ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት የአገራቸውን ሉዓላዊነት ለማስከበርና ነፃነታቸውን ለማስጠበቅ አስደናቂ ገድሎችን ፈፅመዋል፡፡ ዛሬም እየፈፀሙ ናቸው፡፡ ዛሬ በሳምንቱ በታሪኩ አምዳችን በአገሪቱ የነፃነትና የሉዓላዊነት መጠበቅ ታሪክ ተጠቃሽ ከሆኑ ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች መካከል አንዱን አንስተን ልናወጋችሁ ወደድን፡፡
ልክ የዛሬ 85 ዓመት በዚህ ሳምንት የተከሰተውን ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ለህዝብዋ ነፃነት የተከፈለውን መስዋዕትነት መዘከር ይገባናልና መስዋዕቱ አቡነ ጴጥሮስ የተሰውበትን ምክንያትና ስለ ኢትዮጵያዊያን ነፃነት ቤዛ የሆኑበትን ስብዕናና ታሪካቸውን ዘክረነዋል። ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም አንድ ታላቅ ሁነት አዲስ አበባ ላይ ተከሰተ፡፡ አድዋ ላይ በኢትዮጵያዊን ብርቱ ተጋድሎ ድል የተነሳው ጣሊያን ለአራት አስርት ዓመታት አድብቶና ተዘጋጅቶ ኢትዮጵያን በመውረር የኢትዮጵያዊያንን ነፃነት ለመንሳት ደግም ተመለሰ፡፡ ወቅቱም ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ ኢትዮጵያን ከመርዳት ልቅ ፊቱን ያዞረበት ጊዜ ነበርና ለጊዜውም ቢሆን ጣሊያኖች ኢትዮጵያን የመቆጣጠር ሙከራ አድረገው ነበር፡፡ ኢትጵያዊያን በዱር በገደሉ በመመከት አገራቸውን ከወራሪው ጦር ለመታደግ መታተራቸውን ቀጥለዋል፡፡
አቡነ ጴጥሮስ ለኢትዮጵያ ህዝብና ለእውነት ብለው መስዋዕት የሆኑትም በዚህ ጊዜ ነው፡፡ ታሪኩ የተፈጸመው የኢጣሊያኑ ፋሺስት ጦር አዲስ አበባን በተቆጣጠረበት ወቅት ነው። አቡኑ በዱር በገደሉ ጣልያንን እረፍት ከነሱት ኢትዮጵያዊያን ጋር በማበር በከተሞችም ለኢትዮጵያ ነፃነት በብርቱ ከተፋለሙት ዋንኛ ኢትዮጵያውያን መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ብጹዕ አቡነ ጴጥሮስ ለእውነት የቆሙ ለሚጠብቁት ሕዝብ ከቃላት ባለፈ የተሰዉ ናቸው።
ህዝቡ ነፃነቱን እንዲጠብቅ እያስተማሩና እያጠናከሩ ለመጣው ጠላት እጅ እንዳይሰጥ እያበረቱ ብርቱ ትግል አደረጉ፡፡ እያደር ግን የፋሽስት ጣሊያን ወራሪ ሀይል የአቡነ ጴጥሮስ ተግባርና ስራ ደረሰበት፡፡ በዚህ ተግባራቸው እጅጉን ተቆጣ፡፡
ለህዝባቸው ነፃነት ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ሲተጉ የነበሩት አቡነ ጴጥሮስ ጠላት ጦር ፊት ለፍርድ ሊቀርቡ ግድ ሆነ። ኢትዮጵያዊ ግርማ ሞገስ የተላበሱት ቁመታቸው ረዘም ፊታቸው ዘለግ፣ መልካቸው ጠየም ያለው አቡኑ፣ አዋቂነታቸውና ትህትናቸው ከገጻቸው ይነበባል፤ አቡነ ጴጥሮስ ችሎት ሲቀርቡ ለፍርድ የተሰየሙት ዳኞች ጣሊያኖች እና የጦር ሹማምንት ናቸው። መካከለኛው ዳኛም ኮሎኔል ነበር ።
የመጨረሻው የፍርድ ሂደት
በብርቱው ኢትዮጵያዊ ጀግና ላይ የቀረበው የወንጀል ክስ “በጣሊያን ላይ ሕዝብን ቀስቅሰዋል፤ ራስዎም አምጸዋል፤ ሌሎችም እንዲያምጹ አድርገዋል” የሚል ነበር። ዳኛውም በችሎቱ ካህናቱም ሆኑ የቤተ ክህነት ሃላፊዎች፣ ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስ የኢጣልያንን መንግሥት ገዥነት አምነው አሜን ብለው ሲቀበሉ እርሶ ለምን ዓመጹ፣ ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ ?” ሲል ጠየቃቸው፡፡
አቡነ ጴጥሮስም “አቡነ ቄርሎስ ግብጻዊ ናቸው። ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም። እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ፤ ኃላፊነትም ያለብኝ የቤተክርስቲያን አባት ነኝ። ስለዚህ ስለ ሀገሬና ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆሮቆራለሁ። ከዚህ በቀር ለእናንተ ችሎት የማቀርበው ነገር የለኝም። ለፈጣሪዬ ብቻ የምናገረውን እናገራለሁ። እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ። ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለገችሁትን አድርጉ ሲሉ ምላሻቸውን ሰጡ። ግን ተከታዮቼን አትንኩ ሲሉ አስገነዘቡ። የኢትዮጵያ ህዝብ ለዚህ ጠላት እንዳይገዛ ገዘቱ፤ ‹‹የኢትዮጵያ መሬትም ጠላትን ብትቀበል የተረገመች ትሁን፡፡” በማለት በጀግንነት ተሞልተው ዳኛው ፊት ተናገሩ።
ንግግራቸው በአስተርጓሚ ለዳኞቹ የቀረበ ቢሆንም አስተርጓሚው በጳጳሱ ላይ ተጽዕኖ ስላሳደረባቸው እውነተኛ ንግግራቸው ሳይገለጥ ቀረ ። ቀጥሎም ብጹዕነታቸው በፍርድ ችሎት ላይ እንዳሉ ሕዝቡ ሁሉ ስለ ርሳቸው እያዘነ ሳለ መስቀላቸውን አውጥተው እየጸለዩ ሕዝቡን ባረኩ። ወዲያው የሞት ቅጣቱ ፍርድ ሲሰማ ሕዝቡ በኢጣልያ የእጅ ሰላምታ አይነት እጁን እንዲያነሳ ታዘዘ ።
ለመሰዋትዕነት መቅረብ
በዚያን ጊዜ አቡነ ጴጥሮስ የሞታቸው ሰዓት መድረሱን አውቀው፤ የእጅ ሰዓታቸውን ከኪሳቸው አውጥተው ተመለከቱ። ምንም አይነት ፍርሀት አይታይባቸውም ነበር ። የሞታቸውን ፍርድ ያነብ የነበረው ኢጣሊያዊው ዳኛ ግን ይንቀጠቀጥ ነበር። ታላቅ ፍርሀትም በፊቱ ላይ ይታይ ነበር። የሞት ቅጣት የተፈረደባቸው በእጹዕ አቡነ ጴጥሮስ፣ በችሎቱ ፊት ለብዙ ሰዓታት ቆመው ስለዋሉና ደክሟቸው ስለነበር ለመቀመጥ ፈልገው ዳኛውን በትሕትና በፈገግታ ጠየቁት። እንዲቀመጡ ፈቀደላቸው። የሞት ፍርዱ ከተነበበ በኋላ የፈረዱባቸውን ዳኞች በመስቀላቸው ባረኳቸው ።
ፍርድ ከተሰጠበት ስፍራ 10 ሜትር ርቆ ወደሚገኝ ቦታ ተወሰዱ። ከገዳዮቹም አንዱ ቀርቦ “ፊትዎን ለመሸፈን ይፈልጋሉን ?” ሲል ጠየቃቸው። ይህ የአንተ ስራ ነው ሲሉ ብጹዕነታቸው መለሱ። ከዚያም በኋላ 8 ወታደሮች ከበስተጀርባቸው ሃያ እርምጃ ርቀው ተንበርክከው በተጠንቀቅ ቆሙ። ወዲያው አዛዡ “ተኩስ” በማለት ትዕዛዝ ሲሰጥ። ስምንቱም ተኩሰው መቷቸው። ግን በስምንት ጥይት ሳይሞቱ ቀሩ። መሞታቸውን እና አለመሞታቸውን ለማረጋገጥ ዶክተር ተጠራ። ዶክተሩም እንዳልሞቱ አረጋገጠ። ከዚያም ሌላ ወታደር በሦስት የሽጉጥ ጥይት ራስ ቅላቸውን መትቶ ገደለቻው።
ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ማን ናቸው?
የእኚህን ታላቅ ኢትዮጵያዊ ታሪክ እዚህ ላይ ማንሳቱ እጅጉን አስፈላጊ ነው፡፡ ይህም ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያዊያን ነፃነትና ህልውና ራሳቸውን የሰጡበት ስብዕናቸው በምን መልክ ተገነባ የሚለውን ለማወቅ ይረዳል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የአገር ባለውለታን ማወቅ እጅጉን ጠቃሚ ነው፡፡
የተወለዱት በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሰላሌ አውራጃ ፍቼ ከተማ አካባቢ በ1875 ዓ.ም ነው። ወላጆቻቸው ዕድሜያቸው ገና ለትምህርት ሳይደርስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመውሰድ ባሕታዊ ተድላ ለተባሉ መምህር አደራ ሰጧቸው።
በዚያው ገዳም የንባብ ቤቱንና የዜማውን የትምህርት ደረጃዎች በሚያስገርም ሁኔታ በአጭር ጊዜ አቀላጥፈው በመጨረስ ገና በልጅነት ዕድሜያቸው ሦስተኛውን የቅኔ ትምህርት ጀምረው በአጭር ጊዜ ሙሉ ቤት ተቀኙ። ይህንኑ የቅኔ ትምህርት ለማስፋፋት በምዕራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት ወደሚገኘው የቅኔ ትምህርት ማዕከል ዋሸራ ተሻግረው ለመምህርነት የሚያበቃቸውን ትምህርት ፈጽመው አስመሰከሩ።
ከዚያም ከቅኔው አውድማ ጎጃም ወደዜማው አዝመራ ጎንደር ተሻገሩ። በዚያም እንደ ቅኔው ሁሉ እስከ ማስመስከር ባይደርሱም የዜማውን ትምህርት በአጥጋቢ ሁኔታ ቀጸሉ። ከጎንደርም በወቅቱ ወሎ ቦሩሜዳ በተባለው ቦታ ላይ ወንበር ዘርግተው የመጻሕፍትን ምሥጢር በየዓይነቱ ሲመግቡ ወደ ነበሩት ስመ ጥሩው መምህር አካለወልድ ዘንድ በመሔድ ዋና ዋናዎቹን የመጻሕፍት ትርጓሜ ትምህርቶች ማለትም ብሉያትን፣ ሐዲሳትንና ሊቃውንትን በብቃት አካሔዱ።
ከዚህ በኋላ ልክ በ1900 ዓ.ም. እዚያው ወሎ አማራ ሳይንት በተባለው ቦታ ወደሚገኘው ምስካበ ቅዱሳን ገዳም በመሔድ ወንበር ዘረጉ። በዚያው ቦታ ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ቅኔንና መጻሕፍትን አስተማሩ። በዚህ ዓይነት በመማርና በማስተማር ራሳቸውን በእግዚአብሔር ቃል በሚገባ ካበቁ በኋላ በ1909 ዓ.ም. ወደ ደብረሊባኖስ ገዳም በመሔድ ሥርዓተ ምንኩስናን ፈጸሙ። ብዙም ሳይቆዩ ማዕረገ ቅስናን ተቀብለው ከወንበሩ አገልግሎት ጋር የቤተመቅደሱን ተልእኮም ደርበው ያዙ።
በ1910 ዓ.ም. መምህር ኃይለ ማርያም ተብለው በወላይታ ሶዶ በሚገኘው ደብረ መንክራት ምሁር ኢየሱስ ገዳም ተሾሙ። በ1916 ዓ.ም. እንደገና በዝዋይ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም በመምህርነት ተሾሙ። በ1919 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ በመምጣት የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ማርቆስ መምህርና በቤተ መንግሥት የግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አበ ንስሐ ሆኑ።
የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ከአንድ ሺ ስድስት መቶ ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዕውቀት መንፈሳዊ ከእርሷ ተወልደው በእቅፏ ውስጥ ባደጉ ኢትዮጵያውያን ጳጳሳት እንድትመራ ፈቃዷን ስትገልጽ ከተመረጡት አባቶች አንዱ በመሆን ግንቦት 18 ቀን 1921 ዓ.ም. በእስክንድርያው መንበረ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን ማዕረገ ጵጵስናን ተቀበሉ። ከዓመት በኋላም “አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ ዘምሥራቅ ኢትዮጵያ ተላዌአሠሩ ለአቡነ ኢየሱስ ሞዓ” ተብለው በያኔው መንዝና ወሎ ሀገረ ስብከት ተሾሙ።
ፋሺስት ኢጣሊያ በ1928 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ላይ የግፍ ጦርነት ስትከፍት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ከጦር ስፍራ መለየት ስላልሆነላቸው፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ተከትለው ወደ ሰሜን ጦር ግንባር ዘምተዋል፡፡ ፋሺስቱ በማይጨው የመርዝ ጦርነት ከማድረጉ የተነሣ፣ የኢትዮጵያ ሠራዊት ሲበታተንም ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር የተመለሱት አቡነ ጴጥሮስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ሄደው ለአገርና ለነፃነት መሞት ቅዱስ ተግባር መሆኑን ለሥላሴ አርበኞች በመስበክም ይታወቃሉ፡፡
አርበኞች አዲስ አበባን በሁለት አቅጣጫዎች ከሰሜናዊ ምዕራብ እና ከደቡባዊ ምሥራቅ አቅጣጫ ለመቆጣጠር ውጊያ በከፈቱበት ጊዜ የተማረኩት አቡነ ጴጥሮስ፣ ለፋሺሽት እንዲገዙ የኢጣሊያ መንግሥት ገዢነትንም አምነው አሜን ብለው እንዲቀበሉ ግፊት ቢያደርጉባቸውም፤ እምቢኝ ለሀገሬ ብለው ለሰማዕትነት ያበቃቸውን የሞት ጽዋ ተቀብለዋል፡፡
ከጋዜጠኛ ኮርዬር ዴላሴር ወኪል እና የምስራቅ አፍሪካ ዜና መዋዕል አዘጋጅ ማስታወሻ ፣ ዜና ጳጳሳት ኢትዮጵያውያን (ዲ/ን መርሻ አለኸኝ )፣ ታሪካዊ መዝገበ ሠብ ( ፈንታሁን እንግዳ ) ይህ የታሪክ ሁነት በትውስታ ስንዘግብ በምንጭነት የተጠቀምንባቸው ሰነዶች ናቸው፡፡ አበቃን ፤ ቸር ይግጠመን፡፡
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 25/2013