
አዲስ አበባ፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን፣ የአማራ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻን የሚደግፍ እንዲሁም የሽብር ቡድኑን ህወሓት የሚያወግዙ ሰልፎች በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ተካሄደዋል ። ሰልፈኞቹ የአሸባሪው ህወሓት ትንኮሳን በመታገል አገር የማዳን ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አስታውቀዋል ።
በደብረ ማርቆስ ከተማ ትናንት በተካሄደ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የተሳተፉት ነዋሪዎች ፣የህወሓት የሽብር ቡድንን እኩይ ተግባር የሚያወግዝ እና ከሀገር መከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ ጎን መሆናቸውን ገልፀዋል።
ነዋሪዎቹ የህወሓት የሽብር ቡድን ሀገርን ለሽያጭ ያቀረበ አሸባሪ ቡድን ነው፤ የክተት ጥሪውን ተቀብለን የክልላችን እና የሀገራችን ጠላት የሆነውን የሽብር ቡድን እንፋለማለን፤ የኢትዮጵያ ትንሣኤ በተንኮል እና በሴራ አይደናቀፍም የሚሉ መልዕክቶችን አስተላልፈዋል።
የምሥራቅ ጎጃም ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብርሃም አያሌው÷ ህወሓት የሽብር ቡድን ሀገርን ለማፍረስ እያደረገ ያለውን ሙከራ ለመቀልበስ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ መናገራቸውን ከደብረማርቆስ ኮሙዩኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የዞኑ ነዋሪዎች ሀገርን ለማጥፋት ጉዞ የጀመረውን ጁንታ ለመደምሰስ አና ሀገርን ለማስቀጠል ሁሉም አካል ለክተት ጥሪው ፈጣን ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል ብለዋል።
በሌላ በኩል በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች አሸባሪው ህወሓትን በማውገዝና የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በመደገፍ ሰላማዊ ሰልፍ እካሂደዋል።
ነዋሪዎቹ ባካሄዱት ሰላማዊ ሰለፍ የሀገር መከላከያ ሠራዊት አለኝታችን ነው፣ ለሀገራችን አንድነት ከመከለከያ ሠራዊታችን ጎን እንቆማለን፣ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግደብ ግንባታ ከመጨረስ የሚያግደን አንዳችም ምድራዊ ሃይል የለም የሚሉና ሌሎችንም መልዕክቶች አስተላልፈዋል።በሰላማዊ ሰልፉ ከአሶሳ ከተማና አካባቢዋ የተሰባሰቡ የህብረተሰብ ክፍሎች መሳተፋቸውን ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በተመሳሳይ የጋምቤላ ክልል ነዋሪዎች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ያላቸውን ድጋፍ በሰላማዊ ሰልፍ ገልጸዋል። የአሸባሪው የህወሓት ቡድን ትንኮሳን አጥብቀን እንደሚያወግዙም አስታውቀዋል።
ለሀገር ሉዓላዊነት እና ለዜጎች ክብር እራሱን በመስጠት በጀግንነት በመፋለም ላይ የሚገኘውን የኢፌዴሪ የመከላከያ ሠራዊት በሙሉ አቅም እንደሚደግፉም ገልጸዋል።
የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ በሰልፉ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት፣ ሁሉም ዜጋ በአሸባሪው የህወሓት ቡድንን ትንኮሳን በመታገል አገር የማዳን ኃላፊነቱን በጋራ መወጣት እንዳለበት አሳስበዋል።
የክልሉ ህዝብ እና መንግሥት ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጎን በመሆን የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋገጠዋል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2013