የተሟላ ምግብ ለማግኘት የተሟላ የአመራረት ዘዴ መከተል ወሳኝ ነው። አርሶና አርብቶ አደሩ ማምረት የሚችለው መጀመርያ እራሱ የተመጣጠነ ምግብ ሲያገኝ በመሆኑ የተሟላ ምግብ ለሸማቹ ብቻ ሳይሆን ለምግብ አምራቹም ያስፈልጋል። እንደ ሀገር ሲቃኝም በጥቅሉ በየትኛውም ዘርፍ አምራች ዜጋ ለማፍራት የተመጣጠነ ምግብ አቅርቦትና ተጠቃሚነት የግድ ነው። በተለይ ሰፊውን ሕዝብ የመመገብ ኃላፊነት የተጣለበት በየገጠሩና በየከተሞች ዳርቻ ጭምር ያለው አርሶና አርብቶ አደር ሸምተህና ከውጪ የሚገባውን ገዝተህ ብላ ተብሎ አይመከርም። ምክንያቱም አንድም አቅሙ አይፈቅድም፤ ሁለትም እራሱን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ዜጎችን ጭምር የመመገብ ታላቅ ሀገራዊ ኃላፊነት ተጥሎበታልና ነው። በመሆኑም የግብርናውን ዘርፍ የሚመራው ግብርና ሚኒስቴር አርሶና አርብቶ አደሩ በእጁ ያሉትን መሬትና እንስሳትን ተጠቅሞ የተሟላ የአመራረት ዘዴ እንዲከተል ይፈልጋል። በዚህ መልኩ ለራሱም የተሟላ ምግብ እንዲያገኝና ለዜጎችም እንዲያስገኝ እየሠራ ይገኛል። በግብርና ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ቡድን መሪ አቶ ዳንኤል ዴንታሞ እንደሚሉት በግብርና ሚኒስቴር አምራች መሆን የሚያስችል የአመጋገብ ስርዓት እንዲኖር መሥራት ከተጀመረ ዋል አደር ብሏል።
‹‹ሳይንስ እንደሚለው የተስተካከለ አመጋገብ ስርዓት ያለው ሕብረተሰብ አምራች ይሆናል›› የሚሉት አቶ ዳንኤል ግብርና ሚኒስቴር የጤናውን ዘርፍ ጨምሮ ከአስር ባለድርሻ አካላት ዘርፎች ጋር በዚሁ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ በቅንጅት እየሠራ እንደሚገኝም አበክረው ይገልጻሉ። ወደዚህ የቅንጅት ሥራ የተገባው ከዚህ ቀደም በሚኒስቴር መሥርያ ቤቱ ሲሠራበት የነበረው ሥራ ክፍተት ያለው ሆኖ በመገኘቱ ነው። እንደ ቡድን መሪው የግብርና ሚኒስቴር አንዱና ዋንኛው ተልዕኮ የሀገራችንን ሕዝብ ምግብና ስርዓተ ምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ነው። ሆኖም ከዚህ ቀደም ይህን ተልዕኮ አንግቦ ይሠራ የነበረው ሥራ ምርት ማምረት ላይ ብቻ ያተኮረ ነበር።
በመሆኑም አርሶና አርብቶ አደሩን ጨምሮ ሕብረተሰቡ በቀን ሦስት ጊዜ እንዲመገብ ይደረግበት የነበረውን ጥረት አካትቶ ሲተገበር ቆይቷል። እርግጥ ነው በትግበራው ምርት መጨመር የቻለ ቢሆንም በርካታ ክፍተቶችም ነበሩት። ከክፍተቶቹ መካከልም አምራች ዜጎችን መፍጠር አለማስቻሉ ነው። ምክንያቱም ሥራው ወደ ትግበራ ሲገባ አመጋገብ ላይ የሰውን ደህንነትና ጤንነትን እንዲጠብቅ ከማድረግ አንፃር መታሰብና መሠራት የነበረባቸው ጉዳዮች ተካትተው የታሰቡበት አልነበረም። በመሆኑም በተወሰኑ ክልሎች ላይ ከፍተኛ የሆነ የመቀንጨርና የመቀጨጭ ችግር ተከስቶ 37 በመቶ የሚሆነው የሕብረተሰብ ክፍል የችግሩ ሰለባ ሆኗል።
በተለይም ሕፃናትና እናቶች የተሟላ ምግብ ባለማግኘታቸው የተነሳ ለችግር መዳረጋቸው ይታወቃል። አምራቹ ዜጋም የዚሁ ችግር ተጋላጭ በመሆኑ ለሰቆጣ ዲክላሬሽን መነሻ የሆኑ ጥናቶች ያመላክታሉ። ጥናቶቹ ተቋማቱ የሕብረተሰቡን ሁለንተናዊ ለውጥ የሚፈጥር ሥራ መሥራት እንዳለባቸው የሚያሳስቡ ናቸው። ግብርና ሚኒስቴር አምራች ነው። በመሆኑም ከአትክልትና ፍራፍሬ፣ ከእንስሳትና ከእንስሳት ተዋፅኦ ውጤቶች አንፃር ትልቁን ድርሻ ይይዛል። ስለዚህም ሕፃናት እና እናቶች የተሟላ ምግብ እንዲያገኙ የማድረግ ስልትን ጨምሮ በአጠቃላይ ዜጎች ጠንካራ አምራች እንዲሆኑ የማስቻሉ ትልቅ ሥራና ኃላፊነት የሚያርፈው ግብርና ሚኒስቴር ላይ ይሆናል።
ትልቁን ድርሻ የሚወስደውን የግብርናውን ዘርፍ ጨምሮ 11 የዘርፍ መሥርያ ቤቶች እየሠሩ ያሉትም 37 በመቶው የሕብረተሰብ ክፍል ለችግሩ ተጋላጭ የሆነበትን ጉዳይ ይፋ የማድረጉን ውጤት ተከትሎ ነው። በዚህም መሰረት ቀደም ሲል በተቋሙ ችግሩን ለመቅረፍ ይሠራ የነበረው ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ላይ ብቻ ትኩረት ያደረገ ሥራ ነበር። በተለይ አምራቹ አርሶ አደር በአብዛኛው የሚያመርተው፣ የሚመገበው፣ ለገበያ የሚያቀርበው አንድ ዓይነት ምርትና ምግብ ነበር። ይህ ችግሩን በዘላቂነት መቅረፍ አላስቻለም። በመሆኑም ሚኒስቴሩ የአመጋገብ ስርዓትን የሚያሟላና የሕብረተሰቡን ጤና የሚጠብቅ አመራረት ጭምር መከተል እንዳለበት በማመን ወደ ሥራ ገብቷል። እየሠራ ያለው ሥራም ኒውትሬሽን ሴንሴቲቭ አግሪካልቸር ወይም ስርዓተ ምግብን መሰረት ያደረገ ግብርና ይሰኛል።
ተግባሩ አርሶ አደሩ ለገበያ የሚያቀርበውንም ለራሱ የሚመገበውንም የተሟላ አመጋገብ እንዲኖር በሚያስችል ዘዴ እንዲያመርት ያግዛል። ቢያንስ ስድስት ዓይነት ምግቦች የሚያመርትበትን ዕድልም ይሰጣል። እንደ ቡድን መሪው ከእነዚህ ምርቶች ውስጥ አንድ ቤተሰብ በቀን ውስጥ ቢያንስ አራቱን የምግብ ዓይነቶች አሟልቶ መመገብ መቻል አለበት። እርሶ አደሩ ይህን ያሟላ ያመራረት ዘዴ በመከተል ቢያንስ የራሱን ቤተሰብ የተሟላ ምግብ እንዲመግብ ማድረግ ይጠበቅበታል። ቤተሰቡና እሱ አምራች ከመሆናቸውም አንፃር የተሟላ ምግብ ያስፈልጋቸዋል። መደበኛ ምግቦችን ቂጣ ወይም እንጀራም ሆነ ገንፎን ጨምሮ አትክልት ፍራፍሬ ሊሆን ይችላል። አመጋገቡ ጥራጥሬ፣ ሥጋና የቅባት እህል በአጠቃላይ የሚገነቡና ሌሎች ተመጣጣኝ የሆኑ ምግቦችን ሊይዝ ይገባል። አርሶና አርብቶ አደሩም ሆነ ቤተሰቡ እንዲሁም ሌላው ከገበያ የሚሸምት እነዚህን አሟልቶ ሲመገብ ጤናማና ጠንካራ፣ አምራች በተጨማሪም አዕምሮው ብሩህ የሆነ ዜጋ ይሆናል።
ለዚህ ተግባርም በግብርና ሚኒስቴር የስርዓተ ምግብ ተኮር ግብርና አተገባበር ፖሊሲና ስትራቴጂ ወጥቷል። አተገባበሩንና ሥልጠና አሰጣጡን በተመለከተ ማኑዋሎች እስከ ታችኛው የግብርና መዋቅር ድረስ እንዲወርዱ ተደርጓል። በወጣው ማኑዋል መሰረትም ለአርሶና አርብቶ አደሩ እንዲሁም ለግብርና ባለሙያው ተከታታይ ስልጠና የተሰጠበት ሁኔታ አለ። ከፓርላማ ግብርናን የተመለከተ ቋሚ ኮሚቴ ውስጥ ተካትተው ከሚገኙት ጀምሮ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ለመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ጭምር ግንዛቤ እንዲያገኙ መደረጉንም አቶ ዳንኤል አብራርተዋል።
ስንዴ ወይም በቆሎ አልያም ማሽላ የሚያመርት አርሶ አደር ካለ ለልጆቹ በጓሮው ላይ ዶሮ፣ ፍየልና በግ ማርባትና አትክልት መትከል ይችላል። በተለይም ዶሮ ቢያረባ ዕንቁላሉን ልጆቹን ሊመግብበት ይችላል። አልፎ ተርፎም ትርፉን መሸጥ ይችላል። እነዚህ አርሶ አደሩ በቀላሉ ሊሠራቸው የሚችሉ ተግባራትና ሰፊ ቦታን የማይጠይቁ ናቸው።
ለአርሶ አደሩ የሚሰጠው ስልጠና ምርቱን ካመረተ በኋላ ምግቡን እንዴት ማዘጋጀት እንደሚችል ግንዛቤ የሚሰጡ ናቸው። ለአብነትም አርሶ አደሩ በጓሮው ያመረታቸው አንዳንድ አትክልቶች ለረጅም ጊዜ ላይቆዩ ይችላሉ። ስለዚህ ምርቶቹን አንድ ጊዜ ከሰበሰበ በኋላ ለረጅም ጊዜ እንዴት አቆይቶ መጠቀም እንደሚችል ትምህርት የሚሰምበት ሂደት ስለመኖሩም አቶ ዳንኤል አስረድተዋል።
አሁን ላይ አርሶና አርብቶ አደሩ በተከታታይ በቀሰመው ዕውቀት ታግዞ በንጥረ ነገር የዳበሩ ሰብሎችን ማምረት ችሏል። ለአብነት በሎቄ ተወስዶ ቢታይ ዚንክና አይረን የሚባሉ ለሰውነት ጤና ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው ንጥረ ነገሮችን እንዲያመርት እየተደረገ ይገኛል። ለመቀጨጭና ለመቀንጨር በሽታ ከሚዳርጉት ችግሮች መካከል ደግሞ የዚንክና የአይረን ንጥረ ነገር እጥረቶች ይጠቀሳሉ። በመሆኑም በዚህ በኩል ያለውን ችግር መቀነስ እየተቻለ ነው። በተጨማሪም አርሶ አደሩ ፕሮቲን ያለው በቆሎ እንዲያመርት እየተደረገ ያለበት ሂደትም አለ። በዚህ በኩል የቤተሰቡንም ሆነ የራሱን እንዲሁም ምርቱን ወደ ገበያ አውጥቶ በሚሸጥበት ጊዜ የሸማቹን ጉልበት የሚገነባና ኃይል የሚሰጥ ምርት ማምረት ይችላል። ሌሎቹንም ምርቶች እንዲሁ አበልጽጎ እንዲያመርት የተደረገበት ሂደት አለ።
በተጨማሪም በቀሰመው ትምህርት በመታገዝ የለውዝ ፍለሽ ያለው ስኳር ድንች እያመረተም ይገኛል። በግብርና ሚኒስቴር እንዲያመርት የሚደረገው ስኳር ድንች ቫይታሚን ጭምር ያለው ነው። በመሆኑም በአጠቃላይ ካርቦ ሀይድሬት፣ ቫይታሚንና ሚኒራል የሚያገኝበት የአመራረት ስርዓት ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል። አሠራሩ ክልሎች ላይ ወርዶም ሥራው ባለቤት እንዲኖረውና ክልሎች የስርዓተ ምግብ ባለሙያ እንዲመድቡ ተደርጓል።
የግብርና ባለሙያው ሳያሰልስ ለአርሶ አደሩ ማህበረሰብም ሆነ ለሌላው ሕብረተሰብ አሠራሩን፣ አመራረቱን፣ አያያዙንና አጠቃቀሙን እያስተማረ መሆኑን አቶ ዳንኤል አስረድተዋል። በዚህ መሰረት ምን ድጋፍ አገኛችሁ በማለት ላነሳነው ጥያቄም ሴት አርሶ አደር ብዙ ፀጋ ሃሳባቸውን አካፍለውናል። አርሶ አደሯ ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ ዙርያ ወረዳ በሚገኝ በመልካ ጡሪ የኦሮሚያ ክልል አካባቢ ነው። ማሳቸው ግማሽ ሄክታር ብቻ በመሆኑ እንደልባቸው ማምረት የሚፈልጉትን ማምረት አላስቻላቸውም። ይሁንና ከበስተጓሯቸው የሚገኘውን ሥፍራ ጨምሮ ግማሽ ሄክታሩን በመከፋፈል በአንድ ጊዜ አደንጓሬ፣ በቆሎና ስኳር ድንች እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬ ማምረት ችለዋል።
ይህን ማድርግ የቻሉትም ግብርና ሚኒስቴር በግብርና ባለሙያዎች አማካኝነት በሰጣቸው ስልጠና ታግዘው እንደሆነና ከዚህ ቀደም በቆሎ ብቻ የሚያመርቱ እንደነበር አስታውሰዋል። በዓመቱ ደግሞ ስኳር ድንች ወይም ቦሎቄ ያመርታሉ። በቆሎውም ቢሆን ካርቦ ሃይድሬት ብቻ እንጂ አሁን ላይ እንዳመረቱት ዓይነት ለሰውነት ጤና አስፈላጊ የሆነ የፕሮቲን ንጥረ ነገር አልነበረውም። የሚያመርቱት ቦሎቄም እንዲሁ ዚንክና አይረን ያልነበረውም። ፊት ያመርቱት የነበረው ስኳር ድንችም ካርቦ ሀይድሬት ብቻ የያዘ በመሆኑ ሆድ ከመሙላት ያለፈ ጥቅም አልይሰጥም። በመሆኑም ልጆቻቸውን ጨምሮ እራሳቸውም ብዙ ጊዜ ተመጣጣኝ ምግብ ባለማግኘታቸው ይታመሙ ነበር።
ነገር ግን ትምህርቱን ካገኙ በኋላ ያመረቱት ስኳር ድንች ቫይታሚን ጭምር ያለው በመሆኑ አሁን ላይ ወደ ገበያ ወስደው የሚሸጡትም ሆነ ቤተሰባቸውንና እራሳቸውን የሚመግቡት ይህንኑ በንጥረ ነገሮች የዳበረ ምርት ነው። ታድያ ከዚህ ቀደም በጓሯቸው አትክልትና ፍራፍሬ ቀርቶ ዶሮ እንኳን የሚያረቡበት ግንዛቤ ያልነበራቸው ወይዘሮ ብዙ፤ ትምህርቱን ከወሰዱ በኋላ ዶሮ በማርባት ዕንቁላሉንም ዶሮውንም ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው መመገብ ጀምረዋል። የተረፋቸውን ወደ ገበያ በማውጣት ከከተማ ዘይትና ሌሎች የሚያስፈልጓቸውን መግዛት ችለዋል። በተለይም በጓሯቸው ያለሙትን አትክልት ሳይበላሽ ለረጅም ጊዜ ማቆየት የሚያስችል ስልጠና ካገኙ በኋላ በዚሁ ዘዴ ቤት ውስጥ መጠቀም ችለዋል። በዚህም ጎመን ደርቆና ተፈጭቶ እንደ ትኩስ ጎመን ለረጅም ጊዜ የሚያገለግልበትን ዘዴ ጠቅሰውልናል።
አርሶ አደር አራርሳ ጉዳ በበኩላቸው እንደገለጹልን በአዳአ ዙርያ ወረዳ ገጠር ቀበሌ ነዋሪ ናቸው። ስርዓተ ምግብን መሰረት ያደረገ ግብርና ላይ ያተኮረ ስልጠና በተከታታይ ወስደው እየተገበሩ ይገኛሉ። ከዚህ ቀደም ያመረቱትን ጤፍ ገበያ አውጥተው በመሸጥ ለቤተሰባቸው ምግብ በቆሎ ይሸምቱ የነበረበትን ሁኔታ ያስታውሳሉ። በእንስሳው እርባታም ሆነ በአትክልትና ፍራፍሬው ምርት ቢሳተፉም ገበያ አውጥተው መሸጥ እንጂ ለቤተሰባቸው የመመገብ ልምዳቸው አናሳ እንደነበረ ይጠቅሳሉ።
ነገር ግን ስልጠናውን ካገኙ በኋላ ለራሳቸውና ለቤተሰባቸው በተለይም ለሕፃናትና ለባለቤታቸው ትኩረት የሰጠ የአመጋገብ ስርዓት መዘርጋታቸውን አጫውተውናል። ‹‹አሁን ቅቤ፣ ወተትና ስጋ ለቤቴም መጠቀም ጀምሬያለሁ›› የሚሉት አርሶ አደሩ የየዕለቱ ገበታቸው በተመጣጠነ ምግብ የተሞላ እንደሆነም አልደበቁም። አትክልትና ፍራፍሬ፣ የዓሣና የበግ ስጋን ጨምሮ ከስድስት በላይ ምግቦችን ያገኛሉ። ሁሉም ምግቦች ደግሞ በተለያዩ ንጥረ ነገሮች የዳበሩ ናቸው። በዚህም ጤናቸው ተጠብቋል፤ ምርታማነታቸውም ጨምሯል።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 22/2013