በዚህ የግብርና ሥራ ወቅት የሰብል ምርት ሥራው በቅደም ተከተል የሚከናወን ሲሆን፣ የብርዕና አገዳ ሰብሎች ዘር የሚዘራው በመጀመሪያ የክረምት መግቢያ ላይ ነው። የጥራጥሬ ሰብሎች ይከተላሉ፡፡ በያዝነው ከሀምሌ አምስት ጀምሮ ደግሞ ስንዴ፣ ጤፍና ገብስ ያሉ ሰብሎች ይዘራሉ። ወቅቶቹን ተከትሎ የግብርና ሥራውን ማከናወን ለአርሶ አደሩ መንገር ለቀባሪው ማርዳት ቢሆንም ሳይዘናጋ ጊዜውን ተከትሎ ሥራውን እንዲያጠናክር ማስታወስ ግን ተገቢ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአንዳንድ አካባቢዎች ካልሆነ በስተቀር የማሣ ዝግጅት ከ95 በመቶ በላይ ተከናውኖ ለዘር ዝግጁ ሆኗል።
በግብርና ሚኒስቴር የሰብል ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኢሳያስ ለማ የምርት ዘመኑን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ በዘንድሮ መኽር 12 ነጥብ 78 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለማረስና 374 ሚሊዮን ኩንታል ምርት በዕቅድ ተይዟል። በዕቅድ የተያዘው የእርሻ መሬት መካከልም የትግራይ ክልልን ጨምሮ 11 ሚሊዮን ሄክታር መሬት ታርሷል። ከታረሰው መሬትም ከ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ሄክታር በላይ ማሳ በትራክተር ነው የታረሰው፡፡ ለእርሻ ሥራው የሚያግዙ አራት ዓይነት የአፈር ማዳበሪያ፣ ምርጥ ዘር፣ የአሲዳማ አፈር ማከሚያ ኖራና ሊከሰቱ የሚችሉ የሰብል ተባዮችን መከላከል የሚያስችል የተለያዩ የኬሚካል ግብአቶች አቅርቦትም ቀድሞ በመዘጋጀቱ በዚህ በኩል ስጋት አይኖርም፡፡
እስካሁንም በተከናወነው የእርሻ ሥራ ወደ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ዘር ተሸፍኗል። በተለይም በትግራይ ክልል ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ ሲሰራ ቆይቷል። በዚሁ መሠረትም 700 ሺ ሄክታር መሬት የታረሰ ሲሆን፣ 200 ሺ የሚሆነው መሬት በተለያየ ሰብል ተሸፍኗል፡፡ የትግራይ ክልል በልግ አምራች ባለመሆኑ በመኽሩ ሰብል ምርት ወቅት በየዓመቱ በአንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር ማሣ ላይ የሚያመርተው አነስተኛ ምርት ነው፡፡ ክልሉ በአንድ ወቅት ብቻ ማምረቱ በምርት ራሱን እንዳይችል አደርጎታል፡፡ ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ክፍሎች ምርት በመውሰድ ክፍተቱን ለመሙላት ጥረት ይደረጋል፡፡ ይህ ተጨባጭ ሁኔታ እየታወቀ አሁን በተፈጠረው ወቅታዊ ሁኔታ አካባቢው ለድርቅ እንደተጋለጠ ተደርጎ በተለያየ የውጭ መገናኛ ብዙሃን መናፈሱ እውነታውን አያሳይም፡፡
ክልሉ በወቅታዊ ችግር ውስጥም ሆኖ ግብርና ሚኒስቴር የአካባቢው የእርሻ ሥራ እንዳይስተጓጎል ጥረት አድርጓል፡፡ ወቅቱን ግምት ውስጥ በማስገባትም መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም በማድረግ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ከክልሉ እንዲወጣ ማድረጉም ይታወሳል፡፡ እነዚህ ቅድመ ምቹ ሁኔታዎች በክልሉ ይታረስ ከነበረው አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን ሄክታር መሬት 700 ሺህ ሄክታር ማሳ እንዲታረስና በዘር እንዲሸፈን ማድረግ ተችሏል፡፡ ይሄ ጥረት ቢደረግም ክልሉን በሌሎች አካባቢዎች ከተመረቱ ምርቶች መደጎሙ አይቀሬ ነው፡፡ ክልሉ በመኽሩ የግብርና ሥራ ውጤታማ እንዲሆን መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት ጎን ለጎን የውጭና የሀገር ውስጥ የተለያዩ ድርጅቶች በግብአት አቅርቦትና በተለያየ እገዛ ሲያደረጉ መቆየታቸውም አይዘነጋም፡፡
አቶ ኢሳያስ በምርት ዘመኑ ለክልሉ ከወጣውና ለአርሶ አደሩ በነፃ እንዲሰራጭ ከተደረገው የግብዓት አቅርቦት ወጪ ለአብነት እንደገለፁትም፤ ለክልሉ የተመደበውን 60 ሚሊዮን ብር ጨምሮ በድምሩ በ150 ሚሊዮን ብር ወጪ የቀረበው ዘርና ማዳበሪያ ግብአት እንዲሁም አንበጣን ለመከላከል የተከናወነው ተግባር ይጠቀሳል።
በተጨማሪም የዓለም አቀፍ ምግብና እርሻ ድርጅት በሚያስተባብራቸው የግብርና ክላስተር ላይ ያሉና ሌሎች አካላት ከ44 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለክልሉ ድጋፍ እንዲያደርጉ ተደርጓል። በአጠቃላይ ለመኸሩ እርሻ ከ60 ሺህ ኩንታል በላይ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሩ በነፃ ተከፋፍሏል። ይሄም ለክልሉ በመደበኛ መቅረብ ከነበረበት ከእጥፍ እጅ በላይ ብልጫ ያሳያል፡፡ በክልሉ አሁን ካለው ተጨባጭ ሁኔታና ካለፈባቸው ጊዜያት አኳያ ምርቱ አስፈላጊ መሆኑን ታሳቢ በማድረግ ቀሪውን ማሳ ማረስና በዘር መሸፈን ይኖርበታል ተብሎ ይጠበቃል። ይሄ ከፍተኛ ተስፋ የተጣለበት ነው። በመሆኑን አርሶ አደሩ ጊዜውን ሙሉ በሙሉ ለመኸሩ እርሻ በማዋል ተጠቃሚነቱን ማሳደግ ይኖርበታል። በእርግጥ አሁን ባለው ሁኔታ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ከበልግ ወደ መኽር ይዞራሉ ተብለው የሚጠበቁ ማሳዎች አሉ። እነዚህ ማሳዎች ቶሎ ካልተለቀቁ በተለይ የበልጉን ምርት አንስተው የመኸር እርሻቸውን ሀምሌና ነሀሴ ወራት መጨረሻ ላይ የሚዘሩ ናቸው። የደቡብ ብሄር ብሄረሰብ ህዝቦች ክልል የሰገን ህዝቦች ፣ ደቡብ ኦሞ ኮንሶ ቡርጅና ሌሎች በልግ ስለሚዘገይባቸው ዘግይተው የሚዘሩ አካባቢዎች ናቸው። ኦሮሚያ ቦረና አካባቢም እንዲሁ በልግ የሚዘገይባቸው በመሆናቸው ዘግይተው ይዘራሉ። በባሌ አካባቢም በተመሳሳይ የበልጉ እርሻ ተሰብስቦ ነው የመኸሩ የሚዘራው። እነዚህ አካባቢዎች የዘር ወቅታቸው በአብዛኛው ከሀምሌ መጨረሻ እስከ ነሀሴ መጀመሪያ ሳምንት ድረስ ነው። በእነዚህ ቦታዎች የወቅቱ የእርሻ እንቅስቃሴ ሲቃኝ የደቡብ ክልል በመኸር የሚሸፈነው 50 በመቶው ነው። በበልግም በተመሳሳይ የሚሸፈንበት ሁኔታ አለ። ይሄ ከሌሎች ክልሎች ጋር ሲነፃፀር ቁጥሩ ከፍተኛ ነው።
በዘንድሮ በልግ የተሸፈነው ማሳ 900 ሺህ ሄክታር ነበር። እስከ አሁን በበልግ ከለማው ውስጥ ከ25 እስከ 40 በመቶ የሚሆነው ወደ መኸር የዞረበት ሁኔታ አለ። በኦሮሚያ ክልል በበልግ እስከ 900 ሺህ በመኽር ደግሞ 6 ሚሊዮን ይሸፈናል። አማራ ክልል ላይ በበልግ የሚሸፈነው 300 ሺህ ሲሆን በመኽር ደግሞ 4 ሚሊዮን አካባቢ ነው። 10 ቀን ዘግይቶ የመጣው ዝናብ ታዲያ በአመዛኙ ተፅዕኖ ሊፈጥር ይችላል ተብሎ የሚሰጋው በበልግ ምርት ላይ ነው። እንደ ሀገር አስር ቀን ዘግይቶ የመጣው የዘንድሮ ክረምት ዝናብ ሁኔታ በተለይ በመኽር ምርት ላይ ያሰጋል የሚል ግምት ካልሆነ በስተቀር ተፅዕኖ አይኖረውም ተብሎ ነው የሚታመነው ።
በአጠቃላይ በ2013/14 መኽር ምርት ዘመን 12 ነጥብ 78 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በማረስ የሚጠበቀውን 374 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት የገበያ ስርጭቱ የሰብል ቀመር መርሐ ግብርን ተከትሎ እንዲሄድ ከማድረግ ጀምሮ በግብዓት አቅርቦት፣ በቴክኖሎጂ ስርፀትና የአርሶ አደሩን ንቃተ ህሊና በማዳበር በርካታ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን አቶ ኢሳይያስ ይናገራሉ። የእርሻ መሳሪያዎች (ሜካናይዜሽን)፣ የብድር አገልግሎት ለሁሉም ክልሎች ተደራሽ ተደርጓል።በዚህ ቴክኖሎጂን በማስገባትና ተደራሽ በማድረግ የኦሮሚያ ክልል በአፈፃፀም ቀዳሚነቱን ይዟል።
በአርሲ፣ በባሌ፣ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ከፍተኛ ለእርሻ ሥራ የሚውል ትራክተር የማቅረብና አርሶ አደሩ እንዲጠቀም የማድረግ አቅም መፍጠሩ ታይቷል። አማራ ክልልም ከመካናይዜሽን አጠቃቀም አንፃር ከኦሮሚያ ጋር በተመሳሳይ ደረጃ ላይ ይገኛል። እስከ አሁን ባለው አማራና ኦሮሚያ ላይ 1ነጥብ 4ሚሊዮን ሄክታር ማሳ በትራክተር መታረሱ ማሣያ ነው። የትራክተር ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያስቻላቸው በተለይ ኦሮሚያ ላይ ምዕራብ ሸዋ ፣ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ብድር በወቅቱ እንዲያገኙ በመመቻቸቱ ነው። የምዕራብ አርሲና የባሌ አካባቢዎች፣ ደቡብ ላይ ስልጤና ጉራጌ ትራክተር ሜካናይዜሽን ተጠቃሚዎች ናቸው። ሰሊጥ አምራቾች በሆኑት የትግራይና የአማራ ክልል አካባቢዎች ላይ ሰፋፊ እርሻም የትራክተር ተጠቃሚነት ጎልቶ ተስተውሏል። በአጠቃላይ የሚጠበቀውን ምርት ማግኘት የሚቻለው አርሶ አደሩ የተሻለ ማዳበርያ፣ምርጥ ዘር ፣የአስተራረስ ዘዴ ሲጠቀም እንዲሁም የማሳ እንክብካቤ ሲያደርግ ፣በአረምና ተባይ ቁጥጥር ያለውን አቅሙን አሟጦ ሲተገብርና ሰብሉን በጊዜ መሰብሰብ ሲችል ነው። አሁንም አርሶ አደሩ ትኩረቱን ከማሳው ላይ ሳያነሳ ትኩረት ሰጥቶ ይስራ የሚለው መልዕክታችን ነው።
ሰላማዊት ውቤ
አዲስ ዘመን ሐምሌ 15/2013