
አዲስ አበባ፡- ህዝቡ ለመከላከያ ሰራዊቱ እያደረገ ያለው ድጋፍ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ በአንድነት እንደሚቆሙ ያሳየ ነው ሲሉ የኢፌዴሪ አገር መከላከያ ሰራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ገለፁ። እስካሁን በኦሮሚያ ክልል አንድ ሺህ 712 በሬዎችና አንድ ሺህ 820 ፍየሎችና በጎች ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ መደረጉ ተጠቆመ።
የኢፌዴሪ አገር መከላከያ ሰራዊት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ ከኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ዞኖች ከሚኖረው ህዝብ ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ በተረከቡበት ወቅት እንደገለጹት፣ ድጋፉ ኢትዮጵያውያን ሲነኩ ምን ማድረግ እንደሚችሉ ደጋግመው የሚያሳዩበት አንዱ የታሪክ ምዕራፍ ነው። ችግሩ ይዞት የመጣው መጥፎ ነገር ብቻ ሳይሆን ይዞት የመጣውን መልካም ዕድልንም ለይተን አይተናል። በብሔር፣ በሃይማኖትና በፖለቲካ ህዝቡ ተለያይቷል የሚሉ ወገኖችን አስተሳሰብ ውድቅ ያደረገና በአንድነት ጠንክረን መነሳታችን የሚያሳይ ትልቅ ድጋፍ ነው ብለዋል።
ለመከላከያ ሰራዊቱና ለፀጥታ ኃይሉ የሚደረግ ድጋፍ የሰራዊቱ ሞራል በድል አድራጊነት እንዲያሸንፍ የሚያደርግ ነው ያሉት ኮሌኔል ጌትነት ህዝቡ በአሉባልተኞች ሳይበገር ›› የቄሳርን ለቄሳር››እንደሚባለው አሉቧልታዎችን በማስወገድ ሙያውን ለውትድርና መተውና ከአላስፈላጊ መደነጋገሮችና የሀሰት መረጃዎች መቆጠብ መቻል ይገባል ሲሉ አስገንዝበዋል። አሉባልታዎች የስነ ልቦና ጦርነት መሆናቸውን በመገንዘብ የኢትዮጵያ ህዝብ ማንም ይምጣ ማን መመከት የሚችል ህዝብ መሆኑን ማሳየት መቻል ይገባል።
የመከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ማርታ ሎዊጅ በርክክቡ ወቅት እንደገለጹት፣ የሀገርን ሉኣላዊነት በመዳፈር መከላከያን በማጥቃት ሀገርን ለመበተን የተነሳውን ቡድን ለመመከት ህዝቡ እያደረገ ያለው ድጋፍ ትልቅ ሞራል ነው። በሁሉም ወረዳዎች ዞኖችና ክልሎች ህብረተሰቡ በሙያው በጉልበቱና በገንዘቡ ድጋፍ እያደረገ ነው። ሰራዊቱ እየተዋደቀ ያለው ለሀገር ሉአላዊነትና ለህዝቦች አንድነት መጠበቅ በመሆኑ ህዝቡ እያደረገ ላለው ያልተቋረጠ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ ቶሎሳ ዋቅ ጋሪ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት በበኩላቸው እንደገለጹት፣ አሸባሪው ቡድን ሀገራችን ላይ የከፈተውን ጦርነት ለመመከትና የሀገራችን ሰላምና ደህንነት ብሎም ዳር ድንበር ለመጠበቅ ለተሰማራው ጀግናው መከላከያ ሰራዊት ለመደገፍ የኦሮሞ ህዝብ ከጫፍ ጫፍ ተነስቶ እንቅስቃሴ እያደረገ ነው። ህዝቡ ልጆቹን መርቆ ለህልውና ዘመቻ ከመሸኘት ባሻገር አንድነቱን በመጠበቅ ስንቅና ትጥቅ በማዘጋጀት ድጋፍ እያደረገ ነው። እስካሁን ከኦሮሚያ ክልል ባሉ ዞኖችና የከተማ አስተዳደሮች አንድ ሺህ 712 በሬዎችና አንድ ሺህ 820 በግና ፍየሎችን ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል።
ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊትና በስፍራው ለተሰማሩ የፀጥታ ኃይሎች የተለያዩ ሀገራዊ የሆነ ከፍተኛ ንቅናቄ እየተደረገ መሆኑን የገለጹት በድጋፍ ርክክቡ የተገኙት በብልጽግና ዋና ጽህፈት ቤት የጥናትና ምርምር አስተባባሪና የክልሎች ድጋፍ አሰባሳቢ ንዑስ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ተመስገን ቡርቃ ናቸው።
የድጋፍ ንቅናቄው ፋና ወጊ ሆኖ የተንቀሳቀሰው የኦሮሚያ ክልል መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለያዩ ግንባሮች ለተሰለፉ የመከላከያ ሰራዊትና የፀጥታ ኃይሎች የተለያዩ የቁም እንስሳትና ሌሎች ሀብቶችን በማሰባሰብ እያደረሰ ነው። ከሰሞኑ በጎንደር በኩል በዳንሻና በደባርቅ ግንባር ድረስ አባገዳዎች ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በወልዲያ ራያ ግንባርና በአፋር ጭፍራ ግንባር ድጋፍ ተደርጓል ብለዋል። ሌሎች ክልሎችም ድጋፍ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ዝግጅት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ለመከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ለማድረግ ከጉጂ ዞን ኦዶ ሻኪሶ ዞን ወረዳ 12 በሬ ድጋፍ ይዘው ከመጡት አባገዳዎች መካከል አቶ ሽብሩ ገመዳ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያን አንድነት ለመበተን፣ በህዝቦች መካከል መለያየት በመፍጠር ሀገርን ለማጥፋት ለተነሳው ቡድን ከገንዘባችን እስከ ህይወታችን ድረስ መስዋእት ለመሆን መላው የኦሮም ህዝብ ተነስቷል ብለዋል።
ሞገስ ተስፋ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 19/2013