
አዲስ አበባ፡- አሜሪካ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተከናወነ ስላለው እውነታ እያወቀች አይናችሁን ጨፍኑ ማለቷ የ100 ዓመት እድሜ ያለውን የኢትዮ-አሜሪካ የህዝብ ለህዝብ የግንኙነት ድልድይ ሰባሪ መሆኑን የአሜሪካ ዲያስፖራ የሰላም ጓድ ሰብሳቢ ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ አስታወቁ። የአሜሪካንን ፖለቲካ መለወጥ መቻል አለብን፤ እንለውጠዋለንም ብለዋል።
ፕሮፌሰር ብሩክ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንዳስታወቁት፤ አሜሪካ በአሁን ወቅት በኢትዮጵያ ላይ የያዘችው አቋምም ሆነ ፖሊሲ የኢትዮጵያን አንድነት የሚያናጋ፤ የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም የሚጎዳና በሀገራቱ መካከል ከ100 ዓመት እድሜ በላይ ያስቆጠረውን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት የሚያፍረስ ብሎም የግንኙነትን ድልድይ የሚሰብር ነው ።
እኛ በአሜሪካ አገር ታክስ ከፋይ ሆነን እየኖርን በአገራችን ላይ የሚደርሰውን ተጽዕኖ እንዲሁ ማለፍ አንችልም ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ የጆባይደን አስተዳደርን፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ናሽናል ሴኩሪቲ ካውንስሉም ሆነ ኮንገረንሱ በጉዳዩ ላይ አቋም ወስደው መፍትሄ እንዲሰጡ ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በውድቅት ሌሊት በጁንታው ሲመታ እየታወቀና ጀማሪው ራሱ ሆኖ እያለ እስካሁን አይናችሁን ጨፍኑ እያሉን ነው፤ የመከላከያ ሠራዊታችን መስዋዕትነት ከፍሎ የትግራይን ህዝብ ነጻ እንዲወጣ ለማድረግ ሞክሯል፤ ስለዚህ ጉዳይም አይወራም። መከላከያ ሠራዊታችን መቀሌ ከተማን ከተቆጣጠረ በኋላ ሁኔታዎች እየሰከኑ መምጣታቸው ቢስተዋሉም እውነቱን በእውነትነት አላቀረቡትም ብለዋል ።
በሌላ በኩል መንግሥት ለህዝቡ በመቆርቆር እርዳታ እንዲገባ ለማድረግ ጥረት እያደረገ እንኳ የሰብዓዊ መብት አይከበርም፤ እርዳታ እየተሰጠ አይደለም እየተባለ ጥፋተኛ እየተደረገ ነው። የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንኳ ይህን በአግባቡ ለመረዳት አልፈለጉም። መጠየቅ ያለበትን አካልም ለመጠየቅ ፈቃደኝነት እንዳላሳዩ አስታውቀዋል ።
የኢትዮጵያ መንግሥትን በተፈጠሩ ችግሮች ዙሪያ ተጠያቂ ለማድረግ እንደተሞከረው ሁሉ ተቀናቃኙ የሆነውን አካል ለመጠየቅ ማንም ፍላጎት አላሳየም ያሉት ፕሮፌሰር ብሩክ፣ ላለመጠየቃቸው ዋናው ጉዳይ ምንድን ነው ከተባለ ምላሽ የሚሆነው ለቡድኑ ተባባሪ ናቸው የሚል ነው ብለዋል።
ምንም እንኳን ኢትዮጵያ አሁን ፈተና ውስጥ ብትሆንም በሁላችንም ውስጥ ኢትዮጵያዊነት ስሜት በመኖሩ በምንም አይነት ሁኔታ አንሸነፍም ያሉት ፕሮፌሰሩ፤ አሁን ላይ ችግር ውስጥ የገባን ቢሆንም ተጠናክረን እንደምንወጣው ምንም ጥርጥር የለውም ብለዋል።
የትራንፕ አስተዳደር በባይደን አስተዳደር እንዲተካ በማድረግ ሂደት ውስጥ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ከፍተኛ ሚና እንዳለው የጠቆሙት ፕሮፌሰር ብሩክ፤ በዚህም የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አባላት በጆርጂያ ግዛት በ25 እና 30 ሺህ ድምፅ ሁለት ሴናተሮችን እንዲያሸንፉ ማስደረጋቸውን ጠቁመዋል። በዚህ ምርጫ ከሰሜን ካሮላይና እርሳቸውም መሳተፋቸውን በመግለጽ፣ አሁንም በዚህ መሰረት የአሜሪካንን ፖለቲካ መለወጥ መቻል አለብን። እንለውጠዋለን ሲሉም ተናግረዋል።
በአሜሪካ አገር በየሁለት ዓመቱ የሚደረግ ምርጫ መኖሩን የጠቀሱት ፕሮፌሰር ብሩክ፣ ይህን ምርጫ በተመለከተ ከቀጣዩ ሁለት ወር በኋላ ቅስቀሳው ይጀመራል። ይህን በተመለከተ ሁላችንም የእኛን ድምጽ አታገኙም በሚል ለአሜሪካውያኑ ከወዲሁ በግልጽ እየነገርናቸው ነው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰውን ተጽዕኖ ከመቀነስ አኳያም በአሁኑ ወቅት ገንዘብም እውቀት በማሰባሰብ ላይ ነን። ከዚህ በተጨማሪ ወጣቱንም በየዩኒቨርሲቲው በማህበር እንዲደራጁ እያረግን ነው። ባለሀብቱን፣ ምሁሩንና ሴቶችንም በጋራ እንዲሆኑ ህብረት እየፈጠርን ነው። ለኢትዮጵያ ሰላም የተነሳነው በእልህ ነው። ውጤታማ እንደምንሆን ጥርጥር የለውም ብለዋል።
ከአሜሪካ የተለያዩ እስቴቶች የመጡት የዲያስፖራ የሰላም ጓዶች ወደ ደቡብ ክልል ኮንሶ አካባቢና ወደአማራ ክልል አጣዬ እና ከሚሴ በአካል በመገኘት ተፈናቆዮችን የጎበኙ ሲሆን፣ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጋቸውን የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ካዘጋጀው የፓናል ውይይት ለማወቅ ተችሏል።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 20/2013