
አዲስ አበባ፡- አሸባሪነት እንደ አየር ንብረት ለውጥ ሁሉ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብን የጋራ ርብርብ የሚሻ የዓለም አደጋ መሆኑ እየታወቀ የምዕራቡ ዓለም ከኢትዮጵያ በተቃራኒ መቆሙ አስነዋሪ መሆኑን በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲ መምህር የሆኑት አቶ እንዳለ ንጉሴ አመላከቱ፡፡
አቶ እንዳለ ምዕራቡ ዓለም አሸባሪው ህወሓት እየፈጸመ ያለውን የሽብር ተግባር ለማውገዝ ፈቃደኝነት ማጣታቸውን አስመልክቶ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፣ አሸባሪነት እንደ አየር ንብረት ለውጥ ሁሉ የዓለም አቀፍ ማህበረሰብን የጋራ ርብርብ የሚሻ የዓለም አደጋ ነው ፤ የምዕራቡ ዓለም ይህንን ሀቅ ወደ ጎን በመተው ከኢትዮጵያ በተቃራኒ መቆሙ አስነዋሪ ነው ።
ሽብርተኝነት የኢትዮጵያ ብቻ ስጋት አድርጎ መውሰድ ትልቅ ስህተት እንደሆነ ያመለከቱት አቶ እንዳለ፣ ችግሩ በመጨረሻ ከኢትዮጵያ አልፎ የምዕራቡን ዓለም ጭምር የሚጎዳ መሆኑ የማይቀር እንደሆነ አመልክተዋል።
የምዕራቡ ዓለም በሂደት ራሱን ጭምር የሚጎዳ ተግባር ላይ ሲሳተፍ የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም ያሉት አቶ እንዳለ፤ ኢትዮጵያ በጣሊያን ስትወረር የምዕራቡ ዓለም ከናዚዎች ጎን በመሆን የኢትዮጵያን ጉዳይ አይቶ እንዳላየ አልፎ እንደነበር ጠቁመዋል።
የምዕራቡ ዓለም የአሸባሪውን የህወሓት የሽብር እንቅስቃሴዎችን እና ተግባራትን አይቶ እንዳላየ ማለፉ መልሶ ራሱን እንደሚጎዳ በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የዲፕሎማሲ መምህሩ አቶ እንዳለ ጠቆሙ።
አቶ እንዳለ እንዳስታወቁት፣ ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ለዓለም ሰላምና ጸጥታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክታለች፤ በተለይም የምስራቅ አፍሪካ ሰላም እና ደህንነት አደጋ የሆነውን ዓለም አቀፍ አሸባሪውን አልሸባብን ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጋር በመሆን በመዋጋት ከፍተኛ ድል ስታስመዘግብ ቆይታለች። በዚህም አልሸባብ በቀጣናው ሊያደርስ ይችል የነበረውን ጉዳት መቀነስ ተችሏል።
ሀገሪቱ በሽብርተኝነት ላይ ትልቅ ድል ስታስመዘግብ የነበረች ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ የውስጥ የሽብር ቡድን እያስቸገራት እንደሆነ ያመለከቱት አቶ እንዳለ፣ የህወሓት ቡድን ከፍጥረቱ ጀምሮ በሰብዓዊ መብት አያያዝ ችግሮች እና በሌሎች መብቶች ጥሰት የሚታወቅ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ይህንን የቡድኑን እኩይ ተግባራት ምዕራባዊያኑ ራሳቸው እንደሚያውቁትና በማስረጃ የተደገፈ እንደሆነ አስታውቀዋል። ሆኖም የምዕራቡ ዓለም ኢትዮጵያ ይህን ኃይል ለማጥፋት የምታደርገውን ጥረት ከመደገፍ ይልቅ ተመልሰው እየደገፉት ነው። ይህ እጅግ አሳዛኝ ተግባር ነው ብለዋል።
እንደ አቶ እንዳለ ማብራሪያ ፣ህወሓት በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት የምዕራቡ ዓለም ጉዳይ አስፈጻሚ ሆኖ ሲያገለግል የነበረ ኃይል ነው ። በቀጣይም የጥቅማቸው አስጠባቂ ይሆናል ብለው ስለሚያስቡ እንዲጠፋ አይፈልጉም ።ከዚህ የተነሳም ኢትዮጵያ ይህን ኃይል ለማጥፋት የምታደርገውን ጥረት እየደገፉ አይደለም።
በአሁኑ ወቅት ህወሓትን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ፈርጃ እየተዋጋች ቢሆንም ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በተለይም ራሱን የሰብዓዊ መብት እና የዴሞክራሲ ጠበቃ አድርጎ የሚያየው የምዕራቡ ዓለም ኢትዮጵያን ከመደገፍ ይልቅ በአሸባሪነት ለተፈረጀው አካል የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
የምዕራቡ ዓለም በሂደት ራሱን ጭምር የሚጎዳ ተግባር ላይ ሲሳተፍ የአሁኑ የመጀመሪያው አይደለም ያሉት አቶ እንዳለ፤ ኢትዮጵያ በጣሊያን ስትወረር የምዕራቡ ዓለም ከናዚዎች ጎን በመሆን የኢትዮጵያን ጉዳይ አይቶ እንዳላየ አልፎ እንደነበር ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያን የወረረው የጣሊያን ፋሺስት ቡድን እና ግብረ አበሮቹ ብዙም ሳይቆዩ መልሰው ራሳቸውን እንዳጠቋቸው ያስታወሱት አቶ እንዳለ፤ በወቅቱ ኢትዮጵያ ስሞታ ስታሰማ ከኢትዮጵያ ጎን በመሆን ለፍትህ እና ርትዕ ወግነው ቆመው ቢሆን ናዚዎችን ቀድሞ መከላከል ይቻል እንደነበር አመልክተዋል።
አሁንም ቢሆን ከአሸባሪው የህወሓት ቡድን ጎን መሆናቸው ውሎ አድሮ ራሳቸውን እንደሚጎዳ የጠቆሙት አቶ እንዳለ፤ እንደ አልቃይዳ፤ እና እንደ ናዚ እነሱንም መልሶ መጉዳቱ አይቀሬ ነው። ይህም ትልቅ ስህተት ነው ብለዋል።
የምዕራቡ ዓለም አካሄዱን ቆም ብሎ መመልከት አለበት። ኢትዮጵያዊያን ደግሞ ለዓለም እውነታውን ከማጋለጥ ጎን ለጎን የምዕራቡን ዓለም ድርብ መስፈርት (ደብል ስታንዳርድ) አካሄድ ማጋለጣቸውን መቀጠል እንዳለባቸው አመልክተዋል።
መላኩ ኤሮሴ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2013