋሽን ማድረግና ከወቅቱ ጋር ማራመድ እንደሚቻል እያንዳንዱን ነገር ሊያሳይ የሚችል ዘመናዊ መሣሪያ ስላለ በየጊዜው ሥልጠናዎች ይሰጣሉ።ከፋብሪካዎች የሚሰበሰቡ ግብረ መልሶች 80በመቶዎቹ በሥልጠናው አግዛችሁናል የሚል መሆኑን የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ።በህንድ የሰለጠኑት ባለሙያዎች ፋብሪካ ድረስ ሄደው በተግባር እያሰለጠኑ በዘርፉ የነበረውን ችግር እያቀለለው መጥቷል፡፡
በጥቃቅንና አነስተኛ ለተደራጁትም በፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪዎች ጥያቄ ሲመጣ ሥልጠና እንደሚሰጥ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ያስረዳሉ።አንዳንድ ቦታ አመራር የቤተሰብ ይሆንና ለሥራው መሰናክል ይፈጥራል፤ አመራሩን ለባለሙያዎች ቢለቁት የበለጠ ውጤታማ ይሆናሉ።በዘርፉ በርካታ ባለሙያዎች እየተፈጠሩ ነው።ለባለሙያዎችም ቦታ ቢሰጣቸው አቅማቸውን ገበያቸውንም ያሳድጋሉ ፋሽኑንም ዲዛይኑንም ለማሳደግ ባለሙያዎችን መጠቀሙ ተመራጭ መሆኑን የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ልማት ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተሩ ይመክራሉ፡፡
በኢንስቲትዩቱም የተለያዩ ባለሙያዎች እየለቀቁ ነው ያሉት ዕውቀቱ ክህሎቱ አላቸው፤የተሻለ ክፍያ ወዳለበት እየፈሰሰ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የወጣቱን ትውልድ የፋሽን ፍላጎት ለማሟላት በጣም ፋሽን የሆኑ ጥሩ ዲዛይን ያላቸው ልብሶች ማምረት ያስፈልጋል ፡፡የሚፈልጋቸውን የፋሽን ምርቶች ለማምረት ብቃት ተወዳዳሪና የሙያ ክህሎት ያለው የፋሽንና የዲዛይን ባለሙያ እና አመራር ያስፈልጋል።
የኢንዱስትሪ አምራቾቹ የመምራት ችሎታቸው እየለመዱት መጥተዋል ክህሎታቸውን እያሳደጉ መጥተዋል፤ በአመለካከት ደረጃ ሙያተኛውም ሠራተኛውም አመራሩም በትኩረት በዕቅዳቸው መሠረት ሥራ ቢሠራ ውጤት እንዴት ማምጣት እንደሚቻል በየፋብሪካው እያረጋገጡ ነው ያሉት።
ዘርፉን ለማገዝ ብዙ ሥራዎች ይሠራሉ፤ጨርቃ ጨርቅና አልባሳት በሀገሪቱ ሠፊ ገበያ አላቸው ለዘርፉም የተመቸች ናት።ያለው ሠፊ ጉልበት ለመጠቀምም ለፋብሪካው ምቹ ነው፡፡
ኃይለማርያም ወንድሙ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2013