አባት በልጆቹ ጉዳይ ዳኝነት መቀመጥ የዘወትር ተግባሩ ከሆነ ሰነበተ። በተለይ የመጨረሻ ልጁ ከሁሉም ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር ተጣልቶ ጉዳዩ አባት ጋር ይደርሳል። አባትም ለልጁ ያለውን መሳሳት ስለሚያውቁ ሌሎቹ ጥፋተኛ ሆነው ላለመቅረብ ይጥራሉ።
አንድ ቀን ግን ጸቡ ሁሉ ድብልቅልቅ አለ። ወደ ድብድብም ተቀየረ። አባትም ጣልቃ ገብቶ በመገላገል የተደባደቡትን ወንድምና እህት ይዞ ተቀመጠ። በቁጣም “እናንተ ግን ምን ይሻላችኋል? እኔ እናንተን ማገድ ሆነ እንዴ ዋና ስራዬ? ደግሞ ዛሬ ምን አጣላችሁ? ምንስ ለድብድብ የሚወስድ ነገር አደረሳችሁ?” ብሎ ጠየቀ።
የመጨረሻ ልጁን በሁለት ዓመት የምትበልጠው እህትም እያለቀሰች “አባ እኔ ምን ላድርገው እራሱ ተዘርክርኮ እርሳሱን ላጲሱን ይጥልና አንቺ ነሽ የጣልሽው አምጪ ብሎ ይደበድበኛል። እንዴ አሁንስ አበዛው? እኔን ሲያየኝ በቃ የእርሱን ጉዳይ አስፈጻሚ እመስለዋለሁ እንዴ? ከአሁን በኋላ ጫፌን ቢነካኝ አለቀውም።” አለች። አባትም ወንዱን ልጅ ጠየቁት “ምን ሆነህ ነው አንተስ?” አሉት። እርሱም “አባ ላጲሱን ሌላ ሰው ሊወስድ አይችልም፤ እርሷ ነው የወሰደችው ከገባበት ታምጣ። ጫፌን ብትነካኝ እኔም አለቃትም። ልታስፈራራኝ ትፈልጋለች እንዴ?” ሲል መለሰ።
አባት አግባብተዋቸውና ይቅርታ እንዲጠያየቁ አድርገው ልጆቻቸውን ከሸኙ በኋላ በሃሳባቸው ነጎዱ። እርሳቸውም የቤታቸው የመጨረሻ ልጅ ነበሩ፤ ልክ አሁን በቤታቸው እንደሚሆነው እርሳቸውም ልጅ እያሉ በወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው መካከል እንደሚሆን አስታወሱ። ምክንያቱ ምን እንደሆነ ለማወቅ ማሰብ ጀመሩ። ታላቅ ወንድማቸው ሁልጊዜ የሚለው ነገር ትዝ አላቸው “ጎረምሳው አንተ በቃ የዩኒቨርስ የማእከል ስበት እንደሆንክ ነው አይደል የምታስበው?” ይላቸው ነበር። እርሳቸውም መላ ቤተሰቡ በሙሉ ለእርሳቸው የተፈጠሩ፤ ሳር ቅጠሉ ለእርሳቸው የተለየ ቦታ እንደሚሰጣቸው ወይንም ሊሰጣቸው እንደሚገባ ይረዱ ነበር። ይህ አይነቱ ስሜት የመጨረሻ ልጅ ከመሆናቸው፣ እናታቸውም ሆነ አባታቸው በልዩ ትኩረት ይመለከቷቸው የነበረ ከመሆኑ በዋናነት የመነጨ ሊሆን እንደሚችልም ያስባሉ። የመጨረሻ ልጃቸው ላይ የሚያዩትን ተመሳሳይ ነገር ለማስተካከል ልጃቸው ላይ ምን መስራት እንዳለባቸው አሰቡ።
ከእዚያ በፊት ልጆቻቸውን በሙሉ ሰብስበው አንዳቸው ስለሌላቸው አስተያየት እንዲሰጡ ለማድረግ አሰቡ። ማታውኑ ከእራት በኋላ ሁሉም ልጆች እንዲሰበሰቡ ጠሯቸው። እንደተለመደው አንድ ታሪክ ነገሯቸውና ወደ እለቱ ጉዳይ ገቡ። የእለቱ አጀንዳ ሲነገራቸው ሁሉም ሳቃቸው መጣ። ያልጠበቁት ስለነበር። አባታቸውን የሚወዱና የሚያከብሩ ልጆች በመሆናቸው አባታቸው ያላቸውን ለማድረግ አንዳቸው በአንዳቸው ላይ አስተያየት ሰጡ። ስለመጨረሻው ልጃቸው ከተሰጡት አስተያየት መካከል ያሳዝነኛል፣ እወደዋለሁ፣ ምንም እንዲሆን አልፈልግም፣ እርሱ ግን ያበዛዋል፣ እኔን ብቻ ተንከባከቡኝ ይላል፣ ደግሞም አይሰማንም ወዘተ የሚሉ አስተያየት ተሰጠ። እርሱ እየሳቀ ይሰማቸው ነበር። አባትም ውይይቱ በመዝናናት መንፈስ እንዲሆን ጥረት እያደረገ ነው። ሌላ ታሪክ በመንገር ስብሰባው እንዲጠናቀቅ ቀድሞ ላወጣው ልጅ እድል ተሰጥቶት ታሪክ ተናገረ። ሁሉም ወደ መኝታው ሲሄድ አባትና እናት ወደ ክፍላቸው አመሩ። ስለልጆቻቸው ቀጣይ ሁኔታ ሲነገሩ ከነበረው እያነሱ መከሩ። ሁለቱም በአንድ ሃሳብ ተስማሙ፤ የመጨረሻው ልጃቸው ያልተገባ ለራስ ትርጉም መስጠት ውስጥ እያደገ መሆኑን። ይህንን ዛሬ ማስተካከል ካልተቻለ ነገር በውስንነት በሚኖርባት ምድር ውስጥ ውስንነት በገጠመው ልክ በተሳሳተ መንገድ ችግርን ለመፍታት በመሞከር እንዲኖር፤ የራሱን ሚናን መዘንጋት እንዲሁም ምድር ላይ ካለው እውነታ አንጻር ያልተቃኘን ኑሮ ሊኖር እንደሚችል አሰቡ።
ለራስ የተለየ ትርጉም፣ ውስንነትን አለመረዳት፣ የተሳሳተ የመፍትሄ ፍለጋ መንገድ የሚሉትን ሃሳቦች እንደመሸጋገሪያ ይዘን፤ በእኛስ ህይወት ብለን ጠይቀን እንለፍ።
ለራስ የተለየ ትርጉም መስጠት
ራስን መቀበል መቻል የሚበረታታ እያንዳንዱ ሰው ሊያደርገው የሚገባ ነው። ለራስ ቦታ መስጠት ተገቢነቱ እንዲሁ አያጠያይቅም። ፈጣሪም ባልንጀራችንን እንደ ራሳችን እንድንወድ ሲጋብዘን ለራሳችን ከምንሰጠው ቦታ ተነስተን መሆኑን መረዳት ይገባል። ለራስ ቦታ መስጠትና ለራስ የተለየ ትርጉም መስጠት ሁለቱ ይለያያሉ።
ራስን በመቀበልና ለራስ የተለየ ትርጉም መካከል ያለውን ልዩነት በመረዳት ጤናማ ህይወትን እርሱም ከሌሎች ጋር በሰላም የመኖርን ጥበብ ማግኘትን ይገባል። ብቻችንን ልንኖረው የምንችለው ህይወት ምድር ላይ እንደሌለ በመረዳት በዙሪያችን ላሉት ሰዎች ከየትኛውም ልዩነት ባሻገር ትርጉም በመስጠት መኖርን መልመድ አለብን።
ሁላችንንም ያለብንን ውስንነት በመረዳት በውስንነት ውስጥ የምንኖር በመሆናችን መደጋገፋችን የግድ መሆኑን በመገንዘብ መኖር ብልህነት ነው። ራስን ውስንነት የሌለበት፤ ሌላውን ግን በውስንነት የሚኖር አድርጎ የመሳል ውስንነትን በማስወገድ።
ውስንነትን አለመረዳት
የምንኖርበትን ነባራዊ ሁኔታ ህይወትን በአግባቡ ለመምራት አስፈላጊ ነው። ነባራዊ ሁኔታን ማወቅን ተከትሎ ሁኔታውን መቀበል ወይንም መቀየር ያለበትን ለመቀየር መነሳሳትን ያመጣል። ከነባራዊ ሁኔታ ግምገማ ውስጥ ከምናወጣቸው ነጥቦች መካከል አንዱ ውስንነትን መረዳት ነው።
ውስንነት በምድር ላይ ባለ በየትኛውም ፍጥረት ላይ የሚኖር የጋራ መገለጫ ነው። የሰው ልጅ ውስንነቱን ለማሸነፍ የሚያደርገው ጥረት አሁንም የቀጠለ ቢሆንም ከውስንነቱ ግን ሊላቀቅ ፈጽሞውኑ አልቻለም፤ እንደሚላቀቅም አይታሰብም። አንዳንድ ውስንነቶችን እየቀነሱ መሄድ የሚቻልበት እድል ያለ ሲሆን ውስንነትን ማጥፋት ግን የማይታሰብ ነው።
ውስንነትን ሳይረዱ ግብ ማድረግ ያሰብነው ግብ በማይሳካ ወይንም ያልጠበቅነው በሚሆንበት ጊዜ ስብራትን የሚያስከትል ነው። አንዳንዱ ውስንነት ቀን በቀን የምናውቀው ሲሆን ሌላው ግን ድንገተኛ ክስተትም ሊሆን ይችላል። ሞክሮ ሞክሮ አልሳካ ሲል የምንቀበለው ውስንነት እርሱ የትህትናን መንገድ የሚያሳይ፤ በውስንነት ውስጥ የመኖርን ጥበብ መረዳትን የሚያመጣ ነው።
ውስንነትን ለመረዳት የሚረዱንን ውስንነት የሚያሳዩ ዝርዝሮችን እንመልከት፤
• አካላዊ ውስንነት – አካላችን አንድ ቀን ወደ አፈርነት ይቀየራል፤ እያንዳንዱ ቀን ወደ እዚያ ቀን የምንቀርብበትም ቀን ነው። ለመኖር መተኛት፣ መብላት እና መጠጣት ይገባናል። በዓለማችን ላይ ያለው የትኛውም የፕላስቲክ ቀዶ ጥገና የእድሜያችንን የመቁጠር ሂደት ሊቀይረው አይችልም። አካላዊ ውስንነታችንም ግባችንን እና ህልማችንን ሳንጨርስ ማለፍን የሚያስከትል ውስንነት ነው። አካላዊ ውስንነት የሌለበት እኔ የተለየሁ ሰው ነኝ የሚል ማን ይኖር ይሆን?
• የተወለድክበት ቤተሰብ – ቤተሰብህ፣ ብሔርህ፣ የተወለድክበት ሀገር፣ ባህል ሁሉም ስጦታም እንዲሁ ውስንነትን ያወርሱናል። ሁለት ወላጆች ጋር ብንሆን ወይንም ከአንድ ወላጅ ጋር ወይንም በማደጎ ውስጥ በእድገት ውስጥ በውስንነት እናልፋለን ከቤተሰባችን የሚሰጠን ውስንነት። ከቤተሰብህ የተቀበልኩት ውስንነት የለብኝም እኔ እኮ ፍጹም የተለየሁ ነኝ የሚል ይኖር ይሆን?
• የትዳር ሁኔታ – ትዳርም ሆነ ላጤነት ውስጥ ከተፈጥሮ የተቀበልነው ውስንነት አለበት። ልጆች ካሉህ በልጆች ቁጥር እንዲሁም በልጆቹ አይነት ላይ ውስንነት ይኖራል። የትዳር ሁኔታዬ ውስንነት የሌለበት ከሁሉም የሚለይ ነው የሚል አንድ ሰው ይገኝ ?
• አእምሯዊ አቅም – ማንኛችንም በሥነ-ጽሁፍ፣ በሂሳብ፣ በኢንጂነሪንግ፣ በአናጺነት፣ በፊዚክስ እንዲሁም በሌሎቹም ዘርፎች በሙሉ በአንድ ላይ ባለምጡቅ አእምሮ ባለቤት ልንሆን አንችልም፤ እንዴት ሆኖ። በአንድ ዘርፍ የተለየ አስተዋጽኦ አድራጊ መሆን መቻል በሁሉም ዘርፍ ቀዳሚ መሆን ያስችላል ማለት አይደለም። አዕምሯዊ አቅም የሚሰጠን ውስንነትን መቀበል መቻል ማተኮር በሚገባን ተሰጥኦ ላይ አስተዋጽኦ እንድናደርግ የራሳችንን ዘርፍ እንድንፈልግ ያደርገናል። አሁንም እንጠይቅ እኔ ውስንነት አልባ የሆንኩ በሁሉም ዘርፎች ላይ ስኬታማ መሆን የምችል ልዩ ሰው ነኝ የሚል ይኖር ይሆን?
• ጊዜህ – ልትኖርለት የምትችለው አንድ ህይወት ብቻ ነው ያለህ። ሁሉንም ነገር ልታደርገው አትችልም። በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፣ በኤዢያ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች መኖር ትፈልግ ይሆናል። የተወሰኑ ሙያዎችን መሞከርም እንዲሁ ትፈልግ ይሆናል። ግን አትችልም። ምክንያቱም ጊዜህ የፈለከው ቦታ ሁሉ እንድትኖር፤ የፈለከውን ትምህርት ሁሉ እንድትማር ስለማይፈቅድ። ጥያቄውን እንቀጥል ከጊዜ በላይ የምሄድ ጊዜ የማይገታን የተለየሁ ነኝ የሚል ይኖር ይሆን?
• የሥራ እና ግንኙነት እውነታ – ሥራችን እሾህና አሜክላ የሚያበቅል ሊሆን ይችላል። ሥራችንን ሙሉ ለሙሉ መጨረስም አንችልም ይሆናል። እንዳሰብነው ሙሉ ለሙሉ መጨረስ ባለመቻል የሚሰማን ሃዘንም ሊኖር ይችላል። ከሰዎች ጋርም ያለን ግንኙነት እንዲሁ እንዳሰብነው ሙሉ ሳይሆን ዘመናችን ያልቅ ይሆናል። በፍጹም ፍቅር ሁሉንም ሰው ልንወድና ልናስደስት የምንችልበት የሥራ እና ግንኙነት እውነታ ይኖረን ይሆን? በፍጹም!።
• መንፈሳዊ መረዳታችን – መጽሐፍ ቅዱስን መነሻ አድርገን ስንመለከት መንፈሳዊ መረዳት እራሱ ለሰው ልጆች በሙላት የተገለጠ አለመሆኑን እንረዳለን። ምሥጢሩ ለአምላካችን ለእግዚአብሔር ነው፤ የተገለጠው ግን የዚህን ሕግ ቃሎች ሁሉ እናደርግ ዘንድ ለእኛ ለዘላለምም ለልጆቻችን ነው (ዘዳግም 29፡29)። ይህ ቃል የሚነግረን መንፈሳዊ መረዳታችን ውስንነት ያለበት መሆኑን ነው።
ውስንነትን ተቀብሎ የመኖርን አስፈላጊነት በጥሩ ሁኔታ ልንረዳ ይገባናል። የታሪካችን መግቢያ ያደረግነው ልጅን ባህሪ በራሳችን ውስጥ እንፈልግ። እንደ ህጻን ሆነን እራሳችንን እናገኝ እንደሆን እንጠይቅ። ህጻን እናቱ እንድትመግበው እንድትንከባከበው በሙሉ ትኩረት እርሱ ጋር ብቻ እንድትሆን አስቦ ይጠብቃል፤ መናገር ሳይችል ሲቀር ያለቅሳል። ለህጻኑ እርሱ ማለት የዩኒቨርስ የስበት ማእከል ነው። ሌሎች በሙሉ ስለእርሱ የሚኖር እርሱ ግን የዩኒቨርስ ማእከል ሆኖ ራሱን ያውቃል። እድገት ሲመጣ ግን ህጻንነት የሰጠው የዩኒቨርስ ማእከልነት ትክክል አለመሆኑን መረዳት ይመጣል። ዩኒቨርስ የአንድን ሰው ፍላጎት ለማሟላት ብቻ የተፈጠረ አለመሆኑንንም ይረዳል። በውስንነት የሚኖር፤ ሁሉም ሰው ያው ሰው መሆኑን የሚረዳም ይሆናል።
ይህ ሁላችንም ልንማረው የሚገባ ህመም ያለበት ትምህርት ነው። ለራሳችን የምንሰጠው የተሳሳተና የተጋነነ ግምት እንደ ህጻን እይታ ነገሮችን እንድናይ ሊያደርገን ይችላል። ፈጣሪም እንድንሰራ ካሰበልን ስራም በተቃራኒው እንድንሰራም እንድናስብ ያደርገናል። ከምንችለው በላይ መስራት እንደምንችል በማሰብም ራሳችንን እናነዳለን። ራሳችን ላይ ጭንቀትን እንፈጥራለን፤ ሌሎችንም ተጠያቂ እናደርጋለን።
ለራስ ከሚሰጥ የተሳሳተ ግምት እና ውስንነትን ካለመረዳት የሚመጣው ኪሳራን እንዴት እንፍታው የሚለው ጥያቄን ለመመለስ የሚደረገው ሙከራ መጨረሻው ያልተገባ መንገድ ውስጥ እንዳይከተን ማሰብ ያስፈልጋል። እውነታን ተቀብሎ ለእውነታው ምላሽ መስጠት አስፈላጊ ቢሆንም ብዙ ጊዜ ዘላቂ መፍትሄ ላይ በማያደርሱ በተሳሳቱ የመፍትሄ ፍለጋ መንገዶች ውስጥ እንጠመዳለን።
የተሳሳተ የመፍትሄ ፍለጋ መንገዶች
ለራስ ከሚሰጥ የተሳሳተ ግምት እንዲሁም ከምንኖርበት ውስንነት የተነሳ የሚገጥሙንን ፈተናዎች ለመፍታት ስንነሳ የተሳሳተ የመፍትሄ ፍለጋ መንገድ ውስጥ እራሳችንን እናገኝ ይሆናል። መፍትሄ ፍለጋን ትክክል እንዳይሆን የሚያደርጉትን ሰባት ነጥቦች ቀጥሎ እንመልከት።
1. መካድ – ውጫዊም ሆነ ውሳጣዊ የሆኑ እውነታ ተኮር የሆኑ ህመሞችን ከመቀበል ስናቅማማ ወይንም ክደን ስንቆም የሚፈጠር የመከላከያ መንገድ ነው። ለምሣሌ ጥሩ ስሜት እኮ ነው የሚሰማኝ። ያን ያህል የሚያስጨንቀኝ ጉዳይ አይደለም። በፍጹም ምን የሚያሰጋኝ ነገር የለም ወዘተ። የሚሉ ምላሾች እውነታውን በመካድ ውስጥ መፍትሄ ፍለጋ ላይ መሆናችንን ያስረዳናል።
2. ማሳነስ – ስህተት የሆነውን ነገር ተቀብለን፤ ነገር ግን ከሚገባው በታች ጉዳዩን አሳንሶ መመልከት። ልጁ ጠጪ ሆኖ በጣም እያመሸ እየመጣ የሚቸገር አባት ነገሩን አሳንሶ በማየት ልጄ ህይወቱ ደህና የሚባል ነው፤ ከእዚህም የባሰ ስላለ ተመስገን ማለት ነው ቢል ለልጁ የስካር ህይወት ጎጂነት አሳንሶ ማየት ይሆናል። ችግርን ለመፍታት በምናደርገው ሂደት ውስጥ ችግሩን አተልቀን የማይፈታ አድርገን እናስብ ማለት አይደለም። ነገር ግን የሚፈጠር ቀውስን ለመፍታት በልኩ ጉዳዩን ማየት ተገቢ ነው። አሳንሶ ማየት ችግሩ እየገዘፈ እንድሄድ እድል የሚሰጠው እንዳይሆን።
3. ሌሎችን ተጠያቂ ማድረግ – የራሳችንን ሃላፊነት በመዘንጋት ጥፋቱን በሙሉ ወደ ሌሎች የመውሰድ አካሄድ በስፋት የሚስተዋል ነው። ለራስ የተሳሳተ ግምት መስጠት እና ውስንነትን አለመቀበል የሚፈጥረው ችግር ወደ ሌሎች ወገኖች እጃችንን እንድንቀስር የሚያደርገን ሲሆን ይታያል። ለምሣሌ የወንድሜ የጤንነት ሁኔታ የተበላሸው በዶክተሮቹ ህክምናውን ማበላሸት ነው ብሎ የሚከራከር ወንድም ንግግሩ ውስጥ እውነታ ሊኖር እንደሚችል ቢታሰብም ዶክተሮቹ ህክምናን የማበላሸታቸው ማረጋገጫን ግን መጠየቅ ያስፈልጋል። በህክምና ስህተት የህሙማን ጤንነት መፍትሄ አያገኝም ማለት ሁሌም ነው ማለት ስላልሆነ። ወደ ሌሎች ከመመልከት በፊት በራስ ዙሪያ መመልከቱ አስፈላጊነቱ መዘንጋት የለበትም።
4. ራስን አላስፈላጊ የሆነ ወቀሳን መውቀስ – አንዳንድ ሰዎች ለተፈጠረው ችግር ሁሉ ራሳቸውን ተጠያቂ ማድረግ ይቀናቸዋል። ራስን መመልከቱ አስፈላጊ ቢሆንም አሁንም ከእውነታው የራቀ ሲሆን ወደ መፍትሄ አያመጣም። ከአስተዳደግ በቤተሰብ ውስጥ የሚመጣን ተጽእኖ ራስን ተጠያቂ በማድረግ ልንፈታው አንችልም። ሌሎችን ተጠያቂ ለማድረግ አለመፍጠን ተገቢነት ቢኖረውም ሁሉን ወደ ራስ ማምጣትም ከእውነታው ውጭ ከሆነ ተገቢነት የለውም። ለምሳሌ እኔ እንደ ልጅ መሆን እንደሚገባኝ ባለመሆኔ ነው እናቴ ከመጠን በላይ የምትናደደው ለእኔም እንደሚገባኝ እንድትንከባከበኝ ያልሆነችው በሚለው ምክንያት ውስጥ እናትን ሙሉ ለሙሉ ከማወቅና ምክንያቱን ራስን ተጠያቂ በማድረግ የሚገለጽ ነው። እውነታው ግን ሌላም ሊሆን ይችላል። ፈጥኖ ወቀሳን ከራስ ጋር ከማምጣት እውነታውን በአራቱም አቅጣጫ መመልከት ይገባል።
5. ምክንያት ማቅረብ/Rationalizing – ስለሆነው ነገር ምክንያቶች መደርደር ወይንም አግባብነት የሌለው ማብራሪያን ማቅረብ። ስብሰባው በአግባቡ ሊሆን ያልቻለው ዮሐንስ ከቤተሰቡ የወረሰው ቁጣን መቆጣጠር አለመቻል ነው።
6. ሙህራዊ ትንታኔ መስጠት/Intellectualizing – ሙህራዊ ትንታኔ ወይንም ቲዮሪን በማቅረብ ስለራሳችን ሊኖረን ይገባ የነበረን ግንዛቤ እና አስቸጋሪ ስሜቶችን መሸፈን በዓለም ላይ መከራ እየተቀበሉ ካሉ ሰዎች አንጻር የእኔ ሁኔታ ሊወዳደር የሚችል አይደለም። ስለሆንም ስለምን ብዬ አለቅሳለሁ? አዎን አላስፈላጊ ለቅሶ ተገቢነት የለውም። ነገር ግን አላስፈላጊ ለቅሶው መታየት ያለበት ከራሱ አንጻር ነው እንጂ በዓለም ላይ ካለው የለቅሶ ብዛት ጋር አይደለም።
7. ሃሳብን ማዛባት/Distracting – ርእስ ጉዳዩን አዛብተን ወደ ሌላ አቅጣጫ በመቀየር እውነተኛ ምልከታ ከማድረግ መቆጠብ ለምሳሌ በአሉታዊ ነገር ላይ ለምን ትኩረት ታደርጋለህ፤ ባለፈው ገናን እንደ ቤተሰብ ስናከብር የተፈጠረውን መልካም ስሜት ለምን አታስብም? የሚለው ሙግት ዘላቂነት መፍትሄ ላይ መድረስ እንዳይቻል ሃሳብን ነጣጥሎ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ መዛባትን የሚፈጥር ነው።
በመነሻ ታሪካችን ውስጥ ያነሳነው ልጅ ራሱን የዩኒቨርስ ማእከል አድርጎ ማሰቡ ሊገጥመው ያለውን ለራስ የተሳሳተ ግምት የመስጠት ችግርን አባት አሻግረው ተመልክተዋል። እኛም ራሳችንን በልጁ ቦታ አድርገን እንድንፈትሽ ተጋብዘናል። ለራስ የተሳሳተ ትርጉም መውጣት እንዲቻል ውስንነታችንን መቀበል ተገቢነት መሆኑን እንዲሁም ሌሎችም በውስንነት የሚኖሩ መሆኑን ማወቅ እይታችንን እንደሚያስተካክልንን ይታመናል። ችግሩን እንደ ችግር ተቀብለን የመፍትሄ መንገድ እንፈልግ ብለን ስንነሳ ትክክለኛው መንገድ ውስጥ እንዳንሆን የሚያደርጉንን የተሳሳቱ መንገዶችን ዘርዝረናል።
እንደ ሀገር፣ እንደ ግለሰብ ለራሳችን የሚገባንን ትክክለኛውን ቦታ ሰጥተን በሰላም መኖርን እንለመድ ዘንድ ጸሃፊው ይመኛል። ይህ እንዲሆን ሁላችንም ያለብንን ውስንነት ማወቅ፤ ሁሉንም በሰውነቱ መመልከት፤ ከገባንበት ችግር ለመውጣት በትክክለኛው መንገድ ላይ መሆንን ይጠይቃል። ባልንጀራን እንደራስ መውደድ ውስጥ ያለው ጥበብ ለሁላችንም ይሁን። በእይታ መስተካከል ውስጥ ያለው ጥበብ።
በአገልጋይ ዮናታን አክሊሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 24/2013