ሰዎች የሚበዙበት የገበያ ስፍራ ይመስል ግቢው በሰዎች ጫጫታ ተሞልቷል፡፡ “ ቢሾፍቱ፣ ዝዋይ፣ ሀዋሳ፣ ሻሸመኔ” የበዙ ድምፆች የተለያየ አገር ስም ይጣራሉ፡፡ የመኪኖች ጥሩንባ በተለያየ ድምፀት ይሰማል፡፡ ለመኪናም ለእግረኛም መግቢያና መውጫ ይሆን ዘንድ በሰፊው የተከፈተውን በር አልፌ ወደ ውስጥ ስዘልቅ የመኪና ረዳቶችና የደላሎች ድምጽ ከቅድሙ ይበልጥ ጎልቶ ይሰማኝ ጀመር፡፡ የዓውዳ ዓመት ዋዜማ እንደ መሆኑ ትርምሱ ከሌላ ጊዜ በዝቷል፡፡
በየመኪኖቻቸው አቅራቢያ ቆመው የሚጣሩት ቀላጣፋዎቹ ረዳቶች ተሳፋሪው ወደነሱ ሲቀርብ በእጁ ያለውን እቃ እየተቀበሉ ወደመኪኖቻቸው ወስደው ይጭናሉ፡፡ አንዳንዴም የመኪና ረዳቶቹ መንገደኛ ወደ መናኸሪያው ሲገባ ቀርበው ክንዱን ይዘው የሚሄድበትን ይጠይቃሉ፡፡ በሌላ እንዳይቀደሙ መሆኑ ነው፡፡ ድምፃቸውን ከፍ አድረገው “ጋሼ የት ነህ? እሙዬ ወዴት ነሽ?” እያሉ ገና ወደ ግቢው ሲዘልቅ የሚያዋክቡት ተሳፋሪ አዲስ ከሆነ በሁኔታቸው መደናገጡ አይቀርም፡፡
እኔም እዚያ የተገኘሁት ለዓውዳ ዓመት ሀዋሳ ወዳሉ ቤተሰቦቼ ለመሄድ ነው፡፡ “ሀዋሳ…. ሀዋሳ” ብለው ወደሚጣሩት ረዳቶች ተጠግቼ ስቆም፤ አንድ ወጣት ቀርቦ የምሄድትን ጠይቆኝ ወደ አንድ ሀይሩፍ የሚባል መኪና አደረሰኝና ግባ አለኝ፡፡ መኪና ውስጥ ሁለት ሰዎች ብቻ ነው ያሉት፡፡ ጋቢና አንድ ሰው መሆኑን ስመለከት በር ከፍቼ ገባሁ፡፡ አረፍ እንዳልኩ በደንብ በሚያስመለክተው በመኪናው የፊት መስታወት ከፊት እርጅና የተጫጫናቸው እናት ወደ መኪናው ሲቀርቡ ተመለከትኩ፡፡
ረዳቱ ከሴትየዋ አንድ በልብስ የተሞላ አሮጌ ሻንጣ ተቀብሎ በር ከፍቶ አስገባቸው፡፡ ካለሁበት ዞር ብዬ ስመለከታቸው ፊታቸው ላይ የበዛ ዘመን የሚያስቆጥር የቆዳ መሸብሸብና በድካም የዛለ ሰውነት ታየኝ፡፡ ፀጉራቸውን በረጅም ሻሽ ጠምጥመውታል፡፡ በእጆቻቸው ላይ ጎልተው የሚታዩት ደምስሮቻቸው ከቆዳቸው ላይ የበቀሉ ሀረጎች ይመስላሉ፡፡ እርጅና እጅጉን ተጫጭኗቸዋል፡፡ ሳያቸው አሳዘኑኝ፡፡ ወደነበርኩበት ተመልሼ፤ እናቴን ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ሴትየዋን ሳይ እናቴ ትዝ አለችኝ፡፡ የእም እናት አሮጊ ናት፡፡
እናቶች ሁሌም ይገርሙኛል፡፡ ያላቸውን ሁሉ ሰጥተው ከራሳቸው በላይ ልጆቻቸውን መውደዳቸው በተፈጥሮ እንድደነቅ ያደርገኛል፡፡ ይሄኔ እኚህ እናት በዚህ ረጅም እድሜያቸው ወደ ምድር ምክንያት ሆነው ያመጡዋቸው ልጆቻቸውን አምጠው ሲወልዱ ሲያጠቡ ተንከባክበው ሲያሳድጉና ሰው ሆነው እንዲቆሙ ሲጥሩ እድሜያቸውን የጨረሱ እናት ይሆናሉ፡፡
ብዙ እያሰብኩ ስለመኪናው መሙላት እና አንድ ሰው ብቻ መጉደል ረዳቱና ሹፌሩ ሲነጋገሩ ሰማሁ። ወዲያው ከተቀመጥኩት ፊት ለፊት በመስታወት አሻግሬ ተመለከትኩ። አንዲት ቆንጆና ቄንጠኛ ወጣት ወደመኪናው እየመጣች ነው፡፡ እድሜዬ የፈጠረብኝ ልዩ ስሜት ይሁን አልያም የልጅትዋ ውበት አፍጥጬ አየኋት። ውብ ናት፤ ቁመናዋ ይማርካል፡፡ ፀጉርዋን ተተኩሳው እንደነገሩ በጀርባዋ ላይ ነስንሳዋለች፡፡ አጠገቤ ያለው ሰው ወርዶ እስዋ ከኔ ጎን እንድትቀመጥና አብሬያት በሄድኩ ብዬ ተመኘሁ። ወዲያው ረዳቱ ወደ መኪናው ይዟት ገባ። ዞሬ ስቀመጥ ቅድም ካየኋቸው እናት አጠገብ ተቀምጣ ተመለከትኩ፡፡
ሁለቱን በተነፃፅሮ ማሰብ ጀመርኩ፡፡ ብቻ የሆነ ነገር ያቁነጠንጠኝ ጀመር.፤ ምክንያት እየፈለግሁ ፊቴን አዙሬ ሁለቱንም ደጋግሜ ማየት ቀጠልኩ፡፡ አሮጊቷ በእድሜ ምክንያት ቆዳቸው ተሸብሽቦ፣ በህይወት ፈተና አካላቸው ዝሎ ወደርሳቸው በኑሮ ትግል ጉልበታቸው ደክሞ ይታያሉ። በአንፃሩ ደግሞ ደም ግባት የተላበሰች፣ ገና አብቦ እንደፈካ ፅጌሬዳ ፍንትው ብላ የምትታይ ልቅም ያለች ቆንጆ ከጎናቸው ሻጥ ብላ ትታያለች፡፡ ልዩነታቸውን ለተመለከተ አይ ዕድሜ ያሰኛሉ፡፡ መኪናው ግቢውን ለቆ ወጥቶ ጉዞውን ከጀመረ ከ20 ደቂቃ በኋላ የሆነ ድምፅ ከኋላ ስሰማ ዞርኩ፡፡
ያቺ ውብ ያልኳት ልጅ በጨለማ ውስጥ ፏ ብሎ እንደ በራ አምፖል የደመቀችዋ ቆንጆ ፊትዋን አጨፍግጋው ተመለከትኩ፡፡ “ምን ነክቷት ይሆን?” ብዬ ራሴን መጠየቅ ጀመርኩ፡፡ ጆሮዬን አቅንቼ የሚወራውን መስማት ጀመርኩ፡፡ ልጅቷ ትነጫነጫለች፡፡ “ቦታ ቀይረኝ፤ ግማቱን አልቻልኩትም” ስትል ሰማኋት፡፡ “ምን ሸቷት ይሆን?” አሁንም ያልተመለሰልኝን ጥያቄ ለራሴ በውስጥ መስመር እጠይቃለሁ፡፡ ልጅቷ በሁኔታዋ የሁሉንም ተሳፋሪ ትኩረት አገኘች፡፡ አጠገቤ ያለው ሰው ለረዳቱ ዞር ብሎ ምን ሆና ነው ብሎ ጠየቀው፡፡
“ባክህ ጥጋበኛ ቢጤ ናት፤ አጠገብዋ ያሉ እናት ቅቤ ተቀብተዋል ፤ ይሸታሉ ነው የምትለው” ሲል ረዳቱ መለሰለት፡፡ ይህን መልስ ስሰማ ልጅቷን የተመለከትኩበት መነፅሬ ወዲያው ሲጠቁር ታየኝ፡፡ እንዴት በድፍረት የሰው ልጅን ያህል ነገር ለዚያውም እድሜያቸውን ለትውልድ ሰጥተው ዛሬ ላይ የተገኙን እናት “ይሸታሉ” ብላ ትናገራለች። እንዴት እናትን ያህል ሰው ይህን ያህል ታንጓጥጣለች አልኩ። ተናደድኩባት፡፡ መኪናው ጉዞውን ቀጥሏል፡፡ የልጅቷ ስድብና ንጭንጭም አልቆመም፡፡ ተሳፋሪው ሁሉ በልጅቷ መረበሹን አልቆመም፡፡
ግራ የገባቸው ሹፌርና ረዳት በልጅቷ ድርጊት ተማረሩ፡፡ “አቦ ዝም በይ አትበጥብጪን፤ ከፈለግሽ ውረጂ” ይሏት ጀመር፡፡ ይሄኔ እኔ ለሹፌሩ አንድ ሀሳብ አቀረብኩለት፡፡ “እኔ ቦታ ልለውጣትና በሰላም እንሂድ የሚል” ሹፌሩ “ገላገልከን”ብሎ መኪናውን አቆመና እኔ ከጋቢና ወደኋላ ወንበር ልሸጋገር ወረድኩ፡፡ ልጅቷ ተስፈንጥራ ከመኪናው ወርዳ ገቢና ልትገባ ስትል በድጋሚ ተመለከትኳት፡፡ የቅድሙ መልኳ ሁሉ ጠፋብኝ፡፡ አጠገቧ ስለሆነው የገለጸችበት መጥፎ መንገድ ውበቷን ሸፈነብኝ፡፡ ገብታ እስክትቀመጥ ድረስ አፍጥጬ አይቻት ወደኋለኛው ወንበር ሄጄ ተቀመጥኩ፡፡ የገጠር ልጅ ስለሆንኩ የቅቤው ሽታ ብዙም አልጎረበጥኝም፡፡
ጉዞው ቀጠለ፡፡ ሴትየዋ ሳያቸው በልጅቷ የተደበደቡ ያህል ኩምሽሽ ብለዋል፡፡ በቆዳቸው ሽብሻቦ ቅንድባቸው ቆብ ሊጋረድ በተቃረበው አይናቸው አጮልቀው ከአጠገባቸው የራቀችዋን ልጅ ያያሉ፡፡ አንዲትም ቃል አይተነፍሱም፡፡ ምን አልባትም በብዙ እየረግምዋት ይሆናል፡፡
መኪና ውስጥ ያሉ ሰዎች በልጅቷ ተረብሸው ነበርና እፎይ አሉ፡፡ ትንሽ እንደ ተጓዝን ከፊት ለፊት ምን መጣ ሳይባል ከፍተኛ የግጭት ድምፅና ጩኸት ተሰማ፡፡ የነበርንበት መኪና ድብልቅልቁ ወጣ፡፡ የነበርንበት መኪና ከፊት ለፊቱ ከነበረ ከባድ የጭነት መኪና ጋር ክፉኛ ተጋጭቶ ቆመ፡፡ እኔ ድንጋጤ ውስጥ ነበርኩ፤ ራሴንም ያሳትኩ ይመስለኛል፡፡ ከዚህ ስነቃ ነው ይበልጥ የሆነውን ሁሉ ይበልጥ የተረዳሁት፡፡ ስነቃ አንዳንድ መጫጫር ካልሆነ ምንም ነገር አለመሆኔን አረጋገጥኩ፡፡ ከኋላ ከነበርነው አብዛኞቻችን ከወንበርና መስታወት ጋር ተላትመናል፡፡ ክፉኛ የቆሰሉም ነበሩ፡፡
ከፊት ለፊት ጋቢና የነበሩት ግን እጅጉን መጎዳታቸውን ከመኪናው በሰዎች እርዳታ ከወርድን በኋላ ሰማን፡፡ እጅጉን የተጎዱ ሰዎች መለየት ተጀመረ፡፡ በአካባቢው የነበሩ መኪኖች በጣም የተጎዱ ሰዎችን አፋፍሰው ይዘው መሄድ ጀመሩ፡፡ ራሳቸውን ይዘው የሚያልቅሱም ነበሩ፡፡
ሁኔታውን ለማየት ራሴን በማረጋጋት መልሼ ወደ መኪናው ተጠጋሁ፡፡ ከአደጋው በፊት አጠገቤ የነበሩት ሴትዮ ስላላየኋቸው ተጎድተው እንዳይሆን ብዬ ሰጋሁ፡፡ ትንሽ ራመድ እንዳልኩ አሮጊቷ አንድ ጥግ ላይ ተቀምጠው ተመለከትኩ፡፡ ምንም አለመጎዳታቸውን ሳይ ደስ አለኝ፡፡
ታዲያ ማን ምን ሆኖ ነው ብዬ ወደፊት ተጠጋሁ፡፡ ቅድም አሮጊቷን ስትሸሽ የነበረችው እና እኔ ቦታ ቀይሬያት ከፊት ገብታ የነበረችው ወጣትና ቆንጆዋ ልጅ ህይወቷ ማለፉን ተረዳሁ፡፡ ሰዎች በሀዘን ተውጠው የልጅቷም አስከሬን አንስተው መኪና ላይ ሲጭኑ ተመለከትኩ፡፡… ተፈፀመ
ተገኝ ብሩ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 23/2013