የሴት ልጅ ውበት ሲታሰብ ተደጋግሞ ከሚጠሩት መካከል አንዱ ወገብ ነው። ችቦ አይሞላም ወገቧ ማር እሸት ነው ቀለቧ መባሉስ ለእዚህ አይደል።ወገብ በአለባበስ ይበልጥ ወጥቶ እንዲታይ የሚያርጉም ሞልተዋል። ምክንያቱም ውበት ነዋ።በተለይ ሞዴሊስቶች ለወገብ ትልቅ ስፍራ ይሰጡታል። በሚገባም ይጠብቁታል። ብቻ ወገብ በሴቶች ዘንድ ብዙ ዋጋ ያወጣል። ታዲያ ችቦ አይሞላም …ሲሆን ነው፡፡
ኦዲቲ ሴንትራል የተሰኘው ድረ ገጽ ሰሞኑን ወገቧን በጣም ማቅጠን ስለቻለች አንዲት ሴት አስነብቧል። ችቦ አይሞላም ወገቧ ሆነች እንበል ይሆን? ኧረ ከዚያም ልታቀጥነው አስባ ተሳክቶላታል። ቬትናማዊት ናት። የወገቧን ዙሪያ ገባ 46 ሴንቲሜትር ለማድረግ አቅዳ ብዙ ደክማለች እቅዷን ለማሳካትም በቅድሚያ አመጋገቧ ላይ ነው እርምጃ የወሰደችው። በቀን አንዴ ብቻ መመገብ ውጤታማ እንደሚያደርጋት አስባ ወደ መተግበሩ ትገባለች።
አን ኬዋይ የተባለችው ይህች ሴት በአሜሪካ ዳንስ ቤቶች በትርፍ ሰዓት በተወዛዋዥነት እየሰራች ነው የምትተዳደረው። እዚህ ስራ ውስጥ የገባቸውም በታወቂዋ የሀገሯ ባለመዝናኛ ተቋምና ኮሜዲያን ቴይ ኤንጋ አማካይነት ነው።
ባለመዝናኛዋ በአንድ ወቅት በአሜሪካ ጉብኝት ስታደርግ ነው ኬዋይን የተዋወቀቻት። ኬዋይ በምትሰራበት ካፌ ተቀምጣ እያለ ይህች ቬትናማዊ ኮሜዲያን የኬዋይን በጣም ቀጭን ወገብ ትመለከታለች። በወገቧም በጣም ትገረማለች።በዚህ አስደናቂ ወገብ ላይ ቪዲዮ መሰራት አለብኝ ብላም ታስባለች። ለእዚህ ደግሞ ኬዋይን መቅረብ እንደሚያስፈልግ ታምናለች፡፡
እንደፈለገችውም ኬዋይን ቀረበቻት።የወገቧ ዙሪያ ገባ 46 ሴንቲሜትር መሆኑን ተረዳች፤ እንዴት ብታደርግ ወገቧን እንዲህ አርጋ ልታቀጥነው እንደቻለች ለመጠየቅ ፈለገች። ትልቅ ስራ እንደሚፈልግ አሰበች። ደፍራም ይህን ማድረግ እንዴት እንደቻለች ኬዋይን ጠየቃቻት፡፡
ኬዋይ ወገቧን ማቀጥን መመኮር የጀመረችው ገና የ18 ዓመት ልጃገረድ እያለች መሆኑን ነገረቻት።ያኔ ክብደቷ 50 ኪሎ ግራም ነበር።የወገቧ ዙሪያ ገባ ደግሞ 60 ሳንቲ ሜትር።በአሁኑ ወቅት ክብደቷ ወደ 37 ኪሎ ግራም ወርዷል፡፡
የ26 ዓመቷ አን ኬዋይ ለጥያቄው መልስ ለመስጠት አላቅማማችም። የወገቧን መጠን ለመቀነስ ብዙ ስራዎችን መስራቷን ነገረቻት። አመጋገቧን በቀን ሶስቴ ከመብላት ወደ አንዴ መብላት ዝቅ ማድረጓን፣ አንዳንዴም በሁለት ቀን አንዴ የምትበላበት ሁኔታም እንደነበር አብራራችላት። ከዚህ በተጨማሪ ስታርች የሚበዛባቸውን ምግቦች መብላት ካቆመች ሁለት ዓመታት መቆጠራቸውን ገለጸችላት።
አመጋገብሽ በጤናሽ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሮብሽ አያውቅም ወይ ሲሉ ብዙዎች ይጠይቋት እንደነበርም ኬዋይ ታስታውሳለች። እሷ ግን በርካታ ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን፣ ዶሮ/ችክን/ እንደምትመገብና አንድ ጊዜም ቢሆን በምግብ የተነሳ የደረሰባት ችግር የሌለ መሆኑን እንደገለጸችላቸው ትናገራለች።
ሁሌም ወገቧን ጥብቅ የሚያደርግላትን አለባብስም ትመርጣለች። ለእዚህም ወገቧን ጥብቅ አርገው የሚይዙ ልጥፍ የሚሉ ልብሶችን ታዘውትራለች። ምን ይሄ ብቻ ወገቧን ጥፍር አርጋ የሚይዝ ሌላ ቁስም ታስራለች፡፡ የምታወልቃቸውም ስትተኛ ብቻ ነው፡፡
እሷን ሁሌም የሚያሳስባት ግን ሌላ ነገር ነው።ለእሷ የሚሆን የውስጥ ሱሪ ማግኘት አለመቻሏ።ይህ በእጅጉ ያሳስባታል።አዲስ የውስጥ ሱሪ ለመግዛት ገበያ በወጣች ቁጥር በልኳ ማግኘት ስለማትችል ብዙ ለመዞር ትገደዳለች። ማንኛውንም አይነት የውስጥ ሱሪ ገዝታ ለማስጠበብ ብትሞክርም ለማስጠበብ የሚያስፈልገው ወጪ የውስጥ ሱሪውን ከምትገዛበት በላይ እያስወጣት ተቸግራለች።በቃ ችግሯ ይህ ብቻ ነው፡፡
ኮሜዲያኗ ቱይ ኤንጋ በዚህች ሸንቃጣ ላይ የሰራችው ቪዲዮ ባለፈው የፈረንጆቹ ጥር በዩቲዩብ ላይ የተለቀቀ ሲሆን፣ ተመልካች ያገኘው ግን በቅርቡ ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ወገቧን አስመልክቶ መረጃ ከተለቀቀ በኋላ ነው።መረጃውን የተመለከቱት በሙሉ ግን ድርጊቷን አልወደዱትም። ሁኔታው ተፈጥሯዊ እንዳልሆነ ተችተዋል። አንዳንዶች ደግሞ ወገቧን በዚህ ልኩ ማሰሯ በውስጥ አካሎቿ ላይ ችግር አያስከትልም ተብሎ አይገመትም ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በጋዜጣው ሪፖርተር
አዲስ ዘመን ሐምሌ 26/2013