አባትየው “በውሸት የትምህርት ዘርፍ” እስከ ዶክትሬት ዲግሪውን ወስዷል:: በውሸት ወሬው አለምን ያስደመመ ነው:: ቀዬውን በመወከል በተለያዩ የውሸት ውድድሮች ላይ ተሳትፏል:: ብዙ ሽልማቶችንም አግኝቷል:: የአባትየውን ፈለግ መከተል የፈለገው ልጁ ደግሞ አባቱን ውሸት ካላስተማርከኝ እያለ ይወተውተዋል:: ምክንያቱም ውሸት እዚህ ቤት ዋጋ አላት:: የእለት ጉርስ ፣የዓመት ልብስ ማግኛ ብቻም አይደለችም፤ ከዚያም በላይ ናት::
ከዕለታት በአንዱ ቀን ልጅና አባት ተያይዘው ከቤት ወጡ:: የሚፈልጉበት ሥፍራ ላይ አረፍ አሉ:: ልጁ ውትወታውን ቀጠለ:: “አባቴ ቢያንስ ለዛሬ እንኳን አንድ ሁነኛ ውሸት ንገረኝ” አለው:: በእርግጥ እስከ ዛሬም እውነት አውርቶለት አያውቅም:: ወደ ልብ ዘልቆ የሚገባ የውሸት ወሬ አውርቶለት ስለማያውቅ ነው ደጋግሞ መወትወቱ::
ከጥቂት እረፍት በኋላ አባትየው ወደ ሰማይ ቀና ብሎ “ተመልከት ሰማዩ ላይ እህል ሲወቃ” አለው በድፍረት ሰማዩን በጣቱ እያመለከተ:: ልጁ ከሀሳብ እንደ መባነን ብሎ ሰማዩን ተመለከተና፤ “አዎ እውነትህን ነው አባዬ፤ ይኸው እብቁ አይኔ ውስጥ ገባ” ብሎ አይኑን ማሻሸት ጀመር:: ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ ነው የሚባለው እንዲህ:: የልጁ ውሸት ባሰ::
በህይወት ዘመኔ እንደዚህ ዘመን የተገረምኩበትን አጋጣሚ ብፈልግ አጣሁ:: ብዙ ጊዜ ተገርሜያለሁ፤ እጅጉንም ተደንቄ አውቃለሁ:: እንዲህ በመሳሰሉ ውሸቶች አገሬ ስትታመስ ግን አይቼ አላውቅም:: ሰምቼም አላውቅም::
“እውን ደርግ አለ?” የምትለዋን የኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ታዋቂ ንግግርን በቀብድነት ላስይዝና ሞራላዊ ሕይወት ሳይኖረው በድርቅና ብቻ፤ በምላስ ብቻ፤ … ጥቂት አጋፋሪዎቹ አለን ስላሉ፤ ሳይኖር በሌለበት አለሁ እያለ ሁሉ ነገር በቁጥጥሬ ስር ነው ስለሚለው ውሸታም ትንሽ ላውራችሁ::
መንጌ መለዮኣቸውን ያወለቁ ደርጎችን እንደ አዲስ ሰዎች ቆጥሮ ነበር “እውን ደርግ አለ?” ያለው፤ ሲሉ ሰምቻለሁ:: መለዮ ማውለቅ ብቻውን ደርግ አያሰኝም ያለው ማነው፤ አመለካከቱ ላይ ለውጥ መኖር ያለበት፡፡
ከሞራላዊ ሁኔታ አኳያ እኔ እንዳለ የማልቆጥረው ራሱን “ደምሳሽ” ብሎ የሚጠራው ዋሾ ልክ መንግስቱ እንደ ጠራው አይነት ደርግ ነው:: ዳሩ ግን ጠፍቶም መጥፋቱን አላመነም እንጂ:: ዛሬም ከተሸሸገበት ወጣ እያለ በብዙ ቅመማ ቅመሞች ያበደ ውሸት /መርዞች የተለወሰ/ እያሰማን ይገኛል::
መቼም አልዋሽም፤ ውሸት የሚባል ነገር አልወድም:: የሚል ሰው ካለ የመጀመሪያው ውሸታም እሱ ነው:: ለጥሩም ይሁን ለክፉ ነገር ሁላችንም እንዋሻለን:: አንዋሽም ብለን አንወሻሽ:: አንዋሽም ማለት በራሱ ውሸት ስለሆነ:: ማጋነንም ውሸት ነው፤ እውነትን ላለመናገር መታቀብም ውሸት ነው፤ ላለመዋሸት ዝምታን መምረጥም ውሸት ነው፤ የቅሌት ክብደቱ ደረጃና ዓላማው ይለያይ እንጂ ሁላችንም እንዋሻለን:: ሽማግሌ ዋሽቶ ያስታርቃል ይባልስ አይደል፤ ውሸት ወይም ሀሰት የሕይወት አንዱ ቅመም ነው:: ጠቃሚ ነው ማለቴ ግን አይደለም:: ግቡ ለደግ ከሆነ መዋሸት ብዙም ችግር የለውም፤ ሽማግሌዎች ለማስታረቅ ብለው ነው የሚዋሹት፤ የሰሙትን ደባብቀው ይቅር ለእግዚአብሄር አንዲባባሉ ያደርጋሉ:: ይህ ሲሆን፣ ውሸት ለደግ ይውላል::
ውሸት ግን ደርዝ ፣ ለከት አለው:: ዘንድሮ የምንሰማው ውሸት ግን ለከት የለውም፤ ልዩ ነው:: መተርተር ብቻ:: በሪከርድ ደረጃ ታላላቅ ዓለም አቀፍ የጊነስ ቡክ ኦፍ ሪከርድስን መዝገብ ያለ ተቀናቃኝ በአንደኝነት የሚወጡት ውሸታሞች ከወዲያ ሰፈር እየተፈለፈሉ ነው::
ውሸት በድንቃድንቅ መዝገብ የመስፈር እድል ቢኖረው፣ ዘንድሮ ያለምንም ተቀናቃኝ እነ ደምሳሽ ይሰፍሩ ነበር:: ውሸት እንደ ፋሽን ሆኖ የሚያኮራ እንጂ የሚያሳፍር አልሆን አለ:: ከመሬት እየተነሣ በማህበራዊ ሚዲያው እንደ ጣቃ ሲቀደድ የሚውልን ማየት የዘመኑ አሳዛኝና አሳሳቢ ትዕይንት ሆኗል:: ተተኪው ትውልድ ይህን መረን የለቀቀ ዘመን አመጣሽ መጥፎ ልማድ እየተከተለ እንዳይጠፋ እሰጋለሁ::
በየጥጋ ጥጉ ተደብቀው ክፋትን የሚያመነዥኩና የተንኮልን ሀሳብ የሚያንሸራሽሩ፤ ውሸትን እንደ ሸቀጥ የሚቸበችቡ ከህሊናቸው መሸሽ ያልቻሉ አገር በቀል ‘’እንቶኔዎች” አልቀመጥ ብለዋል:: እንቶኔ ማለቴ ስማቸውን በቀጥታ ላለመጥራት እንጂ ስም አልባ ሆነው አይደለም፡፡
ውሸት የልብ ልብ በመስጠት ያጀገናቸው “የደምሳሹና ማራኪው” የፌስ ቡክ ትውልድ ዝቅጠት ተስፋፍቷል:: እንደምናውቀው ውሸት ከተፈጥሮ ባሕርይም፣ ከጤና መቃወስም፣ ከኅልውና ማስቀጠያነት፣ ከቅጣትና ወቀሳ ማምለጫም፣ ከአመልም ይቀራረባል:: የአሁኑ ውሸት ከየትኛው እንደሆነ ለመገመት አስቸጋሪ ነው:: ከጤና ጋር የተያያዘ ነው እንዳንለው የደምሳሹ ቀኝ እጅ የሆኑት ዶክተር ተብዬዎች ሳይቀሩ ነው የሚዋሹት:: ከኅልውና ማስቀጠያነት ጋር የተያያዘ ነው እንዳንል ዋሾዎቹ ኅልውናቸው አክትሟል:: ከቅጣትና ወቀሳ ማምለጫም አይሆንም:: ምክንያቱም ቅጣቱን ሲቀምሱት ቆይተዋል፤ ለነገሩ አሁንም ይጠብቃቸዋል:: ወቀሳውም አልቀረባቸውም:: ምናልባት የዓመል ይሆናል:: “ሌባ ለአመሉ” ይባል የለ::
የእንቆጣጠራለን፤ አራት ኪሎ እንገባለን ሀሰት ትንቢታቸውን ለማስፈጸም ቆርጠው ሳይነሱ አልቀሩም:: ለዚህም ዘወትር አፋቸውን በሀሰት ንግግር በመክፈት ከአገር ውስጥ እስከ ባህር ማዶ እየተንጫጩ ነው:: በሰከንድ ውስጥ ኮረም፣ አላማጣ፣ ቆቦና ወልዲያን አልፈው ደሴ ላይ ምሽግ እንደሰሩ ይነግሩናል:: ከዛም ኮምቦልቻና ከሚሴን ተሻግረው ሸዋሮቢት ላይ መትረየስና ሌሎች የጦር መሳሪያዎችን እንደማረኩ ያሰሙናል:: ደብረ ብርሀን ምሳ በልተው እራታቸውን አዲስ አበባ ላይ ሲበሉ የሚያሳይ ፎቶ መልቀቃቸውስ መች ቀረ:: ጉድ ነው ብቻ:: በአንድ ጊዜ ሁሉም ቦታ መድረስ የሚያስችል መንፈስ ያደረባቸው ማለት እነርሱ ናቸው::
የፍጥነታቸውን ነገር ተውት:: ከ800ኪሎ ሜትር ላይ ጥይት ይተኩሱና ጥይቱ ሳይደርስ እነርሱ ቀድመው ይደርሳሉ:: ከጎሬ ውስጥ ሆነው ከብዙ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ተኩሰው ህንጻ ይመቱና ህንጻው ሳይወድቅ ቀድመው በመድረስ አብረው ፎቶ ይነሳሉ::
ብዙ የእከሌን ልዩ ኃይሎችን በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ እንደደመሰሱ፣ በርካታ የኤርትራ ክፍለጦሮችንም ከብዙ ታንኮች ጋር ድባቅ እንደመቱ፣ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ወታደሮችን እንደማረኩ ይናገሩና፤ ኮሽታ ሲሰሙ የዘር ማጥፋት ተፈጸመብን ይላሉ:: ሌላ ትልቅ ውሽት::
እንደው እናንተዬ “ለአፍ አቀበት የለውም” የሚባለው እንዴት ያለ ትክክለኛ አባባል መሰላችሁ:: እነዚህ ውሸታሞች አእምሯቸው በተለየ ሁኔታ ካልተመረመረና መንስኤው ካልታወቀ ጦሱ ለሰው ልጅ አጠቃላይ ኅልውና ትልቅ አደጋ እንደሚያስከትል ሊታወቅ ይገባል::
ሌሎች የሚያናድዱኝ ደግሞ የእነርሱ ፌስቡከሮች ናቸው:: የሰበር ዜናቸው ብዛት:: “በሬ ወለደ” ብለው ነው እኮ የሚጽፉት፤ “ኮሜንተሮቹ” ደግሞ “አዎ እኛም ወተቱን ጠጥተናል” ብለው ነው ምስክርነት የሚሰጡት። እብቁ አይኔ ገባ እንዳለው ዋሾ:: ውሸት እዚህ ደርሷል::
አንዳንድ በቅርብ ርቀት የማውቃቸው ምስኪኖች፤ እነርሱ እኮ አፋቸው እንጂ ውስጣቸው ባዶ ነው ይሉኛል:: ማነህ ወዳጄ …እሱማ ሽጉጥም ከተተኮሰ በኋላ ውስጡ እኮ ባዶ ነው:: ይልቅ ሃያ አራት ሰአት ሙሉ እንደ ጣቃ አይቀደዱብን:: ንገርልኝማ::
አዲሱ ገረመው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 21 ቀን 2013 ዓ.ም