አንድ አገር በሌላ አገር ጣልቃ መግባትን የሚመለከተው ፅንሰ-ሀሳብ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ አለም አቀፍ ሕግ ወጥቶለት የተከለከለ መሆኑ ተደንግጓል፡፡ በዓለም ዓቀፍ ህግ በአንድ አገር የውስጥ ጉዳዮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጣልቃ መግባት አይፈቀድም፡፡ ንፁህ እና ቀላል ሰብአዊነትን ብቻ ማዕከል ያደረገ ጣልቃ ገብነት የግለሰቦችን ሉዓላዊነት፣ የአገርን አንድነት እና የፖለቲካ ነፃነትን እስካልነካ ድረስ የማይከለክል መሆን አለበት የሚል ክርክር ቢኖርም፤ እ.አ.አ ከ1990ዎቹ ጀምሮ የተለያዩ ጣልቃ-ገብነት አጋጣሚዎች ተፈፅመው በዓለም ዙሪያ ካስከተሉት ጥቅም ይልቅ ያመጡት ጉዳት ጎልቶ በመታየቱ ጣልቃ ገብነት በፍፁም ሊደገፍ የማይገባ መሆኑን በመጠቆም ተግባሩን ኮንነው የሚሞግቱም አልጠፉም፡፡
በሚለዋወጠው የዓለም አቀፍ ሁኔታ ውስጥ በግድ ወይም በአምባገነንነት የሚፈፀም ጣልቃ ገብነት ጉዳቱ የከፋ መሆኑ በተለያዩ ማሳያዎች ይነገራሉ፡፡ ለአብነት የኢራቅ ፣ የሶማሊያ ፣ የሄይቲ እና በኮሶቮ ውስጥ በወታደራዊ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት የተፈፀመ ቢሆንም ያስመዘገቡት ስኬት ጥያቄ ውስጥ ነው፡፡ የመሞገቻው ነጥቡ የሰዎች ህይወት መታደግን የሚመለከት ቢሆንም፤ በዕውን ስለሰብአዊነት ከታሰበ እ.አ.አ በ1994 በሩዋንዳ የተፈፀመው የዘር ፍጅት ላይ ጣልቃ መግባት ሲኖርበት በነበረው መዘግየት የነበረውን ዕልቂት በመጥቀስ፤ የሰብአዊነት ጣልቃ ገብነት ጉዳይ አሁንም ድረስ አከራካሪ ሆኖ ቀጥሏል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር እና አማካሪ ዶክተር ዮናስ ተስፋ እንደሚናገሩት፤ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የማቋቋሚያ ቻርተር አገራት የተስማሙበት መርህ በሉዓላዊ አገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ አለመግባትን መሰረት አድርገዋል፡፡ ይህ በተባበሩት መንግስታት ቻርተር በአንቀፅ ሁለት ንዑስ አንቀፅ 4 ላይ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ለዚህም በምክንያትነት የቀረበው በማንኛውም መልኩ አንዱ አገር በሌላኛው አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚገባ ከሆነ ለአለም ሰላም እና ደህንነት የሚያስከትለው ጉዳት እጅግ የከፋ ይሆናል በሚል ነው፡፡
ጣልቃ ያለመግባትን ጉዳይ በሚመለከት የዓለም አቀፍ ህግ የመነጨበት ዘመን እንደሚያሳየው አገራት ሉዓላዊ ናቸው ብሎ መቀበል የግድ የሆነበት ጊዜ ነበር፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ አገር የሉኣላዊ ሥልጣን ባለቤት ነው ከሚል መነሻ የአገራት ግንኙነት ሉአላዊ ሥልጣንን ያከበረ ሊሆን ይገባል የሚል ድምዳሜ ላይ ተደረሰ፡፡ ሉዓላዊነት ሲባል የውስጥ እና የውጪ ሉዓላዊነት ተብሎ የሚከፈል ሲሆን፤ የውጪ ሉዓላዊነት ሲታሰብ አንድ አገር ተለይቶ በአገርነት ዕውቅና የተሰጠው ከሆነ ማንኛውም ሌላ አገር በሌላ አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት እንደማይችል ያብራራሉ፡፡
ነገር ግን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ለዓለም ሰላም እና ደህንነት ሲባል ጣልቃ የሚገባበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል የሚሉት የህግ መምህሩ፤ አንዳንድ የምዕራባውያን አገራት የፀጥታው ምክር ቤት ለዓለም ሰላም እና ደህንነት ጣልቃ የሚገባበትን ሁኔታ ላልተገባ ዓላማ ለማዋል ሲሞክሩ በተደጋጋሚ እንደሚስተዋል ያመለክታሉ፡፡ ለምሳሌ ባይሳካላቸውም በዩጎዝላቪያ እና በሩዋንዳ የነበረውን የጣልቃ መግባት ሙከራ መጥቀስ ይቻላል በማለት በማሳያነት ይጠቅሳሉ፡፡
የምክር ቤቱ ቋሚ ዓባላት አሜሪካን፣ እንግሊዝ እና ፈረንሳይ ጣልቃ ለመግባት የሚሞክሩበት ሁኔታ አለ፡፡ ቻይና እና ሩሲያ በበኩላቸው በምንም መልኩ በአንድ አገር የውስጥ ጉዳይ ላይ የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ጣልቃ ሊገባ አይገባም የሚል ቋሚ አቋም ሲያራምዱ ተደምጠዋል፡፡ ድምፅ የመስጠት ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ከዚህ ቀደም የተሞከሩ ጣልቃ ገብነቶችን አስቁመዋል፡፡ የሆነው ሆኖ ከህግ አንፃር ሲታይ ማንም አገር ቢሆን በሌላኛው አገር ጣልቃ መግባት መሞከር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ምሶሶ የሆነውን በማንም አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት የሚለውን መርህ የሚጥስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የህግ አማካሪው ዶክተር ዮናስ እንደተናገሩት፤ ከኢትዮጵያ አንፃር ሲታይ በለውጡ ማግስት ሁሉንም ነገር ጠቅልሎ ይዞ አድራጊ ፈጣሪ የነበረው ሃይል በተደረጉ መጠነ ሰፊ ሰላማዊ ትግል ያልተገባ ሥልጣኑን በማጣቱ ራሱ በግንባር ቀደምትነት ያፀደቀው ህገመንግስትን በሚፃረር መልኩ የማዕከላዊ መንግስቱን በተለያየ መንገድ ተጋፍቷል፡፡ ለማሳያነት ያህል መጀመሪያ ከማንነት እና ከወሰን ጉዳዮች ጋር በተያያዘ በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተወካዮች ምክር ቤት ህግ አውጥቷል፡፡ በህወሓት ይመራ የነበረው የትግራይ ክልል ምክር ቤት ያንን ህግ ኢ-ህገመንግስታዊ ነው ብሎ ውሳኔ አሳልፏል። እንደሚታወቀው በህገመንግስቱ መሰረት የተወካዮች ምክር ቤት ያወጣውን ህግ ኢ-ህገመንግስታዊ ነው ብሎ መበየን የሚችለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ብቻ ነው፡፡ የህወሓት አጥፊ ቡድን ደግሞ በዚህ መልኩ ህገመንግስቱን የሚፃረር ተግባር ፈፅሟል፡፡
በተጨማሪ በኮቪድ ምክንያት ምርጫ ሲራዘም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ህገመንግስት የመተርጎም ስልጣኑን ተጠቅሞ እንዲራዘም ሲወስን፤ በተመሳሳይ መልኩ ህወሓት ከህገመንግስት ውጪ በመሔድ ውሳኔውን አልቀበልም ብሏል፡፡ ከዛም አልፎ ምርጫን የማካሔድ ሥልጣን የምርጫ ቦርድ ቢሆንም፤ የዚህን ህገመንግስታዊ ተቋም ሥልጣን በሚጋፋ መልኩ ምርጫ አካሂደዋል፡፡ መጨረሻ ላይ የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ፈፅመዋል በማለት ገልፀው፤ ይህ በዝርዝር ሲታይ በአንድ ሉአላዊ አገር ውስጥ ያለን ህገመንግስታዊ ሥርዓት በሚፃረር መልኩ አንድ ቡድን በአመፅ ተነስቷል ማለት መሆኑን አስረድተዋል፡፡
እንደዶክተር ዮናስ ገለፃ፤ በአንድ ሉአላዊ አገር ውስጥ ህገመንግስታዊ መዋቅሩን በመጋፋት በሃይል ያመፀ ሃይል ህግን በማስከበር ተጠያቂ የማድረግ ሃላፊነት የማዕከላዊ መንግስት ነው፡፡ ስለዚህ መንግስት ህግን ለማስከበር በህወሓት ላይ የሚወስዳቸው ማናቸውም እርምጃዎች በማንኛውም መለኪያ የአገር ውስጥ ጉዳዮች ናቸው። በአገር ውስጥ ጉዳይ ደግሞ የሚካሔድን ማናቸውንም ተግባር በተመለከተ የትኛውም አገር የፈለገ ሃይልም ሆነ የቱንም ያህል ሃብት ቢኖረውም ጣልቃ ገብቶ እንዲህ ይደረግ፤ እንዲያ ይደረግ ማለት አይችልም፡፡
የተባበሩት መንግስታት ቻርተር ሲቋቋም እንደተገለፀው በአገራት መካከል እኩልነት አለ፡፡ ስለዚህ ያንን ታሳቢ በማድረግ ማንም በሌላው አገር ላይ አለቃ መሆን አይችልም፡፡ የዓለም አቀፍ ጉዳይ ሊሆን የሚችለው የአገር ውስጥ ጉዳይ ካልሆነ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ በኢትዮጵያ የተፈፀሙ ተግባራትም ሆነ በመንግስት የተወሰዱ እርምጃዎች በማንኛውም መለኪያ የአገር ውስጥ ጉዳዮ ናቸው፡፡ ነገር ግን እንደተለመደው በተለይ ምዕራባውያኑ ለራሳቸው ብሔራዊ ጥቅም በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ እንደሚያግዛቸው ካሰቡ ጣልቃ ለመግባት መሞኮራቸው አይቀርም፡፡
ይህ በኢትዮጵያ እየሆነ ነው፡፡ ይህ ድርጊት በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በሌሎች አገሮችም የተፈፀመ ተግባር ነው። ነገር ግን ይህ ተግባር በተባበሩት መንግስታት ድርጅት መመስረቻ ሰነድ ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው እና የእዚሁ ድርጅት መሰሶ የሆነው በሉዓላዊ ጉዳይ ላይ ጣልቃ አለመግባት የሚለውን መርህ የሚጣረስ ነው፡፡ አሁን ባለው የዓለም አቀፍ ህግ እና ልምድ መሰረት በአገር የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ መግባት አይፈቀድም፡፡ ጣልቃ ለመግባት መሞከር ሉዓላዊ ሥልጣንን መጋፋት ነው፡፡ ስለዚህ ማንም በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት አይችልም፤ መግባትም የለበትም በማለት ሃሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡
ምህረት ሞገስ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 16/2013