
አዲስ አበባ፡- ጥቂት የአሸባሪው ህወሓት ደጋፊዎች ያቀረቡትን ሃሳብ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ አቋም በማስመስል አሜሪካ ጦሯን ወደ ኢትዮጵያ እንድታስገባ ተጠይቀናል በሚል የቀረበው ሃሳብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጥስ እንደሆነ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር ዶክተር ማናዬ ዘገየ ገለጹ።
ዶክተር ማናዬ በአሜሪካ ኮንግረስ የአፍሪካ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ ሊቀመንበር ኬረን ባስ ሰሞኑን ከአፍሪካ ሕብረት ጋር ባደረጉት ውይይት በትግራይ ላለው ችግር አሜሪካ ጦሯን እንድትልክ ውጭ ባሉ ኢትዮጵያውያን ተጠይቄያለሁ ማለታቸውን በመጥቀስ ፣ይህ አይነቱ ሀሳብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚጥስ እንደሆነ አስታውቀዋል።
የኮንግረስ አባሏ በውጭ የሚገኙ ጥቂት የአሸባሪው ህወሓት ደጋፊዎች ያቀረቡትን ሀሳብ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ አቋም በሚመስል መልኩ ማቅረባቸው ትክክል እንዳልሆነም አመልክተዋል።
የወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ሀሳቡ ምስራቅ አፍሪካን የማተራመስ እቅድ ያለው ነው ያሉት ዶክተር ማናዬ፣ ከቀጠናው አገራት አልፎም የተለያየ ፍላጎት ካላቸው ሃያላን አገራት ብርቱ ተቃውሞ ሊገጥማት እንደሚችል አመልክተዋል።
የኮንግረስ አባሏ ባቀረቡት ሃሳብ በኢትዮጵያ ውስጥ ጉዳይ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ማድረግ የሉዓላዊነት ህግ ይጥሳል። ብዙ የዓለም አገራት ትኩረት የሆነውን ምስራቅ አፍሪካን የማተራመስ ሴራ ነው ። ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ሊኖረው የሚችለው ምላሽም ከባድ ነው ብለዋል።
አሜሪካ ኢትዮጵያን አንገት ለማስደፋት ግብጽን በመደገፍ የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ወደ ዓለም አቀፉ የጸጥታው ምክር ቤት በመውሰድ በገጠማት ተቃውሞ ሃፍረት እንደተከናነበች ያስታወቀሱት ዶክተር ማናዬ ፣ አሁንም ዓለም አቀፍ ህግ በመጣስ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ወደጎን በመተው ያቀደችው የወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ምስራቅ አፍሪካን የማተራመስ እቅድ እንዳለው ጠቁመዋል።
አሜሪካ በኢትዮጵያ በአንዳንድ ጉዳዮች ጣልቃ መግባቷ የተለመደ ክስተት ነው። ቢሆንም በኢትዮጵያ ተላላኪና ደካማ መንግሥት ወደ ሥልጣን ለማምጣት በተለየ መልኩ እየሰራች ያለችው ሴራ አደገኛ ነው ብለዋል። በዓለም አቀፍ ህግ የሌላን አገር ሉዓላዊነት የመጣስ፣ ጥላቻን መሰረት ያደረገ በሌላኛው ላይ የሚወሰድ እርምጃ ወይም የጣልቃ ገብነት አዝማሚያ ወንጀል መሆኑን አስታውቀዋል።
በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት የግድ የሚሆነው በአንድ አገር ውስጥ የተፈጠረው ችግር የዓለምን ሰላም አደጋ ላይ ይጥላል ተብሎ ሲታመን ብቻ ነው ያሉት ዶክተር ማናዬ ፤ በጁንታው ለህግ አልገዛም ባይነት ጋር ተያይዞ የተጀመረው ህግን የማስከበር ዘመቻ ወደ ህልውና ቢሸጋገርም ጉዳዩ ከአገር አቅም በላይ ባልሆነበትና ወደየትም አገር ባልተሸጋገረበት ጦርነት ጣልቃ የመግባት አባዜ በየትኛውም ህግ ተቀባይነት እንደሌለው አስገንዝበዋል።
አሜሪካ ሆነ ብላ መሬት ላይ ያለውን እውነታ በውሸት በማመሰቃቀል እየዘገበች የኢትዮጵያ የውስጥ ችግር በይበልጥ እንዲወሳሰብና ለዛሬው ቀውስ የተጫወተችው ሚና ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን በራሷ አቅም መፍታት ስትጀምርና ለሰብዓዊነት ቅድሚያ በመስጠት በተናጠል ተኩስ ለማቆም ስትወስን ምንም ያላለችውና መልካምነቱ ያልታያት አሜሪካ “የኢትዮጵያ ዳያፖራ ስለጠየቁኝ በኢትዮጵያ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት አደርጋለሁ” ማለቷ ዓለም አቀፉን ህግ የጣሰ የሴራ እቅድ መሆኑን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የተጀመረውን የህልውና ጦርነት የህዝቦች አንድነት አጠናክሮ ከማስኬድ ጎን ለጎን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መሬት ላይ ያለውን እውነታ በማሳየት የአሜሪካን ሴራ በየጊዜው የማጋለጥ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።
ዋቅሹም ፍቃዱ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2013