ሰው ከእንስሳ ከሚለይባቸው ነገሮች መካከል አንዱ ከፍ ያለ አስተሳሰብ የሚያራምድ አእምሮ ባለቤት መሆኑ ነው፡፡ ይህ ከፍ ያለ አስተሳሰብ ከሚገለፅባቸው መንገዶች አንዱ ደግሞ ለሰዎች በምናደርገው ድጋፍ ነው፡፡ በአገራችን ሰዎችን መርዳት እንደ ጠንካራ ባህል የሚወሰድ በጎ ተግባር ነው፡፡ ሰውን መርዳት እንደ ፅድቅ የሚቆጠር ተግባርም ነው፡፡ አብዛኛው ለፈጣሪው ይበልጥ የሚቀርብበት መንገድ አድርጎ ስለሚቆጥረው በተለያዩ አካባቢዎች ድሆችን መርዳት የተለመደ ነገርም ነው፡፡ ይሁን እንጂ እንዲህ አይነት በጎ ተግባራት አሁን አሁን ከተወሰኑ ምክንያቶች ጋር ብቻ እየተያያዙ በሌላ ጊዜ የሚጠፉበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡
በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሌሎች አገራት የምንሰማቸው የራስ ወዳድነትና ግለኝነት ባህርያት ተዛምቶብን ከመተዛዘን ይልቅ መጠፋፋት፣ ሌሎችን ከመርዳት ይልቅ ለራስ ከልክ ያለፈ ህይወት እስከመኖር የደረስንባቸው አጋጣሚዎችን እንመለከታለን፡፡ ለዚህም አንዱ ማሳያ ከልክ ያለፉ የቅንጦት እቃዎችና ከልክ ያለፈ የአኗኗር ዘይቤ ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ የሚላስ የሚቀመስ ያጡ በርካታ ህጻናትና አረጋውያን ባሉባት አገር በብዙ ሚሊየን የሚቆጠር ገንዘብ በማውጣት ቅንጡ ተሽከርካሪዎችን ከውጭ የሚያስገቡና ለልደት ብዙ ሺህ የሚመደብበት ነባራዊ ሁኔታ መኖሩን ስንሰማ ምን ያህል በህይወት ተቃርኖ ውስጥ እንደምንኖር ያመላክታል፡፡
ነገር ግን የመረዳዳትም ሆነ በልክ የመኖር ባህሎች ዛሬም እንዳሉ የሚያሳዩ ተግባራት እንዳልጠፉ በርካታ ማሳያዎችን ማንሳት ይቻላል፡፡ በተለይ በቅርቡ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰትን ተከትሎ በርካታ ዜጎች ለከፍተኛ የኑሮ ጫና መዳረጋቸው ይታወሳል፡፡ ይህንን ክፉ ጊዜ ለማለፍ ደግሞ የደጋግና ቅን ልቦች መኖር ትልቅ አስተዋፅኦ ማድረጉን ስንመለከት የመረዳዳት ባህላችን ዛሬም ጠንካራ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወደ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ አቅም የሌላቸውን ሰዎች ለመርዳትና ለመደገፍ ብዙ በጎ አድራጎት ማህበራት ተመስርተዋል፡፡ ማህበራቱ የእለት የምግብ ድጋፍ ከማቅረብ በተጨማሪ በየወሩ የገንዘብ ድጋፍ እስከማድረስ ተሻግረዋል፡፡ ማህበራቱ በወጣቶች የተደራጀ በመሆኑ የደም ልገሳ፣ የከተማ ፅዳት እንዲሁም ቤት ለቤት በመሄድ አቅመ ደካሞችን በስራ እያገዙ ይገኛሉ፡፡ በሁሉም ክልሎች በዓላትን ጠብቆ ቤት የማደስ፣ ማዕድ ማጋራት እንዲሁም በዘላቂነት ድጋፍ የሚፈልጉትን በመደገፍ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውጤታማ ስራ ሰርቷል፡፡ ይህም ስራ ብዙ ወጣቶችን አበረታቶ በአሁኑ ወቅት ብዛት ያላቸው ማህበራት ፈቃድ አውጥተው እንዲንቀሳቀሱ መንገድ ከፍቶላቸዋል፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች የተቋቋሙት የበጎ አድራጎት ማህበራት ድገፍ የሚፈልጉ ሰዎችን ባላቸው አቅም እርዳታ ቢያደርጉም ከህብረተሰቡ ግን የሚፈለገውን ያክል ተቀባይነት እያገኙ አይደሉም፡፡ ህብረተሰቡ ያለውን በአቅሙ እንዲያዋጣ ሲጠየቅ ከመሳደብ እስከ መማታት የደረሰ ሁኔታ እንደሚፈጠር ብዙ ማህበራት እንደ ችግር ያቀርባሉ፡፡ ህብረተሰቡም አጭበርባሪዎች በመብዛታቸው ህጋዊውን ማህበር ለመለየት ተቸግረናል የሚል መማረር ያሰማል፡፡ ለዚህ ደግሞ መፍትሄው የበጎ አድራጎት ማህበራትና ህብረተሰቡ ተጋግዞ የሚሰራበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፡፡
በአገሪቱ በተለያዩ ክልሎች የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ ረጂና ጧሪ ቀባሪ የሌላቸውን ወገኞች በዘመቻ መልክ ድጋፍ ሲደረግላቸው ቆይቷል፡፡ መንግስትም የእለት ቀለብ ሊሆኑ የሚችሉ ምግቦችና ቁሳቁሶችንም ለግሷል፡፡ የዱብቲ በጎ አድራጎት ማህበር በሚል ወጣት ኑሩ ያየውና ጓደኞቹ ለተቸገሩ ሰዎች እንክብካቤና ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ ማህበሩን በሊቀመንበርነት የሚመራው ወጣት ኑሩ ቢሆንም ከተመሰረተ በኋላ በርካታ በጎ ፈቃደኞች አግዘውታል። ማህበሩ ተመስርቶ ድጋፍ ማድረግ ከጀመረ አመትን አስቆጥሯል፡፡
የማህበሩ አመሰራረትና ያከናወናቸው ተግባራት
ማህበሩ የተመሰረተው በ2012 ዓ.ም ትምህርት ቤት ላይ ነበር፡፡ ከዛም የተለያዩ ስራዎችን በማከናወን የተጀመረው ስራ 2013 ዓ.ም በዱብቲ ከተማ ላይ በስፋት መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ ከአካባቢ ፅዳት ጀምሮ በየቦታው ችግኞች እንዲተክሉ ተደርጓል። በጤና ዙሪያ ደግሞ በአካባቢው ተከስቶ የነበረውን የኮሌራ በሽታ ለመከላከል ስራዎች ተከናውነው ነበር። የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከልም ማህበሩ በቅንጅት ስራዎችን ሰርቷል፡፡ በማህበረሰቡ ውስጥ የኮሮና ወረርሽኝ መከላከያ መንገዶችን ግንዛቤ በመፍጠር ለውጦች ታይተዋል፡፡ በየአካባው የእጅ መታጠቢያ በርሚሎችን በማስቀመጥ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
ማህበሩን የመሰረቱት ተማሪዎች በትምህርት ቤት ቆይታቸው ከተማሪዎች መዋጮ በመሰብሰብ በወር ለአምስት ችግረኛ ሰዎች ድጋፍ ይደረግ ነበር፡፡ በየሳምንቱ ድጋፍ የሚደረግላቸው ሰዎች ቤት በመሄድ ያሉበት ሁኔታ ክትትል ይደረጋል፡፡ ማህበሩ በሃያ አባላት ስራዎችን የጀመረ ሲሆን ማህበሩ ህጋዊ እውቅና አግኝቶ ወደ ተግባር ሲገባ አባላቱን ሃምሳ ማድረስ ችሎ ነበር። በተጨማሪም የክብር አባል በሚል ከመቶ በላይ አባላትን መያዝ ችሏል፡፡
በኮሮና ወቅት ማህበሩ ድጋፍ ለሚፈልጉ ሰዎች ረጂ ድርጅቶችን በማፈላግ ድጋፍ እንዲያገኙ አድርጓል። በተጨማሪም በተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ የግንዛቤ ስራ ሰርቷል፡፡ የኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ማህበሩ በገበያ ቦታዎች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎችን ይሰራ ነበር፡፡ በሌላ በኩልም በየአስራ አምስት ቀኑ ከመንገዶች ላይ ማስክ የማፅዳት ስራ ያከናውናል፡፡ ማስክ በማፅዳት ዘመቻው ህፃናት የወደቀ ማስክ አንስተው እንዳያደርጉ ይረዳል፡፡ በማፅዳት ዘመቻው ማስክ ህብረተሰቡ መጠቀምና በአግባቡ ማስወገድ እንዳለበት ግንዛቤ ይሰጣል፡፡ በየሳምንቱ እሁድ በከተማው ደረጃ ፅዳት ይካሄድ ነበር፡፡
በኮቪድ ወረርሽኝ ምክንያት ከቤት መውጣት ለማይችሉ ሰዎች በየወሩ አስቤዛ፣ የተፈጨ በቆሎ፣ ሳሙናና አልባሳት ከህብረተሰቡ በማሰባሰብ፣ ከአባላት መዋጮ በየወሩ ሀምሳ ብር በመሰብሰብ እንዲሁም ውጪ ከሚገኙ የአካባቢው ተወላጆች ገንዘብ በመሰብሰብ ድጋፍ ሲደረግ እንደነበር ይናገራል፡፡ በዚህም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ወቅት አቅም የሌላቸው ሰዎች ተደግፈዋል።
ሌላው ደግሞ ድጋፍ ለሚደረግላቸው ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁሶች ይሰጧቸዋል፡፡ ደብተር፣ እስኪርቢቶ፣ ዩኒፎርም፣ የስፖርት ትጥቅና ቦርሳ እንደሚሰጣቸው ያመለክታል፡፡ ቁሳቁሶቹን ከስፖንሰር በሚገኝ ድጋፍ የሚገዛ ሲሆን አልባሳትና የተለያዩ ነገሮችን ከማህበሩ አባላት ውስጥ ድጋፍ የሚያደርጉ አሉ፡፡ ከየሰው የሚሰበሰቡ ልብሶችን ለተማሪዎቹ በየልካቸው እንዲሰጣቸው ይደረጋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በማህበር ውስጥ ታቅፈው ድጋፍ እያገኙ ያሉት ህፃናት አሉ፡፡
የህብረሰተቡ አቀባበል
የበጎ አድራጎት ስራው ሲጀመር የህብረተሰቡ አቀባበል በሁለት ፅንፍ የተወጠረ ነበር፡፡ ሀሳቡ ሲመጣ ጀምሮ የተወሰኑ ሰዎች ከዚህ በፊት የሚደረገውን በማየት ወይም ደግሞ ውስጣቸው ያለውን ፍራቻ በመመልከት ብቻ አይሳካም በሚል ተስፋ ይቆርጣሉ። የመደገፍ ሀሳቡ ወደ መሬት ወርዶ ተግባር ላይ ሲውል ሁሉም ሰው ተደስቶ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል፡፡ በገንዘብ ለማገዝ አቅም ባይኖራቸው በጉልበት እያገዙ ናቸው፡፡
የበጎ አድራጎት ስራዎች ሲሰሩ የማህበረሰቡ አቀባበል ሁለት አይነት ነው፡፡ አንዱ በደንብ ተረድቶ ገብቶት የማህበሩን ሀሳብ ለመደገፍ በጣም የሚጥር ሲሆን የተወሰነው የማህበረሰቡ ክፍል ደግሞ የማህበሩ ስራ አጠራጣሪ ወይም ደግሞ ስራው የሚሰራው ለግል ጥቅም እንጂ ለማህበረሰቡ አስበው አይደለም ብሎ የሚያምን አለ፡፡ የኮልፌ አጠና ተራ ከነዋሪዎች ከተሳትፎ አንፃር በሀሳብ በገንዘብ በተለይም በጉልበት ከፍተኛ ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ የማህበር የአባላት መዋጮ እንዳለ ሆኖ አንድ ሰው ለአንድ ቤተሰብ በሚል ሶስት ቤተሰቦች በግለሰቦች ቀጥተኛ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑ ለየት ያደርገዋል፡፡
የአካባቢው ማህበረሰብ ደግ ማድረግን የሚወድና የኖረበት ነው፡፡ በተደራጀ መንገድ በአግባቡ የሚመራ ከሆነ ህብረተሰቡ ድጋፎችን ለማድረግ ዝግጁ ነው። ለአቅመ ደካሞች ቤት በሚሰራበት ወቅት የቤት መስሪያውን አጠቃላይ ቁሳቁስ ህብረተሰቡ ያቀርባል። ማህበሩ በሚያስተባብራቸው ስራዎች ላይ እገዛ ያደርጋል፡፡
ማህበሩ ስራዎችን ሲሰራ በበጎነትና በመልካም ሀሳብ ተነሳስቶ ነው፡፡ በአካባቢው ማህበረሰብ ውስጥ እስካሁን ማህበሩ ላይ የተለየ ነገር አላሳየም፡፡ በማንኛውም ስራ ላይ ህብረተሰቡ በማድነቅና በማበረታታት እገዛ ያደርግ ነበር፡፡ የዱብቲ ከተማ አስተዳደር ለማህበሩ በማንኛውም መንገድ ድጋፍ ሲደርግ የቆየ ነው፡፡ በማንኛውም የቁሳቁስ ድጋፍ አስተዳደሩ ሁሌም ቀና ትብብር ያደርጋል፡፡ ማህበረሰቡ የማህበሩን ስራ በቻለው አቅም ሊደግፍ ይገባል፡፡
የአካባቢው ማህበረሰብ ማህበሩ ከተመሰረተ ጊዜ አንስቶ በቻሉት አቅም ከገንዘብ ጀምሮ ድጋፎችን የሚያደርጉ መሆናቸውን የማህበሩ አባላት ይናገራሉ፡፡ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት ህብረተሰቡ ከማህበሩ የሚወርድለትን መልዕክት በመቀበል ጥንቃቄ እያደረገ የሚገኝ ሲሆን በደም ልገሳና በሌሎች ፕሮግራሞች ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝም ያመለክታሉ፡፡
ማህበሩን ያጋጠሙ ችግሮች
ማህበሩ ከተመሰረተ በኋላ የገንዘብ ችግሮች ስራዎች በአግባቡ እንዳይከናወኑ እንቅፋት ፈጥረው ነበር። ለችግረኛ ሰዎች የሚሆኑ ድጋፎች በተወሰነ መልኩ ከሰዎች ማግኘት ቢቻልም አብዛኛው እየተሸፈነ ያለው በማህበሩ በራሱ ነበር፡፡ ማህበሩ የገንዘብ እጥረት ስለነበረበት የተፈለገውን ያክል ድጋፍ አላደረገም፡፡ ህብረተሰቡም በተመሳሳይ የኑሮ ደረጃ ውስጥ ስለሚገኝ ገንዘብ ለማዋጣት ይቸግረው ነበር፡፡
የማህበሩ ቀጣይ እቅድ
በቀጣይ ማህበሩ ቋሚ አባላትን በመያዝ መዋጮ በመሰብሰብ የተቸገሩ አምስት ቤተሰቦች በየወሩ በቀጣይነት መርዳት ሲሆን በሂደት ድጋፍ የሚደረግላቸውን ሰዎች ቁጥር ለማሳደግ ሀሳብ አለ። በተጨማሪም ለተቸገሩ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሰቁስ ለመርዳት እቅድ አለ፡፡ ከማህበረሰቡ ጋር በመተባበር የአረንጓዴ አሻራውን ስራ በአግባቡ ለመስራት ታስቧል። የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ስራዎች ይከናወናሉ፡፡ በችግኝ ዙሪያና በከተማ ፅዳት ላይ በቀጣይነት ለመስራት እቅዶች ተቀምጠዋል፡፡
መርድ ክፍሉ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2013